ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 19

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

ታላቁ ቅዱስ መቃርስ
ታላቁ ቅዱስ መቃርስ መቃሬ "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት: የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::
በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሳቸው አጥምቀዋል::
በተሰደዱባት ሃገርምጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን ቅዱሳን ሐዋርያትን፤ አዕላፍ መላእክትን በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን ዮሐንስን መጥምቁንና ወንጌላዊውን:ጴጥሮስን፤ጳውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::
ታላቁ ቅዱስ መቃርስና መቃርዮስ ከ2 ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት በዚችው ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::
ይህች ዕለት ለአባታችን መቃሬ በዓለ ፍልሠቱ ናት:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ) የኖሩባት ቦታ ናት::
የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው::
በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት (በረከትን ሲሹ) አደረጉት::
ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት::
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ::
ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን" ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው::
መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው:: በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ::
ሕዝቡም በዝማሬና በማሕኅሌት: ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ:: ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል:: ይህ የተደረገው በዚህች ዕለት ነው::
አባታችን ቅዱስ አብርሃም
የሃይማኖት-የደግነት-የምጽዋት-የፍቅር አባት የሆነው አብርሃም ደጉ በዚህች ቀን ይታሠባል:: በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የአብርሃም አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር:: ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር::
በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር:: አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ:: "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ:: መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው::
"እርቦኛል አብላኝ" አለው:: መልስ የለም:: "እሺ አጠጣኝ" አለው:: አሁንም ያው ነው:: "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው:: ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር:: ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ: ጀሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር::
ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል:: ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ:: "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው::
ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው:: ይህ የተደረገው ከ2,000 ዓመታት በፊት በዚህች ቀን ነው:: የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ: የእግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም በመጨረሻው በውሃ: በነፋስ: በእሳትና በፀሐይ ተመራምሮ ፈጣሪውን አግኝቷል::
ቅዱስ ፊንሐስ ካህን
ካህኑ ፊንሐስ የብሉይ ኪዳን ዘመን አገልጋይ: ከነገደ ሌዊ: የሊቀ ካህናቱ የአሮን የልጅ ልጅ ነው:: አባቱም ሊቀ ካህናቱ አልዓዛር ነው:: ፊንሐስ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ ሕጻን የነበረ ሲሆን አድጐ በመጀመሪያ ካህን: አባቱ አልዓዛርና አያቱ አሮን ሲያርፉ ደግሞ ሊቀ ካህንነትን ተሹሟል::
አንድ ቀን በጠንቅ-ዋዩ በበለዓም ክፉ ምክር እሥራኤላውያን ከሞዐብ ሴቶች ጋር በኃጢአት በመሳተፋቸው እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነበር:: ያጠፋቸው ዘንድም መቅሰፍት ተጀምሮ ሳለ ፊንሐስ ወንድና ሴት: በደብተራ ኦሪቱ አንጻር የማይገባውን ሲሠሩ አያቸው::
ለፈጣሪው ቀንቶ በአንድ ጦር ሁለቱንም በአንድ ላይ ጥሏቸዋል:: ያን ጊዜ ጌታ "አስተንፈስካ ለነፍስየ" ብሎታል:: መቅሰፍቱም ተከልክሏል:: በዚህም ምክንያት ካህኑ ፊንሐስ የ300 ዓመት ዕድሜ ተጨምሮለት: እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል:: (ዘኁ. 25:7, መዝ. 105:30)
ለአበው ቅዱሳን የተለመነ አምላክ ለእኛም ይለመነን:: ክብራቸውንም በእኛ ላይ ይሳልብን::
ነሐሴ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (4ኛ ቀን)
2.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ፍልሠቱ)
3.አባታችን ቅዱስ አብርሃም (ጣዖቱን የሰበረበት)
4.ቅዱስ ፊንሐስ ካህን (ወልደ አልዓዛር)
ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም
"እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:- 'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ:: እያበዛሁም አበዛሃለሁ' ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ:: እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በሁዋላ ተስፋውን አገኘ::"
(ዕብ. 6:13)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages