ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 5 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 13, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 5

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሰኔ አምስት በዚች ቀን ታማኝና ተጋዳይ የሆነ ምሥራቃዊው አባት ቅዱስ ያዕቆብ አረፈ፣ የተመረጠ ኃያል ተጋዳይ አባ ብሶይ አረፈ፣ ቅዱስ ቢፋሞይ ምስክር ሆነ፣ ሃይማኖቷ የጸና ምግባርዋም የቀና መነኰሳዪት ድስት ማርታ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው።


ቅዱስ ያዕቆብ ምሥራቃዊ
ሰኔ አምስት በዚህች ቀን ታማኝና ተጋዳይ ይሆነ ምሥራቃዊው አባት ያዕቆብ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከምእመን ዋልንጦስ ዘመን በኋላ የታላቁ ቈስጠንጢኖስ ልጅ በሆነ በታናሹ ቈስጠንጢኖስ ዘመንና በከሀዲው ሉልያኖስ ዘመን በምሥራቅ ካሉ ገዳማት በአንዱ ገዳም በገድል ተጠምዶ ኖረ።
ዋልንጦስ ከተገደለ በኋላም በእርሱ ፈንታ ወንድሙ ነገሠ እርሱም አርዮሳዊ ነበር የጣዖት ቤቶቻቸውን እንዲከፍቱ ሃይማኖታቸው የቀናውን የምእመናንን አብያተ ክርስቲያናትንም እንዲዘጉ አርዮሳውያንን አዘዛቸው ወደ ከፋችና ወደ ተበላሸች ሃይማኖታቸው ምእመናን በግዳጅ እስቲገቡ ድረስ እንዲሁ አደረጉ።
ይህም የንጉሡ ትእዛዝ በሚገዛው አገር ሁሉ ደረሰ። ይህ አባ ያዕቆብም ይህን በሰማ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር እሳትነት ልቡ ነደደ ያንጊዜም ተነሥቶ ወደ ቊስጥንጥንያ ሔደ በምዕራብ በኩል የተነሡበትን ጠላቶቹን ሒዶ ለመውጋት ሲወጣ ንጉሡን አገኘው።
ይህ አባት ያዕቆብም በፊቱ ቆሞ ንጉሥ ሆይ በጠላቶችህ ላይ እግዚአብሔር ይረዳህ ዘንድ ምእመናን እንዲጸልዩልህ አብያተ ክርስቲያናቸውን ክፈትላቸው ብዬ እለምንሃለሁ ይህን ካላደረግህ ግን እግዚአብሔር ይጥልሃል ከጠላቶችህም ሸሽተህ በእሳት ቃጠሎ ትሞታለህ አለው።
ንጉሡም ይዞ ለሚጠብቀው ወታደር በሰላምና በደኅንነት እስከምመለስ ጠብቀው ብሎ ሰጠው። ቅዱስ ያዕቆብም አንተ በደኅና ከተመለስክ በእኔ አንደበት እግዚአብሔር አልተናገረም ማለት ነዋ አለው።
ያንጊዜም ቅዱሱን ይዘው ደብድበው አሠሩት ንጉሡም ከሠራዊቱ ጋራ ወደ ጦርነቱ ሔደ በረከሰች ጸሎታቸው አርዮሳውያን ምንም ቢራዱት ክብር ይግባውና ጌታችን በጠላቶቹ አንጻር ጣለው እነርሱም ጠላቶቹ እየተከተሉት ሸሽቶ ከአንዲት አአድ ውስጥ ገባ በዚያም በረከሰች ሃይማኖት ከሚያምኑ ወገኖቹ ጋራ በእሳት አቃጠሉት።
የቀሩትም ሠራዊት ሁሉ ሽሽተው ወደ ቊስጥንጥንያ ተመለሱ ይህንንም መልካም ዜና ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን ተናገሩ የዚህ ጻድቅ አባት ያዕቆብም ትንቢቱ ተፈጸመ ከእሥር ቤትም በክብር አስወጡት። ምእመናንም ከሀዲያንም በላዩ መንፈስ ቅዱስ እንዳደረበት ተረዱ ከአርዮሳውያንም ብዙዎቹ የአባቶቻችን ሐዋርያት ወደሆነች ቅን ሃይማኖት ተመለሱ በዚህ አባት እግር በታች ሰግደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በመለኮቱ ትክክል እንደሆነ ታመኑ።
ከዚህም በኋላ ይህ አባት ወደ ቦታው ተመለሰ አርፎ የሕይወትና የሰማዕትነት አክሊልን እስከ ተቀበለ ድረስ እንደ ቀድሞው በገድል ተጠምዶ ኖረ።
✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟
ቅዱስ አባ ብሶይ (ኃያል ሰማዕት)
በዚህችም ዕለት የተመረጠ ኃያል ተጋዳይ አባ ብሶይ አረፈ። የዚህ ቅዱስ አባቶቹ ክብር ይግባውና ጌታ ክርስቶስን የሚያመልኩና ትእዛዙን የሚጠብቁ ክርስቲያን ነበሩ የአባቱም ስም ታግኅስጦስ ነው እርሱም ከአንጾኪያ የቃው ገዥ ነበር የእናቱም ስም ክሪስ ይባላል።
እነርሱም ልጅ ሳይኖራቸው ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖሩ ስለዚህም እጅግ እያዘኑ ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ይለምኑ ነበር። ከሌሊቶችም በአንዲቱ ለታግኀስጦስ ብርሃን የለበሰ ሰው ተገልጦለት እንዲህ አለው የእግዚአብሔር ወዳጅ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን እነሆ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰምቷል ሚስትህም ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች ስሙንም ብሶይ ትለዋለች እርሱም ለእግዚአብሔር የተመረጠ ዕቃ ይሆናል እርሱም ደግሞ ክብር ይግባውና ለክርስቶስ ምስክር ይሆናልና ብዙ ሥቃይና መከራም ተቀብሎ የሰማዕትነት አክሊልን ይቀዳጃል።
ከእንቅልፉ ነቅቶ ራእይ እንዳየ ለሚስቱ ነገራት። ከጥቂት ቀኖች በኋላም ፀንሳ ይህን ቅዱስ ሚያዝያ አንድ ቀን ወለደችው ዕውቀትን ጥበብንና ፈሪሀ እግዚአብሔርን በማስተማር አሳደጉት። ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ ወደ አክሚም ዮሴፍ ወደሚባል አንድ አረጋዊ መምህር ላኩት በዚያም እየተማረ ከወንድሙ ጴጥሮስ ጋራ በጸሎትና በጾም ተጠምዶ ድንቆች ተአምራትን እያደረገ ኖረ።
ከዚህ በኋላም ሃያ ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ የስዒድ መኰንን ወዳለበት ወደ ቃው ከተማ መጣ እርሱም ክርስቲያኖችን እያሳደደ ከእርሳቸው ይገድል ነበር። ያን ጊዜም ክፉዎች ሰዎች ወደ መኰንኑ መጥተው ለቃልህ የማይታዘዙና ለአማልክት መስገድንም እምቢ የሚሉ ሁለት ዲያቆናት አሉ ብለው እኒህ የከበሩ አባ ብሶይንና አባ ጴጥሮስን ከሰሱአቸው።
በዚያን ጊዜም እንዲአቀርቧቸው አዘዘና አቅርበው በፊቱ አቆሙአቸው ስለ ሥራቸውም መረመራቸው ክርስቲያን እንደ ሆኑም ከቃላቸው ሰምቶ እንዲአሥሩአቸው አዘዘ። ከሦስት ወር በኋላም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦላቸው እኔ የምሥራች የምናገር ገብርኤል ረዳችሁና እነግራችሁ ዘንድ ወደ እናንተ እግዚአብሔር ላከኝ ስም አጠራራችሁና መታሰቢያችሁ ለዘላለሙ ይኖር ዘንድ አለውና አላቸው። አንተም ወዳጄ ብሶይ ታላቅ ተጋድሎ አንተን ይጠብቅሃል ወደ እስክንድርያ ከተማ ሊሰዱህ አላቸው ከዚያም ወደ አንጾኪያ ወስደውህ በዚያ የምስክርነትህ ገድል ይፈጸማል።
ከዚህ በኋላም መኰንኑ ከወህኒ ቤት አውጥቶ ለጣዖት እንዲሰግድ አስገደደው እምቢ ባለውም ጊዜ ከባላ ላይ አውጥተው በግንድ ውስጥ እጅግ እንዲጨምቁት ወታደሮችን አዘዘ። በዚያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ወረደ ግንዱን ሰብሮ ቅዱስ ብሶይን በመዳሠሥ አዳነው። ከዚያም ወደ ወህኒ ቤት ጨመሩት በዚያም ብዙ በሽተኞችን ፈወሳቸው።
ዳግመኛም እንዲህ አዘዘ ከወህኒ ቤት አውጥተው በመርከብ ሆድ ውስጥ አስገብተው አንገቱን በብረት ሰንሰለት እጆቹንና እግሮቹንም እንዲሁ በብረት ማሠሪያ እንዲአሥሩት እንጀራና ውኃ እንዳይሰጡት አዘዘ እንዲዚህም ሆኖ ዐሥር ቀን ኖረ።
ከዚህም በኋላ አውጥቶ በፊቱ አቁሞ ለአማልክቶቼ ስገድ አለው እምቢ ባለውም ጊዜ ደሙ እንደ ውኃ እስቲፈስ ከባላ ግንድ ላይ አውጥተው አጥብቀው እንዲጨምቁት ሁለተኛ አዘዘ። እንዲሁም በእርሱ ላይ አድርገው በውህኒ ቤት አሠሩት።
የእግዚአብሔር መልአክ ገብርኤልም ደግሞ ተገለጠለትና አይዞህ መልካም ገድልህን እስከምትፈጽም እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁና አትፍራ አለው። ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ወደ ቁልቁልያኖስ መኰንን ሰደዱት እርሱም ስለ ሥራው ሁሉ መረመረውና ሕዋሳቱ ተቆራርጦ እስቲወድቅ ድረስ ይደበድቡት ዘንድ አዘዘ።
ሁለተኛም ዘይትን አፍልተው በጆሮው በአፉና በደረቱ ላይ እንዲአፈስሱ ጐኖቹንም በእሳት መብራት እንዲአቃጥሉ አዘዘ ደግሞም በእሳት የጋሉ የብረት ችንካሮችን አምጥተው በዐይኖቹ ውስጥ አደረጓቸው። ሁለተኛም የእጆቹንና የእግሮቹን ሥሮች ሕዋሳቱንም ሁሉ እንዲነቅሉ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት በዚያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ሕዋሳቱን ሁሉ ፈወሰው።
ከዚህም በኋላ አንጾኪያ ከተማ አደረሱትና ወደ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አቀረቡት እርሱም በእሳት በአፈሉት በወይን በሙጫ ድፍድፍ በማቃጠል አሠቃየው ከዚያም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል አዳነው።
ዳግመኛም በአንገቱ ከባድ ደንጊያ በሰንሰለት አሥረው ወደ ባሕርም አንከባለው ግማሽ ሥጋውን እንዲአሠጥሙ ግማሹን ግን እንዳያሠጥሙ አዘዘ እነርሱም በባሕሩ ዳር ታላቅ ምሰሶ ተከሉ በዚያም እንዳዘዛቸው አድርገው አሥረው ተውት በዚህ ሥቃይም ከቀኑ እስከ ሰባት ሰዓት ዋለ ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ፈትቶ አወጣው እንደ ቀድሞውም ጤነኛ አደረገው ንጉሡም አይቶ አደነቀ ሰያፊውንም ፈጥኖ አንገቱን እንዲቆርጥ አዘዘው ያን ጊዜም አንገቱን ቆርጦ በባሕር ዳር ከምድር ላይ ጣለው ሥጋውንም አንሥቶ ከቁርበት በተሠራ ጋን ውስጥ ጨመረው ሥጋውም ከራሱ ጋራ ተገናኘና እንዳልተቆረጠ ሆነ ጋኑም በሃያ ቀን እስክንድርያ እስከሚደርስ ድረስ ሰው ሳይሸከመው ብቻውን የሚጓዝ ሆነ። የቦሀ ሀገር ሰዎችም በሰሙ ጊዜ መጡ ተሸክመውም በቦሀ አገር ከአለው ቤቱ ውስጥ አስገብተው ከወንድሙ ጴጥሮስ ጋራ ቀበሩት።
✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟
ቅዱስ ብፋሞይ ሰማዕት
በዚህችም ዕለት ደግሞ ቅዱስ ቢፋሞን ምስክር ሆነ። ይህ ቅዱስ ለዮሐንስ ዘሐራቅሊ የእናቱ ወንድም ልጅ ነበር ዮሐንስም ታሥሮ ሳለ ያገለግለው ነበር። ዮሐንስም ገድሉን በፈጸመ ጊዜ ሥጋውን ገነዘ በበድኑ ላይም እንዲህ ብሎ አለቀሰ ከእግዚአብሔር የተለየሁ ሁኜ ብቻዬን እንዴት ትተወኛለህ ከቅዱስ ዮሐንስ ሥጋም እንዲህ የሚል ቃል ወጣ ወዳጄ ቢፋሞን ከእኔ ጋራ መኖርን ከፈለግህ ፈጥነህ ወደ መኰንኑ ሒደህ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ታመን ነገም ወደ እኔ ትመጣለህ።
ይህንንም ሰምቶ የዮሐንስን ሥጋውን ቀበረ ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ሔደ። ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየታመነ የረከሱ ጣዖታቱን ሰደበ። መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይ አሠቃየው ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጠ የምስክርነትንም አክሊል ተቀበለ።
✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟✟
ቅድስት ማርታ
በዚህችም ዕለት ሃይማኖቷ የጸና ምግባርዋም የቀና ክርስቶስ ያደረባት የመነኰሳዪት የቅድስት ማርታ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው በስደት ሳለችም አረፈችና በተራራ ውስጥ ተቀበረች።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውምም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages