ሐምሌ ዐሥራ ሦስት በዚች ቀን የሀገረ ቅፍጥ ኤጲስቆጶስ አባ ብስንድዮስ አረፈ፣ ቅዱስ አሞን ምስክር ሁኖ አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ኤጲስቆጶስ አባ ብስንድዮስ
ሐምሌ ዐሥራ ሦስት በዚች ቀን የሀገረ ቅፍጥ ኤጲስቆጶስ አባ ብስንድዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ሰው መንኩሶ በታላቅ ገድል ተጠመደ ቅዱሳት መጻሕፍትንም አጠና ከቅዱሳት መጻሕፍትም ውስጥ የዳዊትን መዝሙርና የነቢያትን መጻሕፍት አጥንቶ ነበር። ከነቢያት ትንቢትም አንዳንዱን መጽሐፍ ያነብ ነበረ። ትንቢቱ የሚነበብለት ነቢያም ወደርሱ መጥቶ ንባቡን እስቲፈጽም ይቆይ ነበር።
ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ እጆቹን አንሥቶ በሚጸልይ ጊዜ ጣቶቹ እንደ ፋና ይበሩ ነበር እግዚአብሔርም በእጆቹ ታላላቅ ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ።
እርሱም በዕድሜው ዘመን ሁሉ የሴት ፊት አላየም።ራሱን ወደ ምድር ያዘነብል ነበር እንጂ። በሆድዋ ውስጥ ታላቅ ደዌ የነበረባትም አንዲት ሴት ነበረች ከበዓቱ ደጅ ጠበቀችውና በድንገት አገኘችው። እርሱም ሮጠ እርስዋም ተከትላው ሮጠች። ወደርሱ መድረስም በተሳናት ጊዜ እግሩ የረገጠቻትን አንዲት እፍኝ አፈር ዘግና በእምነት በላች ከደዌዋም ፈጥና ተፈወሰች።
በአንዲት ዕለትም የሚያበሩ ሦስት ሰዎችን አየ እነርሱም አንተ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትመግባት ዘንድ አለህ እያሉ መክፈቻ ቁልፍን ሰጡት። ከዚህ በኃላ ቅፍጥ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ተሾመ። የቁርባን ቅዳሴ በሚቀድስ ጊዜም ጌታችንን እጆቹ በመሠዊያው ላይ ሁነው ይመለከተው ነበር መላእክቶቹንም በዙሪያው ቁመው ያያቸው ነበር።
በአንዲት ዕለትም አንድ ቄስ ሊቀድስ ገባ በቅዳሴ እኩሌታ ላይም በመሠዊያው ፊት እያለ ምራቁን ተፋ። ቅዳሴውም በተፈጸመ ጊዜ ይህ አባት ገሠጸው እንዲህም አለው በሚያስፈራ መሠዊያው ፊት በምትቆም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጌትነት የተነሣ አትፈራምን የተፋኸውስ ምራቅ በመሠዊያው ዙሪያ በቆመ ኪሩብ ክንፎች ላይ እንደደረሰ አታውቅምን ።ያን ጊዜም ያንን ቄስ መንቀጥቀጥ ያዘው ተሸክመውም ወደ ቤቱ ወሰዱትና ታሞ ሞተ።
ይህም ቅዱስ አባት አንደበቱ ጣዕም ያለው ነበር በሚያነብ ጊዜ በሚያስተምርም በሚመክርም ጊዜ አይጠገብም ነበር። የዕረፍቱም ቀን በቀረበ ጊዜ አውቆ ሕዝቡን ጠራቸውና አስተማራቸው መከራቸውም በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህም በኃላ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጠ።ከሥጋውም ብዙ ተአምር ተገለጠ ደቀ መዝሙሩ ከመግነዙ ጥቂት ቁራጭ ወስዶ በእምነት በሽተኞችን ሁሉ ይፈውስ ነበር።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አሞን
ዳግመኛም በዚች ቀን ከግብጽ ደቡብ ከቡና አውራጃ ጡሕ ከሚባል አገር ቅዱስ አሞን ምስክር ሁኖ አረፈ። ለዚህም ቅዱስ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተገለጸለት ከእርሱ የሚሆነውንም ሁሉ ነገረው።
ከዚህ በኃላ ወደ እንዴናው ከተማ ሒዶ አውግስጦስ በሚባል መኮንን ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። መኮንኑም በመንኩራኩር ውስጥ በእሳት ላይ በመጣል በእሳት በአጋሉት በብረት ዐልጋ ላይ በማጋደም ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ በውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥ በመጨመር ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃዩት።
የራሱንም ቆዳ ገፈው በራሱ ላይ የእሳት ፍም አኖሩ እግዚአብሔርም ያጸናው ነበር ያለ ምንም ጉዳት ጤነኛ አድርጎ ያስነሣው ነበር። ከዚህም በኃላ ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ክርስቶስ በጎልማሳ አምሳል በብርሃን ሠረገላ ላይ ሁኖ ተገለጠለትና አጽናናው እንዲህም አለው ወዳጄ አሞን እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁ ስምህን የሚጠራውን መታሰቢያህን የሚደርግውን ሁሉ ወይም ገድልህን የሚጽፈውን ሁሉ እኔ በመንግሥቴ ውስጥ አስበዋለሁ እጠብቃለሁ ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጥቶት ከእርሱ ዘንድ ዐረገ።
ይህም ቅዱስ በሥጋው ሳለ ታላላቅ ተአምራቶችንና ድንቆችን አደረገ ወዲያውኑም በሰይፍ ራሱን ቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ። ቅዱስ ዮልዮስም በዚያ ነበረ ሥጋውን ወስዶ በመልካም ልብስ ገነዘው ከሁለት አገልጋዮቹም ጋራ ወደ አገሩ ላከው በላይኛው ግብጽም ታላላቅ የሆኑ ድንቆችንና ተአምራቶችን እያሳየ እስከ ዛሬ አለ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
No comments:
Post a Comment