ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, August 12, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 2

 እንኩዋን ለቅዱሳት እናቶቻችን አትናስያ እና ኢዮጰራቅስያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ።



እናቶቻችን አትናስያ
የዚህች ቅድስት ሕይወት በብዛት የእግዚአብሔርን ቸርነትና የንስሃን ፍጹምነት የሚያሳይ ነው:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
+ቅድስት አትናስያ ግብፃዊት ስትሆን የነበረችውም መኑፍ በሚባል አውራጃ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ይህ ዘመን "ዘመነ ከዋክብት" ይባል ነበር:: ከቁጥር የበዙ ቅዱሳንም በዘመኑ ነበሩ::
+ቅድስት አትናስያም ከክርስቲያን ወላጆች ተወልዳ: እንደሚገባ አድጋ: ገና በወጣትነቷ ሁለቱም ወላጆቿ ሞቱባት:: ነገር ግን ብዙ ሃብት ትተውላታልና ምን እንደምታደርገው ሃሳብ ሆናት:: መንፈስ ቅዱስ ግን መልካሙን ሕሊና አደላትና አብርሃማዊ ሥራን ለመሥራት ቆረጠች::
+መጀመሪያ አገልጋዮችን አዘጋጀች:: እንደየ ወገኑ ለእንግዶችና ለነዳያን ቤትን ሠራች:: በጐውን እድል መርጣለችና ለብዙ ዓመታት ለነዳያን በማድላት: እንግዶችን በመቀበል ተጠመደች:: በዚህ ሥራዋም እግዚአብሔርንም ሰውንም ደስ አሰኘች::
+ግብሯ እንዲህ ነው:: በሌሊት ጸሎት: በመዓልት ግን እንግዶችን መቀበል: እግር ማጠብ: ማስትናገድ: ማስተኛት: ስንቅ አሰንቆ መስደድ ነው:: በዚህ ግብሯ ከምንም በላይ የወቅቱን ጻድቃን አስደስታለች::
+በዚያው ልክ ግን ዲያብሎስ ተቆጥቶ ይከተላት ጀመር:: በብዙ ጐዳና አልሳካልህ ቢለውም በክፉ ጐረቤቶቿ አማካኝነት ግን ተሳካለት:: የአካባቢዋ ሰወች ወደ እርሷ ተሰብስበው በብዙ ማታለል ከቅድስና ሕይወቷ ፈቀቅ እንድትል አደረጉ::
+እነርሱ መልካም ሥራዋን ያስተዋት በመልክ ቆንጆ ነበረችና ይህንን ተጠቅመው ነው:: "ውበትና ሀብትሽን አታባክኚ" ብለው ከጐዳና አስወጧት:: መጽሐፍ ክፉ ባልንጀርነትን የሚቃወመው ለዛ ነው:: መልካም ክርስቲያን ማለት ባልንጀራውን የሚመርጥ ነው::
+የሚገርመው ያን ያህል እንግዳ ተቀብላበት ያላለቀ ገንዘብ አሁን ግን ተመናመነ:: ክፉዎቹ ምክራቸውን ቀጠሉ:: አካሏን እንድትሸጥ አሳምነው ሴተኛ አዳሪ አደረጉዋት:: ባንዴ ከዚያ የቅድስና ከፍታ ወርዳ አካሏን ለዝሙት የምትሸጥ ሆነች::
+ነገሩን የሰሙ ገዳማውያን ሁሉ አዘኑ: አለቀሱላት:: ይልቁኑ ለእነሱ የእናት ያህል ደግ ነበረችና ከዲያብሎስ ሴራ ሊታደጉዋት ቆረጡ:: ከመካከላቸውም ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ለዚህ ተግባር መረጡ:: እርሱ በአጋንንት ላይ ስልጣን ያለው ሰው ነውና::
+እነርሱ ሱባ዗ ይዘውላት አባ ዮሐንስ ሐጺር ወደ መኑፍ ከተማ ሔደ: ወደ ቤቷም ደረሰ:: ጠባቂዋን አስፈቅዶ ሲገባ ለረከሰው ድርጊት የመጣ ሰው መስሏት ተዘጋጅታ ነበር:: አባ ዮሐንስ ሐጺር ግን አጋንንትን ያርቅ ዘንድ እየዘመረ ገባ::
"እመኒ ሖርኩ ማዕከለ ጽላሎተ ሞት . . . በሞት ጥላ ሥር እንኩዋ ብሔድ አንተ ከኔ ጋር ነሕና ክፉን አልፈራም" እያለ ቀረባት:: (መዝ. 22)
+ፈጠን ብሎ ከጐኗ ተቀምጦ ቅዱሱ ምርር ብሎ አለቀሰ:: አትናስያ ደንግጣ "ምነው?" አለችው:: "የአጋንንት ሠራዊት በራስሽ ላይ ሆነው እየጨፈሩኮ ነው" አላት:: አስከትሎም አጋንንቱን በጸሎቱ ቢያርቅላት በአንዴ ወደ ልቧ ተመለሰች::
+ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው የሠራችውን ሁሉ ማመን አቃታት:: ተስፋም ቆረጠች:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን "ግዴለሽም: ንስሃ ግቢ:: ፈጣሪ ይምርሻል" ብሎ አሳመናት:: "እሺ አባቴ" ብላ ከቀደመው ዘመን ሥርዓት ያለውን አንዱን ቀሚስ ለብሳ: ጫማ ሳትጫማ: ሌላ ልብስ ሳትደርብ: ምንም ነገር ሳትይዝ ከቤት ወጣች::
+ቤቷን አልዘጋችም:: ዘወር ብላ ወደ ሁዋላም አልተመለከተችም:: ቅዱሱን ተከትላ ጉዞ ወደ በርሃ ሆነ:: ያ በእንክብካቤ የኖረ አካል እሾህና እንቅፋት: ብርድና ፀሐይ ጐበኘው:: ሲመሽ እጅግ ደክሟታልና "እረፊ" ብሏት ሊጸልይ ፈቀቅ አለ::
+መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ መላእክት ከሰማይ የብርሃን ዓምድ ዘርግተው አንዲትን ነፍስ በዝማሬ ሲያሳርጉ አየ:: "የማን ነፍስ ትሆን" ብሎ ወደ አትናስያ ሲሔድ መሬት ላይ ዘንበል ብላ ዐርፋ አገኛት:: ቅዱሱም "ጌታ ሆይ! ምነው ለንስሃ እንኩዋ ብታበቃት?" ብሎ አለቀሰ::
+ፈጣሪ ከሰማይ ተናገረ:- "ገና ከቤቷ ተጸጽታ ስትወጣ ነው ይቅር ያልኩዋትና ደስ ይበላችሁ" አለው:: ይህንን የአምላክ ቃል ሁሉም ገዳማውያን ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው:: "ጻድቅ 7 ጊዜ ይወድቃልና: 7 ጊዜ ይነሳል::"
ቅድስት ኢዮጰራቅስያ
=>ይህቺ ቅድስት እናት የ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሰው ስትሆን ወደ ምናኔው የገባችው ገና በ6 ዓመቷ ነው:: አባቷ ገና በልጅነቷ የሞተባት ኢዮዸራቅስያ ከእናቷ ጋር ለሥራ ወደ ግብፅ ገዳማት ይሔዳሉ:: በዚያ ደንግል ጌታችንና እመቤታችንን ሲያገለግሉ ተመልክታ ተደነቀች::
+ምክንያቱን ብትጠይቃቸው ስለ ሰማያዊ ተስፋ ነገሯት:: የሰማችው ነገር ቢመስጣት እዚያው ገዳም ውስጥ መኖርን መረጠች:: እናት ሥራቸውን ሲጨርሱ "እንሂድ" ብትላትም ያቺ የ6 ዓመት ብላቴና "እኔ ከእንግዲህ የክርስቶስና የድንግል እናቱ ንብረት ነኝና የትም አልሔድም" አለቻት::
+እናት የሕጻን ልጇን ነገር ሰምታ "ልጄ! አንቺ ያልፈለግሺው ዓለም ለእኔስ ምን ይሰራልኛል?" ብላ እርሷም እንደ ልጇ ገዳሙ ውስጥ ቀረች:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላም እናት ታማ ዐረፈች:: ቅድስት ኢዮዸራቅስያም ንጹሕ ተጋድሎዋን ቀጠለች::
+ትዕግስት: ትሕትና: ፍቅር: ደግነትና ታዛዥነት በእርሷ ሕይወት ላይ በዝተው መገለጥ ያዙ:: እህል የምትቀምሰው በ7 ቀን አንዴ ብቻ ሆነ:: ለጸሎት ስትቆምም እስከ 40 ቀናት በተመስጦ ትቆይ ነበር:: ያቺ ብላቴና ሰይጣንን ከነ ሠራዊቱ አሳፍራዋለችና ታገላት::
+በዱላና በመጥረቢያ ሳይቀር ይመታት ነበር:: እርሷ ግን ታገሰችው:: እጅግ ብዙ ድውያንን ከመፈወስ ደርሳ ድንቅ ተአምራትን ሠራች:: በዚህች ቀንም ዐርፋ ለክብረ መንግስቱ በቃች:: ድንግል ኢዮጰራቅስያ ለገዳሙ ሞገስ ነበረችና በዕረፍቷ ታላቅ ሐዘን ተደረገ::
የቅዱሳት አንስት አምላክ ከንጽሕናቸው: ትጋታቸውና ማስተዋላቸው በረከትን ይክፈለን::
ነሐሴ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት አትናስያ ቡርክት
2.ቅድስት ኢዮዸራቅስያ ድንግል
3.ቅዱስ ዴሚና ሰማዕት
ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
7.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ:: (1ጢሞ. 1:15)
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages