ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 16 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, February 22, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 16

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ዕርገተ ድንግል ማርያም
ይሕች ዕለት እጅጉን ታላቅና ክብርት ናት:: ምክንያቱም የድንግል ማርያም ሥጋዋ ተነስቶ ዐርጐባታልና:: ድንግል እመቤታችን ተነሳች: ዐረገች ስንል እንደ እንግዳ ደርሶ: እንደ ውሃ ፈሶ: ወይም በአጋጣሚ የተደረገ አይደለም:: ጥንቱን በአምላክ ልቡና ታስቦ: ሁዋላም ትንቢት ተነግሮለት ነው::
¤ታሪኩ: ነገሩ: ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር:: ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር::
¤ዓለም ተፈጥሮ: አዳምና ሔዋን ስተው: መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው: በኃዘን ንስሃ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከ5 ቀን ተኩል (5500 ዘመናት) በሁዋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ ጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው::

¤ከአዳም አንስቶ ለ5500 ዓመታት አበው: ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ:: መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት:: ምሳሌም መሰሉላት:: ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት:: "እምርሑቅሰ ርእይዋ: ወተአምኅዋ" እንዲል::
የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ
*ከአዳም በሴት
*ከያሬድ በሔኖክ
*ከኖኅ በሴም
*ከአብርሃም በይስሐቅ
*ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
*ከይሁዳ በእሴይ: በዳዊት: በሰሎሞንና በሕዝቅያስ
ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች::
¤ከሌዊ ደግሞ
በአሮን፦
* አል ዓዛር፤ ፊንሐስ፤ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች::
¤አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በ5,485 ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት: ኃጢአት ሳያገኛት: ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች:: (ኢሳ. 1:9, መኃ. 4:7) "ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ:: (ቅዱስ ቴዎዳጦስ ዘዕንቆራ)

¤ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለ3 ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች:: በቤተ መቅደስም ለ12
ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች: እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት: ሕብስት ሰማያዊ: ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች:: 15 ዓመት በሞላት ጊዜ ጻድቅ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት::
¤በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማሕጸንዋ ጸነሰችው:: ነደ እሳትን ተሸከመችው: ቻለችው:: "ጾርኪ ዘኢይትጸወር: ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ:: (ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ)

¤ወልደ እግዚአብሔርን ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ጸንሳ: እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14) ኤየሱስ " ብላ ስም አውጥታለት በናዝሬት ገሊላ ለ2 ዓመታት ቆዩ::
¤አርዌ ሔሮድስ "እገድላለሁ" ብሎ በተሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም: በላበትና በድካም: በዕንባና በኃዘን ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ከገሊላ እስከ ኢትዮጵያ ተሰዳለች:: ልጇ ጌታችን 5 ዓመት ከ6 ወር ሲሆነው: ለርሷ ለድንግል ደግሞ 21 ዓመት ከ3 ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ::
¤በናዝሬትም ለ24 ዓመታት ከ6 ወራት ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች: ነዳያንን እያሰበች ኑራለች:: እርሷ 45 ዓመት: ልጇ 30 ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምሕርት: ተአምራት ጀመረ:: ለ3ዓመታት ከ3 ወራትም ከዋለበት እየዋለች: ካደረበትም እያደረች ትምሕርቱን ሰማች::
¤የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም መጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች:: አንጀቷ በኃዘን ተቃጠለ:: በነፍሷም ሰይፍ አለፈ:: (ሉቃ. 2:35) ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሳኤውን አየች:: ለ40 ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች::
¤ከልጇ ዕርገት በሁዋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች:: በጽርሐ ጽዮን ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለ15 ዓመታት ኖረች:: በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ: ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል: ሐዋርያትን ስታጽናና: ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች::
¤ዕድሜዋ 64 በደረሰ ጊዜ ጥር 21 ቀን መድሃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ:: ኢየሩሳሌምን ጨነቃት:: አካባቢውም በፈውስ ተሞላ:: በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ:: እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ: ለዘለዓለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ: ክብርና ተአምራት ዐረፈች:: ሞቷ ብዙዎችን አስደንቁአል::
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ:
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ" እንዲል::
¤ከዚህ በሁዋላ መላእክት እየዘመሩ: ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ: በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ:: ይሕንን ሊቃውንት:-
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ:
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ:
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል::
¤በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው) እነርሱን ቀጥቶ እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል:: በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለ205 ቀናት ቆይታለች::
¤ ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ 1 ሱባኤ ጀመሩ:: 2ኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው:: እየዘመሩም በጌቴ ሰማኒ ቀብረዋታል::
¤በ3ኛው ቀን (ነሐሴ 16) እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ ተነስታ ዐርጋለች:: ትንሳኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ: መግነዟን ተቀብሏል:: ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው: እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ::
¤ለ2 ሳምንታት ቆይተው: በዚህች ቀንም ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው:: በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ: ደስታና ምሥጢርንም አዩ:: ጌታ ራሱ ድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው: ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረዘይት ተመልሰዋል::
ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን::
ቅዱስ ጊጋር ሶርያዊ
ይሕ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን የሶርያ መስፍን የነበረ ሲሆን #ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰምቷል:: እመ ብርሃን ለስደት ስትወጣ በመጀመሪያ የሔደችው ወደ ሊባኖስ ተራሮች ነው:: መስፍኑ ጊጋር ነበርና እርሱም የአምላክ እናትነቷን
አምኖ አክብሮ አስተናግዷታል::
ሔሮድስም ይሕንን ሲሰማ ጦር አስከትቶ ወደ ጊጋር ሔደ:: መስፍኑ ጊጋር ሔሮድስን እንደማይችለው ሲረዳ ድንግል ማርያምን ወደ #ግብጽ ሸሽጐ አሸሻት:: ሔሮድስንም ፊት ለፊት ተገናኘው:: ከአቅሙ በላይ ስለነበረም በወታደሮች ተማርኮ ወደ ሔሮድስ ቀረበ::
+እመቤታችንንና ልጇን "አምጣ" ቢለው "አልናገርም" አለው:: በዚህ ምክንያት አካሉን ከብዙ ቆራርጦ ገድሎታል:: በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ስለ እመ አምላክ ፍቅር የተሰዋ የመጀመሪያው ሰው ተብሎ ይታወቃል:: ጌታም ስለ ሃይማኖቱ: ፍቅሩና ሰማዕትነቱ 3 አክሊላትን ሰጥቶታል::=>አምላከ ቅዱሳን ከድንግል እመ ብርሃን ፍቅር: ከጣዕሟ: ከረድኤቷ ያድለን:: የወዳጆቿን (ጊጋርና ጊዮርጊስን) በረከትም ያብዛልን::
ነሐሴ 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም (ፍልሠቷ:
ትንሳኤዋና ዕርገቷ)
2.ቅዱሳን ሐዋርያት
3.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት (ፍልሠቱ)
4.ቅዱስ ጊጋር ሶርያዊ (ሰማዕት)
ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/
ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዳንኤል ጻድቅ
7.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)
ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን::
እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን::
አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ::
አንተና #የመቅደስህ_ታቦት::
ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ::
ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው::
ስለ ባሪያህ ስለ #ዳዊት . . ." (መዝ. 131:7)
ወዳጄ ሆይ! ተነሺ::
ውበቴ ሆይ! ነዪ::
በዓለት: በንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ!
ቃልሽ መልካም: ውበትሽም ያማረ ነውና:
መልክሽን አሳዪኝ::
ድምጽሽንም አሰሚኝ:: (መኃ. 2:13)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages