ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 22 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, May 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 22

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ #ቅዱስ_ተክለ_ሃይማኖት በዚህች ቀን ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል፣ የከበረ #አባት_ይስሐቅ አረፈ፣ የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የሆነ #ቅዱስ_እለእስክንድሮስ አረፈ፣ #የሐዲስ_ማርቆስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ፣ የከበረ አባት #አባ_ሚካኤል የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አረፈ።


ሚያዝያ ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በዚህች ቀን ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል::
ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር:: የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል::
ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም::
በገሃድ በቤተ መቅደስ ብስራቱን፣ በቤተ ልሔም ልደቱን፣ በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣ በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣ በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::
የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ:: በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::
በዚያም የብርሃን ዐይን ተቀብለው፣ 6 ክንፍ አብቅለው፣ የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣ ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣ ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው፣ ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን ከግብጽ ደቡብ ከእብክ አውራጃ ከሆሪን ከተማ የከበረ አባት ይስሐቅ አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብርሃም የእናቱም ስም ሶስና ነው ታናሽም ሆኖ ሳለ እናቱ ሙታብቻውን ያለእናት አባቱ እያሳደገው ኖረ።
ጥቂት በአደገም ጊዜ የአባቱን በጎች የሚጠብቅ ሆነ አባቱም ሌላ ሚስት አገባ በዚያ ወራትም ታላቅ ረኃብ ሆነ የአባቱም ሚስት ትጠላው ነበረ ከጥቂትም በቀር እንጀራ አትሰጠውም ያንኑም ሁልጊዜ ለእረኞች ሰጥቶ እርሱ ግን እሰከምሽት ይፈጸማል።
ምሳውን ለእረኞች እንደሚሰጥና ሁልጊዜ እስከምሽት እንደሚጾም አባቱ ሰምቶ ዕውነት እንደሆነ ሊያይ ወደርሱ ሔደ ። ቅዱሱም ሕፃን የአባቱን መምጣት ዐውቆ በልብሱ ሦስት ጭቃ አድበልብሎ አሠረ እንደ ታሠረ በሚያየው ጊዜ ለአባቱ አምባሻ እንዲመሰለው ብሎ
አባቱም በመጣ ጊዜ የልጁን ልብስ ፈትቶ አየ አምባሻም ሁነው አገኛቸው። የነገረውንም ሰው ምግቡን ለእረኞች ከሰጠ በዛሬዪቱ ቀን ይህ አምባሻ ከወዴት ተገኘለት ብሎ ጠየቀው እርሱም በእውነት ሰጥቷል አለ ሌሎችም ብዙዎች መጥተው በዚህ ነገር ምስክሮች ሆኑ አባቱም አደነቀ እግዚአብሔርንም አመሰገነ።
ይህም በአደገ ጊዜ አባ ኤልያስ ወደሚባል ሰው ሔዶ መንኲሶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዓመታት ኖረ። አባ ኤልያስም በአረፈ ጊዜ በርኑግ ወደሚባል ገዳም ሔደ ስሙ ዘካርያስ ከሚባል አረጋዊ ዘንድ በታላቅ ገድል ተጠምዶ ኖረ።
አባቱም ያገኘው ዘንድ በሀገሮች ሁሉ ይዞር ነበረ በዚህ በበርኑግ ገዳምም በአገኘው ጊዜ ከእርሱ ጋራ እንዲመለስ አባቱ ለመነው አይሆንም አለ አባ ዘካርያስም ከአባቱ ጋራ ይሔድ ዘንድ እስከ ሚዐርፍም ከእርሱ ዘንድ እንዲኖር አዘዘው ይህ ቅዱስም ከአባቱ ጋራ ሔዶ እስከሚዐርፍ ድረስ ከእርሱ ዘንድ ኖረ።
አባቱም በአረፈ ጊዜ አባቱ የተወውን ገንዘብ ሁሉንም ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ ከከተማውም ጥቂት ራቅ ብሎ ለራሱ ታናሽ ማደሪያ ሠራ በሰላም እስከ ሚዐርፍባት ቀን ድረስ ያለ ማቋረጥ በበጎ ገድል በጾም በጸሎት በስግደት ኖረ በአረፈ ጊዜም በመልካም ቦታ አኖሩት ከዚያም ተሠወረ።
ከብዙ ዘመናትም በኋላ እግዚአብሔር ሊገልጠው ወዶ በመቃብሩ ላይ መብራት ሲበራ እህል ለሚዐጭዱ ሰዎች ሦስት ቀን ያህል ታየ ሊያዩትም ወደቦታው ሲደርሱ ያ መብራት ከእርሳቸው ይሠወራል በሁሉ ዘንድ እስቲሰማም እንዲህ ሁኖ ኖረ።
ከዚህም በኋላ በመቃብሩ ላይ እያበራ ያ መብራት ደግሞ ታያቸው ሥጋውም በዚያ እንዳለ ሁለተኛ በሕልም ነገራቸው ምእመናንም አክብረው በግመል ጭነው ወደ ሀገሩ መካከል ወደ ሆሪን ወሰዱት ነስሪን ከሚባል አገር መካከል ሲደርሱ ግመሉ በዚያ ተንበረከከ እንዲነሣም መቱት መነሣትንም እምቢ አለ መኖሪያው በዚያ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ ዐወቁ።
በዚያም በስሙ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ሥጋውን በውስጥዋ አኖሩ ከእርሱም ብዙ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳትም ዐሥራ ዘጠነኛ የሆነ እለእስክንድሮስ አረፈ። ስለርሱም ሐዋርያዊ አባት አትናቴዎስ እንዲህ አለ አባቴ እለእስክንድሮስ ተቀምጦ ወንጌልን አያነብም ቁሞ ያነባል እንጂ ከርሱ ጋራም ብርሃን አለ።
ሁለተኛም ስለርሱ ሲናገር ወደርሱ እመምኔቶች መጥተው በእኛ ዘንድ ሰባት ሰባት ቀን የሚጾሙ ደናግል አሉ ። በእጅዎቻቸውም ምንም ምን ሥራ አይሠሩም ብለው ነገሩት ።
እርሱም እኅቶቼ ሆይ እኔ ሁለት ቀን እንኳ ከቶ አልጾምኩም ፀሐይ እስኪገባም ቆይቼ አልበላሁም በልክ እበላለሁ በልክም እጾናለሁ በልክ በመጠንም እሠራለሁ በልክ ይበሉ ዘንድ በልክም ይጾሙ ዘንድ በልክም ሥራ ይሠሩ ዘንድ ንጉሩአቸው በበጎ ሥራ ሁሉ ይሰለፉ አለ።
የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ደጎች ምእመናን ናቸው እርሱም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ሁኖ ከታናሽነቱ ጀምሮ በውስጥዋ አደገ ። አባ መክሲሞስ አናጉንስጢስነት አባ ቴዎናስ ዲቁና ተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስም ቅስና ሹመውታልና እርሱም ከታናሽነቱ ጀምሮ ንጹሕ ድንግል ነው።
አባ ጴጥሮስ በሰማዕትነት የሚሞትበት ጊዜ ሲቀርብ በግዞት ቤት ሳለ ይህ እለእስክንድሮስና አኪላስ ከውግዘቱ ይፈታው ዘንድ ስለ አርዮስ ወደርሱ ገብተው ለመኑት ስለርሱ አባ ጴጥሮስን ይማልዱለት ዘንድ ሁለቱን ለምኖአቸዋልና።
አባት ጴጥሮስ ግን በውግዘት ላይ ውግዘትን ጨመረበት እንዲህም ብሎ ነገራቸው የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀደደ ልብስ ለብሶ ተገለጸልኝ ልብሴን አርዮስ ቀደዳት አለኝ። ይህም የባሕርይ አንድነቴን ለያት ማለት ነው ውግዘቱንም እንድጨምርበት እርሱ አዘዘኝ።
ደግሞ እንዲህ ገለጠላቸው አኪላስ ሊቀ ጵጵስና እንዲሾም ከርሱ በኋላም እለእስክንድሮስ እንደሚሾም አርዮስን እንዳይቀበሉት በምንም ሥራው እንዳይተባበሩት አዘዛቸው።
አባ ጴጥሮስም ምስክርነቱን በፈጸመ ጊዜ አኪላስ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ፡፡ የአባት ጴጥሮስንም ትእዛዝ ተላልፎ አርዮስን ከውግዘቱ ፈታው። ቅስናም ሾመው ስለዚህም አኪላስ በመንበረ ሢመቱ ያለ ስድስት ወር አልኖረም በድንገት ሞተ።
ከዚህ በኋላ ይህ አባት እለእስክንድሮስ ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ በመንበረ ሢመቱ ላይ ተቀመጠ አርዮስንም ከወገኖቹ ጋራ አውግዞ አሳደደው። የሀገር ታላላቆችም ከሕዝቡ መጡ ከውግዙቱ እንዲፈረታውም ለመኑት። በውግዘት ላይ ውግዘትን እንዲጨምር እንጂ እንዳይፈታ አባ ጴጥሮስ እንዳዘዘው ነገራቸው።
ከዚህ በኋላ አርዮስ ወደ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሒዶ በግፍ አወገዘኝ ብሎ እለእስክንድሮስን ከሰሰው። ስለዚህም ንጉሡ ሦስት መቶ አሥራ ስምንት የከበሩ አባቶችን በኒቅያ ከተማ ሰበሰበ፡፡ ይህም አባት እለእስክንድሮስ ተመርጦ ለጉባኤው ሊቀ መንበር ሆነ አትናቴዎስም ጸሐፊ ነበር። አርዮስንም ተከራክረው ክህደቱን ግልጽ አደረጉ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከአባቱ ከአብ ጋራ ከሕይወቱ መንፈስ ቅዱስም ጋራ በመለኮቱ ትክክል እንደሆነ አስረዱት።
ከክህደቱ ባልተመለሰ ጊዜ አውግዘው ለይተው ከቤተ ክርስቲያን አሳደዱት። በአንድ ቃልም ጸሎተ ሃይማኖትን ከአባቶች ጋራ ሠሩልን ደግሞ በእርሳቸው ቤተ ክርስቲያን ለዘላለም የምትመራባቸው ሃያ ቀኖናን ሠርተው ወሰኑ።
ከዚህ በኋላም ይህ አባት እለእስክንድሮስ ወደ መንበረ ሢመቱ ከድል ጋራ ተመለሰ። በበጎ አጠባበቅም መንጋውን ጠበቀ በወንጌላዊ ማርቆስ መንበርም አሥራ ሰባት ዓመት ኖሮ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የሐዲስ ማርቆስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ፡፡ እርሱም በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች አርባ ዘጠነኛ ነው ። ይህም አባት ከእስክንድርያ አገር ነው እርሱም በሥራው ሁሉ ቅድስናውን ጠብቆ ኖረ የተማረም ዐዋቂ ሆነ ለወንጌላዊ ማርቆስም በስም ሁለተኛ ነው ።
አባ ዮሐንስም ዲቁና ሾመው እጅግ መልካም ካህን ሆነ መጻሕፍትን በሚያነብ ጊዜ በአንደበቱ ቅልጥፍና በነገሩ ጣዕም የሚሰሙት ሁሉ ደስ የሚላቸው ሆኑ ። ከዚያም አባ ዮሐንስ ከእርሱ ጋራ አኖረው በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ሁሉ ሥልጣን ሰጠው ያለ እርሱም ምክር አባ ዮሐንስ ምንም ምን አይሠራም ።
ከዚህ በኋላ በአባ መቃርስ ገዳም የምንኲስና ልብስ አለበሰው በዚያች የምንኵስና ልብስ በለበሰባትም ቀን ከቅዱሳን አረጋውያን አንድ ጻድቅ ሰው መጥቶ በእርሱ ላይ እንዲህ ብሎ በሕዝብ ፊት ይህ ስሙ ማርቆስ የሚባል ዲያቆን በአባቱ በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ሊቀመጥ አለው ብሎ ትንቢት ተናገረለት ።
የአባ ዮሐንስም የሚሞትበት ጊዜ ሲቀርብ አባ ማርቆስን ሊቀ ጵጵስና እንዲሾሙት ኤጲስቆጶሳቱን አዘዛቸው በእርሱ መሾምም ደስ አላቸው ። ከአባ ዮሐንስ ዕረፍት በኋላም ያለ ፈቃዱ ሾሙት እርሱ ግን ከእርሳቸው ሸሽቶ ወደ አስቄጥስ ሔደ ሰዎችንም ልከው አሥረው ወደ መንበረ ሢመቱ አመጡት ።
ከዚህ በኋላም ጸጥ ብሎ ስለ አብያተ ክርስቲያን የሚያስብ ሆኖ የፈረሰውን አነፀ ጠገነ፡፡ በዘመኑም የመናፍቃንን ጠባይ ከሕዝቡ ውስጥ አስወገደ ይኸውም በግብጽ አገር የተገለጡ ለብቻቸውም ቤተ ክርስቲያን ሠርተው የሚኖሩ ናቸው እርሱም አስተምሮ መክሮ መልሶ ከመንጋዎቹ ጋራ አንድ አደረጋቸው። እግዚአብሔርም በዚህ አባት እጅ ድውያንን በመፈወስ አጋንንትን በማስወጣት ብዙ ድንቆች ምልክቶችን ገለጠላቸው።
ከእርሳቸውም አንዱን አስተውል አንተ ያለ ፍርሀት በድፍረት ሥጋውንና ደሙን የምትቀበል ባትሆን ይህ ባላገኘህም ነበር ከእንግዲህ ከክፉ ሥራና ከአንደበትህ ከሚወጣ ከከንቱ ነገርም ሰውነትህን ጠብቅ አለው።
በዘመኑም በምዕራብ ያሉ እስላሞች ይሸጡአቸው ዘንድ ብዙ ክርስቲያኖችን ከሮም ግዛት ውስጥ ማርከው ወደ እስክንድርያ አመጡአቸው ይህም አባት እጅግ አዘነ ከየገዳማቱና ከምእመናን ብዙ ገንዘብ ለምኖ ከእስላሞች እጅ በሠላሳ ሽህ የወርቅ ዲናር ዋጃቸው የነፃነትም ደብዳቤ ጽፎ ነፃ አወጣቸው ። እንዲህም አላቸው ወደ አገሩ መመለስ የሚሻ እኔ ስንቅ ሰጥቼ አሰናብተዋለሁ ከእኔ ጋራ መኖር የሚሻም ካለ እኔ እጠብቀዋለሁ አላቸው። የተመለሱ አሉ ስንቅ ሰጥቶም ያሰናበታቸው አሉ ከእርሱ ዘንድ የቀሩትንም ጠበቃቸው አጋባቸውም።
ከዚህ በኋላ ስለ መድኃኒታችን ቤተ ክርስቲያን አሰበ አደሳትም ሰይጣንም በሀገር ውስጥ ሁከት አስነሥቶ በእሳት አቃጠላት ይህም አባት መልሶ ዳግመኛ አደሳት። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ሊአሳርፈው በወደደ ጊዜ ጥቂት ታመመ በፋሲካ በዓል በእሑድ ቀንም ወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ተገለጠለት ለሚወዱት እግዚአብሔር ስለ አዘጋጀው ተድላ ደስታ ነገረውና ሥጋውንና ደሙን ከተቀበልክ በኋላ ታርፋለህ አለው። በነቃ ጊዜም እንዴት እንዳየ ከእርሱ ዘንድ ላሉ ኤጲስቆጶሳት ነገራቸው።
ከዚያም የቅዳሴውን ሥርዓት ጀምሮ ቀድሶ ሥጋውን ደሙን ተቀበለ በዚያን ጊዜም አረፈ የሹመቱም ዘመን ሃያ ዓመት ሆነ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ አባት አባ ሚካኤል የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አረፈ፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሳ ሦስተኛ ነው ። ይህም ቅዱስ ጻድቅ መንኲሶ በአስቄጥስ በቅዱስ ዮሐንስ ገዳም አበ ምኔት ሁኖ ተሾመ ከዚያም ያለ ፈቃዱ ወስደው በግድ ሊቀ ጵጵስና በእስክንድርያ አገር ላይ ኅዳር ሃያ አራት ቀን ሾሙት ። በሊቀ ጵጵስናውም ሥራ ተጠምዶ የሚጋደል ሆነ እንደ ሐዋርያትም አጠባበቅ መንጋውን ጠበቀ ።
ታላቁ ጾምም በደረሰ ጊዜ ወደ አስቄጥስ በዚያ ሊጾም ወጣ ከመሾሙ በፊት በዚያ ገዳም ውስጥ በብሕትውና ሁኖ መጠመዱንና የቀድሞ መጋደሉን አሰበ ።
ወደ ጌታችንም እንዲህ ብሎ ለመነ አቤቱ እኔ በብቸኛነት መኖርን እንደምሻ አንተ ታውቃለህ ለዚች ለተሾምኩባትም ሹመት ችሎታ የለኝምና የምትገባኝም አይደለችምና በይቅርታህም ብዛት ነፍሴን ወስደህ ከዚህ ድካም ታሳርፈኝ ዘንድ እለምንሃለሁ ጌታም ልመናውን ተቀበለ ከፋሲካ በዓል በኋላም በፍቅር አንድነት አረፈ፡፡ የሹመቱም ዘመን ሁለት ዓመት ከአምስት ወር ነው።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages