ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, May 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 10

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ዐሥር በዚች ቀን የከበሩ ጻድቃን_ሠለስቱ_ደቂቅ አናንያ አዛርያ ሚሳኤል የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው፣ የከበረ አባት ቅዱስ_አብርሃም_ ፀራቢ በሰማዕትነት አረፈ፣ የአባ_ሚካኤል መታሰቢያውና ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ሆነ።


ግንቦት ዐሥር በዚች ቀን የከበሩ ጻድቃን ሠለስቱ ደቂቅ አናንያ አዛርያ ሚሳኤል የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። እሊህም ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮአቄም ልጆቹ ናቸው ዳንኤልም የእኅታቸው ልጅ ነው በምርኮ ጊዜም ከእስራኤል ልጆች ጋራ ተማርከው ወደ ባቢሎን ወረዱ።
ከእስራኤል ልጆች ምርኮ ውስጥ በመብልና በመጠጥ እያስተማረ አሳድጎ በሠራዊቱ መካከል ጭፍሮቹ ያደርጋቸው ዘንድ ነውር ነቀፋ የሌለባቸውን ወጣቶች ንጉሥ መረጠ። እሊህም ከተመረጡት ውስጥ የተቆጠሩ ሆኑ የእኅታቸው ልጅ ዳንኤልም። ምግባቸውን በሚሰጡአቸው ጊዜ አረማውያን ከአረዱአቸው ውስጥ መብላትን አልወደዱም ከንጉሥ ማዕድም ከሚመጣ ከሥጋው እንዳያበላቸውና እንዳያጠጣቸው አለቃውን ለመኑት።
እግዚአብሔርም በባለሟሎች አለቃ ፊት ቸርነቱን አደረገላቸው። የባለሟሎች አለቃም ንጉሡ ጌታዬን እፈራዋለሁ የምትበሉትንና የምትጠጡትን ምግባችሁን ስለ አዘዘ ከባልንጀሮቻችሁ እናንተን ከስታችሁ ቢያያችሁ ንጉሥ ራሴን ይቀጣኛል አላቸው።
በእነርሱ ላይ የተሾመ አሚሳድን እንዲህ አሉት እኛን ባሮችህን ዐሥር ቀን ፈትነን ከምድር ዘር ሽምብራን ይስጡን እንበላ ዘንድ ውኃንም እንጠጣ ዘንድ። ቃላቸውንም ሰምቶ ዐሥር ቀን ፈተናቸው ዐሥር ቀንም ከአለፈ በኋላ የንጉሡን ማዕድ ከሚመገቡ ከእነዚያ ልጆች ይልቅ ሰውነታቸው ወፍሮ መልካቸውም አምሮ ታየ።
ከዚህ በኋላ አሚሳድ የሚበሉትን ምግብ የሚጠጡትን ወይን እየወሰደ ለአራቱ ሁሉ ልጆች ሽምብራ ይሰጣቸው ነበር። እግዚአብሔርም ዕውቀትንና ጥበብን መጻሕፍትን በማንበብ ሁሉ ማስተዋልን ሰጣቸው። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ያዘዘው ቀን በተፈጸመ ጊዜ ወደርሱ አመጡአቸው የባለሟሎችም አለቃ ወደ ንጉሡ ወደ ናቡከደነፆር አገባቸው።
ንጉሡም ጠየቃቸው በሰው ሁሉ ዘንድ እንደ አናንያና እንደ ዳንኤል እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም በንጉሡም ፊት ቆሙ። ንጉሡም የፈለገውን የምክርና የጥበብን ነገር ሁሉ በግዛቱ ካሉ ጠንቋዮችና አስማተኞች ሰዎች ሁሉ ይልቅ በነሳቸው ዘንድ ዐሥር እጥፍ አገኘ። ንጉሡም እጅግ ወደዳቸው በባቢሎን አገር ሁሉ ላይ ገዢዎች አድርጎ ሾማቸው።
ንጉሥም ጣዖትን ከወርቅ ባሠራ ጊዜ ሰዎችን ሁሉ እንዲሰግዱለት አዘዛቸው። ሦስቱ ልጆችም ለዚያ ጣዖት ባልሰገዱ ጊዜ የሚቀኑባቸው ወደ ንጉሥ ነገር ሠርተው በንጉሥ ፊት አቀረቧቸው ስለ አልሰገዱለትም ጠየቃቸው እነርሱም እኛስ ለሠራኸው ለወርቅ ምስል አንሰግድም አሉት። ንጉሥም ተቆጥቶ ከምትነድ የእሳት ምድጃ ውስጥ ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ።
እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ የእሳቱን ነበልባል አጠፋው በጥዋት ጊዜ እንደሚቀዘቅዝ በእሊህ በሦስቱ ልጆች ዘንድ እንደ ጥዋት ውኃ ቀዝቃዛ አደረገው። ከዚያም የእሳቱ ነበልባል አርባ ዘጠኝ ክንድ ያህል ከፍ ከፍ ብሎ በውጪ ያሉትን አቃጠላቸው እሊህን ሠለስቱ ደቂቅን ግን ምንም አልነካቸውም።
ንጉሥም ይህን ድንቅ ሥራ አይቶ በፊታቸው ሰገደ። የሰማይና የምድር ፈጣሪ እግዚአብሔርንም አመነ ለእሊህም ልጆች ሹመታቸውን ከፍ ከፍ አድርጎ ክብርን ጨመረላቸው። ከዚህም ዓለም የሚወጡበት ጊዜ ሲደርስ በበዐታቸው እየጸለዩ ሳሉ ሰግደው ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ።
ወዲያውኑ ታላቅ ንውጽውጽታ በባቢሎን አገር ሆነ። ንጉሡም ፈርቶ ስለ ምን ይህ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ ብሎ ዳንኤልን ጠየቀው ነቢይ ዳንኤልም ይህ ሦስቱ ልጆች ስለ አረፉ ከዓለም ለመውጣታቸው ምልክት ነው ብሎ ነገረው። ንጉሡም ወደርሳቸው ደርሶ ታላቅ ኀዘንን አዘነ ከዝሆን ጥርስም ሦስት ሣጥኖችን እንዲሠሩላቸው በሐር በግምጃ ልብሶች ገንዘው ቅዱሳኑን በሣጥኑ ውስጥ እንዲያኖሩአቸው አዘዘ ንጉሡ እንዳዘዛቸውም አደረጉ።
ሁለተኛም የወርቅ ሣጥን ሠርተው እርሱ በሚሞት ጊዜ ሥጋውን በውስጡ አድርገው በከበሩ ሠለስቱ ደቂቅ መካከል እንዲያኖሩት አዘዘ እንዲሁም አደረጉለት።
ከዚህ በኋላ የከበረ አባት አባ ቴዎፍሎስ በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና በተሾመበት ወራት በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ሠራ ሥጋቸውን ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን ሊያመጣ ወዶ ሥጋቸውን እንዲያመጣለት አባ ዮሐንስ ሐፂርን ወደ እርሳቸው ሀገረ ባቢሎን ላከው።
ወደ ባቢሎን ሀገርም በደረሰ ጊዜ ወንዞቿን አየ በውስጧ ከቶ ሰው አልነበረም የወርቁ ምስልም በዚያ አለ። ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክም የቅዱሳን ሥጋ ወደአለበት አደረሰው የንጉሡም ሥጋ በመካከላቸው ነበረ። ሥጋቸው በአለበትም ቦታ ሰገደ። እንዲህም ብሎ በማልቀስ ጸለየ የከበራችሁ አባቶቼ ሆይ የከበረ አባት ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ በስማችሁ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ሥጋችሁን በውስጧ ሊያኖር እኔን ልኮኛልና ከእኔ ጋራ ትሔዱ ዘንድ ፈቃዳችሁ ይሁን።
በዚያን ጊዜ እንዲህ የሚል ቃል ከሥጋቸው ወጣ ለሃይማኖት አባት ለአባ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው የድካምህን ዋጋ እግዚአብሔር ይስጥህ ነገር ግን እኛን እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ሥጋዎቻችን ከንጉሡ ሥጋ እንዳይለዩ እግዚአብሔር ስለአዘዘን ከዚህ አንወጣም ድካሙንም ከንቱ አናደርግም። ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትከብርበት ዕለት በሌሊት መብራቶችን ይሰቅሉ ዘንድ እንዲአዝ በውስጣቸውም ዘይትና ፈትል እንዲያደርጉ በእሳት ግን አይለኩሱአቸው። እኛም ከዚያ ደርሰን በእኛ የእግዚአብሔር ኃይል በዚያ ይገለጣል ብለህ ንገረው አሉት።
አባ ዮሐንስ ሐፂርም ተመልሶ እንደነገሩት እንዴትም እንዳዘዙት ሁሉንም ለአባ ቴዎፍሎስ ነገረው እርሱም ሠለስቱ ደቂቅ እንዳዘዙ አደረገ። በዚችም በግንቦት ወር በዐሥር ቀን ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትከብርበት ሌሊት የከበሩ ሠለስቱ ደቂቅ ተገለጡ ያለ እሳትም መብራቶችን አበሩ ሊቀ ጳጳሳቱና ለዚህ ጸጋ የታደሉ ሁሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ እርከን ላይ ሲዞሩ ሠለስቱ ደቂቅን አዩአቸው በየአይነቱ በሆነ ደዌ የታመሙ ብዙ በሽተኞችም ከቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ መገለጥ የተነሣ ያን ጊዜ ተፈወሱ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን አብርሃም ፀራቢ በሰማዕትነት አረፈ፡፡ ይህም ቅዱስ የሰማዕት ቴዎድሮስ ገዳም ተብላ ከምትጠራ ከመርቅያስ አገር ሰዎች ነው።
ወላጅ እናቱም የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስን ሃይማኖት እንዲማር ለመምህር ሰጠችው። ጌታችንም ዐይነ ልቡናውን ገልጦለት ትምህርቱን ሁሉ የቤተ ክርስቲያንንም ሕግ ተማረ።
ከዚህም በኋላ መጾም መጸለይና መስገድ ጀመረ ዘጠኝ ዓመትም በሆነው ጊዜ ከደንጊያ የሚሠራ የውኃ መሔጃ መጥረብን ተማረ በዚህም ብዙ ገንዘብ አከማቸ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች የሚመጸውት ሆነ። በአንዲት ዕለትም በሌሊት ሲጸልይ የዚችን ዓለምና በውስጧ ያለው ሁሉ ኃላፊ መሆኑን አሰበ። የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ ስም ምስክር ሆኖ መሞትን ወደደ።
በዚያንም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት ሰላምታም ሰጥቶት ጽና አትፍራ አንተ ጠላቶችህን ድል አድርገህ የሰማዕትነትን አክሊል ትቀበላለህና አለው።
ከዚህም በኋላ የክርስትና ጥምቀትን ወደ ተጠመቀባት ወደ ቅዱስ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ በሥዕሉ ፊት ቁሞ ጸለየ። በርሱም ዘንድ ሰውነቱን አደራ አስጠበቀ ወደ መኰንኑም ወጥቶ ክርስቲያን እንደ ሆነ ታመነ። ያንጊዜም ከከባዶች እንጨቶች ጋራ የኋሊት አሥረው ከረኃብና ከጽምዕ ጋራ ከፀሐይ ውስጥ ጣሉት። መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ጌታችን ተገለጠለት። ሰላምታም ሰጠው ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግም ቃል ኪዳን ሰጠው።
ከዚህ በኋላም መኰንኑ ራሱን እንዲቆርጡት አዘዘ በቆረጡትም ጊዜ ራሱ እኔ ክርስቲያን ነኝ እያለች ሦስት ጊዜ በተራራው ላይ በረረች ሃምሳ ምዕራፍ ያህልም ሒዳ ከባሕር ወደቀች ።
ከዚህም በኋላ ሆዱን ሰንጥቀው ባሩድና ሙጫ ዘይትን መልተው ከእሳት ውስጥ ጣሉት። እሳቱ ግን ምንም አልነካውም ከዚህም በኋላ በየጥቂቱ ከትፈው በእንቅብ አድርገው ከባሕር ውስጥ ጣሉት። በእግዚአብሔርም ፈቃድ ከራሱ ጋራ አንድ ሆኖ እንደ ቀድሞው እስና በሚባል አገር በባሕሩ ወደብ ታየ ምእመናንም ወስደው በታላቅ ክብር ቀበሩት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የአባ ሚካኤል መታሰቢያውና ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ሆነ። የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ ክርስቲያን ባለጸጎች ናቸው ልጅ ባጡ ጊዜም የክብር ባለቤት ወደ ሆነ እግዚአብሔር ለመኑ እርሱም ይህን የተቀደሰ ልጅ ሰጣቸው የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት አስተማሩት።
ወላጆቹም በሞቱ ጊዜ የዚያች አገር ኤጲስቆጶስ ገንዘቡን አስጠበቀለት ዐሥራ ሁለት ዓመትም ሲሆነው የዚህን ዓለም ኃላፊነት አስቦ ወደ አባ ይስሐቅ ገዳም ሒዶ የምንኲስና ልብስ እንዲያለብሰው ፈለገ። እርሱም ከፈተነውና ብርታቱን ከአየ በኋላ አለበሰው የእግዚአብሔርም ጸጋ አደረበት የፊቱ መልክ ተለውጦ እንደ ደረቅ እንጨት እስኪሆን በጾምና በጸሎት ሰውነቱን አስጨነቀ።
በአንዲት ዕለትም አባቱ አባ ይስሐቅ ወደ አባ ሚካኤል በዓት ሔደ መልኩ እንደ ሞተ ሰው ሆኖ አይቶት አለቀሰ። ልጄ ሆይ እንዴት እንዲህ ሥጋህ ተጎዳ አለው እርሱም አባቴ ሆይ አታልቅስ እግዚአብሔር አልተወኝምና ለመቆምም ኃይሌ አልደከመምና ነገር ግን በሕልሜ ያየሁትን ልንገርህ እኔን የሚፈልጉ የንጉሥ መልእክተኞች ከእስክንድርያ ወደ አንተ ሲመጡ እኔን አትከልክላቸው አንተን እንዳይወቅሱ። በሁለተኛውም ዓመት ታላቅ ረኃብ ይመጣል ምድርንም ያጠፋታልና ለልጆችህ ምግባቸውን አዘጋጅ ብሎ መለሰለት።
ከወራትም በኋላ በንጉሥ ጭፍራ አምሳል ሰዎች አባ ሚካኤልን እየፈለጉ መጥተው አባ ይስሐቅን ያዙት ሚካኤልንም በአገኙትና በአወቁት ጊዜ ከእሳቸው ጋራ ወሰዱት መነኰሳቱም እያዘኑ ቀሩ።
ረኃብም በሆነ ጊዜ አገረ ገዥው በዚያ ገዳም እህል እንዳለ ሰምቶ ሊከባቸው ፈለገ። አባ ይስሐቅም ሊማልድ ወደ መኰንኑ መጣ ያንጊዜም ብዙ ጭፍሮች ከሰይፎች ጋራ ከዚያ ገዳም ወጥተው መኰንኑ እያደነቀ አባ ይስሐቅን ወሰዱት።
ከዚህም በኋላ አባ ሚካኤል መጥቶ ራሱን ገለጠለት እነዚያ የወሰዱት ሰዎች የሰማይ ሰራዊት እርሱን የወሰዱበት አገርም ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እንደሆነች ነገረው።
ከዚህም በኋላ ኤጲስቆጶሱ በአስጠበቀለት ገንዘቡ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራለት አዘዘው በዚያች በበዓቱ ላይ ሠራለትና በዚች ዕለት አከበሩዋት። ደግሞም አባ ሚካኤል ለአባ ይስሐቅ ተገልጾ በመጪው ዓመት እንደሚሞት ነገረው እንደቃሉም ሆነ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages