ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, August 12, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 27

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ ሃያ ሰባት በዚህች ቀን ቅዱስ አሞን በሰማዕትነት ዐረፈ፣ ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት መስቀል ክብራ ዕረፍቷ ነው፣ የአዳም ልጅ ቅዱስ ሴት ዕረፍቱ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አሞን
ሐምሌ ሃያ ሰባት በዚህች ቀን ቅዱስ አሞን በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ይኸውም ቅዱስ ተርኑጥ ከሚባል አገር የተገኘ ሰማዕት ነው፡፡ ወደ ላይኛው ግብጽ በሄደ ጊዜ የእንዴናው ገዥ ሰማዕታትን ይዞ በጽኑ ሲያሠቃያቸው ተመለከተ፡፡ እርሱም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ የጌታችንን አምላክነት መሰከረ፡፡ መኮንኑም ይዞ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው፡፡ ሥጋውን ሁሉ ሰነጣጥቆ ከጣለው በኋላ ዳግመኛ በትላልቅ ችንካሮች ቸነከረው፡፡ ነገር ግን ጌታችን አጽናንቶ ከቁስሉ ፈውሶ ጤነኛ አደርጎ አስነሣው፡፡
መኮንኑም ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ቅዱስ አሞንን ወደ እስክንድርያ ከተማ ላከው፡፡ በዚያም ሳለ ጌታችን ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራና ገድሉን ለሚጽፍ በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍ ቃልከዳን ከገባለት በኋላ ሰማዕትነቱን በድል እንዲፈጽም ነገረው፡፡
ወዲያውም ይዘው ጽኑ በሆኑ ልዩ ልዩ ሥቃዮች አሠቃዩት፡፡ ጌታችንም ከመከራው እያዳነው ልዩ ልዩ ተአምራትን ስላደረገለት ይህንን ያዩ ብዙዎች ‹‹በቅዱስ አሞን አምላክ አምነናል›› እያሉ በመመስከር ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡ እነርሱም ውስጥ ቲዮጲላ የምትባል ድንግል ነበረች፡፡ እርሷም ወደ መኮንኑ ዘንድ በመሄድ በጌታችን ታመነች፡፡ መኮንኑም እቶን እሳት ውስጥ ከተታት ነገር ግን እሳቱ አላቃጠላትም፡፡ በመጨረሻም ራሷን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀች፡፡
ከዚህም በኋላ አባለ ዘሩንና አካሉን ሁሉ በሰይፍ እየቆረጡ ቅዱስ አሞንን እጅግ ካሠቃዩት በኋላ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነቱ ፍጻሜ ሆነ፡፡ በመንግሥተ ሰማያትም የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት መስቀል ክብራ
በዚህችም ቀን ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት መስቀል ክብራ ዕረፍቷ ነው፡፡ ይኽችም ቅድስት የቅዱስ ላሊበላ ባለቤት ስትሆን የትውልድ ሀገሯ ወሎ ላስታ ቡግና ነው፡፡ የታላቁ ጻድቅ ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላ ሚስት ናት፡፡ ከእርሱም ደገኛውን ይትባረክን ወልዳለች፡፡ ቅዱስ ላሊበላን እና ቅድስት መስቀል ክብራን ሁለቱ እንዲጋቡ ያዘዛቸው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ የሚያንጻቸውውን የሕንጻ ዲዛኖችና ሌሎችንም ብዙ ምሥጢራትን ካሳየውና ወደ ምድር ከመለሰው በኃላ ድጋሚ ተገልጦለት "እንዳንተ የተመረጠች ናት እንደ ልብህም ትሆናለች፣ ሥራዋም ከሥራህ አያንስም እርሷ የተመረጠች የእግዚአብሔር አገልጋይ ናትና" በማለት መልአኩ የቅድስት መስቀል ክብራን ንጽሕናና ቅድስና መስክሮላታል፡፡
ቅዱስ ላሊበላ 11 እጅግ አስደናቂ የሆኑ ፍልፍል ቤተ መቅደሶቹን ከመላእክት ጋር ሲያንጽ ብታየው ልቧ በመንፈሳዊ ተመስጦ ተመልቶ እርሷም እግዚአብሔር ፈቅዶላት አስደናቂውን የአባ ሊባኖስን ቤተመቅደስ ራሷ እንዳነጸችው መጽሐፈ ገድሏና ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ያስረዳል፡፡
ቅድስት መስቀል ክብራን ወደ ትግራይ እየመራ የወሰዳት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ እርሷን በትግራይ ቅዱስ ሚካኤል እንዲጠብቃት ከተዋት በኃላ ቅዱስ ላሊበላን ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ መንግሥተ ሰማያት አውጥቶታል፡፡
ቅድስት መስቀል ክብራም በትግራይ ሆና መልአኩ እየጠበቃት ከሰው ተለይታ በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ በቀን እልፍ እልፍ እየሰገደች በታላቅ ተጋድሎ ስትኖር ጌታችን ተገልጦ ክብሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ጋር እኩል መሆኑን ነግሯታል፡፡
ይኽችም ቅድስት ብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽማለች፡፡ ለምሳሌ በመስቀል ጦርነት ጊዜ እስላሞች ከባሕር ማዶ እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በፍቅር እየተቀበለችና እያስተናገደች ሃይማኖትንና ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች ወደ ክርስትና እንደገቡና እንዱጠመቁ አድርጋለች፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሴት
ዳግመኛም በዚህች ቀን የአዳም ልጅ ሴት ዕረፍቱ ነው፡፡ እርሱም ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖረ፡፡ ሔኖስንም ወለደው፡፡ ሔኖስንም ከወለደ በኋላ ሰባት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፡፡ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፡፡ መላ ዕድሜውም ዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሁለት በሆነ ጊዜ በሰላም ዐረፈ፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages