ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, April 24, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 17

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም


ሚያዝያ ዐሥራ ሰባት በዚህች ቀን የዘብዴዎስ ልጅ የወንጌላዊ ዮሐንስ ወንድም ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም በእስያ ውስጥ ከአስተማረ በኋላ ዕርቅ በተገኘባት በእውነተኛ አምላክ በጌታችን ወንጌል ሊያስተምራቸው ወደ ተበተኑ ወደ ዐሥራ ሁለቱ ነገድ ወጣ። እነርሱም አንድ አምላክን የሚአመልኩ አልነበሩም እየራሳቸው የመረጡትን የሚአስቷቸው ጣዖታትን ያመልኩ ነበረ እንጂ። ከቄሣር ሥልጣን በታች የተሾመ ኄሮድስም ሹመቱ በሚዳብር መንግሥቱ በሚያጽና ገንዘብ ብዙ ግብር እንዲገብሩ እጅ መንሻም እንዲአስገቡ አዘዘ።
ያዕቆብ ግን ወደእርሳቸው በደረሰ ጊዜ በአገራቸው ቋንቋ ሰበከላቸው የፍጥረትን ሁሉ ቋንቋ ማወቅን እግዚአብሔር ሰጥቶት ነበርና የሚያውቀው የሰው ቋንቋ ብቻ አልነበረም የእንስሳና የአራዊት የሰማይ ወፎችንም ቋንቋ ነበረ እንጂ። በውስጣቸው በሰበከም ጊዜ የከፋ ሥራቸውን ትተው በሕያው እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በሆነ መንፈስ ቅዱስ ነፍሶቻቸው በእጁ ውስጥ በተያዙ በአንድ አምላክ እንዲያምኑ አዘዛቸው። እርሱም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ የሚመጣ ነው። ዳግመኛም በማይጠፋና በማይበላሽ በሰማያት ድልብ ይሆናቸው ዘንድ ከገንዘባቸው ለችግረኞችና ለድኆች እንዲመጸውቱ አዘዛቸው።
ትምህርቱንም በሰሙ ጊዜ ከክፋ ሥራቸው ተመልሰው በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብም ትምህርቱን ፈጥነው ስለተቀበሉት እጅግ ወደዳቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው በየአገራቸው ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው። ዳግመኛም ከእንስሶቻቸው ከሚዘሩአቸው እህሎችና ወይን አትክልቶች ፍሬዎች ለካህናትና ለድኆች ምግብ ሊሆን ለቤተ ክርሰቲያን የመጀመርያውን መባ እንዲሰጡ አዘዛቸው። ሕዝቡም በአንድ ቃል ያዘዝከንን ሁሉ እኛ እናደርጋለን አሉት። ከዚህ በኋላ ከእንስሳት መጀመሪያ የተወለደውን ከእህሉም ቀዳምያቱንና ዓሥራትን ለቤተ ክርስቲያን አመጡ።
ኄሮድስም ቅዱስ ያዕቆብ ለቤተ ክርስቲያን መባ ይሰጡ ዘንድ እንዲሚያዝ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ጭፍራ ልኮ ወደርሱ አስመጣውና "ሕዝቡ ገንዘባቸውን ሁሉ ለድኆች ምጽዋትና ለቤተ ክርስቲያን መባ እንዲሰጡ የምታዝ አንተ ነህን" አለው። "አዎን እኔ ነኝ" አለው ያን ጊዜ ኄሮድስ ተቆጥቶ ራሱ በሰይፍ አንገቱን መትቶ ቆረጠው። በኢየሩሳሌምም ሁከትና ሽብር ሆነ ደግሞ ከፋሲካ በዓል በኋላ ሊገድለው አስቦ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ወስዶ አሠረው የእግዚአብሔር መልአክም ኄሮድስን ቀሠፈው ተልቶ ተበላሽቶ ሞተ ልዑል አምላክን አላከበረውምና። የቅዱስ ያዕቆብን ሥጋ ግን ምዕመናን ወሰዱት ገንዘው በቤተ መቅደስ ውስጥ ቀበሩት።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ በረከት ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages