ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, August 12, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 28

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ ሃያ ስምንት በዚህች ቀን የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊልጶስ ዕረፍታቸው ነው፣ ክርስቶስን የሚወዱ የቅዱስ እንድራኒቆስና የሚስቱ የቅድስት አትናስያ መታሰቢያቸው ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊልጶስ (ዘደብረ ሊባኖስ)
ሐምሌ ሃያ ስምንት በዚህች ቀን የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊሊጶስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊሊጶስ፡- በተወለዱ በ15 ዓመታቸው በምናኔ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገቡ፡፡ ከብዙ ጊዜ አገልግሎትም በኋላ በአቡነ ተክለሃይማኖት እጅ መንኩሰው ከእርሳቸውም ዕረፍት በኋላ ሦስተኛ አበምኔት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከተወለዱት የመጀመሪያ ፓትርያርክ ሆነዋል፡፡
አባታቸው ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈቀ ኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው ነበር፡፡ በመጀመሪያ የአቡነ ፊሊጶስን የጽድቅ ሕይወትና ሹመታቸውን በተመለከተ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድልና በራሳቸው በአቡነ ፊሊጶስ ገድል ላይ የተጻፈውን እንመልከት፡- ‹‹ክቡር አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ከዚህ ዓለም ተለይቶ የሚሄድበት ጊዜ ሲደርስ ‹ከአንተ በኋላ አንተን ተክቶ በዙፋንህ የሚቀመጥ ማነው?› አሉት፡፡ እርሱም ‹ብዙ ዘመን አይኖርም እንጂ ኤልሳዕ በእኔ ተተክቶ ይቀመጥ› አለ፡፡ ስለ ፊሊጶስ ግን አላነሳም፣ ኤልሳዕ ካረፈ በኋላ በእርሱ ተተክቶ አባት ይሆን ዘንድ ጌታችን የተሸለመ ፊሊጶስን እንደመረጠው ስም አጠራሩ ለልጅ ልጅ ዘመን እንደሚጸና ያውቅ ነበርና ስለዚህ ‹አልሳዕ በእኔ ተተክቶ አባት ይሁናችሁ› አለ፡፡ ክቡር አባታችንም በታላቅ ክብር ዐረፈ፡፡
አንድ ቀን አንድ ዲያቆን ዐረፈና ሬሳውን ገንዘው አጠቡት፣ ይቀብሩትም ዘንድ አስክሬኑን ይዘው ሲሄዱ በአልጋ ላይ ሳለ አስክሬኑ ተንቀሳቀሰ፡፡ የተሸከሙትም ደንግጠው መሬት ላይ አስቀመጡትና ከመግነዙ ፈቱት፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሦስት ጊዜ ተነፈሰ፡፡ ወንድሞችም ‹ምን እያልክ ነው?፣ ወዴትስ ነበርክ?› አሉት፡፡ ያ የከበረና የተመረጠ ዲያቆንም ‹ክቡር አባታችን ተክለሃይማኖት ‹ኤልሳዕ ወደኔ ይምጣ፣ ፊሊጶስ ስለ እኔ ተሹሞ በወንበሬ ይቀመጥ እርሱ ለብዙዎች አሕዛብ አባት ይሆናልና የክርስቶስንም መንጋ በጽድቅና በቅን ይጠብቃል› ብሎኛል› ብሎ ይህን ተናግሮ ተመልሶ ዐረፈ፡፡ ወንድሞችም ኤልሳዕ እንደልማዱ ጎኑን ሳያሳርፍ በወንበር ላይ እንደተደገፈ በሞት ማረፉን አላወቁም ነበር፡፡››
ወደ ጻድቁ የልጅነት ገድላቸው እንመለስና አቡነ ፊሊጶስ በእግዚአብሔር ተመርጠው የመንፈስ ቅዱስም ማደሪያ ሆነዋልና ገና በሕፃንነታቸው በተወለዱባት ሰላሌ ክፍለ ሀገር ዝማ በምትባል ልዩ ቦታ ውስጥ ሰይጣን በጠንቋይ ላይ አድሮ በነደደ በእሳት ውስጥ በመግባትና የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ በአካባቢው ራሱን ያስመልክ የነበረን ሰይጣን በእሳት ውስጥ እንዳለ በስመ ሥላሴ አማትበውበት አመድ አድርገውታል፡፡ በዚህ በአቡነ ፊሊጶስ ድንቅ ተአምር የጠንቋዩ ቤተሰቦችና የአካባቢው ሰዎችም አምነው ሊጠመቁ ችለዋል፡፡ ይህንንም ያደረገው ገና ሕፃን ሳለ ነው፡፡ መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦለት የትውልድ መንደሩን ትቶ ወደ ግራርያ ሀገር ደብረ አስቦ ሄዶ ቅዱስ ተክለሃይማኖትን እንዲያገኝ በነገረው መሠረት አንድ ቀን ያህል ተጉዞ ተክለሃይማኖትን አገኛቸውና ባርከውት ከመነኮሳት ጋር እንዲያርፍ አደረጉት፡፡ ሦስት ዓመት እነርሱን በመልካም ሥራ ፍጹም ሆኖ ሲያገለግላቸው ከቆየ በኋላ ‹‹ሁሉም በአንድነት አሁን ልብሰ ምንኩስና ይገባዋል›› አሉ፡፡ ቅዱስ አባታችን ተክለሃይማኖትም የምንኩስናን ሥራ የሚያሠራ ቅድስናን ሰጠው፡፡ በሌላም ጊዜ ቅስናን ይቀበል ዘንድ ወደ ጳጳሱ ዘንድ ላኩት፡፡
አቡነ ፊሊጶስ በንጉሥ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግሥት ሥጋቸው አልቆ አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ ሲገረፉ ደማቸው እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያሳደደ ቅዱስና ጻዲቅ አባት ናቸው፡፡ ንጉሥ አምደ ጽዮን በክፉ ጠንቋዮች ምክር ተታሎ ‹‹ያልወለደችህን የአባትህን ሚስት ብታገባ መንግሥትህ ትፀናለች›› ብለው ክፉ ምክርን መክረውት የእንጀራ እናቱን አገባትና ንግሥት አደረጋት፡፡ አቡነ ፊሊጶስም ይህን ሲሰሙ ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡ አክአብንና አልዛቤልን በድፍረት እንደገሠጻቸው እርሳቸውም በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ዘልፈው ገሠጹት፡፡ ወደ ንጉሡም ከመሄዳቸውም በፊት በዚህ ምክንያት ሰማዕት እንደሚሆኑ አውቀውት ነበርና ልጆቻቸውን ተሰናብተውና የሚተካቸውን ሰው ነግረዋቸው ነው የሄዱት፡፡ ንጉሡ አምደ ጽዮንም አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ አስገረፋቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም መሬት ላይ እየተቆረሰ የወደቀውን ሥጋቸውን እያነሱ ለበረከት ወሰዱት፡፡ ደማቸውም እንደ እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያቃጥላቸው ነበር፡፡ 300 አንስራ ውኃ አምጥተው ከደሙ በወጣው እሳት ላይ ቢያፈሱትም የውኃው ብዛት እሳቱን ማጥፋት አልቻለም፡፡ ንጉሡም በፍርሃት ከዙፋኑ ላይ ወርዶ ሸሸ፡፡
የንጉሡ ጭፍሮች ግን በጋለ ማረሻ ጀርባና ግንባራቸውን ደረታቸውንም ተኮሷቸው፡፡ ኃፍረታቸውንም እንዳይሸፍኑ እጆቻቸውን ወደ ኋላ አስረው ራቁታቸውንም በከተማው ሁሉ ሲያዞሯቸው ዋሉ፡፡ ማታም ንጉሡ ‹ታስረው ለኖሩ ኃይለኛ ውሾች ስጡት› ብሎ በማዘዝ ውሾቹ እንዲቦጫጭቋቸው ቢያደርጉም ውሾቹ ግን ከእግራቸው ስር ሰግደዋል፣ እርሳቸውም በእግራቸው ባረኳቸው፡፡ አማካሪዎቹም ንጉሡን ‹‹ከዚህ መነኩሴ ጋር ምን አጨቃጨቀህ በግዞት አርቀህ ስደደው ብለው›› ብለው መክረውት ‹‹እስከ ቆርቆራ አገር አውጥታችሁ ወደ ትግሬ አገር ውሰዱት›› ብሎ አዘዘ፡፡ እርሳቸውም ንጉሡን ከ3 ዓመት በኋላ ትሞታለህ ብለው ትንቢት ነገረውት በወታደሮች ተወሰዱ፡፡
በግርፋት ብዛት የተቆረሰ ሥጋቸው ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ደማቸውም አስረው የሚወስዷቸውን የአንዱን ወታደር አንድ ስውር ዐይኑን ፈወሰለትና ወታደሮቹም አምነው ከእርሳቸው ጋር በዚያው ተሰደው መከራን ተቀብለዋል፡፡ እሳቸው በትግራይ ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ ሲያስተምሩ በትንቢታቸው መሠረትም ንጉሡ ከሦስት ዓመት በኋላ ሞተና ልጁ ነገሠ፡፡ ልጁም አባታችንን ከስደት መለሳቸውና ከተክለሃይማኖት መቃብር ደብረ አስቦ ገቡ፡፡ የነገሠውንም ልጅ አንድ ክፉ ሰው ‹‹ከአንድ በላይ ማግባት ትችላለህ፣ በገና ወቅትም ረቡዕና አርብን መጾም ተገቢ አይደለም›› ብሎ ስለመከረው ጳጳሱን ወደ ሀገራቸው ግብፅ እንዲሰደዱ ሲያደርግ አቡነ ፊሊጶስን ደግሞ ‹‹ረቡዕና አርብን በጠዋት ካልቀደስክ›› ብሎ ወደ ደራ ተሰደው እንዲሄዱ አደረገ፡፡
አባታችን በአጠቃላይ አምስት ጊዜ ተሰደው በትግራይ፣ በደራ፣ በዝዋይ ባሕረ ደሴት፣ በዳሞት ገማስቄ እና በወለቃ በስደት ቆይተዋል፡፡ ጳጳሱን አባ ሰላማን በአቃሊት ቅበረኝ ብለዋቸው በቃሬዛ አድርጎ ከጌርጌሳ ወደ አቃሊት ወሰዷቸው፤ እዚያም ሐምሌ 28 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡ አጽማቸውም ከተቀበረ ከ140 ዓመት በኋላ በመጋቢት 23 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር መጥቶ ዐርፏል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰባት አክሊላት አቀዳጅቷቸዋል፡፡
ስለ አሁኑ ዘመን የአቡነ ፊሊጶስ ትንቢት!፡- በወቅቱ የነበሩት ጳጳስ አባ ያዕቆብ በብዙ ልመናና ምክር አቡነ ፊሊጶስን ጳጳሱ ራሱ የሚለብሰውን የክብር ልብስ አልብሶ በሸዋ አገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው፡፡ ከተሾሙም በኋላ አቡነ ፊሊጶስን ‹ሌሎችን ሹምልን› የሚሉ በርካቶች ሲያስቸግሯቸው እሳቸው የሰጡት ምላሽ ‹‹በሥልጣን ፍለጋ ምክንያት ይህችን የትርህምትና የፅሙናን ቦታ (ደብረ ሊባኖስን) የጨዋታ የተድላ ቦታ እናደርጋታለን›› በማለት በወቅቱ ማንንም አልሾምም ብለው ነበር፡፡ አያይዘውም በዚሁ በሹመት ሽኩቻ ምክንያት ወደፊት የሚፈጠረውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ መነፅርነት አይተውት የሚከተለውን ትንቢት ተናግረዋል፡- ‹‹እውነት እላችኋለሁ በመጨረሻው ዘመን ደጋጎች ሰዎችን ክፉዎችና ተሳዳቢዎች የሚያደርጉ፣ ሐሰተኞችና ዋዛ ፈዛዛ የሚወዱትን ደጋጎች የሚያደርጉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡
በመጨረሻው ዘመን ኃጥአን በጻድቃን ይመሰላሉ፣ ጻድቃንን ኃጢአተኞች ያደርጓቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን እውነተኛዎቹ መምህራን አይሾሙም፣ ኃጢአተኞች መማለጃ ሰጥተው ወሬ እያቀበሉ ይሾማሉ፣ እንደ እባብ ክፉ ነገርን ለማድረግ ፍላፃቸውን ያሾሉ ደጋግ ሰዎችን በነገር ያጠፏቸው ዘንድ በእውነት ንጹሕ የሆኑትን ሰዎች አመፅን በተመላ አንደበታቸው ሹመትን ከመውደድ የተነሣ በቅናት ያጠፏቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን መጻሕፍትን የሚያውቁ አይሾሙም፣ ነገርን የሚያመላልሱና የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቁ ከመኳንንትና ከነገሥታት ዘንድ ሔደው ነገርን የሚሠሩ ሰውን የሚያጣሉ በአመፅ ሹመትን የሚያገኙ ብቻቸውን ይሾማሉ እንጂ ደጋጎች አይሾሙም፡፡ በሚመረጡበትም ጊዜ ከአባታቸው ከሰይጣን ጋር ሆነው ‹እገሌ መጻሕፍትን ያውቃል፣ የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቅ ይሾም› ይላሉ፡፡ ያንጊዜም አመፅ ይበዛል፣ ፍቅርም ትጎድላለች፡፡ ከእኔ በኋላ የሚሆነውን እነሆ ነገርኳችሁ ይህንንም አውቃችሁ በልቡናችሁ ያዙ፡፡››
ጌታችን ለአቡነ ፊሊጶስ የገባላቸው ልዩ ቃልኪዳን፡- ‹‹ገድልህንና ስለ እኔ የታገስከካቸውን መከራዎችህን የጻፈውን ከሁላቸው ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በወርቀ ቀለም ለዘለዓለሙ ስሙን እጽፍልሃለሁ፡፡ ሥጋህ ከተቀበረበት ቦታ ይቅርታዬንና ቸርነቴን አደርጋለሁ፡፡ መቃብርህ የበረከት ቦታ ትሆናለች፡፡››
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የቅዱስ እንድራኒቆስና የሚስቱ የቅድስት አትናስያ
በዚህች ቀን ክርስቶስን የሚወዱ የእንድራኒቆስና የሚስቱ የአትናስያ መታሰቢያቸው ነው። እነርሱም ከአንጾኪያ ከተማ ነበሩ። በወርቅና በብርም የከበሩ ባለጸጎች ነበሩ ከገንዘባቸውም ለድኆችና ለችግረኞች ይሰጡ ነበር።
ከዚህም በኃላ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅን ወለዱ ወንዱን ዮሐንስ ሴቲቱንም ማርያም ብለው ሰየሟቸው ልጆችም አደጉ እንዱራኒቅስና ሚስቱም እንግዳ በመቀበል ለድኆችና ለምስኪኖች በመመጽወት በጎ ሥራን አበዙ እነርሱም መገናኘትን ትተው ሰውነታቸውን በንጽሕና ጠበቁ።
ልጆቻቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆናቸው ጊዜ የሆድ ዝማ በሽታ ታመው በአንዲት ቀንም ሞቱ እንዲራኒቆስም አይቶ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል ፊት ራሱን ጥሎ እንዲህ ብሎ አለቀሰ ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ወጣሁ ወደ እግዚአብሔርም ራቁቴን እሔዳለሁ እርሱም ሰጠ እርሱም ወሰደ የእግዚአብሔር የጌትነቱ ስም የተባረከ ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
እናታቸውም ለሞት እስከምትደርስ እጅግ አዘነች ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ወደ ዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች ከኀዘንዋም ብዛት የተነሳ አንቀላፋች በእንቅልፏም ውስጥ በልጆችሽ ሞተ አታልቅሺ እነርሱ ግን በሰማያት ደስ እያላቸው ናቸው እያለ በመነኰስ አምሳል ሲነግራት አየች። ይህንንም ሰምታ ሒዳ ለባሏ ነገረችው።
ከዚህም በኃላ ይህን ዓለም ይተዉ ዘንድ ተስማሙ ገንዘባቸውንም ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጡ በሌሊትም ወጥተው ወደ እስክንድርያ ከተማ ደረሱ ሚስቱንም በዚያ ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአባ ዳንኤል ዘንድ መነኰሰ። ከዚያም ተመልሶ ሚስቱ አትናስያን ወደ ሴቶች ደናግል ገዳም ወሰዳት በዚያም ተዋት።
ከዐሥራ ሁለት ዓመትም በኃላ እንድራኒቆስ ከቅዱሳት መካናት ይባረክ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ አባ ዳንኤልን ለመነው ፈቀደለትም በመድኃኒታችንም ቸርነት ሚስቱ አትናስያ በወንድ አምሳል በጉዞ ላይ ተገናኘችው ሚስቱ እንደሆነችም አለወቀም እርሷ ግን አወቀችው ነገር ግን ሚስቱ እንደሆነች አልገለጠችለትም።
ወደ ቅዱሳት መካናትም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አባ ዳንኤል በአንድነት ተመለሱ። አባ ዳንኤልም ሚስቱ እንደሆነች በመንፈስ ቅዱስ አውቆ እንድራኒቆስን ባልንጀራ ካደረግኸው ከዚህ መነኰስ ጋራ በአንድ ቦታ ኑሩ እርሱ ቅዱስ ነውና አለው። ዐሥራ ሁለት ዓመትም በአንድነት ኖሩ ማንም የአወቀ አልነበረም።
አባ ዳንኤልም ይጎበኛቸውና ስለ ነፍሳቸው ጥቅም ያስተምራቸው ነበር። ከዚህም በኃላ አትናስያ በታመመች ጊዜ ለእንድራኒቆስ አባታችንን አባ ዳንኤልን ጥራልኝ አለችው ሒዶም ለአባ ዳንኤል እንዲህ ብሎ ነገረው ባልንጀራዬ ታሞ ለመሞት ተቃርቧልና ትጎበኘው ዘንድ ና። በደረሰም ጊዜ በታላቅ ሕመም ላይ አገኛት እርሷም ታቆርበኝ ዘንድ እሻለሁ አለችው ያን ጊዜም ተፋጠነና ሥጋውንና ደሙን አቀበላት ከዚህም በኃላ አረፈች በሚገንዟትም ጊዜ ሴት እንደሆነች አገኙ ዳግመኛም ታሪኳንና ለባሏ የረወቻቸውን ምልክቶች አገኙ።
እንድራኒቆስም በአነበበ ጊዜ እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አወቀ ደንግጦም ልቡ ተሠወረ ፊቱንም እየጻፈ ጮኸ ያለቅስ ጀመረ።ከጥቂት ቀን በኃላም ታመመ አረጋውያንም መጥተው በረከቱን ተቀበሉ ሥጋውንና ደሙንም ተቀበሉ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages