ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 26 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 6, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 26

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት ወላዴ አእላፍ ቡነ ኢይሱስ ሞዓ ዘሐይቅ የተወለዱበት ነው፣ የተመሰገነና የከበረ ንጹሕም የሆነ የኢትዮጵያዊ ቡነ ሀብተ ማርያም ልደቱ ነው፣ የአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግም ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፣ ዲዲሞስ የሚባለው የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ በምስክርነት አረፈ፣ መልአከ ሞትን የማያሳይ ታላቅ ቃልኪዳን ያላቸው ጻድቁ አቡነ አሞጽ ዕረፍታቸው ነው፡፡


ቅዱስ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ዘሐይቅ
ግንቦት ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት ወላዴ አእላፍ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ዘሐይቅ የተወለዱበት ነው። በጐንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ዳህና ሚካኤል በተባለው ቦታ ከአባታቸው ከዘክርስቶስና ከእናታቸው ከእግዚእ ክብራ በዚህች ቀን በ1210 ዓ.ም ነው ተወለዱ። ዕድሜያቸው 3ዐ ዓመት እስከሚደርስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ124ዐ ዓ.ም ይኼንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ። በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን እያጠኑ፣ ትምህርተ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ ምንኩስናን ተቀበሉ (1247 ዓ.ም)።
አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ (ገድልህና ትሩፋትህ በዓለም ሕዝብ ሁሉ ትተህ የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራ ሂድ) አላቸው። አባታችን "ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ" በማለት ቢጠይቁት "ተነሥ። ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ" አላቸው። አባ ኢየሱስ ሞዓ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበአታቸው ተነሥተው ተከተሉት። የብዙ ወራት መንገድ የሆነው ጐዳናም በስድስት ሰዓት አለቀላቸው።
በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ። ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከመግባታቸውም በፊት ለ6 ወራት ያህል በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል። ያገለግሉበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር። በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበውም ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው እንደነበር ዛሬ በገዳማቸው የሚገኘው ገድለ ኢየሱስ ሞዓ ያስረዳል።
በመጨረሻም በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ። ሐይቅ እስጢፋኖስ ማለት ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሰረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብጻዊ ጻድቅ ናቸው፤ ገዳሙን ከሰሩ በኃላ የማንን ታቦት እናስገባ ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ ሁለት ታቦት አገኙ አንዱ የእስጢፋኖስ አንዱ የጊዮርጊስ " ይህንን ታቦት በእየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚያብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍም አገኙ ይላል። ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኃላ ነው አባ እየሱስ ሞኣ ወደዚህ ቦታ የመጡት ለ 52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ስራቸውን ይሰራሉ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ።
አባ ኢየሱስ ሞዓ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማስገልበጥ ብሎም በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል። በዚሁ ገዳም ውስጥም የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 8ዐዐ መነኮሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ በመላ ሀገሪቱ እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል።
ከተማሪዎቻቸውም መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ዘደብረ ሊባኖስ)፣ አባ ተክለሃይማኖት ያመነኮሱ አባት ናቸው። አባ ኂሩተ አምላክ (ዘጣና ሐይቅ)፣ አባ ጊዮርጊስ (ዘጋሥጫ)፣ አባ ዘኢየሱስ፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል፣ አባ አሮን (ዘደብረ ዳሬት) ጥቂቶች ናቸው። አፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት ያነፁት እርሳቸው ናቸው።
እንደዚህ ነው የመነኮሳት አባት እንጦንስ ነው እንጦንስ መቃርስን ወለደ መቃርስ ጳኩሚስን ጳኩሚስ አቡነ አረጋዊን አቡነ አረጋዊ አባ ዮሐኒን አባ ዮሐኒ የሐይቁን አባ እየሱስ ሞአን ወለዱ አባ ኢየሱስ ሞዓ ደግሞ ተክለሃይማኖትን ወለዱ።
በዮዲት ጉዲት ተጐድታ የነበረችው ሀገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት እንዲይነጥፉባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኮሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አባ ኢየሱስ ሞዓ ናቸው። በተለይም የሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈራቸው 8ዐዐ ሊቃውንት በመላዋ ሀገሪቱ በመሠማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኞቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውናል።
አባታችን አባ ኢየሱስ ሞዓ ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26/1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ በ82 ዓመታቸው ዐረፉ። በዚያች ዕለትም በቦታው የታየው ብርሃን ሀገሪቱን መልቷት እንደነበረ ገድላቸው ይመሠክራል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አቡነ ሀብተ ማርያም
በዚህችም ቀን የተመሰገነና የከበረ ንጹሕም የሆነ የኢትዮጵያዊ አባታችን የሀብተ ማርያም ልደቱ ነው። የዚህ ቅዱስ አባት የትውልድ አገሩ የራውዕይ በምትባል በስተ ምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ነው በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ሰው ነበረ ይህም ክቡራንና ታላላቅ ከሚባሉት ከዚች አገር ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው ። እጅግም ሀብታም ነበር ብዙ ንብረትም አለው በሕጋዊ ጋብቻም ስሟ ዮስቴና የምትባል ብላቴና ድንግልን አገባ ይቺም የተመረጠች በበጎ ሥራ የተሸለመችና ያጌጠች ናት ።
ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕግ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የዋህነትን ትሕትናን ፍቅርን ትዕግሥትን ገንዘብ አድርጋ በጾም በጸሎት ተወስና እንደኖረች እንነግራችኋለን ። በእንደዚህም ሳለች ጌታችን በወንጌል ሰው ዓለሙን ቢያተርፍ ነፍሱን ካጠፋ ምን ይጠቅመዋል እንዳለ ላንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሽ የሚል ሐሳብ መጣባት ።
ከዚህም በኋላ ወጣች ፈጥናም በሀገርዋ ትይዩ ወደሆነ ምድረ በዳ ደርሳ ወደ መካከሉ ገባች በዚያም በረሀ አራዊት እንጂ ሰው አይኖርበትም በዚያም ደጃፍዋ የተከፈተ ታናሽ ዋሻ አግኝታ ምንም ምን ሳትነጋገር ወደ ውስጧ ገብታ ቆመች የዳዊትንም መዝሙር የሚጸልይ ሰው አይታ ደነገጠች።
እርሱም ባያት ጊዜ ፍርሀትና መንቀጥቀጥ በላዩ ወረደበት በመስቀል ምልክትም በላይዋ አማትቦ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ እንዳልሸሸችም አይቶ ሰው መሆንዋን አወቀ በአወቀም ጊዜ እንዲህ ብሎ ገሠጻት ወደዚህ ምን አመጣሽ ለእኔ እንቅፋት ልትሆኚ ነውን አሁንም ከዚህ ፈጥነሽ ሒጂ አላት ።
እርሷም አባቴ ሆይ አንተ እንዳሰብከው አይደለሁም እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዩ ነኝ እንጂ በእርሱ ፍቅርና በእናቱ በእመቤቴ በቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር ያለኝን ሁሉ ትቼ ንቄ ከዓለም ወጥቼ ወደዚህ መጣሁ በዚህ ቦታም ከአራዊት በቀር ሰው እንዳለ አላወቅሁም አሁንም አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ ወደ ሌላ ቦታ እሔዳለሁ አለችው ።
በዚያንም ጊዜ ከርሷ የሚሆነውን መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት እንዲህ አላት ዜናው ወደ ዓለም ሁሉ የሚወጣ በሕይወተ ሥጋም እያለ የብዙዎች ሰዎች ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣ እንደ መላእክትም ክንፎች ተሰጥተውት ወደ አርያም ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትና የሦስትነትን ምሥጢር የሚያይ ልጅን ትወልጂ ዘንድ አለሽና ወደ ቤትሽ ተመለሽ አላት ።
ቅድስት ዮስቴናም ከዚያ ሽማግሌ ባሕታዊ ይህን በሰማች ጊዜ አድንቃ የፈጣሪዬ ፈቃዱ ከሆነ ብላ ወደቤቷ ተመለሰች። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ፀንሳ ይህን ደም ግባቱ መልኩ የሚያምር ልጅን ወለደች በእናትና በአባቱ ቤትም ታላቅ ደስታ ሁኖ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ለዘመዶቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው ታላቅ ምሳ አደረጉ እነርሱም በጠገቡ ጊዜ እነርሱንም ሕፃኑንም መረቋቸው ።
ሕፃኑም አርባ ቀን በሆነው ጊዜ እንደ ሕጉና እንደ ሥርዓቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱት ካህኑም ተቀብሎ በአጠመቀው ጊዜ ስሙን ሀብተ ማርያም ብሎ ሰይሞ ለክርስትና አባቱ ሰጠው ሕፃኑም ጥቂት በአደገ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ሲሉ ሰምቶ ሕፃኑ ሀብተ ማርያም በልቡ ይቺ ጸሎት መልካም ናት እኔም መርጫታለሁ በዚህ ዓለም ስሕተትን አስቦ ከመሥራት በሚመጣውም ዓለም ከገሀነም እንደምድንባት አውቃለሁና አለ ። ይህንንም ብሎ የሚሠራውን ማንም ሳያውቅበት ይህን ጸሎት ከማዘውተር ጋር ሌሊቱን ሁሉ በመስገድ ይፀልይ ነበር ።
ከዚህም በኋላ አባቱ የበጎች ጠባቂ አደረገው በአንዲት ዕለትም በጎቹን አየጠበቀ ሳለ ብዙ የበግ ጠባቂዎች እሸት ተሸክመው መጥተው ና እንብላ አሉት እርሱ ግን ከወዴት እንዳመጣችሁት የማላውቀውን አልበላም አላቸው እነርሱም በቁጣ ዐይን ተመልክተው ተጠቃቀሱበት ።
እሸቱንም በልተው ከጨረሱ በኋላ የከበረ ሕፃን ሀብተ ማርያምም ታላቅ ዝናም ስለመጣ ወደየቤታችን እንመለስ ከዚህ የምንጠለልበትና የምንጠጋበት ቤት ወይም ዋሻ የለምና አላቸው ። እነርሱም እኛ የማናየውን የሚያይ ሌላ ዐይን አለህን በሰማይ ፊት ምንም ደመና ሳይኖር ሀገሩም ብራ ሆኖ ሲታይ እንዴት ይዘንማል ትላለህ አሉት እርሱም እኔ የማውቀውን እናንተ አታውቁትም ግን ወደ ቤታችሁ ግቡ አላቸው እረኞችም ባልሰሙት ጊዜ ፈጥኖ ተነሥቶ በጎቹን እያስሮጠ ወደ ቤቱ ገባ ። ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ ታላቅ ዝናም መጣ ነፋሳትም ነፈሱ መብረቆችም ተብለጨለጩ ነጎድጓድም ተሰማ ደመናትም ተነዋወጹ ይህ ሁሉ በላያቸው ሲወርድ መሸሺያ አላገኙም ።
ከጥቂት ቀኖችም በኋላ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ ብዙ የበግ እረኞችም አብረውት ነበሩ አንድ የበግ ጠባቂም መጥቶ የወጣት ሀብተ ማርያምን በትር ነጠቀውና ሔደ ብላቴና ሀብተ ምርያምም በትሬን ለምን ትቀማኛለህ አለው እረኛውም በትዕቢት ቃል በጉልበቴ ነጥቄሃለሁ አለው ብላቴና ሀብተ ማርያምም እኔ ኃይል የለኝም ነገር ግን በጎቼን የምጠብቅበትን በትሬን እንዳትወስድብኝ በሕያው እግዚአብሔር ስም አምልሃለሁ አለው ያም የበግ ጠባቂ እምቢ አልኩህ አለው ።
ብላቴናው ሀብተ ማርያምም አንድ ጊዜ በፈጣሪዬ ስም አማልኩህ ከእንግዲህ ወዲያ ደግሜ አላምልህም በአንተ ላይ የሚደረገውን ራስህ ታውቀዋለህ ይህንንም ተናግሮ ዝም አለ፡፡ በዚያንም ጊዜ ያ የበግ ጠባቂ በአየር ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሀብተ ማርያም ማረኝ እያለ ይጮህ ጀመረ የልዑል እግዚአብሔርን ስም አቃልሏልና ተሰቅሎ ዋለ እረኞች ሁሉም አይተው አደነቁ ፈሩትም ይህን ሰነፍ ማርልን እግዚአብሔር ያደረገልህን ኃይል አይተናልና አሁንም ስለ እምቤታችን ድንግል ማርያም ይቅር በለው አሉት። ብላቴናው ሀብተ ማርያምም በውኑ እኔ የሰቀልኩት ነውን በእግዚአብሔር ስም አማልኩት እንጂ የኃይሉን ጽናት በላዩ ሊገልጥ እርሱ እግዚአብሔር ሰቀለው አሁን እርሱ ከፈቀደ ያውርደው እርሱ መሐሪና ይቅር ባይ ነውና ይህንንም በተናገረ ጊዜ ወርዶ በእግሩ ቆመ ወደርሱም መጥቶ ሰገደለት።
ከረጂም ዘመናትም በኋላ ስሟ እለአድባር ወደምትባል ገዳም ሒዶ ከዚያም የምንኩስናን ሥርዓትና ሕግ በአበምኔቱ በተመረጠ አባ መልከጸዴቅ እጅ ተቀበለ ከዚያም ቅዱሳን መነኰሳት ወደሚኖሩበት ሔዶ ታላቅ ተጋድሎ ጀመረ ።
እርሱም በባሕር መካከል በመቆም የዳዊትን መዝሙር ሁሉንም ያነባል በባሕር ውስጥም ሰጥሞ ግምባሩ አሸዋ እስቲነካው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳል ከሰንበት ቀኖችም በቀር እህል አይቀምስም ነበር ከዚህም በኋላ እህልን ትቶ እንደ ዋልያዎች የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ ።
አርባ አርባ ሰማንያ ሰማንያ ቀን የሚጾምበት ጊዜ አለ በባሕር ውስጥ በሌሊት ቁሞ በማደር በቀንም አራቱን ወንጌላት ያነባል ሌሎች መጻሕፍትንም በእንዲህ ያለ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ።
ብዙ ተጋድሎንና ድካምንም በአስረዘመ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ ተገልጦ መጣ ከእርሱ ጋርም የመላእክት አለቆች የከበሩ ሚካኤልና ገብርኤል የመላእክት ማኅበርም ሁሉ በዙሪያው ሁነው እያመሰገኑት ነበር ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ላንተ ይሁን አለው ። በዚያንም ጊዜ ከግርማው የተነሣ ወድቆ እንደ በድን ሆነ ጌታችንም በከበሩ እጆቹ አንሥቶ እፍ አለበትና ጽና ኃይልህን ላድሳት እንጂ ላጠፋህ አልመጣሁምና ተጋድሎህና ድካምህ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት እንደ ተጻፈ በእውነት እነግርሃለሁ ።
እነሆ እኔ በጎ ዋጋህን በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም እከፍልሃለሁ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል በምታነብ ጊዜ በተራራዎችና በዋሻዎች በፍርኩታ ተሠውረው ወደሚኖሩ እንዳንተ ካሉ ቅዱሳን ጋር ለመገናኘት በላዩ ተቀምጠህ ወደ ምሥራቅ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንና ደቡብ የምትበርበት የብርሃን ሠረገላ ሰጠሁህ ሉቃስና ዮሐንስ የጻፉትን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ሥጋዬንና ደሜን በዚያ ትቀበል ዘንድ በላዩ ተቀምጠህ ወደ ኢየሩሳሌም የምትሔድበት የእሳት ሠረገላ ሰጠሁህ አለው ።
ከብዙ ዘመናትና ከብዙ ተጋድሎ በኋላ የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ለሞቱ ምክንያት የሚሆን ቸነፈር ያዘው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጥቶ ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ላንተ ይሁን ዛሬ ግን የመጣሁት ከድካም ወደ እረፍት ልወስድህ ነው እነሆ ሰባት አክሊላትን አዘጋጅቼልሃለሁና አንዱ ስለ ድንግልናህ ሁለተኛው ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉን ትተህ በመውጣትህ ሦስተኛው ፍጹም ስለሆነው ምንኩስናህ አራተኛው አራቱን ወንጌሎች አዘውትረህ የምታነብ በመሆንህ አምስተኛው ስለ እኔ ፍቅር መራብና መጠማትን ስለታገሥክ ስድስተኛው በልብህ ቂምና በቀልን ባለማሳደርህ ሰባተኛውም ስለ ንጹሕ ክህነትህና ስለምታሳርገው ያማረ የተወደደ ዕጣንህና መሥዋዕትህ ሰጠሁህ እሊህ ሰባቱ አክሊላትም ለየአንዳንዳቸው ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ኅብር አላቸው ።
መታሰቢያህን ካደረጉና በጸሎትህ ከተማፀኑ ጋር የምትገባበትን ቤት በውስጧ አምስት መቶ የወርቅ አምዶች የተተከሉባትን ሰጠሁህ ደግሞ የእሳት መስቀልን የወርቅ ጫማን የብርሀን ልብስን ሥውር የሆነ መና እሰጥሃለሁ አለው ።
መድኃኒታችንም ይህን ቃል ኪዳን ሲሰጠው በየነገዳቸውና በየሥርዓታቸው ዘጠና ዘጠኝ የመላእክት ሠራዊት መጥተው ወዳጃችን ሰላም ላንተ ይሁን ዛሬስ ከፀሐይ ሰባት እጅ ወደምታበራ ሀገራችን በዝማሬና በማኅሌት አክብረን ልንወስድህ መጣን አሉት ። አባታችን አባ ሀብተ ማርያምም በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ሆነ የሰው ነጻነቱ ሊሰጠው አለ ።
ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየውና የመጥምቁ ዮሐንስን ሀገር ተጠጋግታ ያለች ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ ሀገርን እሰጥህ ዘንድ በራሴ ማልኩልህ አለው ።
መታሰቢያህን የሚያደርገውን በስምህ ለቤተ ክርስቲያን መባ የሚሰጠውን ስምህንም የጠራውን ወደዚች አገር አገባዋለሁ አራቱን ወንጌሎችም እያነበብክ ስለኖርክ የየአንዲቱን ቃል ፍሬዋን አንዳንድ ሽህ አደረግሁልህ ይኸውም ካንተ በኋላ ለሚመጡ ልጆችህ መጽሐፈ ገድልህን ለሚያነቡና በእምነት ለሚሰሙ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበበት ውኃ ለሚረጩ ለሚነከሩበት ይህን ቃል ኪዳን ሰጥቼሃለሁ ።
ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አፉን ሦስት ጊዜ ሳመው በዚያንም ጊዜ ከፍቅሩ ጣዕም ብዛት የተነሣ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ጌታችንም ተቀብሎ አቅፎ ከእርሱ ጋር አሳረጋት። በመላእክት ጉባኤም ብዙ ምስጋና ተደረገ ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ
ዳግመኛም በዚህች ቀን የአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግም ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ። ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል እንድርያስና አርሶንያ ከሚባሉ የበቁ ደጋግ አባትና እናታቸው የተወለዱት በሸዋ ሀገረ ስብከት ቀድሞ ጽላልሽ ዛሬ ቡልጋ በሚባለው አውራጃ ነው፡፡ የወላጆቻቸው በጎ ምግባርና ሃይማኖት ቅዱስ ተክለሃይማኖትን ከደብረ ሊባኖስ አነሣስቶ በቤታቸው ሄደው እንዲስተናገዱ አድርጓል፡፡ ልጅ ስላልነበራቸው ያዝኑ ነበርና አቡነ ተክለሃይማኖትም በጸጋ እግዚአብሔር ተገልጾላቸው ‹‹እግዚአብሔር ጣዖታትን የሚሰብር፣ አጋንንትን በጸሎቱ የሚያርቅ፣ ሕዝብን ከኃጢአት በሽታ የሚያድን፣ ፈጣሪውን የሚያስደስት ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ብለው ትንቢት ነግረዋቸዋል፡፡ በትንቢቱም መሠረት አቡነ ሳሙኤል ሐምሌ 10 ቀን 1248 ዓ.ም ሲወለዱ መልካቸው በአራት ልዩ ልዩ ሕብረ መልክ እየተለዋወጠ አንድ ጊዜ እንደ በረዶ፣ አንድ ጊዜ እንደ እሳት፣ አንድ ጊዜ እንደ ልምላሜና ቢጫ ሆነው ታይተዋል፡፡
አቡነ ተክለሃይማኖትም በአባቱ እንድሪያስ በኩል የሥጋ ዘመዱ ሲሆኑ የመንፈስ ቅዱስም አባት ሆኑትና በ40 ቀን ክርስትና አንስተው ስመ ክርስትናውን ‹‹ሳሙኤል›› አሉት፡፡ ትርጓሜውም ‹‹እግዚአብሔር ጸለቴን ሰማኝ›› ማለት ነው፡፡ ከሕፃንነትም ጀምረው በምግባር በሃይማኖት ኮትኩተው አሳድገው ለዲቁና አብቅተው በኋላም አመንኩሰውታል፡፡
‹‹ደብረ ወገግ›› የሚለው ስያሜ የተገኘው ከመላእክት ነው፡፡ ድርሳነ ዑራኤል በሰፊው እንደሚያትተው ቅዱስ ዑራኤል የጌታችንን ደም በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ ዓለምን እየረጨ ሲቀድሳት የያዘውን ጽዋ በደብረ አስቦ ቆሞ ሳለ ነው ጨልጦ ያንጠፈጠፈው፡፡ ያንጊዜም ደብረ አስቦን የብርሃን ውጋጋን ሲያጥለቀልቀው መላእክትም ‹‹ቦታውን ደብረ ወገግ›› (የብርሃን ተራራ) ብለው ሰይመውታል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ‹‹ወደፊት ፈጣሪውን የሚያገለግል ታላቅ ጻድቅ ይወጣባታልና ይህችን ቦታ ባርካት›› ብሎ ቅዱስ ዑራኤልን በነገረው መሠረት ባርኳት እንዳረገ ድርሳነ ዑራኤል ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡ በቦታው ላይ ብዙ ጊዜ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ መታየቱን የበቁ ገዳማውያን ብቻ ሳይሆኑ በከተማ ያሉና ለመሳለም ወደ ቦታው የሄዱ ደገኛ ሰዎችም በዐይናቸው ያዩትን ይናገራሉ፡፡ በገዳሙ ዙሪያ እጅግ በጣም ብዙ ስውራን ቅዱሳን እንዳሉ በግልጽ ይታወቃል፡፡ በቦታው ላይ ስለተሰወሩት ቅዱሳን በኋላ በዝርዝር እናያለን፡፡
ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር የአባቱን ሚስት እንጀራ እናቱን በማግባቱ ምክንያት አቡነ ፊሊጶስ ጋር ሆነው ያወገዙትን የቅዱስ ተክለሃይማኖትን ወገኖች በየአውራጃው በተናቸው፡፡ አቡነ ፊሊጶስንም ደሙ በምድር ላይ እስከሚንጣለል ድረስ ገርፈው ወደነበረበት ቤቱ ወሰዱት፤ ፊሊጶስም በሚሄድበት ቦታ ላይ ሳይደርስ በመንገድ ሞተ፡፡ እንድርያስ፣ አኖሬዎስና ተክለ ጽዮን ሁላቸው ከተከታዮቻቸው ጋር በሰማዕትነት አርፈው እነስድስተይ በምትባል ምድር ተቀበሩ፡፡ ጳጳሱን አቡነ ያዕቆብንም ደሙ በምድር ላይ እንደውኃ እስኪወርድ ድረስ ገርፈው ወደ ሀገሩ እንዲሰደደ አደረጉት፡፡
ከዚያም በኋላ ሃይማኖቱ የቀና ደግ ጻድቅ ንጉሥ ዳዊት በነገሠ ጊዜ አባታችን ሳሙኤል ዘወገግን አገኘውና ‹‹መማጸኛ እንዲሆነኝ በእንድርያስ መቃብር ላይ ቤተክርስቲያን ሥራልኝ›› ብሎ ለመነውና የሩፋኤልን ቤተ ክርስቲያን ሠራለት፡፡ የእንድርያስንም አጽም ከመቅደሱ ስር አኖረው፡፡ ንጉሡም በዚያ በእንደግብጦን አውራጃ ሁሉ ላይ ፓትርያርክ አድርጎ ሾመው፡፡ በእነስድስታይ አገር ላሉ ሰዎችም ሁሉ አባት ሆናቸውና የመንፈስ ቅዱስ ልጁንም ታዲዮስን መምህርና
አባት አድርጎ ሾመላቸውና ጽላልሽ ሄዶ እናቱን ይዞ ጽጋጋ ምድረ ወገግ ወስዶ አመነኮሳት፡፡ አቡነ ሳሙኤል ወደ ምድረ ርስቱ ደብረ ወገግ እየሄደ በዚያ ያሉ ልጆቹን እያጽናና ወደ እንደግብጦን አውራጃም እየተመለሰ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ፣ ወንጌልን እያስተማረ፣ ጣዖት አምላኪዎችን ወደ ክርስትና እየቀየረ፣ አጋንንትንና መመለኪያ ቦታዎቻቸውን እያጠፋ፣ አብያተ ክርስቲያናትን እያነጸ በብዙ ተጋድሎ ኖረ፡፡ በቅዱስ ገድሉ ውስጥ በጣም አስገራሚ በሆነ መልኩ እጅግ ብዙ ታሪኮች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም ታሪኮች ውስጥ አቡነ ሳሙኤል በሀገራችን በጣም ብዙ ጣዖታትንና መመለኪያ ቤቶቻቸውን እያጠፉ፣ በሰዎች (በጠንቋዮች) ላይ፣ በዛፍና በባሕር ውስጥ አድሮ ይመለኩ የነበሩ ሰይጣናት አጋንንትን በሚያመልኳቸው ሰዎች ፊት እያጋለጡና እያዋረዱ ሰዎቹን አስተምረው አጥምቀው ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እየመለሷቸው ቤተክርስቲያንም በመሥራት ሐዋርያትን መሰሉ፡፡ ሰይጣን አድሮባቸው የነበሩ ጠንቋዮች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ዕቃዎችን ጻድቁ እየባረኩና እየቀደሱ ለቤተክርስቲያን መሥሪያና መጠቀሚያነት ያውሉት ነበር፡፡ ይህም ገና ሳይወለዱ በአቡነ ተክለሃይማኖት ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ጣዖታትን የሚሰብር፣ አጋንንትን በጸሎቱ የሚያርቅ፣ ሕዝብን ከኃጢአት በሽታ የሚያድን፣ ፈጣሪውን የሚያስደስት ደግ ልጅ ይሆናል›› ብሎው ትንቢት እንደተናገሩላቸው አቡነ ሳሙኤል በሰዎች፣ በባሕርና በዛፍ ላይ እያደሩ ይመለኩ የነበሩ በጣም ብዙ አጋንንትን አጠፏቸው፡፡ ጠንቋዮችንም በውስጣቸው ካደረባቸው ሰይጣን እያላቀቁ የእግዚአብሔር አገልጋይ ያደርጓቸውና ያመነኩሷቸው ነበር፡፡
ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል ወንጌልን ዞረው በማስተማር ሐዋርያትን መሰሉ፣ ከዓላውያን ጋር ለመዋጋት ሰውነታቸውን ለሞት በመስጠት ሰማዕታትን መሰሉ፣ በጾም በጸሎት በስግደት በተጋድሎ ቅዱሳን ጻድቃንን መሰሉ፣ ይህን ኃላፊና ጠፊ ዓለም ንቀው በመተው ባሕታውያንን መሰሉ፣ በደልንና ኃጢአትን በማስተሠረይ ካህናትን መሰሉ፣ በጽሕናና በቅድስና መላእክትን መሰሉ እንደዚሁም ሌሎች ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ በትእምርተ መስቀል አድርገው እንደሙሴ ባሕርን ለሁለት ከፍለዋል፣ እንደ ኢያሱ በጸሎታቸው ፀሐይን አቁመዋል፡፡ አቡነ ሳሙኤል ተጋድሎአቸውን ፈጽመው ከጌታችን ታላቅ ቃኪዳን ተቀብለው ጥቅምት 29 ቀን በሰላም ዐርፈዋል፡፡
በገዳማቸው በአሰቦት ደብረ ወገግ የተሰወሩ እጅግ በጣም ብዙ ቅዱሳን ስለመኖራቸው በገድለ አቡነ ሳሙኤል መቅድም ውስጥ በሰፊው ተጠቅሷል፡፡ በቦታው ላይ ከ1934 ጀምሮ እስከ 1972 ዓ.ም ድረስ የተሠወሩት ቅዱሳን በዝርዝር የታወቁም አሉ፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት እነዚያ በቦታው ላይ የተሰወሩት ቅዱሳን ለገዳማውያንኑም ሆነ በዓለም ለሚኖሩ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረው ለያዙ ሰዎች እየተገለጡላቸው ይታዩዋቸዋል፣ መልእክትም ይነግሯቸዋል፡፡ እንዲሁም ስውራኑ ባሉበት ቦታ የከበሮ ድምጽ ይሰማል፣ ዕጣን ይሸታል፣ ቀንና ሌሊት አራዊት ሲሰግዱበትና ሲጠብቁት ይታያል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
በዚህች ቀን ዲዲሞስ የሚባለው የከበረ ሐዋርያ ቶማስ በምስክርነት አረፈ።
እርሱም በሕንደኬ አገር ሉክዮስ ለሚባል ለአንድ መኰንን ራሱን ባሪያ አደረገ መኰንኑም የንጉሥ ወዳጅ ነው ቅዱስ ቶማስንም የምታውቀው ሙያህ ምንድነው አለው። ቅዱስ ቶማስም እኔ ግምበኛ ነኝ ምኲራቦችንና አዳራሾችን እሠራለሁ ደግሞ ጠራቢ ነኝ ሞፈሮችን ወንበሮችንም ሌሎች ዕቃዎችንም እሠራለሁ። ደግሞ ጥበበኛ ባለ መድኃኒት ነኝ በሽታውን ሁሉ አድናለሁ አለ። መኰንኑም ነገሩን በሰማ ጊዜ ነገሩ እጅግ ደስ አሰኘው ለንጉሥ ጠቃሚ የሆነ ባሪያ አገኘሁ አለ።
በዚያን ጊዜ ለቶማስ ገንዘብ ሰጥቶ ቤተ መንግሥትም እንዲሠራ አዝዞ መኰንኑ ወደ ንጉሡ ሔደ። እርሱ ቶማስም የመኰንኑን ሚስት የእግዚአብሔርን ሕግ ያስተምራት ጀመር በፊቷም ተአምራት አደረገ። እርሷም በክብር ባለቤት ጌታችን አመነች ከርሷ ጋራም ብዙዎች አመኑ ንጽሕናዋን በመጠበቅ እንድትጸና አዘዛት የሃይማኖትንም ምሥጢር እንድታስተውል አደረጋት።
መኰንኑም ከንጉሥ ዘንድ ሲመለስ ሐዋርያ ቶማስ ያደረገውን አየ። ጠራውና አንተ ክፉ ባርያ እሠራቸዋለሁ ያልካቸው በጎ ሥራዎች ወዴት ናቸው አለው። ቅዱስ ቶማስም አልዋሸሁም ምኲራቦችና አዳራሾች የሠራኋቸው ለሰማያዊ ንጉሥ ማደሪያ የሆኑ እሊህ የሰዎች ነፍሳት ናቸው። የጠረብኳቸው ሞፈሮችም የኃጢአትን እሾህና አሜከላ ከሰዎች ልብ የሚነቅሉና አርሰው የሚያለሰልሱ እነርሱ የወንጌል ትምህርቶች ናቸው ጥበብ ያልሁትም አንድ ነው የሚገድል የኃጢአትን መርዝ አጥፍቶ የሚፈውስ የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ነው ብሎ መለሰለት።
መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ ቅዱስ ቶማስንም በምድር ላይ እንዲአስተኙት በአራት ማዕዘንም ችካል ተክለው እጆቹንና እግሮቹን በገመድ ወጥረው አሥረው ቆዳውን እንዲገፉ ጨውና ኮምጣጤ በተገፈፈው ሥጋው ላይ እንዲደፉበት አዘዘ። መኰንኑም እንዳዘዘ ይህን ሁሉ አደረጉበት እርሱም ከእግዚአብሔር በተሰጠው ትዕግስት ይህን ሥቃይ ተቀበለ።
የመኰንኑም ሚስት ቆዳውን ሲገፉት በቤቷ ሰገነት መስኮት በአየችው ጊዜ በድንጋጤ ወድቃ ሞተች መኰንኑም እጅግ አዘነ። የክብር ባለቤት ጌታችንም ቶማስን አጸናው ወዲያውኑ ተነሣ ከላዩ የገፈፉትንም ቆዳ ወስዶ ከመኰንኑ ሚስት በድን ላይ ጥሎ አርሶንያ ሆይ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሺ አለ።
ወዲያውኑ ዐይኗን ገለጠች ፈጥና ተነሥታም ለሐዋርያ ቶማስ ሰገደችለት ሉክዮስም አይቶ ደነገጠ። ለሐዋርያውም ሰገደለት ይቅርታም ያደርግለት ዘንድ በመለማመጥ ለመነው። ቅዱስ ቶማስም በጌታችን ካመንክ ትድናለህ አለው እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። እንዲሁም የሀገር ሰዎች ሁሉም አመኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው። ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው። እያስተማራቸውና በቀናች ሃይማኖትም እያጸናቸው ከእሳቸው ዘንድ ኖረ። ደዌ ያለበትንም በላዩ ቆዳውን ሲያኖርበት ወዲያው ይድናል።
ከዚህ በኋላም ከእነርሱ ዘንድ ወጥቶ ቀንጦርያ ከሚባል አገር ገባ ሲገባም አንድ ሽማግሌ ሰው መራራ ልቅሶ እያለቀሰ አገኘ። ቅዱስ ቶማስም እንዲህ ለምን ታለቅሳለህ አለው ሽማግሌውም ሰባት ልጆች ነበሩኝ በሐሰት ነገር ንጉሥ ገደለብኝ። ደግሞም ዕዳ አለብኝ ከእነርሱ አንዱ እንኳ ቀርቶ ቢሆን ለኑሮዬ በተራዳኝ ነበር ብሎ መለሰለት።
ቅዱስ ቶማስም ሰምቶ ቆዳውን ሰጠውና ይህን ወስደህ በልጆችህ መቃብር ላይ አኑር አለው። እንዳዘዘውም በአደረገ ጊዜ ሰባቱ ሁሉ ልጆቹ ሌሎቹም ስምንት ወንዶች በዚያ አስቀድሞ ተቀብረው የነበሩ በአንድነት ተነሡ።
ይቺም ተአምር በሀገሮች ሁሉ ተሰማች የጣዖታት ካህናትም ተቆጥተው በደንጊያ ሊወግሩት ጀመሩ። ያን ጊዜ እጆቻቸው ደረቁ የቸር አምላክ ሐዋርያ ሆይ ከፈጣሪህ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ አመን። ማረን ይቅርም በለን እያሉ ጮኹ ያን ጊዜም አዳናቸው የቀናች ሃይማኖትንም አስተምሮአቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው። ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም ሾመላቸው።
ከዚህ በኋላም ወደ አቴና ወደ መቄዶንያ ሔዶ በውስጥዋ በክብር ባለቤት ጌታችን ስም ሰበከ ስለእርሱም ነገሥታቱና መኳንንቱ ሰሙ። ይዘውም አሠሩት የንጉሡም ሚስት ከልጅዋ ጋራ ወደ ወህኒ ቤት እየመጣች የቅዱስ ቶማስን ትምህርቱን ትሰማ ነበር። ብዙዎችም በሥውር እየመጡ ያስተምራቸው ነበር በክብር ባለቤት ጌታችንም አመኑ።
ንጉሡም ሰለ ሚስቱ ተቆጣ ነገር ግን በሕዝብ መካከል መግደልን ፈራ። ከከተማውም ውጭ ቅዱስ ሐዋርያ ቶማስን አውጥቶ እስከሚሞትም በጦር እንዲወጉት አራት ወታደሮችን አዘዘ። የንጉሥ ልጅም ቁሞ ይመለከት ነበር። የአገር ሰዎችም በአወቁ ጊዜ ከወታደሮች እጅ ሊያስጥሉት ወጡ ግን ሙቶ አገኙት አንሥተው ገንዘው ከነገሥታት መቃብር በአንዱ አኖሩት።
በንጉሡ ልጅም ሰይጣን ተጭኖበት የሚያንከባልለው ሆነ ከልብሱም ጥቂት ወስደው በንጉሡ ልጅ አንገት ላይ ሊአንጠለጥሉለት ወደ ቅዱስ ቶማስ ሥጋ መጡ መቃብሩንም በከፈቱ ጊዜ አላገኙትም። ጌታችን ከዚያ አፍልሶታልና ከመቃብሩ አፈርም በእምነት ወስደው በንጉሡ ልጅ አንገት ላይ አንጠለጠሉ ያን ጊዜ ዳነ። ንጉሡም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ።
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሐዋርያ ቶማስም ለብዙዎች ተገለጸላቸው እርሱ ሕያው እንደ ሆነ ጌታችንም በመንግሥቱ ውስጥ እንደተቀበለው ነገራቸው። የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አዘዛቸው። የሐዋርያ ቶማስም በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ተአምር ዘቅዱስ ቶማስ
ዳግመኛም ከተአምራቶቹ አንዱን እንጽፋለን። አንድ ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርን የሚፈራ በግብጽ አገር ነበረ ይነግድም ዘንድ ወደ ሕንደኬ ሔደ። ግንቦት ሃያ ስድስትም ሲሆን በሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ በዓል ብዙ ሕዝቦችን የቅዱስ ቶማስ እጅ በውስጡ በምትኖርበት ባሕር ዳር ተሰብስበው አያቸው።
በዚያን ጊዜም የባሕሩን ውኃ ጨርሶ እስከሚአስወግደው ድረስ ጥቅል ነፋስ ተነሣ ሰዎችም ሁሉ በደሴት ወደአለች ቤተ ክርስቲያን ገብተው ሲጸልዩ አደሩ።
በማግሥቱም በቅዱስ ቶማስ በዓል ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል ቀደሱ። የሐዋርያ ቶማስ እጅ ያለ ጥፋት ሕይወት ያላት ስለሆነች የጌታችንን ሥጋ በላይዋ አደረጉ።
በቅዱስ ሐዋርያ ቶመስ እጅም ቅዱስ ቁርባንን ሊቀበሉ አንዱም አንዱ ከሕዝቡ መጡ። አንድ ሕዝባዊ ሰውም ሊቀበል መጥቶ የቅዱስ ቶማስ መሐል እጁን ጨበጠ። ያን ጊዜ ተሠወረች ሁሉም ኪርያላይሶን እያሉ በመጮህ ብዙ ጊዜ ረጅም ጸሎት ጸለዩ። ከዚህ በኋላም የቅዱስ ቶማስ መሐል እጁ ተገለጠችና ያ ሰው ቅዱስ ቁርባንን ተቀበለ። ሕዝቡም ሁሉ ተቀበሉ ከዚህም በኋላ ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው ወደ ቤታቸው በሰላም ገቡ።
ክብር ይግባውና እግዚአብሔርም ባሕሩን በዚያ ዐውሎ ነፋስ እንደ ቀድሞው መለሰው በየዓመቱም እንዲህ ይሆናል ሁልጊዜ እስከ ዛሬ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ጻድቁ አቡነ አሞጽ
ዳግመኛም በዚህች ቀን መልአከ ሞትን የማያሳይ ታላቅ ቃልኪዳን ያላቸው ጻድቁ አቡነ አሞጽ ዕረፍታቸው ነው፡፡ እርሳቸውም ታላቁን ቀብጽያ ገዳምን የመሠረቱት ናቸው።
አቡነ አሞፅ ትውልዳቸው ሸዋ ሲሆን የመነኮሱት ደብረ ሊባኖስ በአቡነ ዮሐንስ ከማ እጅ ነው፡፡ አቡነ ዮሐንስ ከማ በመልአክ ታዘው 10 መነኮሳት 500 ሕዝብ ተከትሏቸው ወደ ትግራይ ሲሄዱ ሳምረ ወረዳ ላይ ሲደርሱ ሕዝቡ ቢራብ ዋርካ ዕለቱን አብቅለው ባርከው መግበውታል፣ ውኃም አፍልቀው አጠጥተውታል፡፡ ከዚኽም በኋላ የበቁትንና ቅዱሳን የሆኑትን ዓሥሩን መነኮሳት ገዳም እንዲገድሙ ወደተለያዩ ቦታዎች ላኳቸው፡፡ ከእነዚኽም ዓሥር ቅዱሳን መነኮሳት መካከል አቡነ አሞፅ አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ጽላተ ማርያምን ይዘው በቅዱሳን መላእክት ታጥራ ወደምትገኘው ምድረ ቀብጽያ መጥተው መቶ ዓመት በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ፡፡
አቡነ አሞፅ ሰቆቃወ ድንግል የሚባለውን የእመቤታችን መከራ የሚተርከውን ድንቅ ድርሰት ሙሉውን ክፍል በብራና ላይ በሥዕል ገልጸው በክብር አስቀምጠውታል፡፡ ከሰማይ የወረደላቸው የወርቅ መስቀላቸውም በገዳሙ ይገኛል፡፡ አቡነ አሞፅ ግንቦት 26 ቀን ሲያርፉ ጌታችን ከድንግል እናቱ ጋር ተገልጾላቸው ከላይ ያየናቸውን አስደናቂ ቃልኪዳኖች ከሰጣቸው በኋላ ነፍሳቸውን እመቤታችን አቅፋ አሳረገቻቸው፡፡ ዐፅማቸው ያረፈበትን መካነ መቃብር ታላላቅ ዘንዶዎች ይጠብቁታል፡፡ ጠበላቸውም የፈለቀው ከመቃብራቸው ሥር ነው፡፡ ቦታው በስውራን ስለሚገለገል የከበሮ ድምፅ የሚሰማ ሲሆን የእጣንም ሽታ ይሸታል፡፡
በዘንዶዎች የሚጠበቀው ይህ አስደናቂ ገዳም በብዙ መልኩ ከሌሎች ገዳማት የተለየ ነው፡፡ የገዳሙን አፈር ቅዱሳን መላእክት ናቸው ከገነት ያመጡት፡፡ ጌታችን 12 እልፍ መላእክቱ ልኮ ከገነት አፈር አምጥተው በዝናብ አምሳል በቀብጽያ ገዳም ላይ እንዲነሰንሱት አዟቸዋል፡፡
ገዳሙን የተሳለመ ሰው ኢየሩሳሌም ጎልጎታን እንደተሳለመ የሚቆጠርለት ሲሆን በገዳሙ ውስጥ የተቀበረ ሰው ወቀሳ የለበትም፡፡ ከአካሉም ላይ ፀጉሩን ወይም ጥፍሩን ቆርጦ በገዳሙ ክልል ውስጥ የቀበረ ሰው ቢኖር መልአከ ሞትን ፈጽሞ እንደማያይና ገዳሙ የሚገኝበት አካባቢ በእግር ለመጓዝ አስቸጋሪ ቢሆንም ቦታውን የረገጠ እስከ 15 ትውልድ ምህረትን እንደሚያገኝ ጌታችን በቃልኪዳን አጽንቶታል፡፡ ሌላው ቀብጽያ ገዳምን ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ፈዋሹ ጠበል ከጻድቁ አቡነ አሞፅ መቃነ መቃብር ሥር የሚፈልቅ መሆኑ ነው፡፡ ከዋሻው ሥር የተንጠባጠበው ጠበል ወደ ጠንካራ ዓለትነት የሚቀየር ሲሆን እርሱን ለእምነት የተጠቀሙበት ሰዎች ከተለያዩ በሽታዎች ተፈውሰዋል፡፡ በቅርቡም ከ6 ዓመት በፊት በዚህ እምነት የተሻሸች አንዲት ሴት ከዘመኑና መድኃኒት ካልተገኘለት ከHIV በሽታና ከመካንነቷ ተፈውሳ ልጅ ወልዳለች፡፡ ይህ አስደናቂ ቀብጽያ ገዳም ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ ቢሆንም ከጊዜና ብዛት ጉዳት ስለደረሰበትና የሚያድሰው አካል ስላላገኘ በአሁኑ ወቅት ሌላ አዲስ ቤተ መቅደስ እየታነጸ ይገኛል፡፡ በቀብጽያ ገዳም ውስጥ 336 ዓመት የሆነው የወይራ ዛፍ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡ ስውራን የሆኑ ቅዱሳን ሦስት ጊዜ ደወል ሲደውሉበት ተሰምቷል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages