አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መጋቢት ሠላሳ በዚህች ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለተሰጠው ስለ ክብሩ ልዕልና ለከበረ መልአክ_ቅዱስ_ገብርኤል የወልደ እግዚአብሔርን ሰው የመሆኑን ዜና ያበሰረበት መታሰቢያ ነው፣ የቅዱስ_ያዕቆብ_ዘግሙድ የስጋው ፍልሰት የሆነበት ነው፣ ከእስራኤል ልጆች መሳፍንት አንዱ የሆነ የመስፍኑ_ሶምሶን መታሰቢያው ነው።
መጋቢት ሠላሳ በዚህች ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለተሰጠው ስለ ክብሩ ልዕልና ለከበረ መልአክ ለገብርኤል የወልደ እግዚአብሔርን ሰው የመሆኑን ዜና ለምትወልደው ለድንግል ማርያም እንዲአበስራት የተገባው ስለሆነ በዓሉን ልናከብር ይገባል።
ስለዚህ በዚች በከበረች ታላቅ ፀጋ በዚህ መልአክ እጅ እግዚአብሔር ይቅር ብሎናልና ፈፅሞ ልናከብረው ይገባናል። እርሱም ደግሞ ስለ ክርስቶስ መምጣትና ለዓለም ድኅነት መገደሉን ለኢየሩሳሌምም መዳኛዋ መሆኑን ስለ ወገኖቹ ከምርኮ መመለስ ሲጸልይ ለዳንኤል የነገረው ሱባዔዎችንም የወሰነለትና በሱባዔዎቹም መጨረሻ ንጹሀን የሚነጹበት የክብር ባለቤት ክርስቶስ ይመጣል ይገድሉታልም ለኢየሩሳሌምም መደኛዋ ይሆናታል ያለው ይህ መልአክ ነው።
ከዚያ በኋላም ለእስራኤል ልጆች የሚደረጉ መስዋእቶችና ቁርባኖች ይሻራሉ። የክብር ባለቤት ጌታችን ስለ ዓለሙ ሁሉ ድኅነት ለእመቤታችን ማርያም ከእርስዋ መወለዱን ይነግራት ዘንድ የተገባው አድርጎታልና ስለዚህ ሁልጊዜ የበዓሉን መታሰቢያ ልናደርግ ይገባናል። ጌታ ከጠላታችን ሰይጣን እጅ ያድነን ዘንድ ስለ እኛ እንዲማልድ በበጎ ስራ ሁሉ እንዲረዳን እንለምነው ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህችም ቀን ደግሞ ለፋርስ ንጉሥ ለሳፎር ልጅ ለንጉሥ ሰክራድ ከጭፍሮቹ ውስጥ የሆነ ሕዋሳቱን የተቆራረጠ የቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ የስጋው ፍልሰት የሆነበት ነው፡፡ ይህም ንጉሥ ሰክራድ እጅግ ይወደው ነበር ስለ መንግሥቱ ሥራ ሁሉ ከእርሱ ጋር ይማከር ነበርና ስለዚህም የቅዱስ ያዕቆብን ልቡና አዘንብሎ ፀሐይንና እሳትን እንዲአመልክ አደረገው፡፡ በሃይማኖቱም ከንጉሡ ጋር እንደተስማማ የተቀደሱ እናቱ ሚስቱና እኅቱ በሰሙ ጊዜ እንዲህ ብለው ጽፈው ወደርሱ ላኩ የቀናች የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ትተህ የፍጡራንን ጠባይ ለምን ተከተልክ እሊህም ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት እሳት ናቸው ዕወቅ ከዛሬ ጀምሮ በንጉሥ ሃይማኖት ከኖርክ እኛ ከአንተ የተለየን ነን።
የመልእክታቸውንም ጽሑፍ በአነበበ ጊዜ መሪር ልቅሶን አለቀሰ በዚህም የጥፋት ምክር ጸንቼ ብኖር ከቤተ ሰቦቼና ከወገኖቼ የተለየሁ መሆኔ ነው። ደግሞስ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እንዴት እቆማለሁ አለ ከዚህም በኋላ የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍቶች ማንበብ ጀመረ የንጉሡን አገልግሎትም ተወ ለንጉሡም ወዳጅህ ያዕቆብ እነሆ አገልግሎትህን አማልክቶችህንም ማምለክ ተወ ብለው ነገሩት።
ንጉሡም ልኮ ወደርሱ አስቀርቦ አገልግሎትህን ለምን ተውክ አለው ቅዱስ ያዕቆብም እንዲህ አለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ወንጌል በሰው ፊት ያመነብኝን ሁሉ እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ በሰው ፊት የካደኝንም በአባቴ ፊትና በመላእክት ፊት እክደዋለሁ ብሏልና ስለዚህ አገልግሎትህን ፍቅርህን አማልክቶችህንም ማምለክ ትቼ ሰማይና ምድርን ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን የሚታየውንና የማይታየውን ለፈጠረ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የምሰግድ ሆንኩ።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ ደሙ እንደ ውኃ በዝቶ እስቲፈስ ታላቅ ግርፋትን እንዲገርፉት አዘዘ እርሱ ግን ከበጎ ምክሩ አልተመለሰም ዳግመኛም ሕዋሳቱን በየዕለቱ እንዲቆርጡ አዘዘ የእጆቹንና የእግሮቹን ጣቶች ሃያውን ቆረጡ ክንዶቹንና እግሮቹን እስከ ጭኖቹ ድረስ ወደ አርባ ሁለት ቁራጭ በየጥቂቱ ቆረጡት። በሚቆርጡትም ጊዜ ሁሉ ጌታዬና ንጉሤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ዕንጨት ቅርንጫፍ ሰውነቴን በይቅርታህ ገናናነት ተቀበል የወይን አታክልት ያለው በየሦስት ዓጽቅ ሲቆርጡለት ዓጽቆቹ በዝተው ይበቅላሉ ይሰፋሉ በሚያዝያ ወር አብቦ ያፈራልና እያለ የሚዘምርና የሚያመሰግን ሆነ።
ደረቱና አካሉ እንደ ግንድ ድብልብል ሆኖ በቀረ ጊዜ ነፍሱን ለመስጠት እንደ ደረሰ አውቆ በዚያን ጊዜ በዓለም ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁሉንም ይምራቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ለመነው እንዲህም አለ ለእኔ ግን ወደ አንተ የማነሣው አካል አልቀረልኝም ሕዋሳቶቼ ተቆርጠው በፊቴ የወደቁ ስለሆነ አሁንም ነፍሴን ተቀበላት አለ።
በዚያንም ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ አረጋጋው አጸናውም ያን ጊዜ ነፍሱ ደስ አላት ነፍሱንም ከመስጠቱ በፊት ወታደሩ በፍጥነት መጥቶ የከበረች ራሱን በሰይፍ ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ሥጋውንም ምእመናን ሰዎች ወስደው በመልካም አገናነዝ ገነዙትና በንጹሕ ቦታ አኖሩት። እናቱ ሚስቱና እኅቱ በሰማዕትነት እንደሞተ በሰሙ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው ወደ ቅዱስ ያዕቆብም ሥጋ መጥተው ተሳለሙት አለቀሱለትም የከበሩ ልብሶችንም በላዩ አኖሩ ጣፋጮች የሆኑ ሽቱዎችንም ረጩበት።
በደጋጎች ነገሥታት በአኖሬዎስና በአርቃዴዎስ በሌሎችም ዘመን አብያተ ክርስቲያን ታነፁ ገዳማትና አድባራትም ተሠሩ የሰማዕታትንም ሥጋ በውስጣቸው አኖሩ ታላላቆች ድንቆች ተአምራትም ከእሳቸው የሚታዩ ሆኑ። የፋርስ ንጉሥም ሰምቶ በቦታው ሁሉ የሰማዕታትን ሥጋ ያቃጥሉ ዘንድ አዘዘ በሚገዛውም አገር ውስጥ ምንም ምን እንዳይተው አማንያን ሰዎችም መጥተው የቅዱስ ያዕቆብን ሥጋ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት ከዚያም ወደ ሀገረ ሮሀ ከሀገረ ሮሀም የከበረ ኤጲስቆጶስ ጴጥሮስ ወደ ግብጽ አገር ወደ ብሕንሳ ከተማ ወሰደው። በዚያም ጥቂት ጊዜ ኖረ ከርሱ ጋርም መነኰሳት ነበሩ ከቀኑ እኩሌታም ሲጸልዩ የቅዱስ ያዕቆብ ሥጋ ከብዙ የፋርስ ሰማዕታት ሥጋ ጋር በአለበት ሰማዕታት አብረዋቸው ዘመሩ ባረኳቸውም ቅዱስ ያዕቆብም እግዚአብሔር እንዳዘዘ ሥጋዬ በዚህ ይኑር አለ ከዚህም በኋላ ተሠወሩ።
ከዚህም በኋላ የከበረ ኤጲስቆጶስ ጴጥሮስ ወደ አገሩ ሊመለስ በወደደ ጊዜ ሥጋዬ በዚህ ቦታ ይኑር ያለውን የቅዱስ ያዕቆብን ቃል ተላልፎ የቅዱስ ያዕቆብን ሥጋ ወሰደ በዚያንም ጊዜ አስቀድሞ ወደ አመለከተው ቦታ ከእጆቻቸው መካከል ተመለሰ ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ተአምራት ተገለጡ ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_ሶምሶን (መስፍነ እስራኤል)
በዚህችም ዕለት ደግሞ ከእስራኤል ልጆች መሳፍንት አንዱ ሶምሶን መታሰቢያው ነው። የዚህም ፃድቅ የአባቱ ስም ማኑሄ ይባላል ከነገደ ዳን ነው እናቱም መካን ነበረች የእግዚአብሔርም መልአክ ወደርስዋ መጥቶ ከርስዋ ልጅ መወለዱን ነገራት። የወይን ጠጅ የማር ጠጅ ከመጠጣት ለመስዋዕት የማይሆን ርኲስ የሆነውን ሁሉ ከመብላት እንድትጠነቀቅ አዘዛት።
ያም ሕፃን ከእናቱ ማሕፀን ከተወለደ ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ገንዘቡ ነውና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት እርሱም እስራኤልን ከኢሎፍላውያን እጅ ሊያድናቸው ይጀምራል አላት። የእግዚአብሔር መልአክም ያላትን ለባሏ በነገረችው ጊዜ ያንን መልአክ ያሳየው ዘንድ እርሱም ወደ እግዚአብሔር ለመነ። ልመናውንም ሰማው። የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጦለት ለሚስትህ ያዘዝኳትን እንድትጠነቀቅ እዘዛት አለው።
ከዚህ በኋላም ፀንሳ ይህን ፃድቅ ሰው ወለደችው እግዚአብሔርም ባረከው የእግዚአብሔርም መንፈሰ ረድኤት አድሮበት ከኃይል ጋር ተወለደ። ሕፃኑም አድጎ ጎለመሰ በአንዲት ዕለትም አንበሳ ሊበላው በእርሱ ላይ ተነሳ የእግዚአብሔርም መንፈስ አደረበትና የፍየል ጠቦትን አንሥተው እንዲጥሉ አንሥቶ ጣለው በእጁም ውስጥ እንደ ኢምንት ሆኖ ገደለው።
ሁለተኛም ስለ ሚስቱ በተቆጣ ጊዜ ሶምሶን ሂዶ በሩጫ ሦስት መቶ ቀበሮዎችን ያዘ። ችቦ አምጥቶ በጅራታቸው አሠረ በሁለቱም ጅራቶቻቸው መካከል አንድ አንድ ችቦ አደረገ። በዚያም ችቦ እሳትን አቀጣጥሎ ወደ ኢሎፍላውያን አዝመራ ሰደዳቸው። የታጨደውን ክምርና እሸቱን ነዶውንም የዘይቱንና የወይኑንም ቦታዎች አቃጠሉ። ሊጣሉትም በተነሱበት ጊዜ ጭን ጭናቸውን ሰበራቸው ብርቱ ሰልፍም ተደርጎ ብዙ ሰዎችን ገደለ ወርዶም በዋሻ ውስጥ ተቀመጠ።
ስለዚህም ኢሎፍላውያን ወደ ይሁዳ ዘምተው የአህያ መንጋጋ በአለበት ሰፈሩ። የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ወደ እኛ ለምን ዘመታችሁ አሉአቸው ኢሎፍላውያንም ሶምሶንን እናስረው ዘንድ እንዳደረገብንም እናደርግበት ዘንድ መጣን አሉ።
ከይሁዳም ሦስት ሺህ ሰዎች በኤጣም ወዳለች ዋሻ ወርደው ሶምሶንን ኢሎፍላውያን እንዲገዙን አታውቅምን በእኛ ለምን እንዲህ አደረግህ አሉት። ሶምሶንም በእናንተ እንዳደረጉባችሁ እኔም በእነሳቸው እንደዚያው አደረግሁባቸው አላቸው።
አሥረን ለኢሎፍላውያን ልንሰጥህ መጣን አሉት ሶምሶንም እናንተ እንዳትገድሉኝ ማሉልኝ ለእነሱ አሳልፋችሁ ስጡኝ እናንተ ግን እኔን በጠብ አትገናኙኝ አላቸው እነሱም ማሉለት።
በሁለት አዲስ ገመዶች አስረው ከዚያች ዋሻ አወጡት አሳልፈውም ሰጡት ኢሎፍላውያንም ደነፉ ሊቀበሉትም ሮጡ የእግዚአብሔርም መንፈሰ ረድኤት አደረበት በክንዱ ያሉ ገመዶች ገለባ እሳት በበላው ጊዜ እንዲያር እርር ኩምትር አሉ እሥራቱም ከክንዱ ተፈታለት የአህያ መንጋጋ አጥንት በጎዳና ወድቆ አገኘ እጁን ዝቅ አድርጎ አነሣት በዚያችም ሺህ ሰዎችን ገደለባት።
ከዚህም በኋላ ውኃን እጅግ ተጠማ ወደ እግዚአብሔርም ጮኸ ይህን ታላቅ ድኅነት በእኔ በባሪያህ እጅ አደረግህ አሁን ግን በውኃ ጥም እሞታለሁ በእነዚህም በቁላፋን እጅ አወድቃለሁ አለ።
እግዚአብሔርም ከዚያች የአህያ መንጋጋ ውኃን አፈለቀለት ያንንም ጠጥቶ ነፍሱ ተመለሰችለት።እስራኤልንም ሃያ ዓመት አስተዳደራቸው። ከዚህም በኋላ ሶምሶን ከዚያ ተነስቶ ወደ ጋዛ ሔደ በዚያም ሚስት አግብቶ ተቀመጠ። ለጋዛም ሰዎች ሶምሶን ወደዚህ መጣ ብለው ነገሩዋቸው በከተማውም በር መላ ሌሊቱን ሁሉ ከበው ሲጠብቁት አደሩ ሌሊቱን ሁሉ ስንጠብቀው አድረን ጠዋት እንግደለው አሉ።
ሶምሶንም እስከ ሌሊቱ እኩሌታ ተኛ ከዚያም በኋላ ተነስቶ በከተማው በር ያሉ የመጠበቂያውን ደጃፍ ሁለቱን የመቃን መድረኮች ያዘ ከሰዎቹ ሁሉ ጋራ በትከሻው ተሸክሞ በኬብሮን አንጻር ወዳለ ተራራ አውጥቶ በዚያ ጣላቸው።
ከዚህም በኋላ በሦራህ ወንዝ አጠገብ የምትኖር ሴትን ወደደ ስምዋም ደሊላ ነው። እርሷንም አግብቶ በዚያ ተቀመጠ። የኢሎፍሊ ሹማምንትም ወደርሱዋ ወጥተው አታሊልን ኃይሉ በምን እንደሆነ በምንም እንድንችለውና እናደክመው ዘንድ በምንም እንድናሥረው ዕወቂ እኛ ሺው ሰዎች ሽህ ብር እንሰጥሻለን አሏት። ደሊላም ሶምሶንን ኃይልህ ጽኑ መሆኑ በምን እንደሆነ ንገረኝ በምንስ ቢያሥሩህ ትደክማለህ አለችው። ሶምሶንም ሦስት ጊዜ ሸነገላት ደሊላም አወድሻለሁ ልቤም ከአንቺ ጋራ ነው ለምን ትለኛለህ እነሆ ስትሸነግለኝ ይህ ሦስተኛህ ነው ኃይልህ ጽኑ መሆኑ በምን እንደሆነ አልነገርከኝም አለችው።
ከዚህ በኋላ መላ ሌሊቱን በነገር ባደከመችው ጊዜ ልሙት ብሎ እስቲበሳጭ ድረስ ዘበዘበችው። በልቡ ያለውን ሁሉ ነገራት እኔ ለእግዚአብሔር የስለት ልጅ ነኝና ከእናቴ ማሕፀን ከተወለድኩ ጀምሮ ምላጭ ራሴን አልነካኝም ጠጉሬን ከተላጨሁ ኃይሌ ተለይቶኝ እደክማለሁ ከሰውም እንዳንዱ እሆናለሁ አላት።
የልቡን ሁሉ እንደገለጠላት በአወቀች ጊዜ በጭኖቿ መካከል አስተኝታ ሲያንቀላፋ ጠጉር ቆራጭ ጠቀሰች ሰባቱንም የራሱን ብርጉዎች ቆርጣ ጠጉሩን ላጨች እርሱም ይደክም ጀመር ኃይልም ተነሣው።
ኢሎፍላውያንም ይዘው ሁለት ዐይኖቹን አወጡአቸው ወደ ጋዛንም አውርደው በእግር ብረት አሰሩት በግዞትም ሆኖ እህልን ይፈጭ ነበር። ከዚህም በኋላ የኢሎፍሊ አለቆች ለጣዖታቸው መስዋዕት ሊሰዉ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም በአዩት ጊዜ ጣዖታቸውን አመሰገኑት አገራችንን ያጠፋት ሬሳዎቻችንን ያበዛ ጠላታችንን በእጃችን ጣለው አሉ።
ከዚህ በኋላ በልተው ጠጥተው ደስ ባላቸው ጊዜ በፊታችን ይጫወት ዘንድ ሶምሶንን ከግዞት ቤት ጥሩት አሉ ጠርተው አምጥተውም ተዘባበቱበት በሁለት ምሰሶዎች መካከልም አቆሙት። ሶምሶንም የሚመራውን ብላቴና አሳርፈኝ ይህ ቤት የቆመባቸው ምሰሶዎችንም አስጨብጠኝ ወደነሳቸውም አስጠጋኝ አለው ያም የሚመራው ብላቴና እንዳለው አደረገለት።
በዚያ ቤት ወንዶችም ሴቶችም መልተው ነበር የኢሎፍሊ ሹማምንትም ሁሉ በዚያ በሰገነት ነበሩ ሶምሶን ሲጫወት ያዩት ዘንድ የተሰበሰቡ ወንዶችም ሴቶችም ሦስት ሽህ ይሆኑ ነበር።
ሶምሶንም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ አቤቱ አቤቱ አስበኝ አንዲት ነገርንም አድምጠኝ እንግዲህ ስለ ሁለቱ ዐይኖቼ ፈንታ ከኢሎፍላውያን አንዲት በቀልን ልመልስ አለ። ሶምሶንም ያ ቤት በላያቸው የተደገፈባቸው በመካከል ያሉ እነዚያን ሁለት ምሶሶዎች ያዛቸው አንዲቱን በቀኙ አንዲቱንም በግራው ይዞ ገፋቸው።
ሶምሶንም ሰውነቴ ከኢሎፍሊ ሰዎች ጋራ ትሙት ብሎ በኃይሉ ነቀነቃቸው ያም ቤት በውስጡ ባሉ በሕዝቡ ላይና በኢሎፍሊ ሹማምንት ላይ ወደቀባቸው የሞቱትም እንዲህ ሆኑ ሶምሶን በሕይወቱ ሳለ ከገደላቸው ሲሞት የገደላቸው በዙ። ያባቱ ወገኖች ሁሉና ወንድሞቹ ወርደው በድኑን አነሱ ወስደውም በአባቱ በማኑሔ መቃብር ቀበሩት፡፡
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment