ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 23 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, May 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 23

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ሃያ ሦስት በዚህች ቀን ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ_የቅዱስ_ጊዮርጊስ የምስክርነት ፍጻሜ ሆነ፣ ተአምራትን እስከ አሳየ ድረስ የተጋደለ ቅዱስ_ሮቆ አረፈ።


ሚያዝያ ሃያ ሦስት በዚህች ቀን ፀሐይና የአጥቢያ ኮከብ የተባለ ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የምስክርነት ፍጻሜ ሆነ። የዚህም ቅዱስ አባቱ መስፍን ነው ስሙም አንስጣስዮስ ይባላል ከቀጰዶቅያ አገር ነው የእናቱም ስም ቴዎብስታ ይባላል ከፍልስጥዔም አገር ናት ታናሽ ሆኖ ሳለ አባቱ አረፈ።
ሃያ ዓመትም በሆነው ጊዜ የአባቱን ሹመት ሊቀበል ወደ ንጉሥ ዱድያኖስ ዘንድ ሔደ፡፡ ንጉሡም ጣዖት አቁሞ ጣዖትን እንዲአመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው። ይህንንም አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ በእርሱ ዘንድ ያለውን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ለምስኪኖች ሰጠ ባሮቹንም ነፃ አወጣቸው።
ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። ንጉሡም አባበለው ብዙ ቃልኪዳንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም። ለመስማት እንኳ የሚያስጨንቅ ሥቃይን አሠቃየው ጌታችን ግን ያጸናዋል ቍስሉንም ያድነዋል ሦስት ጊዜም እንደ ሚሞት እርሱም እንደሚአሰነሣው በአራተኛውም የምስክርነት አክሊልን እንደሚቀበል ነገረው። ቃል ኪዳንም ሰጠው ስሙ በዓለሙ ሁሉ የተገለጠ ይሆን ዘንድ በተጋድሎና መከራ በመቀበልም ጽኑዕ በሆነ ሥቃይም ሰባት ዓመት እንደሚኖር መላእክትም እንደሚአገለግሉት ነገረው።
ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመታዘዙና ባለመመለሱ እጅግ አዘነ ስለዚህም አትናስዮስ የሚባል ታላቅ ሥራየኛ አመጣ እርሱም መርዝን ቀምሞ በጽዋ መልቶ አስማት ደግሞ እንዲጠጣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው። ወዲያውኑ የሚሞት መስሎት ነበር። ቅዱሱም ያንን ጽዋ ጠጣው ምንም ጉዳት አልደረሰበትም።
ያ መሠርይም በክብር ባለቤት በጌታ ኢየሱስ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ። ከእርሱም ጋራ ሌሎች ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሙተው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ ቍጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ሰባት መቶ ነፍስ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስም በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ በዚያም የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮች ነበሩ። ቅዱሱንም እሊህን የተቀመጥንባቸውን ወንበሮች እንዲበቅሉ እንዲአብቡና እንዲአፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን አሉት። በዚያን ጊዜ ጸለየ እንዳሉትም አደረጋቸው ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ቍጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን አመኑ።
ከዚህም በኋላ ቅዱሱን ወስደው በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት። አቃጥለው አሳርረውም ሥጋውንና አጥንቱን ፈጭተው አመድ አድርገው ከረጅም ተራራ ላይ በተኑት። ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው። ወደ ነገሥታቱም ተመልሶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ስም ሰበከ ቁጥር የሌላቸው አሕዛብ አይተው አደነቁ በጌታችንም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።
ነገሥታቱም ደግመው ሙታኖችን ብታሥነሣ አምላክህ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን በእርሱም እናምናለን አሉት። ቅዱሱም ጸለየ ከጉድጓድም ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ጎልማሶችንም አስነሣላቸው እነዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ስም አስተማሩ የገሀነምንም ወሬ ተናገሩ ጥምቀትንም ተቀብለው ተመልሰው አረፉ።
ከሀድያን ነገሥታት ግን ሙታንን ያስነሣህ አይደለም የረቀቁ ሰይጣናትን አሳየህ እንጂ ብለው ተከራከሩ። ከዚያም ከጭንቀታቸው ብዛት የተነሣ ከአንዲት ድኃ ሴት ዘንድ አስጠበቁት እርሷም እንጀራ ልትለምንለት ወጣች የእግዚአብሔርም መልአክ በላዩ ከበጎ ነገር ሁሉ የተመላ ማዕድን አቀረበላት። የዚያች መበለትም የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍን አበቀለ ታላቅ ዛፍም ሆነ። ያቺም መበለት በተመለሰች ጊዜ የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍ አብቅሎ ታላቅ ዛፍ እንደሆነ ስለ ማዕዱም ይህን ታላቅ ምልክት አይታ የክርስቲያኖች አምላክ ሰው ተመስሎ ወደእኔ መጣ አለች።
ቅዱሱም እኔ አምላክ አይደለሁም የአምላክ ባሪያ ነኝ እንጂ አላት። እርሷም እንዲህ ብላ ለመነችው የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ቸርነትህ እንድትደርሰኝ አለምንሃለሁ። ዕውር ደንቆሮ ዲዳ ጐባጣ የሆነ ልጅ አለኝና ታድንልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። ስለ ጌታችን እምነትም አስተማራትና በመስቀል ምልክት አማተበው ያንጊዜም አየ። ቅዱሱም በሌላ ጊዜ እንዲሰማ እንዲናገርና እንዲሔድ እንዲአገለግለኝም እኔ እሻለሁ አላት።
በዚያን ጊዜ ንጉሡ በአገሩ ሜዳ ውስጥ ሲዘዋወር ያቺን ዛፍ አይቶ አደነቀ ስለ እርሷም ጠየቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእርሷ ዘንድ የተቀመጠባት የዚያች መበለት የቤቷ ምሰሶ እንደሆነ ነገሩት። ንጉሡም ተቆጣ ቅዱሱንም ከዚያ ወስዶ አሰገረፈው በመንኰራኩርም አበራዩት ሙቶም ከከተማ ውጭ ጣሉት ጌታም ከሞት አስነሣው ወደ ነገሥታቱም ተመለሰ ንጉሡም አይቶ ደነገጠ ስለ ሕይወቱም አደነቀ።
ከዚህም በኋላ ይሸነግለው ዘንድ ጀመረ በመንግሥቱ ላይም ሁለተኛ ያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት ቅዱስ ጊዮርጊስም እየዘበተበት ነገ በጥዋት ለአማልክቶችህ መሥዋዕትን አቀርባለሁ አንተም ሕዝቡ እንዲሰበሰቡ እዘዝ እኔ ስሠዋ እንዲአዩ አለው፡፡ ንጉሡም ዕውነት የሚሠዋ መስሎት ደስ አለው ወደ ቤተ መንግሥቱም እልፍኝ አስገብቶ አሳደረው፡፡
ለጸሎትም ተነሣ የዳዊትንም መዝሙር አነበበ የዱድያኖስ ሚስቱ እለስክንድርያ ንግሥት ሰምታ ቃሉ ደስ አሰኛት የሚያነበውንም ይተረጒምላት ዘንድ ለመነችው እርሱም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ሰው እስከሆነበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ ሊያስረዳትና ሊያስገነዝባት ጀመረ ትምህርቱም በልቡዋ ተቀርጾ በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች፡፡
በማግሥቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአማልክት ሲሠዋ ለማየት ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ ዐዋጅ ነጋሪ ዞረ የቤቷን ምሰሶ ያበቀለላት ያቺ መበለት ሰምታ ዕውነት መስሏት እጅግ እያዘነች ልጅዋን ተሸክማ እያለቀሰችም ወጣች፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስም በአያት ጊዜ ፈገግ አለ ልጅሽን በምድር ላይ አኑሪው አላት ከዚያም ልጅዋን ጠርቶ ወደ አጵሎን ሒድ ወደእኔም ይመጣ ዘንድ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ስም እዘዘው አለው፡፡ ያን ጊዜ ያ ልጅ ድኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳዘዘው ወደ ጣዖቱ ቦታ ሒዶ አዘዘው፡፡ በጣዖቱ ያደረ ያ ርኵስ መንፈስም ከማደሪያው ወጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አለበት መጥቶ እኔ ሰውን ሁሉ የማስት እንጂ አምላክ አይደለሁም ብሎ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አመነ፡፡ ቅዱሱም ትውጠው ዘንድ ምድርን አዘዛትና ወዲያውኑ ዋጠችው ጣዖታቱንም ከአገልጋዮቻቸው ጋራ አጠፋቸው ንጉሡም ከወገኖቹ ጋር አፈረ፡፡
ብስጭትና ቁጣንም እንደተመላ ወደ ንግሥት ሚስቱ ዘንድ ገባ፡፡ እርሷም አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነውና ክርስቲያኖችን አትጣላቸው አላልኩህምን አለችው፡፡ ይህንንም ከእርስዋ ሰምቶ በእርሷ ላይ እጅግ ተቆጣ ወደ ክብር ባለቤት ክርስቶስ እምነት የከበረ ጊዮርጊስ እንደአስገባት አወቀ፡፡
ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ እንዲጐትቷትና በመጋዝም እንዲሰነጥቋት አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች፡፡ በዚያም ጊዜ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ ነገሥታቱ ሁሉም ደነገጡ ኀፍረት ደግሞ እንዳይጨምርባቸው ከእርሱም እንዲአርፍ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ እንዲጽፍ ንጉሥ ዱድያኖስን መከሩት፡፡
ያን ጊዜም የክቡር ጊዮርጊስን ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ድል አድራጊ ጊዮርጊስም እጅግ ደስ አለው እሳት ከሰማይ አውርዶ ሰባውን ነገሥት ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያን ወገን ጸጥ ይል ዘንድ ጌታችንን ለመነው፡፡ ወዲያው እሳት ወርዶ ከሠራዊታቸው ጋር ሰባውን ነገሥታት አቃጠላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ ይህንንም ጌታችን ተናግሮ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ፡፡
ከዚህ በኋላ ራሱን ዘንበል አድርጎ በሰይፍ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያት አክሊላትን ተቀበለ፡፡ ከአገልጋዮቹም የቀሩት ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀለሉት ወደ ሀገሩ ልዳም ወሰዱት፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው በውስጥዋ አኖሩት ከእርሱም ቍጥር የሌላቸው ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ተአምራትን እስከ አሳየ ድረስ የተጋደለ ቅዱስ ሮቆ አረፈ። በአንዲት ዕለትም ለጸሎት ቁሞ ሳለ የንዳድ ትንኝ ነደፈው ቀስሉን እያሳየ በብዙ ልቅሶ ወደ ጌታችን ለመነ።
ያን ጊዜም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና ላይ ተገለጠለት። በአንጻሩም ቁሞ ወዳጄ ሮቆ አትፍራ ላድንህ ወደ አንተ መጥቻለሁና ።
ደግሞም የሮቆ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከንዳድ በሽታ አድነኝ ብሎ በስምህ ለሚለምነኝ የንዳድ በሽታ በላዩ ላላመጣበት ከአንተ ጋራ ቃል ኪዳንን ላጸና መጣሁ አለው።
ይህንንም ብሎ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ቅዱስ ሮቆም በብዙ ገድል ተጠምዶ ኑሮ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የቅዱሳኑ በረከት ረድኤት ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages