አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ከዚህም በኋላ አቴና ወደሚባል አገር ሒዶ ፍልስፍናን የፀሐይንና የጨረቃን የከዋክብትንም አካሔዳቸውን የዘመናትንም መለኪያና መቊጠሪያ ተምሮ በመልካም አጠና። ከብዙዎችም ከፍ ከፍ አለ። በመንፈሳዊ ትምህርቱም ፍጹም ሁኖ አምላካዊ ትሩፋትን የሚሠራ ሆነ።
በሮሜ አገርም ታላቁ ቴዎዶስዮስ በነገሠ ጊዜ ልጆቹን አኖሬዎስንና አርቃዴዎስን የሚያስተምርለት ጥበበኛ ደግ ሰው ፈለገ። ይህንንም ቅዱስ ወደ ንጉሥ ወሰዱት። ንጉሡም ልጆቹን አኖሬዎስንና አርቃዴዎስን እንዲያስተምርለት አዘዘው እርሱም ታዝዞ የንጉሡን ልጆች እንደሚገባ ሊያስተምር ጀመረ። በብዙ ትግልና ድካም ስለሚአስተምራቸው ያለርኅራኄ ብዙ ድብደባን ይደበድባቸው ነበር።
ንጉሥ ቴዎዶስዮስም በአረፈ ጊዜ ልጆቹ አኖሬዎስ በሮሜ አገር አርቃዴዎስም በቊስጥንጥንያ ነገሡ።እግዚአብሔርም በአርሳንዮስ ልብ ፍርሀትን አሳደረ በታናሽነታቸው ጊዜ ሲአስተምራቸው የሚመታቸው ስለሆነ በዚህ ምክንያት ከዓለም ይወጣ ዘንድ የነፍሳቸውንም ድኅነት ለሚሹ የሚበራ መብራት ሆኖ ሌሎች ይበሩበት ዘንድ አነሣሣው ።
ምን እንደሚአደርግ በልቡ እያሰበ ሳለ እነሆ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ የሚል ቃል መጣ አርሳኒ አርሳኒ ከዚህ ዓለም ውጣ አንተም ትድናለህ። ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ ፈጥኖ ተነሣ እንጂ አልዘገየም ወዲያውኑ ልብሱን ለውጦ ወደ እስክንድርያ አገር ሔደ። ከዚያም የከበረ የአባ መቃርስ ገዳም ወደ አለበት ወደ አስቄጥስ በረሀ ደርሶ በጾም በጸሎት በመስገድ በመትጋት በአርምሞና በትሩፋት ሁሉ ፍጹም ተጋድሎን ተጋደለ።
ስለ ዝምታውም በጠየቁት ጊዜ እኔ ስለራሴ ብዙ አዝናለሁ አላቸው እርሱ ግን በውስጥና በአፍኣ ትሑትና ቅን የዋህ ነው የእግዚአብሔርንም ሥራ ይሠራል። ሁል ጊዜም እጅ ሥራውን አያቋርጥም ከዕለት ምግቡ የሚተርፈውንም ይመጸውታል።
የነፍሳቸውንም ድኅነት ለሚሹ ጥቅም ያላቸውን ብዙ ድርሰቶችንና ተግሣጾችን ደረሰ። ወደ ቤተ ክርስቲያንም በሚገባ ጊዜ ሰው እንዳያየው በምሰሶ ኋላ ይሠወራል። ይህም አባት ድንቆች ተአምራትን ያደርጋል የብዙዎች ሰዎችን ገድል እግዚአብሔር ገልጦለታልና ።
መልኩም ያማረ ሕዋሳቱም የጸኑ ፊቱም ብሩህና እጅግ ደስ የሚል ጽሕሙም ከወገቡ መታጠቂያ የሚደርስ ረጅም ነው። ከልቅሶ ብዛትም የተነሣ የቅንድቡ ጠጉር ተነቀለ ቁመቱም ረጅም ነው ግን ያጐነብሳል ወደ መልካም ሽምግልናም ደረሰ ዕድሜውም ሁሉ መቶ ዓመት ሆነ።
በሮሜም አርባ ዓመት ኖረ። በአስቄጥስ ገዳም ሠላሳ አምስት በምስር ገዳም ሃያ ዓመት በእስክንድርያ ሦስት ዓመት ከዚህም በኋላ ወደ ምስር ገዳም ተመልሶ በዚያ ሁለት ዓመት ተቀምጦ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment