ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 27

 በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::



ነሐሴ 27 በዚህች ቀን ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦርና እናቱ ቅድስት ሣራ መታሰቢያቸው ነው፡፡
የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል በነበረው በገዛ አባቱ እጅግ ተሠቃይቶ ምስክርነቱን የፈጸመው ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር፡- ኅርማኖስ የተባለው ወላጅ አባቱ የክርስቲያኖችን ደም እንደ ውኃ ያፈስ የነበረው የዲዮቅልጥያኖስ ልዩ አማካሪና የሠራዊቱ አለቃ ነበር፡፡ እናቱ ሣራ ግን በክርስቶስ አምና የተጠመቀች ክርስቲያን ነበረች፡፡
እንዲያውም ልጇን ቅዱስ ፊቅጦርን ከመውለዷ በፊት የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዳለበት ሄዳ "እመቤቴ ማርያም ለኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚያሰኘውን ልጅ ስጪኝ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ደስ የማያሰኝ ልጅ ከሆነ ግን ማኅፀኔን ዝጊልኝ" ብላ በጸለየችው ጸሎት ነው ቅዱስ ፊቅጦርን ያገኘችው፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር በዓለም ላይ ያሉ በክርስቶስ ያመኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ በግፍ ያስገድል በነበረበት ወቅት የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ፊቅጦርን ገና 15 ዓመት እንደሆነው ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ "ከፍ ባለ ስልጣን አስቀምጥሃለሁ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና ንብረትም እሰጥሃለሁ፣ በእስክንድርያም ላይ ገዥ አድርጌ እሾምሃለሁ ክርስቶስን ማመንህን ተውና ወደ ቤተ መንግሥቴ ግባ" ቢለውም ቅዱስ ፊቅጦር ግን ብዙ መከራንና ሥቃይን ተቀብሎ ሰማዕት መሆንን መረጠ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ዲዮቅልጥያኖስን "ክርስቶስን በምታፈቅረው ጊዜ አፈቀርኩህ ወደ አንተም መጣሁ፤ ክርስቶስን በጠላኸው ጊዜ ግን እኔም ጠላሁህ፣ ቤትህንም ጠላሁ" ብሎታል፡፡
ከብዙ ጊዜም በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ ቅዱስ ፊቅጦርን በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕረግ አድርጎ ሾመው፡፡ እርሱ ግን ይጾማል ይጸልያል እንጂ በንጉሡ ቤት አይበላ አይጠጣም ነበር፡፡ ዕድሜውም 27 ነበር፡፡ አባቱንም ከጣዖት አምላኪነቱ እንዲመለስ ቢመክረው ሄዶ ለንጉሡ ከሰሰው፡፡ ፊቅጦርም "ለአንተ ለጣዖት አምላኩ አገልጋይ አልሆንም" በማለት በንጉሡ ፊት ትጥቁን ፈቶ ጣለ፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር ወላጅ አባቱ ኅርማኖስ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ የቅርብ እንደራሴና መስፍን ስለነበር ልጁ ፊቅጦርን የንጉሡን ሹመትና ልመና እንዲቀበል ብዙ ሲያግባባው ነበር፤ አባቱም ልጁ በሀሳቡ እንዳልተስማማለት ሲያውቅ ከዲዮቅልጥያኖስ ጋር ተማክሮ ልጁን ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያና ወደ ተለያዩ ሀገሮች በግዞት ተልኮ በዚያም ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈደበት፡፡
ወደ ግብፅም ልከው በዚያ እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ነጥቆ ወስዶ በሰማያት የሰማዕታትን ክብር አሳይቶት ወደ ምድር መለሰው፡፡ ክፉዎቹም በብረት አልጋ አስተኝተው ከሥሩ እሳት አነደደዱበት፡፡ በሌላም ልዩ ልዩ በሆኑ ማሠቃያዎች እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ተገልጦ ፈወሰው፡፡ ወደ እንዴናም አጋዙትና በዚያም ብዙ አሠቃዩት፡፡ ምላሱን ቆረጡት፤ በችንካርም ጎኖቹን በሱት፤ ቁልቁል ሰቅለውም ቸነከሩት፤ በእሳትም ውስጥም ጨመሩት፤ ዐይኖቹን አወጡት፤ እሬትና መራራ ሐሞትንም አጠጡት፡፡ ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት፡፡ ጌታችንም ተገልጦ ካጽናናው በኋላ ፈወሰውና ፍጹም ጤነኛ አደረገው፡፡ ፊቅጦር፣ ፋሲለደስ፣ ቴዎድሮስ በናድልዮስ፣ አውሳብዮስና መቃርዮስ እነዚህ ሰማዕታት በአንድነት በአንድ ዘመን አብረው ኖረው ተሰውተው ሰማዕት የሆኑ የሥጋም ዝምድና ያላቸው የነገሥታት ልጆች ናቸው። ዲዮቅልጥያኖስም የቅዱስ ፊቅጦርን ዐይኑን አስወለቀው፣ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ መጥቶ የዓይኑን ብርሃን መልሶለታል፡፡ ሰማዕቱ በመዝለል ባሕር የሚሻገር እንደ አሞራ የሚመስል ፈረስ ነበረው፡፡ ከዚህም በኋላ ማሠቃየቱ ቢሰለቻቸው ሚያዝያ 27 ቀን አንገቱን ሰይፈው በሰማዕትነት እንዲያርፍ አድርገውታል፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር አንድ የሚነገር ትልቅ ታሪክ አለው፡፡ እርሱም በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ በራእይ ተገልጦ በ8ኛው ሺህ ዘመን በሀገራችን በኢትዮጵያና በግብፅ እንዲሁም በቁስጥንጥንያና በሮም ወደፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ በግልጽ የተናገረ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ስለ ሃይማኖት ቅዱስ ፊቅጦር ያየው ራእይ›› የሚል መጠሪያ ያለው ይህ ራእይ በሀገራችን ጎጃም ደብረ ጽሞና ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
12ቱ አበው ደቂቀ እሥራኤል
👉
እነዚህ አበው የአብርሃምና የይስሐቅ የልጅ ልጆች የያዕቆብ ደግሞ ልጆች ናቸው:: ትውልድ ከአዳም እስከ ቅዱስ ያዕቆብ አንድ ሐረግ ይዞ መጥቶ እዚህ ላይ ሲደርስ ይበተናል:: አባታችን ያዕቆብን እግዚአብሔር ሲባርከው እሥራኤል አለው:: ትርጉሙም "ሕዝበ እግዚአብሔር: ወልድ ዘበኩር (የበኩር ልጅ): ከሃሊ: ነጻሪ (አስተዋይ) እንደ ማለት ነው::
👉
ይህ ቅዱስ አባት ለድንግል ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን: ካህናትን: ነገሥታትንና መሣፍንትን ወልዷል:: ከወንድሙ ኤሳው ጋር ተጣልቶ ወደ ሶርያ በሔደ ጊዜ ከ2ቱ ሚስቶቹ (ልያና ራሔል) 8 ልጆችን: ከ2ቱ የሚስቶቹ ደንገ ጥሮች (ዘለፋና ባላ) 4 ልጆችን: በድምሩ 12 ልጆችን ወልዷል::
👉
ልያ የወለደቻቸው:-
1.ሮቤል
2.ስምዖን
3.ሌዊ
4.ይሁዳ
5.ይሳኮር እና
6.ዛብሎን ይባላሉ::
👉
ራሔል የወለደቻቸው:-
7.ዮሴፍና
8.ብንያም ይባላሉ::
👉
ባላ :- 9.ዳን እና
10.ንፍታሌምን ስትወልድ
👉
ዘለፋ :- ደግሞ
11.ጋድና 12.አሴርን ወልዳለች:: አስራ ሁለቱ ደቂቀ እሥራኤል (ያዕቆብ) ማለት እኒህ ናቸው::
👉
ከ12ቱ በቅድስና ዮሴፍ ከፍ ቢልም እግዚአብሔር ለክህነት ሌዊን: ለመንግስት ደግሞ ይሁዳን መርጧል:: ከእነሱ ዘርም ዓለምን ለማዳን ተወልዷል:: 10ሩ አበው በተለይ በዮሴፍ ላይ ግፍ ሠርተው የነበረ ቢሆንም በኋላ ተጸጽተዋል:: እነሆ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ታስባቸዋለች:: (ዘፍ. ከ28-31)
🌹
" ነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል "
🌹
እሥራኤል ከግብፅ ባርነት ወጥተው ከነዓንን ከወረሱበት ዘመን ጀምረው መሳፍንትና ካህናት ያስተዳድሯቸው ነበር:: በወቅቱ ታዲያ ክህነት ከምስፍና ተስማምቶለት ኤሊ የተባለ ሊቀ ካህናትና ልጆቹ (አፍኒና ፊንሐስ) ያስተዳድሩ ጀመር::
👉
በዘመኑ ደግሞ ማሕጸኗ ተዘግቶባት ዘወትር የምታለቅስ ሐና የሚሏት ደግ ሴት ነበረች:: እግዚአብሔር የእርሷን ጸሎትና የሊቀ ካህናቱን ምርቃት ሰምቷልና ቅዱስ ልጅን ሰጣት:: "ሳሙኤል" አለችው:: "ልመናየን አምላክ ሰማኝ" ማለት ነውና:: ሐና ስዕለቷን ትፈጽም ዘንድ ሳሙኤልን በ3 ዓመቱ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጠችው:: በዚያም ስብሐተ እግዚአብሔርን እየሰማ: ማዕጠንቱን እያሸተተ: ከደብተራ ኦሪቱ ሳይለይ በሞገስ አደገ:: የኤሊ ልጆች (አፍኒና ፊንሐስ) በበደል ላይ በደልን አበዙ::
👉
ወቅቱ የአሁኑን ዘመን ይመስል ነበር:: ሁሉም ሰው ክፋተኛ የሆነበት በመሆኑ እግዚአብሔር ርቆ ስለ ነበር ትንቢትና ራዕይ ብርቅ ነበር:: አምላክ ተቆጥቷልና ሳሙኤልን በሌሊት 3 ጊዜ ጠራው:: ነቢዩም ታጥቆ የፈጣሪውን ቃል ሰማ:: በዚሕም የተነሳ ታቦተ ጽዮን ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ ተማረከች:: ከ34ሺ በላይ ሕዝብ በኢሎፍላውያን አለቀ:: አፍኒና ፊንሐስም ተገደሉ:: ኤሊም ወድቆ ሞተ::
👉
ከዚህች ቀን በኋላ ቅዱስ ሳሙኤል በእሥራኤል ላይ ነቢይና መስፍን ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ ሁሉ እንደሚገባው እየኖረ: የእግዚአብሔርን ለእሥራኤል: የእሥራኤልን ለእግዚአብሔር ሲያደርስ ኑሯል:: ሕዝቡ ንጉሥ በፈለጉ ጊዜ ሳዖልን ቀብቶ አነገሠላቸው:: እርሱ (ሳዖል) እንደ ሕጉ አልሔደምና ፈጣሪ ናቀው::
👉
ሳሙኤል ግን ደግ አባት ነውና ክፋተኛውን (ሳዖልን) ከጌታው ጋር ያስታርቅ ዘንድ ብዙ ደከመ: አለቀሰም:: እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን:- "አትዘን! እንደ ልቤ የሆነ: ፈቃዴን የሚፈጽም ዳዊትን አግኝቸዋለሁና እርሱን በእሥራኤል ላይ አንግሠው" አለው:: ቅዱስ ሳሙኤልም ወደ ቤተ ልሔም ሔዶ: ከእሴይ ልጆችም መርጦ ልበ አምላክ ዳዊትን ቀባው: አነገሠውም::
👉
ቅዱስ ሳሙኤል በተረፈው ዘመኑ ለፈጣሪው እየተገዛ ኑሯል:: ነቢዩ ዘወትር ከእጁ የሽቱ ሙዳይና የቅብዐት እቃ (ቀንድ) አይለይም ነበረ:: እነዚህም የድንግል ማርያም ምሳሌዎች ናቸውና አባ ሕርያቆስ:- "ሙዳየ ዕፍረት ወቀርነ ቅብዕ ዘሳሙኤል" ብሎ አመስግኗታል::
ነቢዩም በወገኖቹ መካከል በዚሕች ቀን አርፏል:: እሥራኤልም አልቅሰውለታል:: ዛሬ ቅዱሱ ነቢይ ለአገልግሎት የተጠራበት ቀን ነው::
🌹
" ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላዕክት "
🌹
👉
ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም:: የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል: ገብርኤል: ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው::
በ3ቱ ሰማያት ካሉት 9ኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው:: መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው:: ለኖኅ መርከብርን ያሳራው: ከጥፋት ውሃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው::
👉
በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው:: ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል:: "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት::
ቸሩ አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ብሎ ይማረን:: ከበረከታቸውም ያድለን::
✍
ነሐሴ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1."12ቱ" ደቂቀ ያዕቆብ (እሥራኤል)
2.ቅዱስ ሳሙኤል ነቢይ (የተጠራበት)
3.ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት
4.ቅዱስ ብንያሚንና እህቱ አውዶከስያ (ሰማዕታት)
5.ቅዱስ ፊቅጦርና እናቱ ሣራ
6.አባ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮዽያ (የተሾሙበት)
"እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገዶች ናቸው:: አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው:: ባረካቸውም:: እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው:: "(ዘፍ. 49:28)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages