ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 9 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, June 16, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 9

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሰኔ ዘጠኝ በዚህች ዕለት የታላቁ ነቢይ ሳሙኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ ቅዱስ ሉክያኖስ ከሌሎች አራት ሰማዕታት ጋራ ሰማዕት ሆነ።


ነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል
ሰኔ ዘጠኝ በዚህች ዕለት የታላቁ ነቢይ ሳሙኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። የዚህ ቅዱስ አባቱ ሕልቃና ይባላል የእናቱም ስሟ ሐና ነው። እነርሱም ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ወገን ናቸው። ሐናም መካን ነበረች ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር እያለቀሰች አዘውትራ ስለ ማለደች ይህን የተባረከ ልጅ ሰጣት በቤቷም ሦስት ዓመት አሳደገችው።
ከዚህም በኋላ ገና ስትፀንሰው እንደተሳለች ወደ እግዚአብሔር መቅደስ አቀረበችው ካህኑ ኤሊንም በመላላክ የሚያገለግለው ሆነ። የካህኑ የኤሊ ልጆች ግን ክፉዎች ነበሩ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር በቅዱስ መሥዋዕቱም ላይ በደሉ። ይህ ሕፃን ሳሙኤል ግን በኤሊ ፊት ለእግዚአብሔር ሲያገለግል ኖረ በነዚያ ወራቶችም ቃለ እግዚአብሔር ውድ ነበር የሚታይ ራእይም አልነበረም።
ከዚህም በኋላ በአንዲት ሌሊት እንዲህ ሆነ ኤሊ በመኝታው ተኝቶ ሳለ ዐይኖቹም መፍዘዝ ጀምረው ነበር ማየትም አይችልም ነበር። የእግዚአብሔርንም መብራት አብርቶ ለማሳደር ገና አላዘጋጁም ነበር ሳሙኤል ግን በቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦት አጠገብ ተኝቶ ነበር።
እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው እነሆ እኔ አለሁ አለ። ወደ ኤሊም ፈጥኖ ሔደ ስለጠራኸኝ እነሆ እኔ መጣሁ አለው ኤሊም አልጠራሁህም ተመልሰኽ ተኛ አለው ሔዶም ተኛ።
እግዚአብሔርም ዳግመኛ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ኤሊ ሔደ ስለጠራኸኝ እነሆ መጣሁ አለው። ኤሊም አልጠራሁህም ተመልሰህ ተኛ አለው። ሳሙኤልም ከዚህ አስቀድሞ እግዚአብሔርን በራእይ ገና አላወቀውም ነበር ቃለ እግዚአብሔርም አልተገለጠለትም ነበር።
ዳግመኛም እግዚአብሔር ሳሙኤልን ሦስተኛ ጊዜ ጠራው ተነሥቶም ወደ ኤሊ ሔደ ስለጠራኸኝ እንሆ መጣሁ አለው ኤሊም ያንን ልጅ እግዚአብሔር እንደጠራው አሰበ። ልጄ ተመልሰህ ተኛ የሚጠራህ ካለ እኔ ባርያህ እሰማለሁና ጌታዬ ተናገር በለው አለው ሳሙኤልም ሒዶ በመኝታው ተኛ።
እግዚአብሔርም መጥቶ እንደ መጀመሪያው በፊቱ ቁሞ ጠራው። ሳሙኤልም እኔ ባሪያህ እሰማሃለሁና ጌታዬ በል ተናገር አለው እግዚአብሔርም ሳሙኤልን የሰማው ሁሉ ሁለቱን ጆሮዎቹን ይይዝ ዘንድ እነሆ እኔ በእስራኤል ላይ የተናገርሁት ቃሌን አደርጋለሁ።
በዚያችም ቀን በኤሊና በወገኑ ላይ የተናገርኹትን ሁሉ አጸናለሁ እጀምራለሁ እፈጽማለሁም። ልጆቹ የእግዚአብሔርን ቃል አቃልለዋልና እርሱም አልገሠጻቸውምና በልጆቹ ኃጢአት እኔ ወገኑን ለዘላለም እንደምበቀለው ነገርሁት። ስለዚህም ነገር በዕጣንም ቢሆን በመሥዋዕትም ቢሆን የኤሊ የወገኑ ኃጢአት እስከ ዘላለሙ ድረስ እንዳይሠረይ ራሴ እንዲህ ብዬ ማልሁ። በኤሊ ወገኖችና ልጆች ላይ እግዚአብሔር የተናገረው ሁሉ ተፈጸመ።
ከዚህም በኋላ የቂስ ልጅ ሳኦልን ቀብቶ ለእስራኤል ልጆች ያነግሠው ዘንድ እግዚአብሔር ሳሙኤልን አዘዘው እንዲአነግሥላቸው ለምነዋልና። ሳኦልም የልዑልን ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ዳግመኛ ለእስራኤል ንጉሥ ሊሆን የዕሴይ ልጅ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ ይህን ነቢይ ሳሙኤልን ዳግመኛ አዘዘው። ይህም ነቢይ ሳሙኤል በሕይወት በኖረበት ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስተዳደራቸው። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሉክያኖስ
በዚህችም ዕለት ቅዱስ ሉክያኖስ ከሌሎች አራት ሰማዕታት ጋራ ሰማዕት ሆነ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ የጣዖት ካህን ነበረ የሰማዕታትንም መከራቸውን በእሳት ሲአቃጥሏቸውና ሕዋሳታቸውን ሲቆራርጧቸው ሲሰቅሏቸው ከእሳት ምድጃ ውስጥም ሲጥሏቸው ምንም ምን ጉዳት እንዳልደረሰባቸው በአየ ጊዜ ከዚህ ሥራ የተነሣ አደነቀ ክብር ይግባውና በጌታችን አመነ ያገለግላቸው የነበሩ ጣዖታት ከእሳት ቢጥሏቸው ፈጥነው ይቃጠላሉ እንጂ ይህን ሥራ ሊሠሩ እንደማይችሉ ተረድቷልና።
ዳግመኛም እንዲህ አለ ይህን ድንቅ ሥራ የሚሠራ አምላክስ በእውነት እርሱ አምላክ ነው። ከዚህ በኋላም በንጉሥ ፊት እኔ ክርስቲያን ነኝ ክብር ይግባውና በክርስቶስ አምናለሁ ብሎ በግልጥ ጮኾ ተናገረ። ንጉሡም ወደርሱ አቅርቦ ጣዖት ማምለክን እንዳይተው መከረው ወደ አምልኮ ጣዖት ይመለስ እንደሆነ ብሎ ብዙ ቃል ኪዳኖችን ገባላት።
እርሱ ግን አልሰማውም ሥቃዩንም አልፈራም ከዚህም በኋላ ንጉሡ ጽኑዕ ሥቃይን ሊአሠቃየው ጀመረ ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉት መንጋጋውንም በደንጊያ እንዲሰብሩት ታላቅ ግርፋትንም እንዲገርፉት አዘዘ።
ከዚህ በኋላም አራት ክርስቲያን እሥረኞች ቀረቡና ከእርሱ ጋራ አቆሟቸው ንጉሡም ለአማልክት ዕጣን ዕጠኑ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሥቃይን አሠቃያችኋለሁ አላቸው። እነርሱም ለስሕተቱ አልታዘዙለትም በላያቸውም ተቆጥቶ በእሳት ምድጃ ውስጥ ጨመራቸው ያንጊዜ ዝናብ ዘነበ እሳቱንም አጠፋው።
ቅዱስ ሉክዮስን ግን እንደ አምላክህ እሰቅልሃለሁ ብሎ በዕንጨት መስቀል ላይ እንዲሰቅሉት አዘዘ በረጃጅም ችንካሮችም ሥጋውን ሁሉ ቸነከሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። እነዚያን አራቱን ሰዎችም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡአቸው የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን። በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages