ስለ ዝቋላ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ያስተላለፉት መልእክት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, February 24, 2024

ስለ ዝቋላ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ያስተላለፉት መልእክት

 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ/ም የሚጀመረውን ጾመ ነነዌ በማስመልከት ያስተላለፉት አባታዊ ቃለ በረከት

**********


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን
“ ተንሥእ ወሑር ኀበ ነነዌ ሀገር ዐባይ: ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ"(ዮና. ፩*)

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት፤መንፈሳዊ ተልእኮ ተቀብላችሁ በየተሰጣችሁ ጸጋ በተለያየ ስፍራ ሆናችሁ የምታገለግሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤በመንፈስ ቅዱስ ልደት የከበራችሁ ምእመናን ወምእመናት ልጆቻችን በሙሉ፤

ዘመንን በዘመን እየተካ፣ መዓቱን በምሕረት እየመለሰ የሚያኖረን እግዚኣብሔር እንኳን ለ2016 ዓ.ም ጾመ ነነዌ አደረሰን አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን፤በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት የሰው ልጆች በኃጢአት በወደቁ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ የሁሉ አባት በመሆኑ “ተወልዶ ብልጫ፣…የለም” እንዲሉ ከእስራኤል ውጭ ወዳለችው ነነዌ ነቢዩ ዮናስንና ነቢዩ ናሆምን ልኳል።

በበደል ውስጥ ሆነው ቢጸሙም ሆነ ቢጸልዩ ጸሎቱ ድል የሚነሣ መሥዋዕቱም የሚያስምር አይሆንምና ንስሐም ለድሀና አቅም ለሌለው የሚሰበክ ሳይሆን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያደፈ ሁሉ የሚጠራበት የሕይወት መስታወት ነውና የሕይወት ትንሣኤ በሆነው ንስሐ ነነዌን ለማንሣት ዮናስ ወደ ንጉሡና ወደ ሠራዊቱ የንስሐ ሰባኪ ሁኖ ተልኳል።

ነነዌ ከተማዋ አድጎ ልማቷ ቢሰለጥንም እግዚአብሔር ግን የተመለከታት ፈርሳና ተበላሽታ ነበር፡: በፈረሰ ልብ የሚገነቡ ከተሞች የቀን ጉዳይ እንጂ ፍርስራሽ መሆናቸው አይቀሬ ስለሆነ ዛሬ ነነዌ ከታሪክ መዝገብ ላይ ብትሰፍርም በዓይን ግን የምትታይ አይደለችም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነነዌን ጾም ያወጀችው ዓመት ሙሉ የተጣላ በነዚህ ሦስት ቀናት እንዲታረቅ፣ ሲካሰስ የሚኖር ሕዝብም ወደፈጣሪው በንስሐ እንዲመለስ ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ነቢዩን ወደ ነነዌ ሲልከው- “ተነሥተህ ሂድ" ማለቱ በበደል የሳተን በሩቅ ሆኖ መተቸት መንፈሳዊ ተልእኮ ባለመሆኑ ተነሥተን ብንሄድ፣ መንገድ አጋምሰን ወገኖቻችንን ብንፈልግ ሁሉንም ለንስሐ ማብቃት እንደምንችል ሲያስተምረን ነው:: ለመነሣት ስንፍናንና ፍርሃትን ድል መንሣት ያስፈልጋል" ለይቅርታ ስንነሣ ትዕቢትን እናሽንፋለን። ፉክክርን እናርቃለን። ለጋራ ሀገራችን የጋራ መፍትሔ ለጋራ ቤተ ክርስቲያናችን የጋራ መድኃኒትን እናገኛለን።

በሌላ በኩል አምላካችን እግዚአብሔር በደለኛይቱን ከተማ ታላቂቱ ከተማ በማለት ሲጠራት ሕዝቡንም ግራና ቀኙን የማያውቅ በማለት ራርቷል።

እግዚአብሔር አምላክ አክባሪ አዛኝ በደለኛውንም በክብር እንጂ በውርደት የማይጠራ አምላክ ነው። እኛም ይህንን የነነዌን ጾም ስንጾም በአንድ በኩል እንጀራን የተራቡ፣ በሌላ በኩል ሰላም የተራቡ ወገኖች ስለአሉን ወደ እነዚህ ወገኖች የንስሐን ስብከት የማጽናናትን መልእክት ይዘን መሄድ አለብን" በተጨማሪም ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን፣ በረሃብ፣ በመታረዝ፣ በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን የመከራ ማቅ በሕሊናችን ተሸክመን ስለጾሙ የተውነው የዕለት ቊርሳችንን ለእነርሱ ሞትን ማባረሪያ እንዲሆን ልንፈቅድ ያስፈልጋል።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! ይህንን የነነዌ ጾም ልንቀበል ዋዜማ ላይ ባለንበት በዚህ ጊዜ በቤተክርስቲያናችን ጥንታዊ ከሆኑት ገዳማት አንዱ በሆነው በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የሚገኙ፣ ዓለሙን ትተው በፈቃዳቸው ረሀብተኛ እና ጥማተኛ ሆነው ሀገርን በጸሎት የሚጠብቁ መነኮሳት ጫካው መኖሪያችሁ፣ ዳዋው ልብሳችሁ፣ ቅጠሉ ምግባችሁ መሆን አይችልም ተብለው የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎንጭተዋል፡፡ እነርሱ በሥጋ እየሞቱ እኛም በየቀኑ ሟቾችን እየቆጠርን በኀዘን ለመኖር የተፈረደብን ሆነናል፡

ይህ ለእነርሱ ክብር ቢሆንም ለቤተክርስቲያን ግን ታላቅ ደወል ያሰማ ክስተት ነውና ውሉደ ክህነት ቤተክርስቲያናችሁን የምትጠብቁበት፣ የመከራውን ማዕበል ለማለፍ በመንፈሳዊ ፍቅር አንድነትን ማጽናት የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን እናሳስባለን።
1
በመረሻም ታላቅ ሀገር ይዘን፣ ምድሩ ሳይጠበን አመል እያጋፋን ነውና ጾማችን፣ጸሎታችን ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ለሀገር ደኅንነት፣ ለሕዝብ ድኅነት እንዲያመጣልንእግዚአብሔር ይቅር ብሎን ዘመኑን በምሕረት ያሻግረን ዘንድ በታላቅ ንስሐ፣ በጸሎትና በአስተብቍዖት ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ አባታዊ መልእክታችንን በመሐሪው አምላክ ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ !
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን"

አባ ማትያስ
ቀዳማዊ ፓትርያርክርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages