ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 3 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 16, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 3አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሦስት በዚህች ቀን በገድል የተጠመደ መስተጋድል የከበረ አባ ስም ዖን ዘዓምድ አረፈ፣ ከመንግሥት ወገን የሆነች ቅድስት ሶፊያ አረፈች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ስም ዖን ዘዓምድ
ነሐሴ ሦስት በዚህች ቀን በገድል የተጠመደ መስተጋድል የከበረ አባ ስምዖን ዘዓምድ አረፈ። ለዚህም ቅዱስ ስድስት ዓመት በሆነው ጊዜ አባቱ የበጎቹ ጠባቂ አደረገው። ወደ ቤተ ክርስቲያንም በመሔድ ሁል ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይሰማ ነበር የእግዚአብሔርም ቸርነት አነሳሥቶት ወደ አንድ ገዳም ሒዶ መነኰሰ ብዙ ዘመናትም በገድል ተጠምዶ ሲጋደልና ሰውነቱን ሲያስጨንቅ ኖረ።
ከዚህም በኋላ ገመዱ ሥጋውን ቆርጦ እስቲገባ ድረስ በወገቡ ላይ ገመድን አሠረ። ሥጋውም ተልቶ ከእርሱ ክፉ ሽታ ይወጣ ነበር ስለ ክፉ ሽታውም መነኰሳቱ አዘኑ ተጸየፉትም ወደ አበ ምኔቱም ተሰብስበው ይህን መነኰስ ስምዖንን ከእኛ ዘንድ ካላወጣኸው አለዚያ አንተን ትተን ወደሌላ እንሔዳለን አሉት እርሱም ምን አደረገ አላቸው እነርሱም ጥራውና አንተ ራስህ እይ አሉት።
ጠርቶትም መጥቶ በፊቱ በቆመ ጊዜ ደም ከመግል ጋራ በእግሮቹ ላይ ሲፈስ አየ አበ ምኔቱንም እጅግ አስጨነቀው። ልብሶቹንም ገልጦ በሥጋው ውስጥ የገባውን ያንን ገመድ አየው አበ ምኔቱም በእርሱ ላይ ተቆጥቶ ይህን ታደርግ ዘንድ እንዴት ደፈርክ አለው በታላቅ ድካምም ያንን ገመድ ከሥጋው ውስጥ አወጡት ቍስሉም እስከሚድን መድኃኒት እያደረጉለት ኃምሳ ቀኖች ያህል ኖረ።
ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱ እንዲህ አለው ልጄ ስምዖን ሆይ እንግዲህስ ወደ ፈለግኸው ቦታ ሒድ ከዚያም ወጥቶ ሔደ በደረቅ ጕድጓድ ውስጥም ገብቶ ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ኖረ።
ከዚህም በኋላ አገልጋዩ ስምዖንን ለምን ሰደድከው አሁንም ፈልገህ መልሰው በፍርድ ቀን እርሱ ከአንተ ይሻላልና ብሎ ሲገሥጸው አበ ምኔቱ ራእይን አየ። አባ ስምዖንንም ከገዳሙ ስለመውጣቱ ገሠጸው።
በነጋም ጊዜ አበ ምኔቱ ራእይን እንዳየ ስለ አባ ስምዖንም እንደገሠጸው ለመነኰሳቱ ነገራቸው ወንድሞችም ደንግጠው እጅግ አዘኑ እስከምታገኙትም ሔዳችሁ በቦታው ሁሉ ፈልጉት አላቸው ሔደውም ፈለጉት ግን አላገኙትም። ከዚህም በኋላ መብራትን አብርተው ወደ ጕድጓድ ውስጥ ገቡ ያለ መብልና መጠጥም ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ተቀምጦ አዩት።
ገመድም አውረዱለትና ከዚያ አወጡት በፊቱም ሰግደው በአንተ ላይ ያደረግነውን በደላችንን ይቅር በለን አሉት እኔንም ስለ አሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ አላቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ገዳማቸው ወሰዱት በብዙ ገድልም ተጠምዶ ሲያገለግል ኖረ።
ከዚህም በኋላ ከዚያ ገዳም በሥውር ወጥቶ ወደ አንዲት ዐለት ቋጥኝ ደረሰ። በእርስዋም ላይ ሳያረፍና ሳይተኛ ስልሳ ቀን ቆመ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ ብዙ ሰዎች ድኅነት እግዚአብሔር እንደ ጠራው ነገረው። ከዚያም ሔዶ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ የሚሆን የድንጋይ ምሰሶ አገኘ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችንም እየፈወሰ ወደርሱ የሚመጡትንም እያስተማረ ዐሥራ ሁለት ዓመት በድንጋይ ምሰሶው ላይ ቆመ።
አባቱም ፍልጎት ነበር ግን ሳያየው ሞተ እናቱ ግን ወሬውን ሰምታ ከብዙ ዘመናት በኋላ ወደርሱ መጣች በድንጋይ ምሰሶውም ላይ ቁሞ አገኘችው አይታውም አለቀሰች ከድንጋይ ምሰሶውም በታች ተኛች። ቅዱስ ስምዖንም ጌታችን በጎ ነገርን ያደርግላት ዘንድ ስለርሷ ለመነ ያን ጊዜም እንደተኛች አረፈችና ከደንጊያው ምሰሶ በታች ቀበሩዋት።
ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ እግሩን መታው ከእግሩ ትል እየወደቀ በአንዲት እግሩ ብዙ ዓመታት ኖረ። ከዚህም በኋላ የሽፍቶች አለቃ ወደርሱ መጥቶ ንስሐ ገባ ጥቂት ቀኖችም ኑሮ አረፈ በጸሎቱም ሕይወትን ወረሰ። ወደርሱ ስለሚመጡ ብዙ ሕዝቦችም የውኃ ጥማት እንዳያስጨንቃቸው ወደ እግዚአብሔር ለምኖ ከድንጋይ ምሰሶው በታች ውኃን አፈለቀላቸው።
ዳግመኛም ወደ ሌላ ምሰሶ ተዛወረ በእርሱም ላይ እየተጋደለ ሠላሳ ዓመት ኖረ። ብዙዎች አረማውያንንና ከሀድያንን ካስተማራቸውና ወደ ፈጠራቸው እግዚአብሔር ከመለሳቸው በኋላ ክብር ይግባውና ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ በሰላምም አርፎ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ።
ከዚህም በኋላ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን እንዳረፈ በሰማ ጊዜ ካህናትን ዲያቆናትንና የአገሩን መኳንንቶች ከእርሱ ጋራ ይዞ የቅዱስ አባ ስምዖን ሥጋው ወዳለበት ደረሰ በታላቅ ክብርም ተሸክመው እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ እስክንድርያ አድርሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ታላቅ ፈውስም ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት ሶፊያ ቡርክትና ደናግል ልጆቿ
በዚችም ቀን ከመንግሥት ወገን የሆነች ሶፍያ አረፈች። ለዚችም ቅድስት ብዙ ሀብትና ብዙ ጥሪት ነበራት ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ፍቅር የክርስቶስን መከራ መስቀል አንሥታ ትሸከም ዘንድ ከሦስት ሴቶች ልጆቿ ጋራ ወደ ሮም ከተማ ሔደች።
ንጉሥ እንድርያሰኖስም ክርስቲያን እንደ ሆነች አውቆ ከልጆቹ ጋራ ወደ አደባባይ አስቀረባትና ስለ ሀገርዋና ስለ ስሟ ጠየቃት እርሷም የሚቀደመው ስሜ ክርስቲያን ነኝ ወላጆቼ ያውጡልኝ ስም ሶፊያ ነው እኔም በኢጣልያ ባለ ብዙ ወገን ነኝ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ፈቃድም ልጆቼን መሥዋዕት አድርጌ ላቀርብ ወደ አገርህ መጣሁ አለችው። ከዚህም በኋላ የከዳተኛው ንጉሥ ሥቃዩ እንዳያስፈራቸው ልጆቿን አበረታቻቸው።
ምስክርነታቸውንም ፈጽመው ከሞቱ በኋላ ገንዛ ከሮሜ ከተማ ውጭ ቀበረቻቸው።
በሦስተኛውም ቀን መታሰቢያቸውን ታደርግ ዘንድ ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ከብዙዎች ከከተማው ሴቶች ጋራ ሔደች እንዲህ ብላም ጸለየች አክሊላትን የተቀዳጃችሁ የምታምሩ ፍጹማት የሆናችሁ ልጆቼ ሆይ እኔንም ከእናንተ ጋራ ውሰዱኝ ይህንንም እንዳለች ወዲያውኑ አረፈች ከልጆቿም ጋር ተቀበረች።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages