ግልጽ ደብዳቤ በመምህር ዮርዳኖስ አበበ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, June 17, 2023

ግልጽ ደብዳቤ በመምህር ዮርዳኖስ አበበ

 ግልጽ ደብዳቤ

ይድረስ
❖ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
❖ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
❖ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አባቶቻችን
☞ በመንግሥትም በቤተ ክህነትም የተገፋን እና በአደባባይ ግፍ የተፈጸመብን ምእመናን
ጉዳዩ፦ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ሂደትን እና የሚያስከትለውን አደገኛ መከራ ስለማስጠንቀቅ የተላከ መልዕክት
ሰኔ 10 ቀን 2015 ዓ.ም
ጥር 14 ቀን 2015 ዓ/ም በሳዊሮስ፥ በኤዎስጣቴዎስ እና በዜና ማርቆስ በተፈጸመው አመፅ የወለደው ኢ-ቀኖናዊ ሲመት ምክንያት በእኛ ኦርቶዶክሳውያን ላይ ብዙ ሞት፥ ብዙ ስደት፥ ብዙ መፈናቀል፥ ብዙ እሥር ደርሶብናል። ግፉ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። ለማሳያ እንዲሆን በሻሸመኔ ብቻ ከ50 በላይ የሚሆኑ ምዕመናንና ካህናት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ ከ105 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በጥይት ተመትተው ቆስለዋል፡፡ ከ400 በላይ ታሥረዋል፥ ቁጥራቸው የማይታወቅ ተሰደዋል፤ ቁጥራቸውን ለማወቅ የሚያዳግት ደካሞች በመሳቀቅ ከእምነታቸው አፈግፍገዋል፤ በአጠቃላይ አሳዛኝና ዘግናኝ የሚባለው ግፍ ሁሉ ተፈጽሟል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ የክርስቲያኖች የእምነት ተጋድሎ፣ ተጋዳዮቹ በግል ሰማዕትነታቸው ከአምላካቸው ከሚያገኙት ሰማያዊ ክብርና በምድር ለትውልድ በሚያተርፉት አርዓያነት ክብር በተጨማሪ ሁላችንም የዚህች ቤተክርስቲያን የጥምቀት ልጆች የምንደሰትበት፥ ቤተክርስቲያን የበለጠ ከፈተናው ተምራ የምትፀናበት ተከታይ እርምጃ ከቅዱስ ሲኖዶስ ስንጠብቅ ተቃራኒው ተፈጽሞ በማየታችን እጅግ አዝነናል።
አባቶች ይህንን መከራ የተቀበሉ ልጆቻችሁ የት እንደወደቁ ጠይቃችሁ፣ ስንት እንደሆኑ ቆጥራችሁ፥ በደል ፈጻሚው እንዲክስና እንዲከሰስ፣ በአካላቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው በመንፈሳቸው ከአፅራረ ቤተክርስቲያን ጋር በመቆም ለመከራው ምክንያት የሆኑት ግለሰቦችም በቤተክርስቲያን ሕግ እንዲወገዙ፥ በዓለሙ ሕግ ደግሞ እንዲከሰሱ አላደረጋችሁም። እንዲያውም በተቃራኒው ለኢ-አማኒ የመንግሥት ባለሥልጣን ድርድር እጅ በመሥጠት ለመከራችን መብዛት ምክንያት የሆኑትን ግለሰቦች ከግዝት በመፍታት ዋናዎቹን መሪዎች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እና እንዲሁም እንርሱን ጥፉዎቹን የሚመስሉ ተጨማሪ አዳዲስ መርጠው እንዲጨምሩበት ኤጲስ ቆጶሳት መራጭ ኮሚቴ በማድረግ ሰየማችሁ። በሕገ ወጥ መንገድ ጵጵስና የተቀበሉ የሐሰት መነኮሳትን ከዲቁና እስከ ቁምስና የያዛችሁባቸውን ሥልጣነ ክህነት መልሳችሁ ሰጣችኋቸው፤ እኛንም “ከዛሬ ጀምሮ አባቶቻችሁ ናቸውና በቀደመ አባትነታቸው ተቀበሏቸው፥ መስቀላቸውን ተሳለሙ፥ ሰው ባስገደሉበትና ባሳደዱበት፥ መናፍቃንና ተንባላትን ሰብስበው ባስገቡበት ቤተመቅደስ ውስጥ ቀድሰው ያቁርቧችሁ” አላችሁን።
የቆሰልነውን፥ የተሰደድነውን፥ የታሰርነውን፣ አባት፣ እናትና ልጅ የተገደለብንን፣ ንስሐ አባቶቻችን የተገደሉብንና ጥለውን እንዲሰደዱ የሆንነውን እኛን ልጆቻችሁን ከሃዘናችን አላጽናናችሁንም፤ ዕንባችንን አላበሳችሁልንም፤ ለተጋደልንለት የቤተክርስቲያናችን ክብር ታምናችሁ የችግሩ ዋና መንስዔ የሆነውን የውስጥና የውጭ ፈታና ያገናዘበና ዘመኑን የዋጀ መፍትሔ አልሰጣችሁንም።
በዚህ ልብ ሰባሪ ሁኔታ ውስጥ ባለንበት በአሁኑ ወቅት በስብራት ላይ ስንጥቃት እንዲሉ አስገዳዮቻችን ንስሐ ሳይገቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ እየተመሩና ባደረጉት የጥፋት ስምምነት እየተመኩ የጀመሩትን የቤተክርስቲያኗን ሕልውና የሚፈታተነውን መንገድ ለማስቀጠል በተዘጋጀ የማስማሚያ ውል መሠረት ዛሬም በአደባባይ የሚሟገቱትን ሰዎች “የቅዱስ ሲኖዶስ አባል” አደረጋችኋቸው፡፡ ይህም ሳይበቃ በግንቦት 2015ቱ ርክበ ካህናት ላይ በወሰናችሁት የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይ ላይ የመራጭ ኮሚቴ አባላትና መሪ አድርጋችሁ ሰየማችኋቸው።
የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ኮሚቴ አድርጋችሁ እነማንን እንደሾማችሁ፥ ለምን ሂደቱ እንደተጣደፈ፥ በማን ትዕዛዝ እንደምትመሩ፥ በጎሣ መሥፈርት አባት ለመሰየም መወሰናችሁ፥ የምእመናንና የሊቃውንትን “የምርጫ ሂደቱ የይቆይ” ጩኸት ችላ ማለታችሁ እኛን ልጆቻችሁን እጅጉን አስፈርቶናል፡፡
ይህ ሂደት በሙሉ የሚያሳየን፣ ልትሾሙአቸው የተዘጋጃችሁት የወደፊት “አባቶቻችንን” ሳይሆን ምእመናን በጥይት እንዲሰዉ ያደረጉ፣ ተንባላትንና ፕሮቴስታንትን ያለቦታቸው ይዘው ወደ ቤተመቅደስ የሚገቡትን ነው፡፡ ይህ እንደሚሆን ደግሞ ከጥር 2015 ዓ/ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለው ሂደት ያሳያል። ይኸውም፣ ደም ያስፈሰሱትን፥ ደም አፍሳሽ ወታደር ያዘዙትን፥ የሐሰት ሲኖዶስ እንዲፈጠር ድጋፍ የሰጡትን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ትዕዛዝ ተቀብላችኋል፡፡ ስለዚህም የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ረቂቅ ደንቡ እንዳይፀድቅ ከሲኖዶስ አጀንዳነት ውጭ እንዲሆንም አድርጋችኋል። በዚህም ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ/ም የሚቀርብላችሁን የጎሣ ምርጫ በሳምንቱ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ለመሾም ቀጠሮ ይዛችኋል። ይህንንም ሹመት ምእመናን፥ ገዳማውያን፥ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች፥ ማኅበራት፥ ካህናት ሳይሳተፉ ልታከናውኑ መሆኑ፣ ከቤተክርስቲያኒቱ ልማድ ውጭ በሳምንት ውስጥ ለመፈጸም መወሰናችሁ ይመሰክራል።
እኛ የመከራው ተቀባይ የምዕራብ አርሲ፥ የምዕራብ ሐረርጌ፥ የወለጋ፥ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ፥ የምዕራብ ሸዋ፥ እንዲሁም የእኛን መከራ የሚካፈሉ የጥምቀት ልጆች ሁላችን የምታደርጉትን ሲመት የኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሲመት ነው ብለን ለመቀበል እንቸገራለን። ይልቁንም የምትሾሙት ለጎሣ ፖለቲካ በመታዘዝና ራሱን ከእምነቶች ሁሉ በላይ ለማስቀመጥ ለሚሠራው “የኦሮሙማ” ለተባለ አዲስ እምነት እንደሆነ እናምናለን። በተመሳሳይ በትግራይም የሚታየው በቋንቋ ሰበብ የተጀመረው በሕወሓትና በብልጽግና መካከል ሲኖዶሱን ለመካፈልና በሐሰተኛ ክርስትና ለመተካት ያላቸውን እቅድ የማስፈጸም ሂደት አካል ሆናችኋል ብለን እናምናለን። እዚህ ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ ያደረገን በጥይት መቁሰላችን፥ መታሠራችን፥ መገደላችንና አሁን በስደት መኖራችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እጩ የመለየት፥ በምእመናን የማስገምገም፥ የኋላ ታሪካቸውን የማስመስከር እና የቅድስና ሕይወታቸውን፥ የጥምቀት ልጆች ሁሉ አባትነት አቋማቸውን የማረጋገጫ ሥርዓቱ መቆረጡ ነው። ይህ ሂደት ፈፅሞ ከሐዋርያት ቀኖናና ሕግ ውጭ ከመሆኑም በላይ ለአላውያን የፖለቲካ ፍላጎት የሚያገለግል፣ ለቅድስትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ፈጽሞ እንቅፋት የሆነ፣ በታሪካችን ላይ አሳፋሪ ጠባሳ የሚያትም እና ለወደፊቱ አሁን ከሚታየው በበለጠ የተወሳሰበ ፈተና የሚያስከትል መሆኑ እሙን ነው። ስለሆነም ሁኔታው ቀደም ሲል ከደረሰው ጥፋት የሚከፋና የበለጠ መከራ የሚያመጣ መሆኑን በትህትና ልናስታውሳችሁ እንፈልጋለን።
የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ከመሰየሙ፥ የምርጫ ቀንም ከመቆረጡ አስቀድሞ ሂደቱን በመቃወም እና ይህ የዘረኝነትና የፖለቲካ ስካር እስኪሰክን ድረስ ምንም አይነት ሲመት እንዳይካሄድ በመጠየቅ ወደ አሥር ሺ የሚጠጉ ምእመናን ተፈራርመው አቤቱታ አስገብተዋል፥ ሊቃውንት የሂደቱን ኢ-ቀኖናዊነት ጽፈዋል፥ ጮኸዋል። ይሁን እንጂ ከመገመት ውጭ በዝርዝር ልንረዳው ባልቻልነው ምክንያት እጅግ በሚያስደነግጥ ተቃርኖ ቆማችሁ ተገኝታችኋል፤ የቤተክርስቲያንን ሕግ፥ የሊቃውንቱን ግብረ መልስና የምእመናንን ድምጽ ከምንም ባለመቁጠር ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት የሚሠራ ዘረኛ የፖለቲካ ባለሥልጣን ትዕዛዝ እንደበለጠባችሁ በሚያመለክት መንገድ ውሳኔዎችን ወስናችኋል። ይህንን ከግምት በማስገባት ለመጀመሪያ ጊዜ እኛ ምእመናን በግልፅ ስለቤተክርስቲያናችንና ስለ ክርስቶስ ብለን እናንተን ለመቃወም እንገደዳለን።
ተቃውሞአችንም መፍትሔ እስከምናገኝና በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና አባትነታችሁ ከፍታ ላይ ተመልሳችሁ እስክትቀመጡ ያለአንዳች ማወላወል ተቃውሞችንን እንደምንቀጥል ዲሁ እንድታውቁልን እንፈልጋለን። የአባትነት ክብራችሁን ያገኛችሁት ክርስቶስ በደሙ ከመሠረታት ከተከበረችዋ ቤተክርስቲያን እንጂ ከኢ-አማንያን የዘር ፖለቲካ ባለሥልጣናት ትዕዛዝና እቅድ ውስጥ አይደለም፤ ሁላችንንም የሚያስከብረንን፥ ከእግዚአብሔር የሚያገናኘንን ከክርስቶስ ያገኛችሁትን የጳጳስነት ክብራችሁን ለማስመለስ ፊታችሁን ወደ ቤተክርስቲያን ቀኖና እና ሕግጋቶቿ መልሳችሁ በመንፈስ ቅዱስ እንድትመሩ እና እንድትመሩን በስሙ “ክርስቲያኖች” ባሰኘን እና እናንተንም “የክርስቲያኖች አባቶች” ባሰኛችሁ በአምላካችን በጌታችን እና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንለምናችኋለን።
ከዚህ በታች በስም የተዘረዘሩት ሰማዕታት፥ ቁስለኞች፥ ታሳሪዎችና ቁጥራቸው የማይታወቁ ተሳዳጆች የእናንተን የአባቶችን “ቤተክርስቲያናችሁን ተከላከሉ፥ ጥቁር ልበሱ፥ ጹሙ፣ ጸልዩ” የሚለውን ትዕዛዝ ተቀብለው የጎሣውን “ኤጲስ ቆጶሳት” ሲፋለሙ የነበሩ ወገኖቻችን ናቸው። ሰማዕትነት የተቀበሉትን ሰማያዊ ዋጋ ለሚሰጠውና ለታመኑለት አምላከቸው ትተን አሁን በስደት፥ በእሥር፥ በአካል መጉደል፥ ከሥራ በመባረር መከራ ውስጥ ለምንገኝ ለእኛ ተጨማሪ በቀል የሚፈጽምብን የጎሣ ኤጲስ ቆጶሳት ልትሾሙልን እንደሆነ ስንመለከት እጅግ አዝነናል። በዚህ ውሳኔአችሁ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጦር በጥይት የተመቱ ኦርቶዶክሳውያን ልጆቻችሁን የሰማዕትነት ዋጋ በማሳጣት መቺውና አስመቺው የፈለገውንና የፈቀደውን ሂደት መርጣችኋል። እነዚህ ልጆቻችሁ የከፈሉትን ዋጋ ችላ ብላችሁ በገዳዩ ትዕዛዝ አስገዳዩን ለመሾም መዘጋጀታችሁ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መጥፎ አሻራ ሆኖ ይኖራል። ይህች ቤተክርስቲያን ከቤተመንግሥት ከተነሳ ኢ-አማኒ እንዴት እንደተጠበቀች ለማስታወስ የቅርቡን የአፄ ሱስንዮስን አዋጅ በመቃወም እየተዋጉ ሰማዕትነት የተቀበሉ መነኮሳትንና የሞቱትን ጳጳስ ማሰቡን አለመፍቀዳችሁ እጅግ የሚያስደነግጥ ነው።
ይህን ሥጋታችንን ችላ በማለት አሁን በተጀመረው ኢቀኖናዊ መንገድ ከቀጠላችሁ ቢያንስ በሰብአዊ ስሌት ስንመለከተው የሚከተሉት ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይከሰታሉ፤ ለዚህም እናንተ አባቶች ድርሻችሁ ከፍተኛና ወሳኝ ነው፦
1. በጎሣ መደብ የሚፈጠረው የኤጲስ ቆጶሳት ስብስብ ከወዲሁ በተግባር እንዳሳየው ለየጎሣው ፖለቲካዊ ግብ በመታዘዝ ንዑስ የወገንተኝነት አቋም ይይዛል፤ በዚህም በጠ/ሚ አብይ አህመድ አመራር ቅዱስ ሲኖዶስ የኦሮሚያ፥ የትግራይ እና የደቡብንም ጨምሮ ቢያንስ በ5 ይከፈላል።
2. የተከፋፈለው ሲኖዶስ የየራሱን መንበርና መንደር መርጦ እንዲሰየም ፖለቲካው በሚያደርገው ግፊት በትግራይ፥ በአዲስ አበባ፥ ምናልባትም በሐዋሳና ባህርዳር ወይንም በበለጠ ቦታ ይበተናል።
3. የ1ኛውንና 2ኛውን ተ/ቁ ክስተት ተከትሎ በቁስ ፍትወት ኅሊናውን፥ ሰብአዊነቱንና ፍትሐዊነቱን ያጣው የዘር ፖለቲካ የንብረት ክፍፍል ክስ በማስጀመር ቁስና ቦታ ያካፍላችኋል።
4. በዚህ ሂደት ውስጥ በጥምቀት አንድ የክርስቶስ አካል የሆኑ ዜጎች፥ በቅዱስ ጋብቻ የተጣመሩ ባለትዳሮች፥ የአንድ ንስሐ አባት ልጅ የሆኑ ክርስቲያኖች ይከፋፈላሉ፤ ትዳር ይፈርሳል፤ ሕዝብ ይፈልሳል፤ ካህን በጎሣ ዘውግ ይሳደዳል፤ በቂ ካህናት የሌላቸው አካባቢዎችና ጎሣዎች የሚያጠምቃቸው ካህንና ሰባኬ ወንጌል ያጣሉ፤ እስከ አሁን ከፈለሰው 10 ሚልዮን ክርስቲያን በላይ ብዙዎች እምነታቸውን ጥለው ይኮበልላሉ።
5. በአንዲት ታሪካዊት አገር ውስጥ የራሳቸውን አገር ለመመሥረት፥ ሌላውን ለማጥፋት የሚሯሯጡት የፖለቲካ ቡድኖች ዜጎችን አሁን ከሚታየው በበለጠ እንዲጠፋፉ ለማድረግ ምክንያት ያገኛሉ።
6. በሃይማኖትና በባህል እርሾው የፖለቲካውን የጥላቻና የመለያየት ፕሮፓጋንዳ ተቋቁሞ በአንድ ቤተ መቅደስ፥ በአንድ ካህን፥ በአንድ ክርስቶስ ተዋሕዶና ታግሶ ጥፋቱን ያዘገየው ምእመን አሁን በምትሾሙት የጎሣ ጳጳስ እየተመራ ይተላለቃል።
ይህ እንዳይሆን አሁን የምትወስኑት ውሳኔ ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ ውሳኔያችሁን በድጋሚ እንድታጤኑት እንለምናችኋለን።
ሆኖም የምእመናንን ደምና ዕንባ፥ የክርስቶስን አደራ፥ የነፍሳችንን ነገር ሁሉ ችላ በማለት ኢ-አማኒና ፀረ-ኦርቶዶክስ ባለሥልጣናትን በማገልገሉ ከቀጠላችሁ “በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” (መጽሐፈ አስቴር 4፥ 14) እንዳለ መርዶኬዎስ፤ ለእኛም እግዚአብሔር መፍትሔ ይሰጠናል። የት እንደደረሱ የማይታወቁ የጥምቀት ልጆች ደምና ዕንባ ያለ ዋጋ አይቀርም።
ቡራኬያችሁ ትድረሰን!
በቤተ መንግሥትም በቤተ ክህነትም የተገፋን የክርስቶስ ልጆች ነን!!
አባሪ፦ ለመታሰቢያና ማስታወሻ በሻሸመኔ የተፈፀሙ ግፎች ከፊል ናሙናዊ መረጃና በዚያ ምክንያት በሌሎች ቦታዎች የደረሱ እስሮችን 14 ገጽ መረጃ አያይዘናል።
በመምህር ዮርዳኖስ አበበNo comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages