ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 16, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 6

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።ነሐሴ ስድስት በዚህች ቀን ጌታችን ሰባት አጋንንትን ከእርሷ ያወጣላት የከበረች ቅድስት መግደላዊት ማርያም አረፈች፣ ከቂሳርያና ከቀጰዶቅያ አገር የከበረች ቅዱስት ኢየሉጣ ምስክር ሁና ሞተች ፣ታላቁ አባት አቡነ ኢዮስያስ መታሰቢያ በዓላቸው ነው
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት መግደላዊት ማርያም
ነሐሴ ስድስት በዚህች ቀን ጌታችን ሰባት አጋንንትን ከእርሷ ያወጣላት የከበረች መግደላዊት ማርያም አረፈች። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስን ተከትላ ያገለገለችው በመከራውም ጊዜ ከባልንጀሮቿ ጋራ የነበረች እስከ ቀበሩትም ድረስ ያልተለየች እናት ነች።
በእሑድ ሰንበትም ገና ጨለማ ሳለ በማለዳ ማርያም ወደ መቃብር ገሥግሣ ሔደች ደንጊያውንም ከመቃብሩ አፍ ተገለባብጦ መልአክም በላዩ ተቀምጦ አየችው ከእርሷም ጋራ ጓደኛዋ ማርያም አለች። መልአኩም እናንተስ አትፍሩ ጌታ ኢየሱስን እንድትሹት አውቃለሁና ግን ከዚህ የለም እነሣለሁ እንዳለ ተነሥቷል አላቸው ።
ለእርሷም ዳግመኛ ተገልጾላት ሒደሽ ለወንድሞቼ እኔ ወደ አባቴ ወደ አባቴታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ እንደማርግ ንገሪያቸው አላት። ወደ ሐዋርያትም መጥታ የመድኃኒታችንን መነሣቱን እንዳየችውና ንገሪ እንዳላትም አበሠረቻቸው።
ከዕርገቱም በኋላ ሐዋርያትን እያገለገለቻቸው ኖረች። በኃምሳኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ ቅዱስ መንፈሴን አሳድራለሁ አለ ብሎ ኢዩኤል ትንቢት እንደ ተናገረ ያንን አጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ከሐዋርያት ጋር ተቀብላለች።
ከዚህም በኋላ ከሐዋርያት ጋራ ወንጌልን ሰበከች ብዙዎች ሴቶችንም የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት መልሳ አስገባቻቸው። ሴቶችን ስለ ማስተማርም ሐዋርያት ዲያቆናዊት አድርገው ሾሟት ከአይሁድም በመገረፍ በመጐሳቈል ብዙ መከራ ደረሰባት። ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም በፍቅር አረፈች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስት ኢየሉጣ ዘቂሳርያ
በዚህች ቀን ከቂሳርያና ከቀጰዶቅያ አገር የከበረች ኢየሉጣ ምስክር ሁና ሞተች። ይቺም ቅድስት ከወላጆቿ ብዙ ገንዘብን ወረሰች ከታጋዮችም አንዱ በግፍ በላይዋ ተነሥቶ ጥሪቷን ሁሉ ወንዶች ሴቶች ባሮቿንም ለዳኛ መማለጃ በመስጠት ነጠቃት።
ይህም ዐመፀኛ እንደምትከሰውና ሐሰቱንም እንደምትገልጥበት በአወቀ ጊዜ ወደ ቂሳርያው ገዢ ሒዶ ክርስቲያን እንደ ሆነች ወነጀላት። በልቧም እንዲህ አለች የዚህ ዓለም ገንዘብ ኃላፊ ጠፊ አይደለምን እነሆ እርሱን ነጠቁኝ የሰማይ ድልብን ገንዘብ ካደረግሁ ማንም ከእኔ ነጥቆ ሊወስድብኝ አይችልም።
ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ቀረበች በፊቱም ቁማ እንዲህ አለች እኔ ክርስቲያዊት ነኝ ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ በፈጠረ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ። መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ ወደ እሳትም ውስጥ እንዲወረውሩዋት አዘዘ ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።
ነገር ግን እሳቱ አልነካትም ምንም ምን አላቃጠላትም ከውኃ ውስጥ እንደሚወጣም ከእሳት ውስጥ አወጧት። ስለ ገንዘቧና ስለ ጥሪቷም የማያልፍ የሰማይ መንግሥትን ወረሰች። ቅዱስ ባስልዮስም ብዙ ወድሷታል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ታላቁ አባት አቡነ ኢዮስያስ
ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቁ አባት አቡነ ኢዮስያስ መታሰቢያ በዓላቸው ነው። ትውልዳቸው ሸዋ ሲሆን የንጉሥ ዓምደ ጽዮን ልጅ ናቸው፡፡ ጥር 6 ቀን ሲወለዱ ቅዱሳን መላእክት ከበዋቸው ታይተዋል፡፡ የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በዓለም ነግሠው መኖርን ንቀው በመመነን በመጀመሪያ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ገቡ፡፡ አቡነ ኢዮስያስ በሐይቅ ገዳም ለ14 ዓመታት በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ በዚያም ብሉይንና ሐዲስን፣ መጽሐፈ መነኮሳትንና መጽሐፈ ሊቃውንትን አጠናቀው ተምረዋል፡፡ በኋላም በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ትግራይ ደብረ በንኮል ገዳም ሄዱ፡፡ በደብረ በንኮልም በታላቅ ተጋድሎ ኖረው በታላቁ አባት በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ መነኮሱ፡፡ ቆብ የተቀበሉት ግን ከአቡነ ተክለሃይማኖት ነው፡፡
አቡነ መድኃኒነ እግዚእም ሰባት ዓመት ከእሳቸው ጋር ካቆዩአቸው በኋላ አቡነ ኢዮስያስን ወንጌልን ዞረው እንዲሰብኩና ገዳም እንዲገድሙ በማዘዝ መርቀው ሸኝተዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢዮስያስም ወደ አዱዋ አውራጃ ዛሬ በስማቸው ወደተጠራው ገዳም ሄደው በቦታው ላይ በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ገዳሙንም ከገደሙት በኋላ በርካታ መነኮሳትን አፍርተዋል፡፡ ጻድቁ ያፈለቁት ጠበል በፈዋሽነቱ የታወቀ ነው፡፡ በየዓመቱ በዕረፍታቸው ዕለት ነሐሴ 6 ቀን ሶሀባ በሚባለው ቦታ ቆመው በጸለዩበት ወንዝ ላይ ዓሣ ከሰማይ ይዘንባል፡፡ ይህ አሁንም ድረስ በየዓመቱ ነሐሴ 6 ቀን በግልጽ እየታየ ይገኛል፡፡
አቡነ ኢዮስያስን ከሃዲያን የሆኑ አረማውያን ቢያስቸግሯቸው ጻድቁም በጸሎት ቢያመለክቱ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ነጭ የንብ መንጋ መጥቶ አረማውያኑን አንጥፍቶላቸዋል፡፡ ጻድቁ በጸሎታቸው አራት ሙታንን በአንድ ጊዜ ከሞት ያስነሡ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በገዳማቸው ውስጥ በበዓላቸው ቀን ገድላቸው ሲነበብ አጋንንት ከሰው ልቡና እንደ ትቢያ በነው ይጠፋሉ፡፡ ጻድቁን እንደ ረድእ ሆኖ የሚያገለግላቸው አንበሳ ነበራቸው፡፡ ወደ ገዳማቸው መጥቶ መካነ ዐፅማቸውን የተሳለመውን እስከ 14 ትውልድ ድረስ እንደሚምርላቸው ጌታችን ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ልጁን በስማቸው የተሰመ ቢኖር የሰይጣንን ፊት ፈጽሞ እንደማያይ ገድላቸው ይናገራል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ነሐሴ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ማርያም መግደላዊት (ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት)
2.ቅድስት ኢየሉጣ ሰማዕት (ዘቂሣርያ)
3.አባ ዊጻ (የታላቁ ሲኖዳ ደቀ መዝሙር)
ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages