አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት ሃያ አምስት በዚች ቀን አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል የእመቤታችን የአክስቷ ልጅ ቅድስት ሰሎሜ አረፈች፣ ከእንዴናው አገር የከበረ ቅዱስ ኮጦሎስ በሰማዕትነት አረፈ፣ ስብስጣ ከሚባል አገር አባ ሄሮዳ በሰማዕትነት አረፈ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ የምንከብርበትን ቅብዓ ሜሮን አፍልቆልናል፡፡
ቅድስት ሰሎሜ
ግንቦት ሃያ አምስት በዚች ቀን አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል የእመቤታችን የአክስቷ ልጅ ብፅዕት ሰሎሜ አረፈች። እርሷም የማጣት ልጅ የሌዊ ልጅ የሚልኪ ልጅ የካህን አሮን ልጅ ናት። ለማጣት ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱ ስም ማርያም ነው የሁለተኛዪቱ ስም ሶፍያ የሦስተኛዪቱም ሐና ነው ይቺም ማርያም ሰሎሜን ወለደቻት ሶፍያም ኤልሳቤጥን ወለደቻት ሐናም አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደቻት።
እመቤታችንም ድንግል ስትሆን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ ይቺ ቅድስት ሰሎሜ የእመቤታችንን አወላለድ እንደ ሴቶች ሁሉ አወላለድ መስሏት ተጠራጠረች ከዚህም በኋላ የድንግል እመቤታችን ገላዋን ዳሠሠቻት ያን ጊዜ እጇ ተቃጠለ ሕፃኑን በዳሠሠችው ጊዜ ደግሞ ዳነች።
በዚህም በኅቱም ድንግልና አምላክን እንደወለደች አወቀች። ከተረገመ ኄሮድስ ፊት እመቤታችን በሸሸች ጊዜ ከዮሴፍ ጋራ በመሆን አብራ በመሰደድ የእመቤታችንን ድካሟን ተካፍላ አገለገለቻት ከስደት እስከ ተመለሱ ድረስ ሕፃኑን ታዝለዋለች የምታጥብበትም ጊዜ አለ።
መድኃኒታችን ሰው በሆነበት ወራት ሁሉ አልተለየችም በመከራውም ቀን ከእመቤታችን ጋራ ከከበሩ ሁሉ ሴቶች በትምህርቱ ወራት ከተከተሉት ጋራ እያለቀሰች ነበረች።
በተነሣባት ዕለት ወደ መቃብር ገሥግሣ ከሐዋርያት ቀድማ ያየች ናት። በኃምሳኛውም ቀን መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከባልንጆሮቿ የከበሩ ሴቶች ጋራ ሰማያዊ ሀብትን ተቀብላ በክብር ባለቤት መድኃኒታችን ስም ሰበከች ብዙዎችንም አሳመነች። ከአይሁድም ብዙ ስድብና ሽሙጥ አገኛት ከዚያም አረፈች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ኮጦሎስ
በዚህችም ቀን ከእንዴናው አገር የከበረ ኮጦሎስ በሰማዕትነት አረፈ። የዚህም ቅዱስ እናትና አባቱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው አባቱም የእንዴናው ገዥ መኰንን ነው ልጅ አልነበረውም ይህን ቅዱስ ልጅ እስከ ሰጠው ድረስ ጌታችንን አዘውትሮ ይለምነው ነበር የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት አስተማረው።
ከታናሽነቱ ጀምሮ ንጹሕ ሆነ ለራሱም ሥርዓት በመሥራት በቀን መቶ እንዲሁ በሌሊትም መቶ ጸሎታትን ይጸልያል። ጥቂት በአደገ ጊዜም ወላጆቹ ሊአጋቡት ፈለጉ እርሱ ግን አልፈቀደም። ነገር ግን ከእርሱ በኋላ የተወለደች ሴት ልጅ ነበረቻቸውና እርሷን ከአርያኖስ ጋራ አጋቧት።
አባቱም ከሞተ በኋላ ለስደተኞች የእንግዳ መቀበያ ቤት ሠርቶ ስደተኛውንና እንግዳ መቀበልን ጀመረ። ከዚህም በኋላ የጥበብ መጽሐፍ ተምሮ ሐኪም ሆነ። በሽተኞቹ ሁሉ ወደ ርሱ ይመጣሉ እርሱም ያለ ዋጋ ይፈውሳቸዋል።
ዲዮቅልጥያኖስም በካደ ጊዜ አርያኖስ ስለ ሹመቱ ከንጉሡ ጋራ ተስማምቶ ሰማዕታትን የሚያሠቃያቸው ሆነ። ይህ ቅዱስም ሰማዕት ለመሆን ይተጋ ነበር ወደ ፍርድ አደባባይም ሒዶ አርያኖስን ንጉሡንም አለቆቹን ሁሉ ረገማቸው ጣዖታቱንም ሰደበ።
አርያኖስም ስለ እኅቱ በእርሱ ክፉ ሊአደርግበት አልተቻለውም ወደ እኅቱ ላከው እንጂ። እርሷም ከመታሠር አዳነችው። ከአርያኖስም በኋላ ሌላ መኰንን ተሾመ የዚህ የቅዱስ ኮጦሎስን ዜና ነገሩት። ጭፍራ ልኮ ወደርሱ አስመጣውና በርሱ ላይ በመቆጣት ለአማልክት ካላጠንክ ይህ ካልሆነ ጽኑ ሥቃይ አሠቃይሃለሁ አለው። ቅዱሱም እኔ ለረከሱ አማልክት ዕጣን አላቀርብም ለክብር ባለቤት ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሕ መሥዋዕትን አቀርባለሁ እንጂ ብሎ መለሰለት። በዚያን ጊዜም መኰንኑ ተቆጥቶ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ እንዲአሠቃዩት አዘዘ። የእግዚአብሔር መልአክም ወደ ርሱ መጥቶ ይፈውሰው ያጽናናውና ያረጋጋው ነበር።
ጌታችንም በእጆቹ ታላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራትን አደረገ። ማሠቃየቱ በሰለቸው ጊዜ በሰይፍ ራሱን ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ። የሰማዕታትንም አክሊል ተቀበለ ቤተ ሰቦቹም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖሩት። ከሥጋውም እጅግ ብዙ ድንቆች ተአምራት የሚታዩ ሆነ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ኄሮዳ ሰማዕት
በዚህችም ቀን ስብስጣ ከሚባል አገር አባ ኄሮዳ በሰማዕትነት አረፈ። ከከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስ በክርስቲያን ወገኖች ላይ የስደት ወራት በሆነ ጊዜ ይህ ቅዱስ አባ ኄሮዳ ከሕፃንነቱ ጀምሮ እግዚአብሔርን ይፈራ ነበር።
በአንዲት ሌሊትም በዐልጋው ተኝቶ ሳለ እርሱም ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ በማሰብ በኃላፊው ዓለም ውስጥ መኖር ምን ይጠቅመኛል። በከበረ ወንጌል የተናገረውን የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ይህን ዓለም ያልካደ ሊያገለግለኝ አይችልም ያለውን ሰምቻለሁና አሁንም ተነሥቼ ሔጄ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ደሜን አፈሳለሁ አለ።
ይህንንም በልቡ ሲያስብ እነሆ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጥቶ የከበርክና የተመሰገንህ ኄሮዳ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን አትፍራ እግዚአብሔር የክብር ዙፋን አዘጋጅቶልሃልና እኔም የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነኝ። እኔም ወደ ፍርድ አደባባይ ከአንተ ጋራ እሔዳለሁ በከበረ ሥጋህም ላይ ምንም የሚበረታብህ የለም ብሎት ሰላምታም ሰጥቶት ወደ ሰማይ ዐረገ።
ከዚህም በኋላ ብፁዕ አባ ኄሮዳ ወደ ምዕራባዊ አገር ወጣ። ፊቱንም ወደ ምሥራቅ መልሶ እንዲህ ብሎ ጸለየ ልዩ ሦስት አንድ አምላክ ሆይ ጌትነት በረከት ክብር ገንዘብህ የሆነ ለአንተም ለብቻህ ስግደትና አምልኮት የሚገባህ የተሳልኩትን እስከምፈጽም ታጸናኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
ይህንንም ብሎ ወደ ፍርድ ሸንጎ ሔዶ እኔ ክርስቲያን ነኝ ብሎ በግልጥ ጮኸ። መኰንኑም ክርስቲያንስ ሆነሃል አገርህ ወዴት ነው አንተ ማነህ ስምህስ ማነው ወገንህስ ምንድነው አለው። የከበረ ኄሮዳም በብህንሳ አውራጃ ስብስጣ ከሚባል አገር ነኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ ለምድራዊ ሟች ለሆነ ንጉሥ ሳገለግል ኖርኩ እንግዲህስ ሕያው ለሆነ ሰማያዊ ንጉሥ አገለግላለሁ ብሎ መለሰለት።
ሉክያኖስ መኰንንም ብዙ ገንዘብ ሰጥቼህ ከጭፍሮቹ ሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ ለአማልክት ለአጵሎንና ለአርዳሚስ ለመሠዋት ተዘጋጅ አለው። ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት ልብ የሌለህ ደንቆሮ ሆይ እምነቱን በሰው ላይ ላደረገ ሰው ወዮለት። ግን እምነቱ በእግዚአብሔር ላይ የሆነ የተመሰገነ ነው የሚል በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፏል እኔም ለረከሱ አማልክት አልሠዋም አለኝታዬ እግዚአብሔር ስለሆነ ለእርሱ ብቻ እሠዋለሁ።
ያን ጊዜም መኰንኑ ተቆጥቶ እንዲገርፉትና እሾህ ባላቸው በብረት ዘንጎችም እንዲደበድቡት ደሙ እንደ ውኃ እስቲፈስ ድረስ እንዲአሠቃዩት አዘዘ። ጌታችንም በመልአኩ እጅ አጽንቶ አዳነው ጤነኛም ሆነ። ሕዝቡም ይህን ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት አረፉ። ቁጥራቸውም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነው። መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸው ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ።
እነሆ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸለትና እንዲህ አለው። ብፁዕ ኄሮዳ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን አትፍራ እኔ ፈጣሪህ ክርስቶስ ነኝ እነሆ መቀመጫህን ከቅዱሳን ጋራ በሰማያት አዘጋጅቼልሃለሁ። በእውነት እነግርሃለሁ በመታሰቢያህ ቀን መከራ ድካምህን አስቦ መሥዋዕት ለሚያቀርብ ለድኃ ምጽዋትን ለሚሰጥ በእንስሶቹ ውስጥ ርባታ ይሆናል። በቤቱም የተባረከ ልጅ አይታጣም ሰይጣንም በእርሱ ላይ በሥራውም ሁሉ ላይ ሊበረታታበት አይችልም።
የገድልህን መጽሐፍና ስምህን የሚጽፈውንም እኔ በሕይወት መዝገብ ስሙን እጽፋለሁ የዕዳ ደብዳቤውን እደመስሳለሁ። ደግሞ በችግር በመከራ ውስጥ ስምህን ጠርቶ የሚለምነኝን ከመከራዉ ሁሉ እኔ አድነዋለሁ። መታሰቢያህንም ለሚያደርግ ሁሉ በደሉን ሁሉ እተውለታለሁ ሰላሜም ከአንተ ጋራ ይሁን ይህንንም ብሎ መድኃኒታችን ከእርሱ ዘንድ ዐረገ።
የከበረ አባ ኄሮዳም ፍጹም ደስታን ተደሰተ። ተጋድሎውንም በሚፈጽምበት ጊዜ በዚያ ወደ አሉት ሕዝብ ተመልሶ ከውስጣችሁ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ያለ ከሆነ ሥጋዬ በጎ በረከትን እስከሚያደርግለት ድረስ ሥጋዬን ወስዶ በእርሱ ዘንድ ያኑረው አላቸው።
ያን ጊዜም አንገቱን ዘረጋላቸው በሰይፍም ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም በግንቦት ወር በሃያ አምስት ቀን ተቀበለ። ከሦስት ወር በኋላም ዘመዶቹ መጡ ሥጋውንም ወሰዱ ተሸክመውም ወደ ሀገሩ ስብስጣ አድርሰው በአነፁለት ቦታ አኖሩት ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ ለድውያን ፈውስ ተገኘ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ቅብዓ ሜሮን
ዳግመኛ በዚህች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ የምንከብርበትን ቅብዐ ሜሮን አፍልቆልናል:: በስደቱ ጊዜ ጌታችን በምድረ ግብፅ ደክሟቸው ካረፉበት ቦታ ላይ የዮሴፍ በትርን ቆራርጦ: በኪነ ጥበቡ ውሃ አፍልቆ: አጠጥቶ: ትልልቅ ዛፎች አደረጋቸው:: እዛውም ላይ ቅብዐ ሜሮንን አፈለቀ:: ቅብዐ በለሶንም ይሏቸዋል::
በሁዋላም የጌታችን ወዙ በታጠበ ጊዜ ተቀላቅሎበታል:: ዛሬ እኛም: ንዋየ ቅድሳትም የምንከብረው በዚሁ ቅዱስ ቅብዐት ነው::
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት
No comments:
Post a Comment