ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 12 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, May 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 12

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን በኢየሩሳሌም ሀገር ወደሚኖር ነቢይ ዕንባቆም የመላእክት አለቃ ቅዱስ_ሚካኤልን እግዚአብሔር ላከው፣ የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የከበረ አባት ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ አረፈ፣ የኢትዮጵያ ብርሃኗ ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት ፍልሠተ ዐፅማቸው ተከናወነ፣ ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ነው፣ በኢየሩሳሌም አገር በጎልጎታ ላይ ከፀሐይ በልጦ በሚበራ ብርሃን የከበረ_መስቀል መገለጥ ሆነ፣ የመላልዔል ልጅ የማቱሳላ አባት ቅዱስ_የያሬድ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።


ግንቦት ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን በኢየሩሳሌም ሀገር ወደሚኖር ነቢይ ዕንባቆም የመላእክት አለቃ ሚካኤልን እግዚአብሔር ላከው እርሱም የማሳውን እህሎች ለሚያጭዱ ምሳ ሊወስድ ወዶ ተሸክሞ ሳለ።
ቅዱስ ሚካኤልም ዕንባቆምን ምግብን እንደተሸከመ በአናቱ ጠጉር ይዞ ወደ ባቢሎንም አገር አድርሶ ዳንኤል ወደ አለበት የአንበሶች ጒድጓድ አስገባው ዳንኤልንም ከዚያ ምግብ መገበው ከዚህም በኋላ ዕንባቆምን ከምግቡ ጋራ ወደ ይሁዳ ምድር መልሶት ወዲያውኑ እህሉን በሚያጭዱት ዘንድ ቆመ።
ስለዚህም ለከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤል በየወሩ ሁሉ መታሰቢያውን እንድናደርግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙን፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የከበረ አባት ዮሐንስ አፈወርቅ አረፈ፡፡ ይህም አባት ከእስክንድርያ አገር ሰዎች ወገን ነው የአባቱም ስም አስፋኒዶስ የእናቱም ስም አትናሲያ ነው እሊህም እጅግ ባለጸጎች ነበሩ ይህንንም ልጃቸውን በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት ትምህርትንና ጥበብንም ሁሉ አስተማሩት እርሱ ወደ አቴና ሒዶ በመምህራን ቤት ተቀምጦ ትምህርትን ሁሉ ተምሮ በዕውቀቱ ከብዙዎች በላይ ከፍ ከፍ ብሏልና።
ከዚህም በኋላ ገና በታናሽነቱ መነኰሰ የዚህንም የኃላፊውን ዓለም ጣዕም ንቆ ተወ ከእርሱም ቀድሞ በዚሁ ገዳም ቅዱስ ባስልዮስ መንኵሶ ነበር በአንድነትም ተስማምተው ብዙ ትሩፋትን ሠሩ ወላጆቹም በሞቱ ጊዜ ከተውለት ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ እንጂ ከዚያም በምንኵስና ሥራ በመጠመድ ፍጹም ገድልን እየተጋደለ ኖረ።
በዚያም ገዳም ሶርያዊ ጻድቅ ሰው ስሙ ሲሲኮስ የሚባል መነኰስ ነበረ እርሱም ወደፊት የሚሆነውን በመንፈስ ቅዱስ ያይ ነበር በአንዲት ሌሊትም ለጸሎት እየተጋ ሳለ ሐዋርያትን ጴጥሮስንና ዮሐንስን አያቸው ወደ ዮሐንስ አፈወርቅ ገብተው ጴጥሮስ መክፈቻ ሰጠው ወንጌላዊ ዮሐንስም ወንጌልን ሰጠው እንዲህም አሉት በምድር ያሠርከው በሰማይ የታሠረ ይሆናል በምድርም የፈታኸው ደግሞ በሰማያት የተፈታ ይሆናልና በውስጥህ መንፈስ ቅዱስ ያደረብህ አዲስ ዳንኤል ሆይ የክብር ባለቤት ከሆነ ከታለቅ መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ወደ አንተ ተልከናልና ዕወቅ እኔም የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የተሰጠኝ ጴጥሮስ ነኝ። ሁለተኛውም እኔም በመጀመሪያው ስብከቴ በከበረ ወንጌል ቃል አስቀድሞ ነበረ ያልኩ ይህም ቃል በጠላት ላይ የእሳት ሰይፍ የሆነ ዮሐንስ ነኝ። ለአንተም ከክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ወገኖችህ ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ታሳድጋቸው ዘንድ ዕውነተኛ አእምሮ ደግሞ ተሰጥቶሃል። ጻድቅ ሲሲኮስም ይህን ራእይ በአየ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ቸር ታማኝ እረኛ ሁኖ እንደሚሾም ዐወቀ። ከዚህም በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በላዩ ወርዶ አደረበትና ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ ዲያቆን ሁኖ ሳለም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ብሉያትንና ሐዲሳትን ተረጐመ።
በአንዲት ሌሊትም ቅዱስ ዮሐንስ ሲጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ በድንገት እንደ በረድ ነጭ በሆነ ልብስ ተገለጠለት ቅዱስ ዮሐንስም ሲያየው ደንግጦ በምድር ላይ ወደቀ መልአኩም አርአያውን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታየው ወዳጄ አዲስ ዳንኤል ሆይ አትፍራ ተነሣ አለው የቅዱስ ዮሐንስም ልቡ ተጽናንቶ ጌታዬ አንተ ማነህ ግርማህ አስፈርቶኛልና አለው የእግዚአብሔር መልአክም ትሠራው ዘንድ የሚገባህን ልነግርህ ወዳንተ የተላክሁ ነኝ። አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘህን ለመሥራት ልብህን አበርታ ቃልህ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በአራቱ ማእዘን ይደርሳልና እልፍ አእላፋትም ትምህርትህን ተቀብለው ትእዛዝህን ሰምተው ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር ተመልሰው ይድናሉና በእግዚአብሔር መንግሥትም ውስጥ የጸና የብርሃን ዐምድ ትሆናለህና። እነሆ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አንተ ይመጣል ከእርሱም ጋራ ሁሉም ካህናትና ዲያቆናት በየማዕረጋቸው የሚያዝህንም አድርግ የእግዚአብሐር ትእዛዝ ነውና ልትተላለፍ አይገባህም አለው።
ከዚህም በኋላ ያ መልአክ ለአባ ፊላትያኖስ ተገልጦ ቅዱስ ዮሐንስን ቅስና እንዲሾመው አዘዘው በማግሥቱም ሊቀ ጳጳሳቱ መጣ ከርሱ ጋራም ካህናት አሉ ይህን ቅዱስ ዮሐንስንም ይዞ ቅስና ሾመው። የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳትም በአረፈ ጊዜ ንጉሥ አርቃድዮስ ልኮ አስመጥቶ ቅዱስ ዮሐንስን በቍስጥንጥንያ ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾመው አባቶቻችን ሐዋርያት እንደሚአደርጉት በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ላይ ጸና ሕይወትነት በአላቸው ትምህርቶችና ተግሣጾች ሕዝቡን ሁልጊዜ የሚአስተምር ሆነ። ከኤጲስቆጶሳትም ሆነ ከመንግሥት ወገን ሕግን የሚተላለፉትን ሁሉ ይገሥጻቸዋል ማንንም አይፈራም ፊት አይቶም አያደላም።
የንጉሥ አርቃድዮስ ሚስት አውዶክስያም ገንዘብ ወዳጅ ስለሆነች የአንዲት ድኃ መበለት ቦታዋን በግፍ ወሰደች ያቺ መበለትም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥታ ንግሥት አውዶክስያ ቦታዋን እንደነጠቀቻት ነገረችው እርሱም የደኃዋን ቦታዋን መልሺላት ብሎ ከብዙ ምክር ጋር እንድትመልስላት ንግሥት አውዶክስያን ለመናት እርሷ ግን እምቢ በማለት አልታዘዘችለትም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውን ደሙን እንዳትቀበል አውግዞ ለያት።
ቍጣንና ብስጭትንም ተመልታ ስለ ክፉ ሥራቸው ከሹመታቸው እርሱ የሻራቸውን ኤጲስቆጶሳት ሰበሰበች እነርሱም ንግሥቲቱን ስለ ተቃወመ ስደት እንደሚገባው በእርሱ ላይ ተስማምተው ጻፉ እርሷም አጥራክያ ወደ ሚባል ደሴት ሰደደችው። ከዚያም በደረሰ ጊዜ የዚያች ደሴት ሰዎች በክፉ ሥራ ጸንተው የሚኖሩ ከሀድያን ሁነው አገኛቸው ቅዱስ ዮሐንስም አስተማራቸው ገሠጻቸውም በፊታቸው ስለ አደረጋቸው ድንቆች ተአምራት ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው።
የሮሜ ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ስደት በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ በንጉሥ አርቃድዮስ ላይም በመቆጣት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ላኩ ከዚህ ከክፉ ሥራ ተጠበቅ ትእዛዛችንንም ተቀብለህ የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ ከአልመለስከው በአንተና በእኛ መካከል ሰላም አይኖርም።
መልእክታቸውንም በአነበበ ጊዜ እጅግ አዘነ ሚስቱንም አግዶ ልኮ ቅዱስ ዮሐንስን ከስደቱ መለሰው በተመለሰ ጊዜም የቍስጥንጥንያ ሰዎች በመመለሱ ታላቅ ደስታ አደረጉ። ከጥቂት ቀኖች በኋላም ንግሥቲቱ ወደ ክፋቷ ተመልሳ ሁለተኛ ወደ አጥራክያ ደሴት ሰደደችውና በዚያው አረፈ።
ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳት ዮናክኒዶስም በሰሙ ጊዜ መልእክትን ላኩ ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ እስከምትመልሰው ድረስ ሥጋውንና ደሙን እንዳትቀበል አውዶክስያን አወገዛት።
ከዚህም በኋላ የከበረ ዮሐንስን ይመልሱት ዘንድ ንጉሥ ላከ ግን ሙቶ አገኙት ሥጋውንም ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ አደረሱት። የከበረ ዮሐንስም በተሰደደበት አገር እንደአረፈና ሥጋውንም ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ እንደአመጡ ወደ አባ ዮናክኒዶስ መልእክት ጽፈው አስረዱት። ሁለተኛም የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውንና ደሙን እንዳትቀበል ልኮ አውድክስያን አወገዛት እየለመነችውም ስምንት ወር ያህል ኖረች በብዙ ልመናም ፈታት። ነገር ግን ጭንቅ በሆነ ደዌ እግዚአብሔር አሠቃያት ያድኗት ዘንድ ገንዘቧን ለባለ መድኃኒቶች ጥበበኞች እስከ ሰጠች ድረስ ግን አልዳነችም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መቃብርም ሔዳ በእርሱ ላይ ያደረገችውን በደል ይቅር ይላት ዘንድ እየሰገደችና እያለቀሰች ለመነችው እርሱም ይቅር አላት ከደዌዋም ፈወሳት። ጌታችንም ከሥጋው ታላላቅ ድንቆች ታአምራትን ገለጠ።
ስለርሱም እንዲህ ተባለ በአንዲት ዕለትም ከንጉሥ አርቃዴዎስ ጋር ተቀምጦ ሳለ ንጉሡ እንዲህ አለው አባቴ ሆይ ስለ አንድ ቃል እንድታስረዳኝ እለምንሃለሁ። ይህም ቃል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በልቤ ውስጥ ይመላለሳል ወንጌላዊ ማቴዎስ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምን የበኵር ልጅዋን እስከ ወለደች ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም ስለምን አለ ወንዶች ሴቶችን እንደሚአውቋቸው ዮሴፍ አወቃትን አለው።
የከበረ ዮሐንስም ንጉሥ ሆይ እንዲህ አትበል እንዲህ አንተ እንደምትለው አይደለም የከበረች ድንግል እመቤታችንስ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሆድዋ ውስጥ በነበረ ጊዜ የእርሱ ኅብረ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋር መልኳ ይለወዋወጥ ነበር። በንጹሕ ብርሌ ውስጥ ውኃ በጨመሩ ጊዜ ውኃ መስሎ እንደሚታይ ወይን ጠጅም ቢጨምሩ ያንኑ መስሎ እንደሚታይ ወይም ከውስጡ በተጨመረው ቀይም ቢሆን ቀልቶ እንደሚታይ ቅጠልያም ቢገባበት ቅጠልያ መስሎ እንደሚታይ።
ድንግልም በሆድዋ ውስጥ የልጅዋ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋራ መልኳ ይለዋወጥ ነበር። እንደ ሮማን አበባ የምትቀላበት ጊዜ አለ እንደናርዶስም የምታብለጨልጭበት ጊዜ አለ የለመለመ ቅጠል የምትመስልበትም ጊዜ አለ ከወለደች በኋላ ግን አልተለወጠችምና ዮሴፍ በአንድ በቀድሞው ኅብረ መልኳ ተወስናለት መልኳን ተረዳ ማለት ነው አለው። በዚያን ጊዜ በንጉሥ አዳራሽ ውስጥ ከወርቅ የተሠራ የእመቤታችን አምላክን የወለደች የድንግል ማርያም ሥዕል ነበረችና አፈ ወርቅ ዮሐንስ ልሳነ ወርቅ ዮሐንስ አፈ በረከት ዮሐንስ መልካም ተናገርክ የሚል ቃል ከእርሷ ወጣ።
ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያሉት በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት በዚያን ጊዜ ንጉሥ አዝዞ ወርቅ ሠሪ አስመጥቶ ለከበረ ዮሐንስ የወርቅ ልሳን አሠርቶ ለሚያየው ሁሉ መታሰቢያ ምልክት ሊሆን አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ሥዕል ዘንድ ሰቀለው። ቅዱስ ዮሐንስንም ከዚያች ቀን ወዲህ ልሳነ ወርቅ ብሎ ጠራው አፈ ወርቅም ተብሎ እስከዛሬ ተጠራ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት የኢትዮጵያ ብርሃኗ ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሠተ ዐፅማቸው ስለመከናወኑ፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው በኋላ ተዘዋውረው ወንጌልን ለመስበክ የማይችሉት ዕድሜ ላይ ደረሱ፡፡ በዚህም ጊዜ ‹‹ለሌሎች አበራሁ ለራሴ ግን ጨለምኩ፣ ዓለም አጣፈጥሁ እኔ ግን አልጫ ሆንኩ…›› ብለው በዓት አጽንተው ከቆሙ ሳይቀመጡ፣ ከዘረጉ ሳያጥፉ ለ7 ዓመት ቆመው ጸለዩ፡፡ ከ1267-1289 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ በደብረ ሊባኖስ ካለችው ገዳመ አስቦ ዋሻ በመግባት 8 ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማምና ሞት፣ ነገረ መስቀልን በማሰብ በተመስጦ ሌትና ቀን ያለማቋረጥ በጾምና በጸሎት በአርምሞ ተወስነው ሲጋደሉ ከቁመት ብዛት የተነሣ ጥር 4 ቀን 1289 ዓ.ም. አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ቅዱስ አባታችን በመዓልትና በሌሊት በትጋትና በቁመት በተጋድሎ ብዛት አንዲት የአገዳ እግራቸው ስትሰበር ዕድሜያቸው 92 ዓመት ሆኗቸው ነበር፡፡
ከ1289-1296 ዓ.ም ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው በመቆም ያለምግብና ያለውኃ በትኅርምት ሌትና ቀን እንቅልፍ በማጣት እንደ ምሰሶ ጸንተው፤ በተመስጦ በትጋት ለሰው ዘር ሁሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ጌታችን ተገልጦላቸው በሰው አእምሮ ሊታሰብና ሊለካ የማይችል ትልቅና ልዩ የመንግሥት አዳራሽ ከሰጣቸው በኋላ የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያላቸው የመንግሥት ልብስ አለበሳቸው፡፡ በመስቀል ምልክት የተጌጡት ሰባት የሕይወት አክሊላትን አቀዳጅቷቸዋል፡፡ ይኸውም ‹‹ስለ ቀናች ሃይማኖትህ፣ ሃይማኖትን ለማስተማር መላዋን ኢትዮጵያን ስለመዞርህ፣ ከአረማውያን ሕዝብ ጋር በሃይማኖት ስትታገል ደምህን ስለማፍሰስህ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ወርደህ ልዩ ልዩ የቅዱሳን ቦታዎች ስለመሳለምህ፣ በሰባት ዓመታት ቊመት የአንዱ አገዳ እግርህ ስለመሰበሩ፣ ስለብዙ ጾም ጸሎት ስግደትህ፣ ስለልብህ ንጽሕናና ቅድስና›› በማለት የሕይወት አክሊላትን ካቀዳጃቸው በኋላ ዝክራቸውን በማዘከር መታሰቢያቸውን የሚያደርጉ ሁሉ በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ፍጹም ዋጋና ፍጹም ክብር እንደሚሰጣቸው ጌታችን ታላቅ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ሥጋቸውም ወዴት ይቀበር ዘንድ እንዳላቸው ሲነግራቸው ‹‹እስከ 57 ዓመት ሥጋህ ከዚህ ይቀበራል፤ ከ57 ዓመት በኋላ ግን ይህች ዋሻ ትናዳላች፤ በዚህም ገዳም አደባባይ በስምህ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ልጆችህ ሠርተው ሥጋህን አፍልሰው በውስጡ ያኖራሉ›› አላቸው፡፡
ቅዱስ አባታችን በሞት ከማረፋቸው በፊት አስቀድሞ ጌታችን እንደነገራቸው ሥጋቸው ከነፍሳቸው ከተለየች ከ57 ዓመት በኋላ የካቲት 19 በጸሎት ላይ ለነበሩት ለአቡነ ሕዝቅያስ ተገልጠውላቸው ‹‹ጌታ የገባልኝ ቃል ይፈጸም ዘንድ ሥጋዬ የሚፈልስበት ደረሰ፣ ቀኒቱንም በምስጋናና በጸሎት መንፈሳዊ በዓል አድርጉ፤ እኔ ኃጥኡ በሞትኩበት ቀን እንደነበረው ምስጋና አቅርቡ፡፡ ሄደህ ለ12 መምህራንና ለልጆቼ ግንቦት 12 እንዲያከብሩ ንገራቸው፡፡ በፍልሰቴ ቀን አባቴ አባቴ የሚለኝ ሁሉ ይምጣ ያኔ እኔ ወዳጄ ሚካኤልና ልጄ ፊልጶስ አብረን መጥተን እንባርካለን፡፡ ምልክት ይሆንህም ዘንድ በምመጣበት ጊዜ የጠፋው የመቅረዙ መብራት ይበራል›› አሉት፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ሕዝቅያስ በአባታችን ተባርከው ሄደው በአራቱም አቅጣጫ ላሉት 12 መምህራንና ለክርስትያኖች ሁሉ አባታችን የነገሩትን የፍልሰታቸው በዓል ስለማድረግ ወደ ፍልሰቱ በዓል ያልመጣም በዚያች ቀን (በሰማይ ለምልጃ) አባቴ እንዳይለው እርሱም ልጄ እንዳይለው ጨምሮ መልእክቱን ላከላቸው፡፡ እነርሱም ከያሉበት ተሰብስበው መጥተው የቅዱስ አባታችንን ሥጋቸውን አውጥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን አፍልሰው 3 ጊዜ መቅደሱን አዙረው በዓሉንም አባታችን እንዳሉት በዝማሬና በምስጋና አክብረው ወደ ውስጥ አስገቡት፡፡ በዚህም ጊዜ ብፁዕ አባታችን ተክለ ሃይማኖት አስቀድመው እንደተናገሩት ጠፍቶ የነበረው መብራት ቦግ ብሎ በራ፡፡ ከቅዱስ ሚካኤልና ከልጃቸው ከአቡነ ፊልጶስ ጋር በመሆንም በዓሉን ያከብር የነበረውን የተክለ ሃይማኖት የጸጋ ልጆቻቸውን ሁሉም ይባርኩ ነበር፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ነው፡፡ በሸዋ ከፍለ አገር በቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሟ ቅዱስ ጌዬ የተባለች አገር ነበረች ይህችም የእናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የትውልድ አገሯ ናት። በዚህም አገር በወርቅና በብር በሐር እና በልዩ ልዩ ልብስ በወንድና በሴት አገልጋዮች በፈረስና በበቅሎ የከበረ አንድ ስሙ የታወቀ ሰው ነበር። የዚህ ሰው ስሙ ቅዱስ ደረሳኒ ሲሆን የሚስቱም ስም ቅድስት ዕሌኒ ይባላል ሁለቱም ባልና ሚስቱ እግዚአብሔር የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች ስለነበሩ በጎ ሥራቸው በዓለም ሁሉ የታወቀ ነበር። እሊህም ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠችና የከበረችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ወልደው በደም ግባቷና በጠባይዋ እየተደሰቱ አሳደጓት ከዚያም የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ሥርዓቶችንም ሁሉ አስተማሯት። ባደገችና ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ የንጉሥ ባለሟል የሆነ ትውልዱ፤ ነገዱ ከአባ ፃሠርጓ ወገን የሆነ ለኢየሱስ ሞዓ ልጅ ለሠምረ ጊዮርጊስ በሕግ አጋቧት። እሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ በጣም የከበረ ከመሆኑም በላይ በይበልጥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነበረ። ከደም ግባቷ የተነሣ ሙሽራይቱ ማለት እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እጅግ አድርጎ ወደዳት። አሟቷ ኢየሱስ ሞዐም ይህች ብላቴና "በታላቅ ቁም ነገር የተመረጠች ነች" በማለት ትንቢት ይናገርላታል ስለዚህ እንደ እመቤቱ አድርጐ ያከብራት ነበር። ከዚህም በኋላም ለሕጋዊ ባሏ ለሠምረ ጊዮርጊስ ዓሥራ አንድ ልጆች ወለደችለት ከነዚህም መካከል ዘጠኙ ወንዶች ሁለቱ ሴቶች ነበሩ። ልጆችዋንም ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች በክብር በሥርዓት አሳደገቻቸው።
በዚያን ዘመን የእግዚአብሔር ባለሟል የሚሆን ዓፄ ገብረ መስቀል የሚባል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር። እርሱም ዝናዋን ሰምቶ ሥነ ምግባሯን ተመልክቶ ይልቁንም በሷ ላይ ያደረውን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለገለጸለት እጅግ አድርጐ ይወዳትና ያከብራት ነበር። ከዕለታት ባንድ ቀን በጸሎትሽ አስቢኝ በማለት በራሱ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ከሚያገለግሉ አገልጋዮች ወይም ሠራተኞች መካከል እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮች ላካላት። ዳግመኛም ፈረስና በቅሎ ከነሥራታቸው እንደዚሁም ለነሥታት ሚስቶች የሚገባ ከሐርና ከወርቅ የተሠራ ልብስና የወርቅ ጫማ ላከላት። ነገር ግን እሷ ይህን ሁሉ ክብር አልፈለገችም ይልቁንም ለዓላማየ ዕንቅፋት ወይም ከንቱ ውዳሴ ይሆንብኛል በዚያውስ ወርቁ ጌጡ ልብሱ ተሸጦ ለነዳያን ይመጸወታል ለቤተ ክርስቲያን መባዕ ይሰጣል እኒህን አገልጋዮች ግን ምን አደርጋቸዋለሁ በማለት ወደ እግዚአብሔር እያመለከተች ቆየች።
ከአገልጋዮችዋ መካከል ምግባሯ የከፋ የምታናድዳትና የምታበሳጫት አገልጋይ ነበረች። ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በጣም ተበሳጨችና በዚያች አገልጋይ አፍ ውስጥ የእሳት ትንታግ ጨመረችባት። ያም እሳት ትንታግ በአገልጋይዋ ጉረሮ ድረስ ዘለቀና ገደላት። በዚህን ጊዜ ቤተሰቦችዋ መጥተው የአገልጋይቱን አስከሬን ወደሌላ ክፍል ወሰዱት። ብፅዕት ክርስቶስ ሠምራም ደንግጣ ካለችበት ቤት ውስጥ ወደ ሌላው ክፍል ገባችና ወደ ሰማይ አቅንታ "ወይኔ ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ የካህን ሚስት ስሆን ነፍስ ገዳይ ሆኛለሁና። ሰውስ ምን ይለኛል ለነፍሴስ ምን እመልስላታለሁ ከእግዲህ ከክርስቲያን ወገን ልቆጠር አይገባኝም በደሌንስ እንደምን አድርጌ ልሸሸሽጋት እችላለሁ" እያለች አለቀሰች።
ከዚህ በኋላ እንዲህ ስትል ለእግዚአብሔር ብፅዓት አደረገች "አቤቱ ይህችን በእኔ እጅ የሞተችውን አገልጋይ ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋህደህ ብታሥነሣልኝ ልጆቼን ቤቴን ንብረቴን ትቼ ባለ ዘመኔ ሁሉ አንተን እከተላለሁ። አንተን ከመከተል ከቶ ወደኋላ አልልም። ለሰውነቴ ጌጥ ወይም ግርማ ሞገስ የሚሆናት ወይም የሚሞቃት ልብስ ከቶ አልለብስም ሥጋዬን የሚያረካ ምግብም አልመገብም። አቤቱ ጌታዬ ሆይ ጸሎቴን ስማኝ ልመናዬም በፊትህ ፈጥኖ ይድረስ አቤቱ ፊትህን ከኔ ከባሪያህ አትመልስ"። እንዲህ እንዲህ እያለች በልቅሶና በኀዘን ለብዙ ሰዓት ከጸለየች በኋላ ድካም ተሰማትና ዕረፍት አደረገች። ከዚህ በኋላ ቤተሰቦችዋ እስዋ ወዳለችበት ክፍል መጥተው "እመቤታችን ሆይ ሙታ የነበረችው አገልጋይሽ በእግዚአብሔር ኃይልና በአንቺ ጸሎት ተነሥታለችና ደስ ይበልሽ" አሏት። በዚህ ጊዜ ፈጥና ተነሥታ ደስ እያላት ሙታ የነበረችው አገልጋይ ካለችበት ቦታ ደረሰችና ሕይወት አገኘቻት ከዚያም ቃሏን ከፍ አድርጋ "ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከኔ ከባሪያው ያላራቀ ፈጣሪ ይክበር ይመስገን" ብላ በታላቅ ምስጋና እግዚአብሔር አመሰገነች።
ከዚህ በኋላ አስቀድሞ ከአፏ የወጣውን ከአንደበቷ የተነገረውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኵስናዋን ማለት ቆቧን ቀሚሷን አጽፏን መታጠቂያዋን አዘጋጀች። ቤተሰቦቿና አገልጋዮቿም "እመቤታችን ሆይ ይህ የምታዘጋጂው የምናኔ ልብስ ለምንሽ ነው ወይስ ለማን ነው የምታዘጋጂው" አሏት። እርሷም " ሃይማኖት ያስተማሩኝ አባቴ ልብስ አልቆባቸዋል ሲሉ ሰምቼ ለሳቸው ነው የማዘጋጀው" አለቻቸው።
ከዚህም በኋላ ከዕለታት ባንደኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ አገልጋዮቿን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ተዘጋጁ አለቻቸውና እነሱም አሺ በጎ ብለው አጅበዋት ወደቤተ ክርስቲያን ሄዱ። ከዚያም እንደደረሱ "በሉ እንዲህ እኔ ከዚህ ጥቂት እቆያለሁና እናንተ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ለኔ ይህች አንድዲት አገልጋይና ይህ ሕፃን ልጅ ብቻ ይበቁኛል አለቻቸው። በዚያኑ ጊዜ አገልጋዮቿ እጅ እየሱ ወይም እየተሰናበቱ ወደቤታቸው ተመለሱ። ከዚያም ከዳዊት መዝሙር "ልቤ ጽኑ ነው አቤቱ ልቤ ጽኑ ነው እግዚአብሔርን ፈጽሜ አመሰግነዋለሁ እግዚአብሔር የደህንነቴ መብራት ስለሆነ ምን ያስደነግጠኛል እግዚአብሔር የሕይወቴ መተማመኛ ነው ምንስ ያስፈራኛል የሚለውን እየጸለየች የሚያልፈን ዓለም በማያልፈው ዓለም ለመተካት ወይም ለመለወጥ አውጭኝ እግሬ ብላ ገሠገሠች። ያ በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግር ከመንገዱ ብዛት እንደዚሁም ከቅርቅፍቱና ከእንቅፋቱ የተነሣ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሙ እንደጒርፍ ውሃ ይወርድ ነበር። ያች የተከተለቻት አገልጋይ ግን ከእመቤቷ እግር እየተቆረጠ የሚወድቀውን የአካል ቊራጭ እያነሳች በልብሷ ትቋጥረው ነበር። በዚህ ዓይነት ችግርና ፀሐይ ሐሩር የብዙ ጐዳና ጉዞ ተጉዛ ከአሰበችበት አገር ደረሰች። በደብረ ሊባኖስ አቅራቢያ ወይም አካባቢ ስትደርስ የራስ ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መፅውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት ...
እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦ ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ። ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት "ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል" ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም "ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ... አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መፃተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገፀች ከእግሩ ሥርም ወደቀች። ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆነ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ" አላት። እስዋም "አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከርው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?" አለችው። "አዋን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ" አላት። "እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው" አለችው። "አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም" በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ ጌታ መልሶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና አደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና "እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል" አላት።
ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ" አላት። በዚህን ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና" አለችው። "የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብየ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋየ እንደሆመኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና" አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ" አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ" ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዞአት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ "እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ" እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህን አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።
ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል "ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው" አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ "ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሣጥናኤል" በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም "ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ" እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ "ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን" አላት። እርሷም "ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ" አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ውካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ "አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?" እያለች አደነቀች። ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን" አላት። እስዋም "አዋ ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ" አለችው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "እሊህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው" አለው። በዚህ ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ የእኔ መኖሪያየ ወዴት ነው?" አለችው። ጌታም "መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች። በየአንዳንዳቸው አክሉል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉ ባቸው የእሊህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ "እሊህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና" አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም "ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?" አላት። እርስዋም "አዎን ጌታየ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ" አለችው። "እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው" አላት። "በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ" አለችው። "ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው ነው" አላት። ይህንንም በአላት ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔርንም ፈጽማ አመሰገነች። ምንጭ፦ ገድለ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_መስቀል (የተአምር በዓሉ)
በዚህችም ቀን በኢየሩሳሌም አገር በጎልጎታ ላይ ከፀሐይ በልጦ በሚበራ ብርሃን የከበረ መስቀል መገለጥ ሆነ።
ይኸውም ለኢየሩሳሌም አባ ቄርሎስ ኤጲስቆጶስ ሆኖ በተሾመበት በታላቁ ቁስጠንጢኖስ ልጅ በሚያንሰው ቁስጠንጢኖስም ዘመነ መንግሥት ነው። መገለጡም የሆነው ከቀኑ በስድስት ሰዓት ነው። የመስቀሉም ብርሃን የፀሐዩን ብርሃን ሸፍኖ በግልጥ እየታየ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ቆየ ሰዎችም ሁሉ ያዩት ዘንድ ከቦታው ሁሉ ይወጡ ነበር።
አባ ቄርሎስም እንዲህ የሚል መልእክትን ወደ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ ሲልክ ንጉሥ ሆይ ዕወቅ አስተውል በከበረ አባትህ በጻድቁ ቁስጠንጢኖስ ዘመን እንደ ከዋክብት መስቀል በሰማይ ታየ። ሁለተኛም በዘመንህ በቀራንዮ ላይ የብርሃን መስቀል የፀሐይንም ብርሃን ሸፈነው የክብር ባለቤት የሆነ እስከ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብርና እስከ ደብረ ዘይት ተዘረጋ አለው።
ሁለተኛም በዚች ደብዳቤ እንዲህ አለው ንጉሥ ሆይ ከከፋችና ከረከሰች ከአርዮስ ሃይማኖት ተጠበቅ የሚያምኑባትንም አትቀበላቸው በምንም በምን አትሳተፋቸው።
ከዚህ በኋላም አባ ቄርሎስ ይህ የከበረ መስቀል በተገለጸበት ቀን በዓልን አደረገ እርሱ በሥውርና በግልጥ ለሚመጣብን ጠላት ተዋግተን የምንድንበት የጦር መሣሪያችን ነውና በጸና እምነት በምንማፀንበት ጊዜ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የመላልዔል ልጅ የማቱሳላ አባት የያሬድ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ያሬድም መቶ ስልሳ ሁለት ዓመት ኑሮ ኄኖክን ወለደው ኄኖክንም ከወለደው በኋላ ስምንት መቶ ዓመት ኖረ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
መላው ዘመኑም ዘጠኝ መቶ ስልሳ ሁለት ዓመት ሆነው በዕለተ ዓርብም በሦስት ሰዓት አረፈ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages