አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት ሃያ አራት በዚች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋራ ወደ ግብጽ ምድር ወረደ፣ ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነቢይ እንባቆም አረፈ፣ የእንጽና አገር የከበረ ቀሲስ አብቍልታ በሰማዕትነት አረፈ።
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስደት
ግንቦት ሃያ አራት በዚች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋራ ወደ ግብጽ ምድር ወረደ። ያን ጊዜም እርሱ ጌታ የሁለት ዓመት ሕፃን ነበር። ወንጌላዊ እንዳለ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ምድር ሽሽ ተመለስ ብዬ እስከምነግርህም በዚያው ኑር።
የጌታችንም ወደ ግብጽ መምጣት ሰለ ሁለት ሥራዎች ነው አንዱ ኄሮድስ ቢያገኘው ሊገድለው እንደአይችል። ስለዚህ ሌሎች ትስብእቱ ምትሐት ነው ብለው እንዳያስቡ። ሁለተኛው የግብጽ ሰዎች በመካከላቸው በመመላለሱ ጸጋውን እንዲያገኙ ጣዖታትንም ቀጥቅጦ ለማጥፋት እነሆ አግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብጽ ይወርዳል ጣዖታትም በፊቱ ይወድቃሉ ያለው የነቢይ ኢሳይያስ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ።
የክብር ባለቤት ጌታችንም በረቀቀ ጥበቡ ሸሸ በመጀመሪያም የደረሱበት አገር ስሙ በስጣ ይባላል አልተቀበሏቸውም በዚያም የውኃ ጉድጓድ ቆፈሩ ያቺም ውኃ ለሩቆች ፈዋሽ ስትሆን ለዚያች አገር ሰዎች ግን መራራ ሆነች።
ከዚያም በገምኑዲ መንገድ ተጉዘው ወንዝ ተሻግረው ወደ ምዕራብ ደረሱ። የክብር ባለቤት ጌታችንም ተረከዙን በአለት ላይ አደረገ በተረከዙም አምሳል በአለቱ ላይ ተቀረጸች እስከ ዛሬ ያም ቦታ የጌታችን የተረከዝ ቅርጽ ተባለ።
ጌታችንም እመቤታችን ድንግል ማርያምን እናቴ ሆይ በዚህ ቦታ ቤተ ክርስቲያን በስምሽ ይሠራ ዘንድ እንዳለው ዕወቂ። በውስጡም ድንቅ ተአምራትን አደርጋለሁ ስሙም ደብረ ምጥማቅ ይባላል አላት።
ከዚያም ወደ ፀሐይ መግቢያ ወዳለ ባሕር ሔዱ የአስቄጥስንም በረሀ ዱር ከሩቅ አዩ። ጌታም በላዩ ባረከ እናቱንም እናቴ ማርያም ሆይ በዚህ ዱር ውስጥ ብዙዎች ሰዎች መነኰሳትን ሁነው በገድልም ተጸምደው በመላእክት አምሳል ያገለግሉኛል።
ከዚያም በፀሐይ መውጫ በኲል ወደአለ ተራራ ሔዱ ዮሴፍም የሚመረኰዘው በትር በእጁ ነበር ጌታችንም ይህ ቦታ የሚያቃጥል በረሀ ነውና እንቀመጥ አለ።
ጌታችንም የዮሴፍን በትር አንሥቶ ሰበራት ጥቃቅን ስብርባሪዎች አድርጎ በዚያ ቦታ ተከላቸው። በከበሩ እጆቹ ጉድጓድ ማሰ መዓዛው የሚጣፍጥ ውኃ ፈልቆ ፈሰሰ ከእዚያ ውኃም በመሐል እጁ እየዘገነ የተከላቸውን ስብርባሪዎች አጠጣቸው። ወዲያውኑ በቀሉ አድገውም ታላላቅ ዛፎች ሆኑ ከእርሳቸውም ጣፋጭ ሽታ ሸተተ። እርሱም ከሽቱዎች ሁሉ እጅግ የሚጣፍጥ ነው በለሳንም ብሎ ጠራቸው። እናቱን ድንግል እመቤታችንንም እናቴ ሆይ ይህ የተከልኩት በለሳን እስከ ዓለም ፍጻሜ ከዚህ ይኖራል የክርስትና ጥምቀትንም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለሚጠመቁ ከእርሱ ቅባት ይገኛል አላት የዚያም ስም መጣሪያ ነው።
ከዚያም ብህንሳ ወደሚባል አገር ሔዱ ትርጓሜው ቤተ ኢየሱስ የሆነ በይሱስ ወደሚባልም ቦታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሽታውን ደዌውን ሁሉ የሚፈውስ የጒድጓድ ውኃ አደረገ።
ሁለተኛም በአንዲት የጕድጓድ ውኃ ምልክትን በየዓመቱ አደረገ ይኸውም ከቀኑ እኲሌታ በማዕጠንትና በጸሎት ጊዜ ለእግዚአብሔር በዚያች የውኃ ጕድጓድ ዕጣንን ሲያሳርጉ የከበረ የወንጌል ንባብም ሲፈጸም በዚያች ጉድጓድ ውስጥ ያለ ውኃ ወደ ላይ ወጥቶ እስከ ጉድጓዱ አፍ ይደርሳል። ከእርሱም ይባረካሉ ከዚያም በኋላ እንደ ቀድሞው ወደ ቦታው ይመለሳል። ውኃው ከነበረበት እስከ ደረሰበት ይሰፍሩታል። ሃያ ክንድ የሆነ እንደሆነ የጥጋብ ዘመን ይሆናል ዐሥራ ሰባት ክንድ ከሆነ ግን በግብጽ አገር ታላቅ ረኃብ ይሆናል።
ከዚያም ወደ እስሙናይን አገር ሔዱ በዚያ ያሉ ጣዖታትም ወድቀው ተሰባበሩ። እነርሱም ስሙ አፍሎን ከሚባል ሰው ዘንድ ተቀመጡ። በዚያም የእሸ እንጨት ዛፎች አሉ ለጌታችንም ሰገዱ እስከ ዛሬም እንደ ሰገዱ ናቸው። ከዚያም ወደ ደብረ ቍስቋም ሔደው በውስጧ ስድስት ወር ተቀመጡ በዚያም በሽታን ሁሉ የሚያድን የጉድጓድ ውኃ አደረገ።
ጌታችንም የፈቀደውን በግብጽ የሚኖርበት ወራት በፈጸመ ጊዜ ይኸውም ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ነው። ኄሮድስም ከሞተ በኋላ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ የሕፃኑን ነፍስ የሚሹት ሙተዋልና ተነሣ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ተመለስ አለው።
ያንጊዜም ተመልሰው ወደ ምስር ደረሱ ወደ መዓልቃም በዚያ በዋሻ ውስጥ አደሩ እርሷም እስከ ዛሬ የቅዱስ ሰርጊስ ቤተ ክርስቲያን ናት። ከዚያም ወጥተው ወደ መጣርያ ደርሰው በውስጧ ታጠቡ። ይቺም የውኃ ምንጭ አስቀድመን እንደተናገርን ጌታችን ያፈለቃት ከዚያች ሰዓት ጀምሮ የተባረከችና የከበረች ሆነች። ከዚያም ጌታችን የተከለው የክርስትና ጥምቀት የሚፈጸምበት በለሳን ቅባት የሚወጣው ነው። በእርሱም ደግሞ አብያተ ክርስቲያናት ንዋየ ቅድሳትና ታቦተ ሕጉም የሚከብርበት ድኅነትም የሚደረግበት ለክርስቲያኖች ሁሉ መመኪያቸው ነው።
በጌታችን መመለስም ልጄን ከግብጽ ጠራሁት ያለው የኦዝያን ትንቢት ተፈጸመ። ስለዚህም ተአምራትን በግብጽ ድንቅ ሥራንም በጣኔዎስ በረሀ ያደረገ በማለት እየዘመርን በዚች ዕለት መንፈሳዊ በዓልን ልናደርግ ይገባናል። ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ስለ እኛ ለተሰደደ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በእኛ ላይም ይቅርታውና ምሕረቱ ይሁን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ እንባቆም ነቢዩ
በዚህችም ዕለት ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነቢይ ዕንባቆም አረፈ። ይህም ቅዱስ በአንዲት ዕለት እህሉን ለሚያጭዱለት ምሳቸውን አዘጋጅቶ ተሸክሞ ሲሔድ መልአክ ተገልጾለት ይህን መብል በባቢሎን አገር በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ላለ ለነቢዩ ዳንኤል ውሰድ አለው።
ዕንባቆምም ጌታዬ ሆይ ባቢሎንን አላየኋት ጉድጓዱንም አላውቀው አለው። የእግዚአብሔር መልአክም በራሱ ጠጉር ያዘው ምግቡን በእጁ እንደያዘ ወሰደውና ጉድጓዱ እንደተዘጋ አስገባው ምግቡንም ሰጥቶ መገበው ወዲያውኑ ዕንባቆምን ወደ ይሁዳ አገር መለሰው።
በአረጀና በሸመገለም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ከተማረኩበት ተመልሰው ቤተ መቅደስን ሠሩ። ዕንባቆምም ኢየሩሳሌም ደርሶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ በታላቅ ደስታም ተቀበሉት ትንቢቱንም ሊሰሙ ወደርሱ ተሰበሰቡ አፉንም ከፍቶ በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለ።
አቤቱ ድምፅህን ሰማሁ ሰምቼም ፈራሁ ሥራህንም አይቼ አደነቅሁ አለ። ስለ መድኃኒታችንም መውረድና በይሁዳ ክፍል በሆነች በቤተ ልሔም ስለመወለዱ ሲናገር የተመሰገነ እግዚአብሔር ግን ከፋራን ተራራ ከቴማን ከይሁዳ አውራጃ ይመጣል ብሎ እስከ መጨረሻው ተናገረ ከነቢያት መጻሕፍትም ጋራ ደመርዋት።
ከዚህ በኋላ ከእስራኤል ልጆች አንዲት ሴት ወደርሱ መጣች እያለቀሰችም እንዲህ አለችው። ሁለት ልጆች ነበሩኝ ጣዖት እንዲአመልኩ ፈለጉአቸው እምቢ በአሉ ጊዜም ገድለው በጐዳና ላይ ጣሉአቸው። ተገድለው ወደ አሉበትም አብሮዋት ሔደ ነፍሳቸውንም ይመልስላቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ለመነው ልመናውንም ተቀበሎ በሕይወት አነሣቸው።
ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ዘመዶቹን ጠራቸው። እንደሚሞትም ነገራቸውና አንዲት ሰዓት ያህል ወደላይ እየተመለከተ ተቀመጠ። እነሆ እንደ ሰው ክንድ ያለች ታላቅ ክንድ የቤቱን ጣሪያ ሠንጥቃ ወረደች ወደ አፉም ተዘርግታ ነፍሱን ወሰደች ያን ጊዜም አረፈ።
በክርስቲያናዊ ንጉሥ በአንስጣስዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ ገድሉን በአነበበ ጊዜ አድንቆ በግብጽ ደቡብ ቀርጣስ በሚባል ቦታ በስሙ ቤተ ክርስቲያን ሠራለት እርሷም በዚች ቀን ከበረች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቀሲስ ቅዱስ አብቍልታ
በዚህችም ዕለት የእንጽና አገር የከበረ ቀሲስ አብቍልታ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ባለ መድኃኒት ነው ለበሽተኞች በጎ ሥራ በመሥራት ያለ ዋጋ ያክማቸዋል ደግሞም የሚበሉትን የሚጠጡትን የሚለብሱትን የሚሹትን ሁሉ ይሰጣቸዋል ።
በዚያም ወራት ወደ ሰዒድ አውራጃ ወደ መኰንኑ አርያኖስ ዲዮቅልጥያኖስ ላከ የዚያቺን አገር ሰዎች ለጣዖታት እንዲሰግዱ ያስገድዳቸው ዘንድ። በዚያንም ጊዜ ይህን ቅዱስ ያዙት ወደ እስሙናይንም ወስደው በመኰንኑ ፊት አቆሙት መኰንኑም ወደርሱ ይመልሰው ዘንድ በጎ ቃልን ተናገረው ሊመልሰውም ባልቻለ ጊዜ ቆዳው እስቲሠነጣጠቅ እንዲገርፉት አዘዘ ከዚህም በኋላ በሕይወት እያለ በእሳት አቃጠሉት። ገድሉንም በዚህ ፈጸመ ምእመናንም መጥተው በድኑን ወሰዱ ከከተማው ደቡባዊ በሆነ ተራራ ላይ ገንዘው በክብር ቀበሩት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን፣አምላክን የወለደች የድንግል እመቤታችን ማርያም በረከቷ የቅዱሳኑ በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት
No comments:
Post a Comment