ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 22 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, April 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 22

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ ሁለት በዚችም ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በአህያ ግልገል ተቀምጦ የገባበት ሆሣዕና እያሉ ያመሰገኑበት ነው፣ የከበረ አባት ኤጲስቆጶስ ቅዱስ_ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም አረፈ።


መጋቢት ሃያ ሁለት በዚችም ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገብቶ ቤተ መቅደሱን በአህያ ግልገል ተቀምጦ በመዞር ሆሣዕና እያሉ እንዲአመሰግኑት አድርጓል። ይህም ስለርሱ እየአንዳንዳቸው በዘመናቸው ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው።
ያዕቆብም በክርስቶስ ስለ ተመሰለው ስለ ልጁ ይሁዳ አህያውን በዘይት ዕንጨት ላይ ያሥራል ውርንጫውንም በወይን አረግ አለ። ዘካርያስም የጽዮን ልጅ አትፍሪ እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል ተቀምጦ ይመጣል አለ።
ኢሳይያስም ንጉሥሽ ጻድቅ የዋህ የሆነ ይመጣል ዋጋውም ከእርሱ ጋራ ነው ሥራውም በፊቱ የተገለጠ ነው በአህያ ግልገልም ላይ ይቀመጣል አለ። አብርሃምም የሰሌን ዝንጣፊ ይዞ መሠውያውን በዞረ ጊዜ ይቺን ዕለት ተድላ ደስታ የሚደረግባት የእግዚአብሔር በዓል ብሎ ጠራት።
ዳዊትም ከሕፃናትና ከልጆች አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ አለ። ሰሎሞንም የሕፃናት አንደበታቸው የተቃናች ሆነች አለ ሁለተኛም ልጆችና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ይጫወታሉ ምርጕዛቸውም በእጃቻቸው ውስጥ ነው አለ። ደግሞ መትከያዎችሽን አስፍተሽ ድንኳኖችሽን ዘርጊ ያለም አለ።
ይህንንም የትንቢት ነገር ለመፈጸም በከበረ ወንጌል እንደተጻፈ ጌታ በአህያዋና በውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ የደብረ ዘይት አጠገብ ከምትሆን ቤተ ፋጌ ደረሰ ደብረ ዘይት ወደሚባል ቢታንያም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ።
ወደ ፊታችሁ ወዳለ አገር ሒዱ። በገባችሁም ጊዜ ሰው ያልተቀመጠበት ያህያ ግልገል ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ለምን ትፈቱታላችሁ የሚል ሰው ቢኖር ጌታው ይሻዋል በሉ። የተላኩትም በሔዱ ጊዜ እንደነገራቸው አገኙ። የአህያውንም ግልገል ፈቱ ጌቶቹም ለምን ትፈቱታላችሁ አሏቸው። ጌታው ይሻዋል አሉ።
ወደ ጌታ ኢየሱስም ይዘውት ሔዱ ልብሳቸውንም በአህያው ግልገል ላይ ጐዘጐዙ ጌታንም አስቀመጡት። ቅጠል ቆርጠው በመንገድ ላይ የጐዘጐዙ ብዙዎች ናቸው። ልብሳቸውንም በመንገድ ላይ ያነጠፉ አሉ። በፊትም በኋላ ይሔዱ የነበሩት በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ መድኃኒት ነው ብለው አሰምተው ተናገሩ። በእግዚአብሔር ስን የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥትም የተባረከች ናት።
ጌታ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ገባ ሕዝቡም ሁሉ አዩት በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አርድእት ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። በነጋውም ከቢታንያ በወጣ ጊዜ ተራበ። በሩቅም ቅጠል ያላትን በለስ አየ። በርሷ ፍሬ ያገኝ እንደሆነ ሊያይ ሔደ ወደርሷም በደረሰ ጊዜ ከቅጠል ብቻ በቀር ያገኘው የለም የበለስ ወራቱ አልነበረምና። ለዘላለም ካንቺ ፍሬ የሚበላ አይኑር አላት ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ።
ወደ ኢየሩሳሌም ደርሶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ በምኲራቡም ግቢ የሚገበያዩትን ያስወጣ ጀመረ የለዋጮችንም ሰደቃቸውን ገለበጠ ርግብ የሚሸጡትንም ወንበራቸውን ። ወደ ምኲራብ ለንግድ ገንዘብ ይዘው እንዳይገቡ ከለከለ። ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይሁን የሚል ጽሑፍ ያለ አይደለምን እናንተ ግን የሌቦችና የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት ብሎ አስተማራቸው።
ዮሐንስም እንዲህ አለ አልዓዛርን ከሙታን ለይቶ ካስነሳው በኋላ። በነጋውም እሑድ ለበዓል የመጡ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ። የሰሌን ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ከኢየሩሳሌም ፈጥነው ወጡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ከአርያም የተገኘ መድኃኒት የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ እየጮኹ ተቀበሉት።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የአህያ ግልገል አገኘ። ተቀመጠበትም እንደ ተጻፈ እንዲህ ሲል። የጽዮን ልጅ አትፍሪ እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ግልግል ተቀምጦ ይመጣል።
አስቀድሞ ግን ደቀ መዛሙርቱ ይህን ነገር አላወቁም ነበር ጌታ ሳይሰቀል ። ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ይህ የተጻፈ ስለ እርሱ እንደሆነ ያን ጊዜ አወቁት እንጂ እንዲህም አደረጉለት።
አልዓዛር አልዓዛር ብሎ ከሙታን ለይቶ እንዳስነሣው ባስነሣው ጊዜ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መሰከሩለት። ስለዚህም ሕዝቡ አመኑበት። ያደረገውን ተአምራት ሰምተዋልና የሕፃናቱንም ምስጋና ደግሞ አልዓዛርን ማስነሣቱን።
የካህናቱ አለቆችና ፈሪሳውያን ግን እርስ በርሳቸው የምታገኙት ረብሕ ጥቅም እንደሌለ አታውቁምን እነሆ ሰው ሁሉ አመነበት አሉ። ማቴዎስና ማርቆስ የሰሌንን ነገር አላወሱም ሌሎች ከእጨንቶች ቅጠሎችን እየቆረጠ በመንገድ ውስጥ ጐዘጐዙ አሉ እንጂ።
ሉቃስም ቅጠልን ወይም ሰሌንን አላወሳም ሲሔዱ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር አለ እንጂ። ዮሐንስ ግን ለብቻው ከኢየሩሳሌም ከሰሌን ዛፍ ላይ ዘንባባ ቆርጠው ያዙ አለ። ሰሌንም በኢየሩሳሌም አልነበረም ጌታችን ሕፃን ሁኖ ሳለ ወደ ግብጽ በወረደ ጊዜ ከእናቱ ቡርክት ቅድስት ከሆነች ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጋር እስሙናይን ከሚባል አገር ደረሱ ከዚያም ሰሌን አገኙ።
ጌታችንም ከሥርዋ ተነቅላ ሒዳ በደብረ ዘይት ላይ እንድትተከል አዘዛት ያንጊዜ ወደ አየር ወጥታ በረረች ሒዳም በዚያ በደብረ ዘይት ተተከለች ከእርስዋም ወስደው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበሉት። ጌታችንም የሆሣዕናን ዑደት በአሳየ ጊዜ የአይሁድ ወገን ቅናት ይዟቸው በሚገድሉት ገንዘብ ምክንያት ፈለጉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት የከበረው መንፈሳዊ አባት የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አባ ቄርሎስ አረፈ። ይህም አባት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመማር ያደገና እጅግ አዋቂ ምሁር ሆነ።
ከእርሱ በፊት የነበረ ኤጲስቆጶስ አባ በርኪሶስ በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው ለኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አድርገው ሾሙት። በተሾመም ጊዜ ከመናንያንና ከአርዮሳውያን ተኵላዎች በመልካም አጠባበቅ ሕዝቡን ጠበቀ።
የኤጲስቆጶሳት ጉባኤ በሰርድቄ በተሰበሰበ ጊዜ ይህ አባት ከዚያ ደርሶ አርዮሳውያንን ተከራከራቸው ምላሽ አሳጥቶም አውግዞ አሳደዳቸው አካክዮስንም ከቂሣርያ ሀገረ ስብከቱ መንበር አሳደደው።
አካክዮስም ወደ ታናሹ አርዮሳዊ ወደ ሆነው ቆስጠንጢኖስ ሒዶ ከማኀበሩ ስለ ደረሰበት ውግዘትና ስደት ይልቁንም ከዚህ አባት ቄርሎስ የደረሰበትን ሁሉ በመናገር ከሰሰው። ስለዚህም አርዮሳዊ ንጉሥ ይህን አባት ከኢየሩሳሌም አሳደደው ሌሎችንም ብዙዎች ኤጲስቆጶሳትን ከሀገረ ስብከት መንበራቸው አሳደዳቸው።
ይህም አባት ቄርሎስ ወደ ተርሴስ ከተማ ሒዶ ከአገሩ ኤጲስቆጶስ ከስልዋኖስ ጋራ ተገናኘ። እርሱም ተራዳው ጥቂት ቀኖችም ከእርሱ ዘንድ አስቀመጠው።
በሉክያኖስ ስብሰባ በሆነ ጊዜም ይህ አባት ከተሰበሰቡት ውስጥ አንዱ እርሱ ነው አካክዮስንም ደግመው አወገዙት ረገሙትም፡፡ ዳግመኛ ወደ ንጉሥ ሒዶ በዚህ በቅዱስ ቄርሎስ ነገር ሠራበት ንጉሡም ወታደሮች ልኮ ከዚያም ካለበተረ አሳደደው።
ከዚህም በኋላ ይህ መናፍቅ ቈስጠንጢኖስ ሞተ። ልጁ ሦስተኛው ቈስጠንጢኖስ ነገሠ ይህንንም አባት ከተሰደደበት ወደ መንበረ ጵጵስናው መለሰው አባቱ ያሳደዳቸውን ኤጲስቆጶሳት ሁሉንም መለሳቸው። ይህም አባት የተረፈውን ዘመን በሰላምና በጸጥታ ኖረ።
ታላቁ ቴዎዶስዮስም በነገሠ ጊዜ ስለ መቅዶንዮስ ስለ ሰባልዮስና ስለ አቡሊናርዮስ በቊስጥንጥንያ መቶ ሃምሳ ኤጲስቆጶሳትን በአንድነት ሰበሰበ። ይህም አባት በጉባኤው ውስጥ አንዱ እርሱ ነበር መናፍቃንም መመለስን እንቢ በአሉ ጊዜ ከወገኖቹ ጋር ረገማቸው አውግዞም ለያቸው።
ሃይማኖትን ያቀኑ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ በሠሩት በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም ከሚለው ቀጥሎ እንዲህ የሚል ጨመረ። "የባሕርይ ገዢ በሚሆን በሚያድን በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን። ከአብ የተገኘ ከአብ ከወልድ ጋር እንስገድለት እናመሰግነውም በነቢያት አድሮ የተናገረ።
ሐዋርያት ሰብስበው አንድ በአደረጓት ከሁሉ በላይ በምትሆን ክብርት ንጽሕት ጽንዕት ልዩ በምትሆን በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።ኃጢአት በሚሠረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን። የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም የዘላለም ሕይውት።"
ከዚህም በኋላ ይህ አባት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ። ሁለተኛም ስለ ጸሎተ ሃይማኖትና ስለ ትርጓሜው ሌላ በውስጡ ዐሥራ ስምንት ያህል ድርሳን ያለው መጽሐፍ ደረሰ። እርሱም ጥበብን እውቀትን ሁሉ የተመላ እጅግ የሚጠቅም ነው። በጵጵስናውም መንበር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከኖረ በኋላ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages