መካነ-ነገስት ግምጃ ቤት ማርያም ዘጎንደር ማን ናት? - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, May 24, 2020

መካነ-ነገስት ግምጃ ቤት ማርያም ዘጎንደር ማን ናት?


በ1650 ዓ/ም በአፄ ፋሲል የታነፀችዉ
መካነ-ነገስት ግምጃ ቤት ማርያም ዘጎንደር ማን ናት?

መካነ ነገስት ግምጃ ቤት ማርያም ቤ/ክ የምsትገኘዉ በጥንታዊቷ መዲና:የነገስታት መናገሻ ፤የሊቃውንት መፍለቂያ እና የባህል ጎተራ በሆነችዉ ጎንደር በአፄ ፋሲል ቤተ መንግስት ቅጽር ዉስጥ ነዉ፡፡ምንም አንኳን አሁን በአጥር ብትከለልም ደብሯ በአፄ ፋሲል በጎንደር ከተተከሉት ከሰባቱ ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም
v  ከፊት አቦ፣ፊት ሚካኤል፣
v  አደባባይ ኢየሱስ፣
v  እልፍኝ ጊዮርጊስ፣
v  መ/መ/መድኃኔዓለም፣
v  አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል አንዷ ናት፡፡
 መካነ ነገስት ግምጃ ቤት ማርያም ብለዉ የሰየሟትም አፄ ፋሲል  እንደሆኑ ታሪክ ያስረዳል፡፡ግምጃ ቤት የሚለዉን ስም ልታገኝ የቻለችዉም ንጉሱ ቤተ ክርስቲያነኗን ከማፃነሳቸዉ በፊት አሁን ቤተ ክርስቲያኗ ባለችበት ቦታ ወንበር በር በሚባለዉ በኩል በእንቁላል ግንብ ወደዋናዉ ቤተ መንግስት በሚወስደዉ የንጉሱ የዕቃ ግምጃ ቤት ነበር፡፡በዚህም ሳቢያ ይኼንን ስም ልታገኝ ችላለች፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ በአፄ ፋሲል ጊዜ የሚያገለግሏት 5-ልዑካን የሚባሉት ሲሆኑ በአፄ ኢያሱ ጊዜ ግን እንደማንኛዉም ደብር የሚያገለግሏት ለቤተ መቅደሱ ቄስ፣ዲያቆን፣ ገበዝ፣ ለቅኔ ማኅሌቱ ደግሞ አለቃ፣ መርጌታ፣ቀኝ ጌታ፣ ግራ ጌታ ፣ከመኳንንቱና ወይዛዝርቱ ጋር በአጠቃላይ 199 አገልጋዮች ተወስኖ ተሰጥቷትም ነበር፡፡
   ይኸች ጥናታዊት ደብር የመጀመሪያዉ አራቱ ጉባኤ የተተከለባት ስትሆን( በነገራችን ላይ አራቱ ጉባኤ ስንል መጽሐፈ ሊቃዉንት፣መጽሐፈ መነኮሳት፣መጽሐፈ ብሉያት፣መጽሐፈ ሐዲሳት ማለታችን ነዉ፡፡) አራቱ ጉባኤ ትምህርት በተለያዩ አባቶች ሲሰጥ ቆይቶ በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት አፄዉ እራሳቸዉ እንዲህ አይነቱ ትምህርት በአንድ ቦታ ብቻ መሰጠት የለበትም በማለት መጽሐፈ ብሉያት በአብየ እግዚእ ኪዳነ ምህረት፣መጽሐፈ ሐዲሳት በመካነ ነገስትግምጃ ቤት ማርያም፣ መጽሐፈ ሊቃዉንት በመ/መ/መድኃኔዓለም፣ መጽሐፈ መነኮሳት በሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምህረት(በለሳቱ ምኢት)ትምህርቱ እንዲሰጥ አዘዉ ለጉባኤዉ በጀት በጅተዉ  ደልደለዉታል፡፡እናም አሁን እርሳቸዉ በደለደሉት መሰረት በቤተ ክርስቲያኗ ያሉት መምህር መጋቤ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ( ብቸኛዉ የአራቱ ጉባኤ መምህር) ምንም እንኳን በአራቱ ጉባኤ የተካኑ ቢሆኑም በንጉሱ እንደተመደበዉ ከመጽሐፈ ሐዲሳት በተጨማሪም የፍትሐ ነገስት ትምህርት በዚሁ ቦታ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ በድርቡሽ መቃጠሏና በተአምር ከቃጠሎ የተረፈችዉ ስዕለ አድህኖ
  በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት በ1881ዓ/ም ድርቡሽ/መሀዲስቶች/ወደ ጎንደር ዘልቀዉ በመግባት አብያተ ክርስቲያንንና የታሪክ መዘክሮችን ባቃጠሉ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ በዉስጧ ከሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት ጋር ተቃጥላለች፡፡ጽላቱን ግን አባቶች አስቀድመዉ ወደ ሌላ ቦታ አሸሽተዉት ነበርና መትረፍ ችሏል፡፡መካነ ነገስት ግምጃ ቤት ማርያም ቤ/ክ በተቃተለች ጊዜ ጻድቁ ዮሐንስ ያሳሏት
የእመቤታችን ማርያም ስዕል ግን በታምር ሳትቃጠል ቀርታለች ስዕለ ማርያሟ አሁንም ድረስ ያለች ሲሆን የምትገኘዉም ቤተ መቅደሷ ዉስጥ ነዉ፡፡ይኸችን ተአምረኛ ስዕል በማየትና በመሳለምም የበረከቷ ተቋዳሽ  ይሁኑ፡
  ቤተ ክርስቲያኗ በድርቡሽ በተቃጠለች ጊዜ አፄ ፋሲል የተከሏት ቤተ ክርስቲያን ፈርሳ ስለ ነበር፡፡አባቶች ጽላቱን ይዘዉ በተመለሱ ጊዜ የሳር ሰቀላ ቤት ሰርተዉ ጽላቱን አስቀመጡት፡፡ከዚኽም በኋላ ከዚህ ቤት እንደቆየች አሁን ያለዉን ህንፃ ቤ/ክ በ1936-1939ዓ/ም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና በህዝበ ክርስቲያኑ ንቁ ተሳትፎ ቅድስቱና መቅደሱ ተሰራ ቅኔ ማኅሌቱን ደግሞ እቴጌ መነን እንዳሰሩት አባቶች ይናገራሉ፡፡ቤተ ክርስቲያኗ የታነፀችዉ በድንጋይና ጭቃ ስለነበር በ1985 ዓ/ም በጊዜዉ የነበሩ የሰበካ ጉባኤ አባላትና ካህናት ምዕመናኑን በማስተባበር የአሁኑን ህንፃ ቤ/ክ መልክ እንድትይዝ አድርገዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ በነገስታት ዘመን መቀደሻና ማስቀደሻዉ ግብር በነገስታቱ እየተሰጣት የምትተዳደር ሲሆን ነገስታቱም ለመምህራኑ ቀረጥ እየቀረጡ ከሚያገኙት ሁለት እጅ ይሰጧቸዋል፡፡ይኽም ማር፣ቅቤ፣ቅመማቅመም ሲሆን በዓበይት በዓላት ደግሞ እንደ ልደት፣ትንሣኤ፣ቅ/ዮሐንስ፣ነገስታቱ ፍሪዳ፣ጉንደ-ማር ያበረክቱላቸዉም ነበር፡፡በአሁን ጊዜ ግን ቤተ ክርስቲያኗ በወርሃዊ ገቢዋ ማለትም ምዕመናን በሚሰጡት ገንዘብ ብቻ መምህራኑን፣ካህናቱን፣ዲያቆናቱን፣መዘምራኑን፣በማስተዳደር ቃለ እግዚአብሔርን ሳታጓድል ማስተማሩዋን ቀጥላለች፡፡
በደብሯ በሰማዕትነት የተሰዉ መምህራን አባቶች
   አፄ ፋሲል በጎንደር ቤተ መንግስት ከመሰረቱበትና መካነ ነገስት ግምጃ ቤት ማርያም ብለዉ ሰይመዉ ቤተ ክርስቲያኗን ከተከሉበት ዘመን ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኗ ያስተማሩ መምህራን ምንም ብዙ ቢሆኑም በቃል ጎልቶ ሲነገር እንደሰማነዉ በጽሁፍም ሰፍሮ እንዳገኝነዉ በመ/ነ/ግምጃ ቤት ማርያም በቅርብ ዘመን ተገኝተዉ የሐዲስ ጉባኤ አስፋፍተዉ ያስተማሩ መምህራን
1. መምህር ወ/ሚካኤል ወልደ አብ
                      2 መምህር ተ/ማርያም ቢሠወር
                      3 መምህር ክፍሌ ይመር እና ሌሎችም ናቸዉ፡፡
*      መምህር ወ/ሚካኤል፤-በቀና በኃይማኖታቸዉ በመልካም ምግባራቸዉና በትሩፋታቸዉ ለደቀ መዛሙርቶቻቸዉ መልካም አብነት የሆኑ መንፈሳዊ መምህር ነበሩ፡፡በ1881 ድርቡሽ የጎንደርን አብያተ ክርስቲያናት በሚያጠፋበት ጊዜ መምህር ወ/ሚካኤል በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ዘርግተዉ ያስተምሩ ነበር፡፡ከደቀ መዛሙርታቸዉ ዉስጥ አንዱ ከዚህ ሰቆቃ እንዲሸሹ አጥብቆ ሲወተዉታቸዉ መምህር ወ/ሚካኤል ግን ለደቀ መዛሙራቶቻቸዉ‹‹ ልጆቸ ስጋችሁን የወደዳቹ ሂዱ ሽሹ ነፍሳችሁን የወደዳቹ ግን ከእኔ ጋር ቆዩ አሏቸዉ፡፡››ደቀ መዛሙርቶቻቸዉም ‹‹አባታችን እርሰዎን ትተን የትም አንሄድም›› ብለዉ መለሱላቸዉ፡፡ሁሉም በአንድ ሀሳብ ተስማምተዉ ቤተ-ክርስቲያኗ ወስጥ ፀንተዉ ቆዩ ድንገት ግን ጠላት ድርቡሽ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጽር ዉስጥ ዘልቆ ገባ መ/ወ/ሚካኤል ከደቀ መዛሙርቶቻቸዉ ጋር ወንጌላቸዉን እንደያዙ ጠላትም ሰይፉን እንደያዘ  ‹‹በእምነትህን ለዉጥ ››አለዉጥም ተፋጠጡ በዚህ ፍጥጫ መሃል ከጠላት ወገን አንድ ድምጽ ተሰማ‹‹ፊሳ ቢላ››የሚል.. እኒህ ታላቅ አባት ግን ወንጌላቸዉን ከፍ በማድረግ ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ ››ሲሉ ተናገሩ ደቀ መዛሙረቱም ይኼንን ቃል አስተጋቡ በዚህ ጊዜ የጠላት ሰይፍ በእነዚህ ቅዱሳን አባቶች ላይ አረፈ ደማቸዉም እንደጎርፍ ፈሰሰ እምነታቸዉንም ጠብቀዉ በሰማዕትነት አረፉ፡፡መምህር ወ/ሚካኤል ከደቀ መዛሙርቶቻቸዉ ጋር እንደ በግ በታረዱ ጊዜ ለጊዜዉ ቀባሪ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ምክንያቱም የሽብርና የመከራ ጊዜ በመሆኑ የከተማዋ ሰዉ ከፊሉ ተገድሎ ከፊሉ ሸሽቶና ተማርኮ ከተማዋ ባዶዋን ስለቀረች  እንደወደቁ ሰንብተዋል፡፡አሞራም ሆነ አዉሬ እንዳይነካቸዉ እግዚአብሔር በጥበቡ ሲጠብቃቸዉ ሰንብቶ ድርቡሽ ከተማዋን ለቆ ሲወጣ ከሽሽት የተመለሱ አንድ ሰዉ ከተማዋን ለማየት ሲዘዋወሩ በመ/ነ/ግምጃ ቤት ማርያም የእነዚህን ቅዱሳን ሬሳ ተጋድሞ አገኙት በአካባቢዉ የነበረዉ ሽታም እንደ መልካም ጽጌረዳ ሽታ ሆኖ ያዉድ ነበር፡፡ከዚህም በኋላ ሰዉየዉ እጅግ ደንግጠዉና አዝነዉ ተጨማሪ ሰዉ ጠርተዉ አንስተዉ በክብር ቀብረዋቸዉል፡፡የእነዚህ ቅዱሳን አባቶች መቃብራቸዉ በቤ/ኗ በላይኛዉ በር መግቢያ ላይ ይገኛል፡፡በቀጣይ ጊዜ በመካነ ነገስት ግምጃ ቤት ማርያም ያስተምሩ ስለነበሩ መምህራን፤ በአሁኑ ሰዓት እያስተማሩ ስለሚገኙት ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ ሕይወት እና ጉባኤ ቤት እንቅስቃሴ እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች እናቀርባለን ፡፡ይቆየን!!
የፈጣሪችን ረድኤት በረከት
የእመቤታችን አማላጅነት
የእነዚህ ቅዱሳን ጸሎት  ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages