ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, May 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 11

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ዐሥራ አንድ በዚህች ዕለት የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ቅዱስ_ያሬድ የተሰወረበት ነው፣ የቅዱስ ዮስጦስ ሚስት ቅድስት_ታውክልያ በሰማዕትነት አረፈች፣ የከበረ ኤጲስቆጶስ አባ_በፍኑትዮስ አረፈ፣ የባሌ መምህር አባ_አሴር በሰማዕትነት አረፈ፣ አቡነ_ኤልያስ ዘውቅሮ መታሰቢያቸው ነው፣ በዲዮቅልጥያኖስ መንግሥት ዘመን ቅዱስት_ኤፎምያ በሰማዕትነት አረፈች፣ ቅድስት_አናሲማ አረፈች፡፡


ግንቦት ዐሥራ አንድ በዚህች ዕለት የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ያሬድ የተሰወረበት ነው። ይህም ቅድስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን ነው እርሱም በኢትዮጵያ አገር ከታነፁ አብያተ ክርስቲያን ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተሰበከና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት።
ይህም አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊአስተምረው በጀመረ ጊዜ መቀበልም ማጥናትም እስከ ብዙ ዘመን ተሳነው። በአንዲት ዕለትም መምህሩ በእርሱ ላይ ተበሳጭቶ መትቶ አሳመመው። ያሬድም ሸሽቶ ከዱር ውስጥ ገባ ከኀዘኑም ብዛት የተነሣ ከዛፍ ሥር ተጠለለ። ወደ ዛፉ ላይም ትል ሲወጣ አየ ትሉም ከዛፉ እኩሌታ ደርሶ ይወድቅ ነበረ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከአደረገ በኋላ በጭንቅ ከዛፉ ላይ ወጣ።
ቅዱስ ያሬድም የትሉን ትጋት በአየ ጊዜ ወደ መንፈሳዊ መምህሩ ተመልሶ አባቴ ሆይ ይቅርታ አድርግልኝና እንደ ወደድክ አድርገኝ አለው መምህሩም ተቀበለው።
ከዚህ በኋላ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር በለመነ ጊዜ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት በአጭር ጊዜ የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን ተምሮ ፈጸመ ዲቁናም ተሾመ።
በዚያም ወራት እንደ ዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማኅሌት የለም ነበር በትሑት እንጂ። እግዚአብሔርም መታሰቢያ ሊአቆምለት በወደደ ጊዜ ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን ላከለት እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ከእሳቸው ጋራ አወጡት በዚያም ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማኅሌታቸውን ተማረ።
ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ጊዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን በሦስት ሰዓት ገባ በታላቅም ቃል ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ የጽዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ። ዳግመኛም እንዴት እንደሚሠራት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው አለ።
ይቺንም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት። የቃሉንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ንጉሡም ንግሥቲቱም ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ የመንግሥት ታላቆችና ሕዝቡ ሁሉ ወደርሱ ሮጡ ሲሰሙትም ዋሉ።
ከዚያም በኋላ ከዓመት እስከ ዓመት በየክፈለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ በመጸውና በጸደይ በአጽዋማትና በበዓላት በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በዓል በነቢያትና በሐዋርያት በጻድቃንና በሰማዕታት በደናግልም በዓል የሚሆን አድርጎ በሦስቱ ዜማው ሠራ ይኸውም ግዕዝ ዕዝል አራራይ ነው።
የሰው ንግግር የአዕዋፍ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ከዚህ ከሦስቱ ዜማው አይወጣም።
በአንዲት ዕለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉሥ ገብረ መስቀል እግር በታች ቁሞ ሲዘምር ንጉሡም የያሬድን ድምፅ እያዳመጠ ልቡ ተመሥጦ የብረት ዘንጉን በያሬድ እግር ላይ ተከለው ከእርሱም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ያሬድም ማኅሌቱን እስከ ሚፈጽም አልተሰማውም።
ንጉሡም አይቶ ደነገጠ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ ስለ ፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለግኸውን ለምነኝ ብሎ ለያሬድ ተናገረው ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው። ንጉሥም በማለለት ጊዜ ወደገዳም ሔጄ እመነኲስ ዘንድ አሰናብተኝ አለው ንጉሡም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋራ እጅግ አዘነ ተከዘም እንዳይከለክለውም መሐላውን ፈራ እያዘነም አሰናበተው።
ከዚህ በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ፈጽሞ የከበረሽና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍም ያልሽ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽ የሚለውን ምስጋና እስከ መጨረሻው በተናገረ ጊዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ።
ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሒዶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ። እግዚአብሔር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጥቶታል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የቅዱስ ዮስጦስ ሚስት ቅድስት ታውክልያ በሰማዕትነት አረፈች። በየካቲት ዐሥር እንደ ተጻፈ የእስክንድር ገዢ እርስበርሳቸው ከአለያያቸው በኋላ ቅድስት ታውክልያን ወደ ሀገረ ፃ ወሰዱዋት። በሀገረ ፃ መኰንንም ፊት የመኰንኑ እስክንድርያን መልእክት በአነበቡ ጊዜ መንግሥታቸውን ትተው እንዴት ከመንግሥታቸው ሞትን መረጡ ብሎ አደነቀ።
ከዚህ በኋላ መኰንኑ ሸነገላት ብዙ ታላላቅ ቃል ኪዳኖችንም ገባላት። የከበረች ታውክልያም እኔ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር መንግሥቴን ተውኩ ከልጅነት ባሌም ተለየሁ በልጆቼም አልተጽናናሁም ለመሆኑ አንተ የምትሰጠኝ ስጦታ ምን ያህል ነው ብላ መለሰችለት።
ይህንንም ሰምቶ ታላቅ ግርፋት እንዲገርፉዋት አዘዘ የሥጋዋም ቊርበት እስከሚቆራረጥ ገረፉዋት። ከዚህ በኋላም ከእሥር ቤት አስገቡዋት የእግዚአብሔርም መልአክ ተገለጠላትና ቊስሎቿን አዳናት።
እሥረኞችም አይተው አደነቁ ብዙዎቹም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት አገፉ።የምስክርነቷ ፍጻሜ በቀረበ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ለከበረች ታውክልያ ተገልጾላት አጽናናት ከክብር ባለቤት ጌታችንም የተሰጡዋትን ቃል ኪዳኖች ነገራት።
በዚያን ጊዜም ራስዋን ይቆርጡ ዘንድ መኰንኑ አዘዘ የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች። ምእመናን ሰዎች መጥተው ለወታደሮች ብር ሰጥተው የቅድስትን ሥጋ ወሰዱ በመልካም መግነዝም ገንዘው የስደቱ ወራት እስኪፈጸም በሣጥን ውስጥ አኖሩዋት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበረ ኤጲስቆጶስ አባ በፍኑትዮስ አረፈ። ይህም ከታናሽነቱ በአባ መቃርስ ደብር በአስቄጥስ ገዳም መነኰሰ ታላቅ ተጋድሎንም በመጋደል ብዙ ትሩፋትን ሠራ። አዘውትሮ ይጾም ነበረ ቅጠላቅጠልን ይበላል እንጂ በእሳት የበሰለ አይበላም በገዳሙ ውስጥም መጻሕፍትንና የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ተምሮ ቅስና ተሾመ በዚያም ሠላሳ አምስት ዓመት ኖረ። እነሆ ትሩፋቱና ጽድቁም በሁሉ ዘንድ ታወቀ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ፊላታዎስም ልኮ ወደ እርሱ አስመጥቶ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾመው።
ኤጲስቆጶስነትም ከተሾመ በኋላ ቅዳሴ በሚቀድስ ጊዜ ካልሆነ በቀር ከቶ ልብሱን አልለወጠም ቅዳሴውንም ሲፈጽም ከጠጉር የተሠራውን ማቅ ይለብሳል።
እንዲህም የሚጋደልና የሚጸመድ ሆኖ ኖረ በዚህ ሁሉ ዘመንም ከመነኰሳት ጋራ ያገለግል ነበረ በታመመ ጊዜም እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል ጠየቀው። የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ኢጲስቆጶስነት ስለተሾምኩ ጸጋህን በውኑ ከኔ ታርቃለህን ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክም ወደርሱ መጥቶ አስተውል ዕወቅ አንተ በገዳም ሳለህ በታመምክ ጊዜ የሚጎበኝህ የለም ወይም የሚአገለግልህና ለደዌህ መድኃኒትን የሚሰጥህ አታገኝም ነበር። ሰለዚህ እግዚአብሔር የሚረዳህና ደዌውንም ከአንተ የሚያርቅልህ ሆነ። ዛሬ ግን እነሆ አንተ በዓለም ውስጥ ነህ በአንተ ዘንድ የሚጐበኝህና የሚአገለግልህ አለ ለደዌህም መድኃኒትን የምትሻውንም ምግብ ታገኛለህ አለው።
ይህም አባት በኤጲስቆጶስነት ሹመት ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ የሚያርፍበትም በቀረበ ጊዜ ካህናቱንና ዲያቆናቱን መምህራኑን ጠራቸው። የአብያተ ክርስቲያናትንም ንዋየ ቅዱሳታቸውንና ገንዘባቸውን ሁሉ ሰጣቸው እንዲህም አላቸው ዕወቁ እኔ ወደ እግዚአብሔር እሔዳለሁና እንደሚገባም በመካከላችሁ እንደ ኖርኩ እናንተ ታውቃላችሁ። ለኤጲስቆጶስነት ሹመቴም እጅ መንሻ ከሚአመጡልኝ እንኳ አንድ የብር አላድ እንዳልሠወርኩ በፊቱ ልቆም ያለኝ የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኔ ላይ ምስክርን ይሁን አላቸው።
ይህንም ሰምተው አለቀሱ ተሳለሙትም እንዲባርካቸውና በክብር ባለቤት ጌታችንም ዘንድ መራዳቱን እንዳይረሳ ለመኑት እርሱም ባረካቸው። እግዚአብሔርም ያክብራችሁ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጽናችሁ ይህንንም ብሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የባሌ መምህር አባ አሴር በሰማዕትነት አረፈ፡፡ ይኸውም በንጉሥ ወናግ ሰገድ ዘመን ወደ ኢየሩሳሌም ወርዶ ሳለ መጀመሪያ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡ። ልደቱም በዚሁ ዕለት ነው፡፡ እርሱም በደብረ ሊባኖስ የመጻሕፍት መምህር ሆኖ ሳለ የበቃ ጻድቅ መሆኑ ቢታወቅበት ወደ ሐይቅ ሄዶ በተጋድሎ የኖረ ሲሆን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተመርጦ በባሌ ሀገር ላይ የተሾመ ነው፡፡ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌምና ግብፅ ሄዶ ከመናፍቃን ጋር ሲከራከር ከሃዲዎች በእሳት አቃጥለውት በመጨረሻም አንገቱን ሰይፈውት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ አካሉንም በእሳት አቃጥለውት ከጣሉት በኋላ በደብረ ቁስቋም ተቀብሯል፡፡ ስንክሳሩ ግን ‹‹በኢየሩሳሌም መግቢያ በእሳት አቃጠሉት›› ብሎ ይገልጸዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የአቡነ ኤልያስ ዘውቅሮ መታሰቢያቸው ነው፡፡ ቅዱሱ የትውልድ ሀገራቸው አክሱም ነው፡፡ የአቡነ አረጋዊ 3ኛ የቆብ ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ውቅሮ የሚገኘው የጥንታዊው የአብርሃ ወአጽብሓ ቤተ መቅደስ አጣኝ ነበሩ፡፡ ይህ ጻድቅ የሚታወቁበት አንድ ትልቅ ገድል አላቸው፡፡ በቀን 548 ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን እየጸለዩ 666 ጊዜ ይሰግዱ ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዓባይ የሀገራችንን አፈርና ዛፉን ሁሉ ጠራርጎ ሲወስድ ቢመለከት ድምጹን ከፍ አድርጎ ኦ አባይ አይቴ ተሐውር ወለመኑ ተሐዲጋ ለኢትዮጵያ ብሎ ሲዘምር ዓባይ ቀጥ ብሎ ቆሟል፡፡ መልአኩም ወዲያው መጥቶ ‹‹ለምን ትደክማለህ? ለምንስ ተፈጥሮን ትከለክላለህ? ሕጉን አታፍርስ›› ሲለው ቅዱስ ያሬድ ደንጎጦ ‹‹አጥፍቻለሁ ዓባይ ሆይ ሂድ የተፈጥሮ ግዴታህን ፈጽም›› ብሎ አሰናብቶታል፡፡ የኢትዮጵያ ብርሃኗ ቅዱስ ያሬድ በዜማው ዓባይን ቀጥ አድርጎ እንዳቆመው ሁሉ አቡነ ኤልያስ ዘውቅሮም በጸሎታቸው ዓባይን ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ አድርገውት ነበር፡፡
ታቦተ አብርሃ ወአጽብሓን ይዘው ከኢትዮጵያ ጠረፍ ዳር ኑብያ ሄደው ድንጋይ ከዓባይ ዳር ደርድረው ታቦቱን አስቀምጠው ሥዕለ ማርያምን አድርገው መሥዋዕት ሰውተው ‹‹ዓባይ ከኢትዮጵያ እንዳትወጣ ገዝቼሃለሁ›› ሲሉት ዓባይም ተመልሶ ቆሟል፡፡ ዓባይ ምድረ ኑብያን ሲያጥለቀልቃት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ ‹‹ለምን የእግዚአብሔርን ስነ ፍጥረት ታስጨንቃለህ?›› ብሎ ተቆጣቸው፡፡ ጻድቁም ‹‹ውኃው ይሂድ ግን ዛፉን አፈሩን ይዞ ከኢትዮጵያ አይውጣ›› ብለው መልአኩን ጠየቁት፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹ውኃ ሲሞላ ዛፉን ቅጠሉን ይዞ መጓዙን እንዴት ትረሳዋለህ? የጸሎት ጊዜህ ደርሷልና ወደ በዓትህ ተመለስ›› ብሎ በቁጣ የእሳት ሰይፉን ሲያዛቸው ግዝታቸውን አንሥተው ታቦታቸውን ይዘው ወደ በዓታቸው ውቅሮ ተመልሰዋል፡፡
አባቶቻችን እንዲህ ናቸው እንኳን ሃይማኖት፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ስብዕና ማንነታችንን ይቅርና የሀገራችንን አፈር እንኳን ለባዕድ አሳልፈው የማይሰጡ ቅዱሳን ጻድቃን ነበሩ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀንም ቅድስት አናሲማ አረፈች፡፡ ይቺም ቅድስት በደናግል ገዳም መንኵሳ ራስዋን እብድ አስመስላ ኖረች። በሌሊትም በጾምና በጸሎት ሥጋዋን በመቅጣት ራሷን ታሠቃያለች ሰዎችም በሚያዩዋት ጊዜ ራስዋን አእምሮዋን እንደሳተች ታስመስላለች መበለቶችም ይሰድቧታል።
እግዚአብሔርም ገድሏን ለአባ ዳንኤል ገለጠ። እርሱም ከደናግል ገዳም ሔዶ ትሩፋቷንና ገድሏን ሁሉ ለእመ ምኔቷ ነገራት እርሷም ለእኀቶች መነኰሳይያት ነገረቻቸው ከዚያችም ዕለት ወዲህ አከበሩዋት።
እርሷም ስለ አዋረዱዋትና ስለ አጐሳቈሉዋት እኀቶችን እያመሰገነች ደብዳቤ ጽፋ ትታ ከንቱ ውዳሴን በመጥላቷ ተሠውራ በሌሊት ወጥታ ወደ ዱር ሸሸች በዚያም በሰላም አረፈች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን በዲዮቅልጥያኖስ መንግሥት ዘመን ቅዱስት ኤፎምያ በሰማዕትነት አረፈች። የዚችም የእናቷ ስም ቴዎድርስያኒ ነው እርሷም የክብር ባለቤት ክርስቶስን የምታምንና የምትፈራው ናት።
ሰይጣንም ክርስቲያኖችን በማስገደድ ለጣዖት እንዲያሰግድ አንቲሂጳጦስን በአነሣሣው ጊዜ ይቺን ቅድስት ኤፎምያን ከብዙ ክርስቲያኖች ጋራ አሥረው አመጡዋት። አንቲሂጳጦስም ለአማልክት ሠዊ አላት። እኔ ከክብር ባለቤት ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አልሠዋም የአባቶቼን ተስፋ ለማግኘት ልቤ የጸና ነውና አለችው።
ያን ጊዜ አንቲሂጳጦስ ተቆጥቶ ዐጥንቷ እንዲሰበር ሕዋሳቷ ሁሉ እንዲለያይ ከሠረገላ መንኰራኩር ውስጥ ይጨምሩዋት ዘንድ አዘዘ። የእግዚአብሔርም መልአክ አዳናት ሁለተኛም ነበልባሉ አርባ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ እስከሚል እሳትን አንድደው ከውስጡ ይወረውሩዋት ዘንድ አዘዘ። በእሳቱ መካከልም ቁማ ጸለየች እየጸለየችም በደኅና ወጣች ብዙዎችም በጌታ አምነው በሰማዕትነት አረፉ።
ከዚህም በኋላ እስከ ማግሥት ከወህኒ ቤት ጨመራትና በማግሥቱ ወደ ሸንጎ አወጧት እርሱም ለአማልክት ሠዊ አላት። ቅድስት ኤፎምያም ሣቅ ብላ እኔስ ለማይናገሩ ደንጊያዎች አልሠዋም አለችው። አንቲሂጳጦስም ሰምቶ ሥጋዋን ይገፉ ዘንድ መቃጥን ያላቸው አራት ደንጊያዎችን እንዲያመጡ አዘዘ። ሁለተኛም አራዊት ከአሉበት ኲሬ ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዝዞ ከዚያ ወረወሩዋት። አራዊት ግን ተሸክመው አውጥተው ከውኃው ዳር አቆሙዋት።
ደግሞ ስለታሞች ደንጊያዎችንና ሰይፎችን በመሬት ውስጥ እንዲተክሉ ተቆራርጣ ትሞት ዘንድ በላያቸው እንዲያስሮጡዋት አዘዘ ሩጣም ተሻገረች ምንም የነካት የለም። ደግሞም በግለቱ ታር ዘንድ ደብድበው ከብረት ምጣድ ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዘዘ ግን ምንም ምን አልነካትም።
ከዚህ በኋላም አራዊትን ሁሉ ድባትንም ሰበሰበ። በላይዋም ወሰዱዋቸው አንበሶችም እግርዋን ሳሙ አንዲትም አውሬ ተሸብራ እግርዋን ነከሰቻት ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ የተመሰገንሽ ኤፎምያ ወጥተሽ ወደ ከበረ ቦታ ነዪ።እንዲህም ገድሏን ምስክርነቷን ፈጸመች እናትና አባቷም መጥተው ገንዘው በአዲስ መቃብር ውስጥ ቀበሩዋት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages