ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, July 16, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 2

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሐምሌ ሁለት በዚች ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የአንዱ ሐዋርያ የቅዱስ ታዴዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህንንም ሐዋርያ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ ጌታችን አስቀድሞ መረጠው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በላያቸው በወረደ ጊዜ ወደ አገሮች ወጥቶ የወንጌልን ትምህርት አስተማረ ከአይሁድና ከአረማውያን ብዙዎቹን ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።
አንድ ቀንም ወደ ሶርያ ከተማ ሲጓዝ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ በሚአምር ጐልማሳ አምሳል ለእርሱ ተገልጦ ወዳጄ ታዴዎስ ቸር አለህን አትፍራ እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁና አለው ሰላምታም ሰጥቶት ከእርሱ ዘንድ ዐረገ። ወደ ከተማውም በቀረበ ጊዜ ከእርሱ ጋራ አባት ጴጥሮስ ነበረ ማሳ የሚያርስ ሽማግሌ ሰውን አዩ ሐዋርያትም ሰላምታ ሰጡትና ሽማግሌ ሆይ የምንበላው እንጀራ ስጠን አሉት።
እርሱም ከዚህ የለም ግን አመጣላችኋለሁ እናንተም ከበሮቹ ዘንድ ተቀመጡ አላቸው እነርሱም እንዳልክ አሉት። ያ ሽማግሌም ከሔደ በኋላ ሐዋርያ ከበሮች ጋር ያለ ሥራ በከንቱ መቀመጥ ለኔ ኅፍረት ነው ያ ሽማግሌ ለእኛ በጎ ሊሠራ ሒዷልና አለ። ይህንንም ብሎ ተነሥቶ እርፉን ይዞ በበሮቹ ላይ ድምፅ አሰማና ያርስ ጀመረ በዚያም ከርሱ ጋራ የሥንዴ ዘር ነበረና ያን ጊዜ ዘሩንና ማሳውን ባርኮ የሐዋርያት አለቃ ጴጥሮስ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእርሻው ላይ ዘራ ሠላሳ ትልሞችንም አረሰ።
የተዘራው ዘርም ወዲያውኑ በቀለና አደገ እሸትም ሆነ ያ ሽማግሌም በተመለሰ ጊዜ ሐዋርያት ያደረጉትን ተመልክቶ ደነገጠ። ከእግራቸውም በታች ወድቆ ሰገደ እናንተ ከሰማይ የወረዳችሁ አማልክት ናችሁን አላቸው እነርሱም እኛ የቸሩ አምላክ ባሮቹ ነን እንጂ አማልክት አይደለንም አሉት ደግሞ እንዲህ አላቸው ስለ አደረጋችሁልኝ በጎ ሥራ በምትሔዱበት ቦታ ሁሉ ልከተላችሁን። ይህን ልታደርግ አይገባም ነገር ግን በሮቹን ለጌታቸው ወስደህ መልስ ቤትህንም አዘጋጅልን የምንበላውንም ታዘጋጅልን ዘንድ ለሚስትህ ንገራት።
እኛም ወደዚች ከተማ ልንገባና እግዚአብሔር እስከ ጠራን ድረስ በውስጧ ለመኖር እንሻለን አሉት። ከዚህም በኋላ ያ ሰው ከዚያ እርሻ እሸት ቆርጦ ተሸከመ በሮቹንም እየነዳ ሔደ የከተማው ሰዎችም የተሸከመውን እሸት አይተው አሁን የእርሻ ወቅት አይደለምን ይህን ከወዴት አገኘህ አሉት ቃልንም አልመለሰላቸውም። በሮቹንም ለጌታቸው መለሰ ወደ ቤቱም ሔዶ ለሐዋርያት ቦታን አዘጋጀ ራትንም እንድታዘጋጅላቸው ለሚስቱ ነገራት።
ወሬውም ወደ ከተማው መኳንንት ደረሰ በክፉ አሟሟት እንዳትሞት ይህን እሸት ከወዴት እንዳገኘህ ንገረን ብለው ወደርሱ ላኩ። ይህንም በሰማ ጊዜ ከእኔ ጋራ ሕይወት ሳለ ሞትን አልፈራም አለ ይህንንም ብሎ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ነገራቸው። ሒደህ ወደእኛ አምጣቸው አሉት እርሱም ጥቂት ቆዩ እነርሱ ወደእኔ ቤት ይመጣሉ በመጡም ጊዜ በዐይኖቻችሁ ታይዋቸዋላችሁ አላቸው።
ሰይጣንም የከተማ መኳንንቱን ልቡና ለውጦ አከፋ እኒህ አይሁድ ከሰቀሉት ከናዝሬቱ ኢየሱስ ዐሥራ ሁለት ወገኖች ውስጥ ከሆኑ ወዮልን እንድንገድላቸውም ተዘጋጁ አሉ። እኩሌቶቹም ልንገድላቸው አንችልም አምላካቸው ኢየሱስ የሚሹትን ሁሉ እንደሚያደርግላቸው ሰምተናልና ነገር ግን አመንዝራ ሴት ወስደን በከተማው መግቢያ በር ራቁቷን እናስቀምጣት በአዩዋትም ጊዜ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ወደ ከተማችንም አይገቡም አሉ።
እንዲሁም አደረጉ ሴትዮዋንም አራቁተው በከተማው መግቢያ በር ላይ አስቀመጧት። ሐዋርያው ታዴዎስም በአያት ጊዜ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወደ ከተማው ገብተን በከበረ ስምህ እስክንሰብክ ድረስ በራሷ ጠጉር በአየር ላይ ይሰቅላት ዘንድ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን ላክልን አለ። በዚያን ጊዜም ተሰቀለች የከተማዋ ስዎችም አዮዋት ያቺ ሴትም ከከተማዋ መኳንንቶች አቤቱ ፍረድልኝ እያለች ጮኸች ነገር ግን የሐዋርያትን ቃል ወደ መቀበል አልተመለሱም ሰይጣን የሰዎችን ልብ አጽንቷልና ።
ከዚህም በኋላ ወዲያውኑ ተነሥተው ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ ያንጊዜም የመላእክት አለቃ ሚካኤል ወረደና የከተማው ሰዎችን ልቡና የማረኩ መናፍስት ርኩሳንን አስወጥቶ ስደዳቸው ሰዎቹም የሐዋርያትን ትምህርት ተቀበሉ። ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ያን ጊዜም ሐዋርያው ታዴዎስ ያቺን በአየር ላይ የተሰቀለችውን ሴት አወረዳት።
ከዚህ በኋላም ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው ያቺንም ተሰቅላ የነበረች ሴት ለቤተ ክርስቲያን የምትላላክ ዲያቆናዊት አደረጋት። በሐዋርያትም እጆች ብዙ ድንቅና ተአምር ተደረገ ዕውሮች አዩ ሐንካሶችም በትክክል ሔዱ ዲዳዎች ተናገሩ ደንቆሮዎች ሰሙ ለምጻሞች ነጹ አጋንንትም ከሰው እየወጡ ተሰደዱ የከተማው ሰዎችም ሁሉ በጌታችን እስኪያምኑ ሙታን ተነሡ።
ሰይጣንም የከተማው ሰዎች ሁሉም በጌታችን እንዳመኑ በአየ ጊዜ ተቆጣ በአንድ ገንዘብ በሚወድ ጎልማሳ ባለጸጋ ልብ አድሮም በሐዋርያው ታዴዎስ ላይ አነሣሣው ወደርሱም መጥቶ ሰገደለትና እንዲህ አለው የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ እኔ ብዙ ገንዘብ አለኝ እድን ዘንድ ምን ላድርግ አለው። ሐዋርያውም ጎልማሳውን ፈጣሪህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹም ኃይልህ ውደደው አትግደል አትስረቅ አታመንዝር በአንተ ሊያደርጉብህ የማትሻውን በሌላው ላይ አታድርግ ደግሞም ገንዘብህን ሸጠህ ለድኆችና ለምስኪኖች ስጥ በሰማያትም ለዘላለም የሚኖር ድልብ ታገኛለህ አለው።
ይህንንም በሰማ ጊዜ ቁጣን ተመልቶ ሐዋርያው ታዴዎስን ይገድለው ዘንድ አነቀው። የእግዚአብሔርም ኃይል ከዚህ ሐዋርያ ጋር ባይኖር ኖሮ ከመታነቁ ጽናት የተነሣ ዐይኖቹ ተመዝዘው በወጡ ነበር። አባት ጴጥሮስም የክርስቶስን ሐዋርያ እንዴት ደፍረህ ታንቃለህ አለው ያን ጊዜም ተወው ሐዋርያው ታዴዎስም ጌታችን እንዳንተ ላለው ሀብታም ባለጸጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ገመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ብሎ በእውነት ተናገረ አለው።
ጐልማሳው ባለጸጋም ይህ ነገር ትክክል አይደለም እንዴት ሊሆን ይችላል አለ። በዚያን ጊዜም በዚያ ጐዳና ሊያልፍ ባለ ገመል መጣ ሐዋርያው ታዴዎስም ጠርቶ አስቆመውና መርፌ ከሚሸጥ ዘንድ መርፌን ፈለገ። መርፌ የሚሸጠው ግን ሐዋርያውን ሊረዳው ፈልጎ ቀዳዳው ሰፊ የሆነ መርፌ አመጣለት ሐዋርያውም እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ ነገር ግን በዚች አገር የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥ ዘንድ ቀዳዳው ጠባብ የሆነ መርፌ አምጣልን አለው።
.ከዚህ በኋላ ባለ መርፌው ቀዳዳው ጠባብ የሆነውን መርፌ ባቀረበለት ጊዜ ኃይልህን ግለጥ ብሎ ወደ ጌታችን ጸለየ እጁንም ዘርግቶ ባለ ገመሉን ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አንተ ከገመልህ ጋራ በመርፌ ቀዳዳ ውስጥ ግባና እለፍ አለው ገብቶም አለፈ ሕዝቡ የፈጣሪያችን የክርስቶስን ኃይል ይረዱ ዘንድ ዳግመኛ ገብተህ እለፍ አለው ባለ ገመሉም በመርፌው ቀዳዳ ሦስት ጊዜ ከገመሉ ጋራ አልፎ ሔደ።
ሕዝቡም አይተው ከቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም እያሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ። ያም ጐልማሳ ባለጸጋ መጥቶ ከሐዋርያው እግር በታች ወድቆ ሰገደና ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር በለኝ ገንዘቤንም ሁሉ ወስደህ ለድኆችና ለምስኪኖች አከፋፍል አለው።
እንደ ለመነውም አደረገለት የሃይማኖትንም ሕግ አስተምሮ የክርስትናን ጥምቀትም አጠመቀው ሥጋውንና ደሙንም አቀበለው ሁሉንም በቀናች ሃይማኖት አጸናቸው። ከዚህ በኋላ ከዚያ ወጣ በሰላምም ሸኙት በብዙ አገሮችም ውስጥ ገብቶ ሰበከ ከአይሁድና ከአረማውያንም መከራ ደረሰበት። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages