ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, April 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 17

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደው በአራተኛውም ቀን ከመቃብር ያስነሣው የከበረ ጻድቅ_አልዓዛር አረፈ፣ አናጕንስጢስ ቅዱሰ_ቴዎቅሪጦስ በሰማዕትነት አረፈ፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ_አቡነ_ዮናስ የበዓለ ዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው፡፡

መጋቢት ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደው በአራተኛውም ቀን ከመቃብር ያስነሣው የከበረ ጻድቅ አልዓዛር አረፈ። ይህም ጻድቅ ሰው ከእስራኤል ልጆች ውስጥ ነው ማርያና ማርታ የተባሉ ሁለት እኅቶች አሉት። ማርያም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሸቱ የቀባችው ናት።
እነርሱም ለጌታ ደቀመዛሙርቶቹ ናቸው ስለ ምግባራቸውም ጌታችን ይወዳቸዋል ሁሉም ያላገቡ ድናግል ናቸው። በሰው ወገን ሁሉ ላይ የተቆረጠና የተወሰነው ሰዎችም ሊጠጡት ያላቸው የሞት ጻዋን የሚጠጣበትና እጁን ለሞት የሚሰጥበት ለዚህ ጻድቅ ጊዜው ሲደርስ እርሱም እጁን በመስጠት አረፈ።
የክብር ባለቤት ጌታችን ግን የሚሠራውን ያውቃልና መጀመርያ ከሞት አላዳነውም ጠርቶ እስከሚአሥነሣው ድረስ ሙቶ በመቃብር አራት ቀን እንዲኖር በዚህ በአራት ቀንም የጻድቃንን ማደሪያዎችንና የኃጥአንን የሥቃይ ቦታዎች እንዲያይ ተወው እንጂ አላዳነውም ያን ጊዜም ታላቅ ምልክት ትሆናለች።
ከአራት ቀኖችም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ አልዓዛር አልዓዛር ና ውጣ ብሎ ከመቃብር ውስጥ ጠራው ያን ጊዜ አጆቹና እግሮቹ እንደታሠሩ ሙታኖችንም እንደሚጠቀልሏቸው በሰበን ፊቱ ተጠቅልሎ ወጣ።
እጆቹና እግሮቹ እንደ ተጠቀለሉና እንደ ታሠሩ ከመቃብር የመውጣቱ ምክንያት ሰዎች ሁሉ መሞቱን እንዲረዱ ሌሎችም ይህ በመካከላቸው በስምምነት የሆነ ነው ብለው እንዳያሰቡ። ስለዚህም እንደ ገነዙት ሁኖ እንዲወጣ ጌታችን አዘዘው ይችም ምልክት እንድትሆን።
ከሀዲዎችም በመቃብር ውስጥ ሕያው እንደ ነበር ቢያስቡም እጆቹና እግሮቹ ፊቱም እንደ ተጠቀለሉ እንዴት ይወጣ ነበር እኛ የክርስቲያን ወገኖች ግን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአራት ቀኖች በኋላ አልዓዛርን ያስነሣው እርሱ እንደሆነ እናምናለን። እንታመናለንም እርሱ በሥራው ሁሉ ላይ ችሎታ አለውና።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት አናጕንስጢስ ቴዎቅሪጦስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ የሮሜ አገር ሰው ነው። ዐላውያንም ለጣዖት እንዲሠዉ ክርስቲያኖችን ይዘው በአስገደዷቸው ጊዜ እርሱንም ከእነርሱ ጋር ያዙት ወደ ንጉሥም አቀረቡት ያንጊዜ የዐሥራ አምስት ዓመት ልጅ ነበር።
ንጉሡም በማመጣብህ ሥቃይ ትፈተናለህን ወይስ ለአማልክት ትሠዋለህ አለው። ቴዎቅሪጦስም እኔስ ለክብር ባለቤት ለጌታዬ ለፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እሠዋለሁ አለው።ንጉሡም ቴዎቅሪጦስ ሆይ በክፉ አሟሟት እንዳትሞት ለአማልክት መሥዋዕት አቅርብ አለው።
እርሱም ንጉሥ ሆይ መሥዋዕቴን እንድታይ ና አለው ንጉሡም ወደ ጣዒቱ ቤት እንዲወስዱትና በዚያ እንዲሠዋ አዘዘና እርሱም በበር ቆመ። ቅዱሱም በጸለየ ጊዜ ንውጸውጽታ ሁኖ አጽቀላጽዮስ የሚሉት አምላካቸው ወድቆ ተሰበረ ።
ንጉሡም እንደ ዘበተበት አይቶ አፍንጫውን ቆረጠው አሥረው በወህኒ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ። በማግሥቱም አውጥተው በብረት ምጣዶች ውስጥ ጨመሩት ደግመው ጥልቅ ግድጓድ ቆፈሩ በውስጡም እንጨት ረብርበው ሥጋው ከመለያያው እስቲቦጫጨቅና ቅልጥሙም ከአጥንቶቹ እስቲፈስ ድረስ ወረወሩት ። በዚህም ሊአጠቁት አለቻሉም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእርሱ ጋር አለና።
ከዚህ በኋላ አማልክቶቻቸው የሚበቀሉት መስሏቸው ከአማልክቶቻቸው ቤት አስገብተው በዚያ ዘጉበት ። ቴዎቅሪጦስ ግን ከጣዖታቱ ላይ ያለውን ወርቅ ቀጥቅጦ በሥውር ይዞ እየወጣ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች መጸወተው። ተመልሶ ሲገባም ደጃፉ እንደ ቀድሞው ራሱ ይዘጋል።
በስምንተኛውም ቀን ንጉሡ መጣ ከደጃፍም ሁኖ አየ አማልክቶቹም ተጥለው ተሰባብረው የከበረ ቴዎቅሪጦስም ሲዘብትባቸው አገኛቸው። ዕውነተኛ ቴዎቅሪጦስንም የሆድ ዕቃው እስቲታይ እንዲሰነጣጥቁት አዘዘ። ደግመው ወደ ጨዋታ ቦታ እንዲአስገቡትና በላዩ አንበሶችን እንዲአስገቡአቸው አዘዘ። አንበሶችም ቁስሎቹን ላሱለት።
ዳግመኛም ሕዋሳቱ እስቲነጣጠል ከሚአጣብቅ ቦታ እንዲአስገቡት መላ አካላቱም ታጥፎ እስቲቆለመም እንዲአሠቃዩት አዘዘ። በዚህም ተሸብሮ አላሸነፉትም ንጉሡም ብርታቱን አይቶ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ።
የከበረ ኤጲስቆጶስ ኤሞሬዎስና ህዝብ ሁሉ በጸሎት እየተራዱት ቅዱስ ቴዎቅሪጦስን ተከተሉት በቅዱሳን ሰላምታም ተሳልመውት ተሰናበቱት ባለወግ ወታደርም ሰይፉን አንስቶ አንገቱን ቆረጠው ምስክርነቱንም ፈጸመ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚኽች ዕለት አቡነ ዮናስ የበዓለ ዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው፡፡ አቡነ ዮናስ አባታቸው ንዋየ እግዚእ እናታቸው ኂሩተ ማርያም ይባላሉ፡፡ በኅዳር 17 ቀን 1357 ዓ.ም በሀገረ ቡር (ሀገረ መስቀል) ሚባል ተወለዱ፡፡ አቡነ ዮናስ በሕፃንነታቸው በጎች እየጠበቁ ሳለ መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም መዝሙረ ዳዊት ኣስተማራቸው፡፡ እርሳቸውም ይህን ዓለም ንቀው ከመነኮሱ በኋላ 150 መዝሙረ ዳዊት በአንድ ጊዜ እየጸለዩ 3 ሺህ ስግደት ይሰግዱ ነበር፡፡ ቀንና ሌሊት ሲጸልዩም "ጠላቂት" በሚባል ሐይቅ ውስጥ እየገቡ እስከ አንገታቸው ድረው በሐይቁ ውስጥ ገብተው ይጸልዩ ነበር፡፡ ከተሰጧቸውም ጸጋዎች ውስጥ አንዱ 10 ጣቶቻቸው ወደ ሐይቁ ሲገቡ ይበሩ ነበር፡፡ አቡነ ዮናስ በየቀኑ ከ5 ፍሬ "ዳዕሮ" ወይም "ዓየ" በቀር ሌላ ምግብ አይመገቡም ነበር፡፡
ከዚኽም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ኀብስተ ኣኩቴትን ጽዋ በረከት ከሰማይ አውርዶላቸዋል፡፡ ጻድቁ እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት ወደተለያዩ ቦታዎች እየዞሩ የተለያዩ ተኣምራት በማድረግ ሕሙማንን በመፈወስ ሙታን በማስነሣት ብዙዎችን ከክህደት ወደ እምነት ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ከጣኦት ኣምልኮ ወደ እግዚአብሔር ኣምልኮ መልሰዋል፡፡
ጌታችን በአምላካዊ ቅዱስ ቃሉ ‹‹ከመቃብርህ ጸበል የተቀባ የጠጣ ከኃጥያቱ ይነጻል›› የሚል ቃልኪዳን አስቀድሞ የሰጣቸው ሲሆን በዚህ ድንቅ ቃልኪዳን መሠረት ዛሬም ድረስ ከመካነ መቃብራቸው ላይ ፈዋሽ የሆነ ቅብዓ ቅዱስ ይፈልቃል፡፡ ይህንንም በ2011 ዓ.ም ለአንድ ወር በአክሱምና ኤርትራ የዞር ጉዞ ባደረግንበት ወቅት ወደዚህ ታላቅ ገዳም ሔደን የጻድቁን ገዳም ተሳልመን ቅብዓ ቅዱሱን በዐይናችን አይተን በአባቶች ተቀብተን በረከታቸውን አግኝተናል፡፡ ቅብዓ ቅዱሱ በተለይም ጆሮውንና ዐይኑን ለሚያመው ሰው መድኃኒት ነው፡፡
አቡነ ዮናስ ይይዙት በነበረው መቋሚያ በውኃ እየታጠበ ውኃው በጣም ለታመሙ ሰዎች እየተሰጠ በቶሎ ከበሽታቸው ይድኑበታል፣ የማይድኑም ከሆነ ቶሎ በሞት ያርፋሉ፡፡ የሚታጠቡበት ሁሉ ለድኅነት ከሆናቸው በአጭር ጊዜ ይድናሉ ወይም ለዕረፍት ከሆናቸው ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት ያሰናብታቸዋል፡፡ አቡ ዮናስ በቁርባን ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በሠረገላ መንፈስ ደርሰው ያስቀድሱ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል፡፡
ከዕረፍታቸው በኋላ የተደረጉ በርካታ ታላላቅ ተአምራት አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ እርሳቸው ካረፉ ከትንሽ ቀናት በኋላ በመቃብራቸው ላይ ዘይት ፈለቀ፡፡ ከዚያም በእንጨት በተሰራ መቅጃ እየተቀዳ ወደ ትልቅ መጠራቀምያ ገብቶ ለቤተ መቅደስ መብራት በ12 ተቅዋም ተደርጎ ከዓመት እስከ ዓመት ይበራ ጀመር፡፡ ከተጠራቀመ ዘይቱም ለታመሙ ይቀቡትና ከተለያዩ ሕመሞች ይድናሉ፡ ያዕ 5:14፡፡ ዳግመኛም ኤርትራ በሚገኙት በሌሎቹ በአባታችን ደብር ውስጥ ከብዙ ጊዜ በኋላ በደብረ ሣህል ደብራቸውና በደብረ ጽጌ ፈለቀ፡፡ ቅብዓ ኑጉም ለታመሙ ፈውስ እየሰጠ ለቤተ መቅደስም መብራት ሆነ፡፡
ዳግመኛም ከተደረጉት ተአምራት ውስጥ አንዱ እንደ ቤተክርስቲያን ሕግጋት ጻድቁ ካረፉ በኋላ ለጸሎትና ለኑዛዜ ሰዎች ተሰብስቦው እህል እና ውሃ ተዘጋጅቶ በነበረበት ሰዓት "በዚ ቀን ሁሉ ሰው ተገኝቶ ያለሥጋ ዋልን›› ሲሉ ሦስት የተለያዩ ሚዳቆዎች በአቡነ ዮናስ ጸሎት ድንገት መጥተው በሰዎቹ መሐል ተገኙ፡፡ ሰዎቹም ሚዳቆዎቹን አረደው በሉ፡፡
ጻድቁ በስማቸው የተገደሙ ገዳማት (ደብረ ድኁኃንበ- ቆሓይን፣ ደብረ ጽጌ ትምዛእ፣ ደብረ ጽዮን ዓዲ ወሰኽ፣ ደብረ ጸሪቅ ትግራይ፣ እና ደብረ ሣህል ዓረዛ) ይባላሉ፡፡
አቡነ ዮናስ ያረፉት መጋቢት 17 ቀን ሲሆን ይህ ወቅት ታላቁ ዐቢይ ጾም የሚውልበት ስለሆነ በዓለ ዕረፍታቸውን ጥር 21 ቀን እንዲያከብሩ ለልጆቻቸው አስቀድመው ነግረዋቸዋል፡፡ በመሆኑም በዚሁ ዕለት ጥር 21 ቀን በሁሉም ገዳማቸው ውስጥ በታላቅ ክብረ በዓል ታስበው ውለዋል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages