ስንክሳር ዘወርኀ ጷጉሜ 5 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 23, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ጷጉሜ 5

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ታላቁ አባ በርሶማ 

ታላቁ ገዳማዊ ሰው ቅዱስ በርሶማ ከኋለኛው ዘመን ጻድቃን አንዱ ሲሆን ተወልዶ ያደገውም በግብጽ ምስር(ካይሮ) ውስጥ ነው:: ዘመኑ በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: የታላቁ በርሶማ ወላጆች ክርስቲያኖች ነበሩና ያሳደጉት በሃይማኖትና በምግባር እየኮተኮቱ ነው::

ቅዱሳት መጻሕፍትንም እንዲማር አድርገውት ወጣት በሆነ ጊዜ አንድ ሰሞን ተከታትለው ዐረፉ:: በወቅቱም ስለ ሃብት ክፍፍል ዘመዶቹ ተናገሩት:: ነገር ግን አንድ ጉልበተኛ አጐት ነበረውና ንብረቱን ሁሉ ቀማው:: ቅዱስ በርሶማ በልቡ አሰበ:- "እንዴት ነገ ለሚጠፋ ገንዘብ ፍርድ ቤት እሔዳለሁ?" አለ::

ቀጥሎም ይህችን ዓለም ይተዋት ዘንድ ወሰነ:: ከቤቱም እየዘመረ ወደ በረሃ ገሰገሰ:: "ምንት ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ - ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ካጐደለ ምን ይረባዋል::" (ማቴ. 16:26) እያለም ጉዞውን ቀጠለ:: ልብሱን በመንገድ ለኔ ቢጤዎች ሰጥቶ ራቁቱን በአምስት ኮረብታዎች ውስጥ ተቀመጠ::

በዚያም የቀኑ ሐሩር: የሌሊቱ ቁር (ብርድ) ሲፈራረቅበት ለብዙ ዓመታት ኖረ:: እርሱ ግን ያ ሁሉ መከራ እያለፈበት ደስተኛ ነበር:: ዘወትር የዳዊትን መዝሙር ያለ ማቋረጥ ይዘምራል:: ገድላተ ቅዱሳንን እያነበበ መንፈሳዊ ቅናትን ይቀናል:: ያነበባትንም ነገር በተግባር ይፈጽማል::

ይህ ቅዱስ ስለ ራቁትነቱ እንዳይከፋው ዘወትር ራሱን "በርሶማ ሆይ! ከእውነተኛው ዳኛ ፊት ራቁትህን መቆምህ አይቀርምና የዛሬውን ጊዜአዊ ራቁትነትህን ታገስ" እያለ ይገስጽ ነበር:: እርሱ ለጸሎት ከቆመ የሚቀመጠው ከቀናት በኋላ ነው:: ያለ ዕለተ ሰንበት እህልን አይቀምስም::

ምግቡም የሻገተ እንጀራና ክፍቱን ያደረ ውኃ ነበር:: በእንዲህ ያለ ተጋድሎ እያለ ውዳሴ ከንቱ ስለ በዛበት ሸሽቶ ወደ ምሥር ሔዶ በቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አደረ:: በዚያም እንዳስለመደ ለሠላሳ ዓመታት ተጋደለ::

በቦታው የጉድጓድ ውኃ ነበርና ሁሌ ሌሊት ወደ ውስጥ ሰጥሞ ይጸልይ ነበር:: እንደ ስለት የሚቆራርጠውን ውርጭም ይታገሥ ነበር:: በዚያ አካባቢ ብዙ ሰውና እንስሳትን የፈጀ አንድ ዘንዶ ነበርና በአካባቢው ሰው አያልፍም ነበር::

ታላቁ በርሶማ ግን ወደ ዘንዶው ዋሻ ሔደና ጸለየ:: "ጌታ ሆይ! በስምህ ለሚያምኑ የሰጠሃቸውን ሥልጣን አትንሳኝ?" ብሎ (ማር. 16:18) "በአንበሳና በዘንዶ ላይ ትጫናለህ::" የሚለውን መዝሙር ዘመረ:: (መዝ. 90:13)

ዘንዶውንም "ና ውጣ::" ብሎ አዘዘው:: ወዲያው ወጥቶ ሰገደለት:: የጻድቁ ሰው አገልጋይም ሆነ:: የአካባቢው ሰውም እጅግ ደስ አላቸው:: ብዙ ጊዜም አገልግሏቸዋል:: (በሥዕሉ ላይ የምታዩት እርሱው ነው::)

ታላቁ አባ በርሶማ የሚያርፍበት ቀን በደረሰ ጊዜ ደቀ መዝሙሩን "እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ 'የብርቱ (የእግዚአብሔር) ልጅ' ብሎ ለሚጠራኝ በረድኤት እመጣለታለሁ::" ብሎ: ምላሱን በምላጭ ቆርጦ ጣለውና አሰምቶ ዘመረ::

"እግዚአብሔር ያበርህ ሊተ . . . እግዚአብሔር ያበራልኛል: ያድነኛልም:: ምን ያስፈራኛል::" አለ:: (መዝ. 26:1) ልብ በሉልኝ! የሰው ልጅ ምላስ ከሌለው መዘመርም: መናገርም አይችልም:: ቅዱሳን ግን ሲበቁ ልሳን መንፈሳዊ ይሰጣቸዋል:: ከዚህ በኋላ በትእምርተ መስቀል አማትቦ ዐረፈ::

ፓትርያርኩን አባ ዮሐንስን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳትና የምስር ሹማምንት ገንዘውት ከበረከቱ ተካፈሉ:: ገድሉ እንዳስቀመጠው በዘመኑ ሁሉ ምንጣፍ ላይ ተኝቶ አያውቅም:: "ማዕከለ ሥጋሁ ወምድር ኢገብረ መንጸፈ" እንዲል:: ያረፈውም በ1340 ዓ/ም ነው::

 ቅዱስ አሞጽ ነቢይ 

አሞጽ ማለት "እግዚአብሔር ጽኑዓ ባሕርይ ነው: አንድም እግዚአብሔር ያጸናል::" ማለት ነው:: "ተወዳጅ ሰው" ተብሎም ይተረጐማል:: የነበረው ቅ.ል.ክርስቶስ በስምንት መቶ ዓመት ሲሆን አባቱ ቴና እናቱ ሜስታ ይባላሉ:: ትውልዱም ከነገደ ስምዖን ነው::

በትውፊት ይህ ቅዱስ ነቢይ የነቢዩ ኢሳይያስ አባት ነው የሚሉ ቢኖሩም ሁለቱ አሞጾች የተለያዩ መሆናቸውን ሊቃውንት ይናገራሉ:: ቅዱስ አሞጽ ዘጠኝ ምዕራፎች ባሉት መጽሐፈ ትንቢቱ ስለ ነገረ ድኅነት ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል::

ስለ ሃገራችን ኢትዮጵያም እንዲህ ብሏል:-
"የእሥራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር::"
ቅዱሱ ነቢይ ወገኖቹን አብዝቶ ይገስጻቸው ስለ ነበር ተቆጥተው በዚህች ቀን ገድለውታል::

††† የቅዱሳን አምላክ አዲሱን ዘመን ቅዱሳኑን አብዝተን የምናስብበት ያድርግልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

 ጳጉሜን 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ አባ በርሶማ
2.ቅዱስ አሞጽ ነቢይ
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘምስር
4.አባ መግደር (እግዚአብሔር በጸሎቱ ይማረን)

ወርኀዊ በዓላት (የለም)

"መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል:: ይህንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያሰረክባል:: ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም::" (፪ጢሞ. ፬፥፯)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 
ስንክሳር ዘወርኀ ጷጉሜ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages