ጩጊ ማርያም ገዳም ታሪክ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, June 28, 2020

ጩጊ ማርያም ገዳም ታሪክ

የጩጊ ማርያም ገዳም ታሪክ
     
የጩጊ ማርያም አንድነት ገዳም ሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት በወገራ ወረዳ ከሚገኙ ገዳማት አንዱ ነው፡፡ገዳሙ ከጎንደር ከተማ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ኮሶዬ ከተማ ሲደርሱ ሶስት ሰአት የእግር መንገድ እንደተጓዙ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡
የጩጊ ማርያም ገዳም በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሰረተ ጥንታዊ ገዳም ሲሆን የመሰረቱትም አባ ምእመነ ድንግል የተባሉ ጻድቅ ናቸው፡፡ገዳሙም ጻድቁ የጸለዩበት እና ከጌታችን ከመድሃኒታች ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ቅዱስ ቦታ ነው፡፡
የአባ ምእመነ ድንግል ታሪክ
አባ ምእመነ ድንግል የተወለዱት በወገራ አውራጃ ሲሆን ገና በህፃንነታቸው በእናት በአባታቸው ቤት እያሉ ጀምሮ መንፈሳዊ ትሩፋቶችን በመስራት በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ምእመነ ድንግል የምንኩስና ልብስና የእግዚአብሔር ጸጋ በመፈለግ አዳጋት ማርያም ወደ ምትባል ገዳም በመሄድ ብዙ ተጋድለዋል፡፡ ከዚያም ወደ ዋልድባ ገዳም በመሄድ ብዙ ተጋድለዋል፤ጽናታችውን ያዩ የዋልድባ ገዳም መነኮሳት አባትና መምህር እንዲሆኗቸው ቢጠይቋቸው እራሳቸውን ዝቅ በማድረግ “እኔ መምህርና አባት ልሆን አይገባኝም ” በማለት እንቢ ቢሉም መነኮሳቱ አበምኔት አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ አባታችንም በተሾሙበት በዚህ ገዳም በከፍተኛ ተጋድሎና በእግዚአብሔር ጸጋ ብዙ መንፈሳዊ መነኮሳትንና መምህራንን በትምህርታቸው አፍርተዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በጊዚው በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት በሃይማኖት ምክንያት በርካታ ቅዱሳን መነኮሳት ሰማዕትነትን እየተቀበሉ ስለነበረ እሳቸውም ስለ ትክክለኛይቱ ሃይማኖት መስክረው ሰማዕትነትን ሊቀበሉ ሲመጡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ጊዜህ ገና ነው፤የተዋሕዶ ሃይማኖት መመለሷን ሳታይ ሰማዕትነትን አትቀበልም” ብሏቸው አሁን በስማቸው በሚጠራው ተራራ ዋሻ ፈልፍለው እንዲጸልዩና እንዲያስተምሩ እስከመቼም ቢሆን በረድኤት እንደማይለያቸው አስረድቷቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ዋሻው ውስጥ እያሉ የኢትዮጰያን ቤተክርስቲያንና ሃይማኖት ለማጥፋት ያቀደ አረመኔ ካቶሊክ ፈረንጅ መጥቶ፤“ክርስቶስን አንድ አካል ሁለት ባሕርይ” ብላችሁ እመኑ እያለና ሕዝቡን እየጨፈጨፈ በሚያስቸግርበት ጊዜ በመቃወም “ክርስቲያን ሁሉ በአበው ሃይማኖት ጽኑ፣እግዚአብሔር በአካል ሦስት በመለኮት፣በአገዛዝ፣በሥልጣን፣ … አንድ ነው እንጂ ከዚህ ውጭ አይደለም፤ በሃይማኖታችሁ ጽኑ” እያሉ ቀን ከሠራዊቱ ጋር እንደሠራዊት እያስተማሩ፣ ያመኑትን እያጠመቁ፣ ቀድሰው ሥጋወደሙን እያቀበሉ፣ በትግሃ ሌሊት በጸሎትና በስግደት የክርስቶስን መከራ በማሰብ ፊታቸውን እየጸፋ በከፍተኛ ተጋድሎ የሃይማኖትን መንገድ በፋናቸው አሳይተዋል (ኤፌ. 4÷5-6)፡፡ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ እያሉም አስተምረዋል፡፡
በዚያን ዘመን ዐፄ ሱስንዮስ ነግሠው በነበሩበት ወቅት ከፖርቹጋል ጋር ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ይህንንም ግንኙነታቸውን ለማዳበርና ለማጠናከር የፖርቹጋል ሴት እንዲያጩ ተገደዱ፤ ዐፄ ሱስንዮስ በዚህ ምክንያት ሃይማኖታቸውን ለውጠው ሲኖሩ በገዳማት የሚኖሩ መነኮሳትና በኢትዮጰያ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት የሚኖሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን ስለተቃወሟቸው መነኮሳት ካሉበት ከበኣታቸው ሊቃውንትን ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና አድባራት እያደኑ ያስፈጇቸው እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ለምሳሌ ከቅዱሳት አንስት እነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን የመሳሰሉ ቅዱሳን በዚያን ጊዜ ነው የተሠውት፡፡
በዚህን ጊዜ ጻድቁ አባ ምእመነ ድንግል ከ40 ልጆቻቸውና ደቀመዛሙርቶቻቸው ጋር ጩጊ ቅድስት ማርያም ገዳምን ጥግ ከለላ አድርገው መኖር ጀመሩ፡፡ በዚህም ቦታ ዋሻ ፈልፍለው በጸሎትና በተጋድሎ በሚኖሩበት ወቅት የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ ምስጋና የባህርይ ገንዘቡ የሆነ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ በታላቅ ቦታ እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክትን፣ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን እና ቅዱሳን አበውን፣ አስከትሎ “ወዳጄ የአባቴ ወዳጅ የመንፈስ ቅዱስ ወዳጅ ሰላም ላንተ ይሁን” አላቸው፡፡ ጻዲቁ ይህን የመሰለ ብርሃንና ልዩ ንውጽውጽታ በማየት ተደንቀው አምላካቸውን እጅ ነስተው (ሰግደው) ለእመቤታችን ለቅድስት ማርያም ሰግደውና እጅ ነስተው ድንቅ ነገር በማየታቸው በሚደሰቱበት ጊዜ ጌታችን በእጅ አንሥቶ አቅፎ ስሟቸው የሚከተለውን ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
“በዚህ ቦታ አንተ በተጋደልክበት ማኀበር መሥርቶ የሚኖረውንና የሚማፀነውን ሁሉ አኗኗኑ እንደ ሰማይ መላእክት ይሆንለታል፡፡ ወደዚህ ቦታ ሥጋዬንና ደሜን አምኖ የተቀበለውን ከቅዱሳን መላእክት ጋር በአባቴ ክብር በመምጣበት ጊዜ ፍጹም ገሃነመ እሳትን አላሳየውም፡፡ ምንም ኃጥያት ቢሠራ አምላከ ምዕመነ ድንግል ይምረኛል ብሎ በፍጹም እምነት የመጣውን ወደ ተወለድኩባት ቤተልሔም፣ ወደ አደኩባት ናዝሬት፣ ወደ አስተማርኩባት ደብረዘይት፣ ወደተጠመኩባት ዮርዳኖስ እና ወደተሰቀልኩበት ቀራንዮ እንደሄደ እቆጥርለታለሁ” በማለት ይህን አማናዊ ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኋላ ካሉበት ከበኣታቸው በስተቀኝ በኩል የኪዳነ ምሕረትን ጸበል በስተግራ የዮርዳኖስ ጸበል አፍልቆላቸዋል፡፡(ገላ.3÷15-18)
ታላቁ ጻድቅ አቡነ ምእመነ ድንግል ይህን ቃልኪዳን በተቀበሉበት በዚህ ቅዱስ ሥፍራቸው ተጋደሎአቸውን በበለጠ ሲጋደሉ “ፈዋሴ ድውያን” ተብለዋል፡፡ ይኽውም ዐፄ ሱስንዮስ ሃይማኖታቸውን ወደ ካቶሊክ ለውጠው እንዲሁም “የሃገሪቷ ሃይማኖት እንዲለወጥ” በማለታቸው ምክንያት 140 ሺህ ቅዱሳን አባቶች ይህን ተቃውመው መስቀል እንደጨበጡ ስለሃይማኖታቸው በሰማዕትነት ሲጋደሉ ንጉሡ በቅዱሳኑ ላይ ባደረሱት ጭቃኔ የተሞላበት ጥፋት ምላሳቸው ተጎልጉሎ ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜም በጣም ደግና ብልህ የነበሩት ልጃቸው ዐፄ ፋሲል ስለ አባታቸው መዳን በጣም ተጨንቀው መፍትሔ ለማግኘት የሚነግራቸው ብቁ ሰው ሲያፈላልጉ አንድ የበቁ አባት ከሞት የተረፉ፣ ከጥላ ያረፉ፣ በዕድሜ የገፉ፣ ግዝቱን ለመፍታት የማይችሉ ፣ አንድም ወለቴ የተባለችው አገልጋያቸውና የአቡነ ምእመነ ድንግል ክብር እንዲገለጽ የተረዱ ታላቅ ባሕታዊ ተገኙና “ከዚያው ከቤትህ ከሴት ሠራተኛ አገልጋዮችህ ውስጥ አንዲት የበቃች አለችና እርሷ መፍትሄውን ትነግርሃለች” ብለው አመላከቷቸው፡፡
ይህችውም ወለቴ የተባለች ስትሆን ከብቃቷ የተነሳ በክንፍ እንደ መላእክት እየበረረች ስትሄድ ያያት ሁሉ “አሞርዬ” ይሏታል፡፡ እሷም እስከ ዛሬ ድረስ በሕቡዕ ተሰውራ ትኖራለች፡፡ የመጸለያ በኣቷ እና ገዳሟ ባሕርዳር ዙርያ አዴት አካባቢ አዳማ ጊዮርጊስ አጠገብ ነው፡፡
ዐፄ ፋሲልም በየበሩ ወታደሮችን አሰልፈው ሲያስጠብቁ ይህችው አገልጋይ በጸሎት አድራ ስትመለስ አግኝታው ይዘው አቀረቧት፤ በዚህ ጊዜ በብዙ ማግባባት ቢጠይቋት ምንም እንደማታውቅ ተራ ኃጢያተኛ እንደሆነች ገለጠችላቸው፡፡ ሆኖም በብዙ ልመና ሲማጸኗት “ድንግል መነኩሴ ቢገኝ አባታቸውን እንደሚፈውስላቸውና ዐፄ ፋሲልም እንደሚነግሡ” ነገረቻቸው፡፡
ዐፄ ፋሲልም “ድንግል መነኩሴ ፈልጎ ላመጣልኝ እሸልማለሁ” ብለው አወጁ፡፡ አቡነ ምእመነ ድንግል ባሉበት አካባቢ የሚኖሩ ይጉይታና ባጅር የሚባሉ ባላባቶች ውሾቻቸውን አስቀድመው ሲያፈላልጉ ጻድቁም እንደሚፈለጉ ስለሚያውቁ አርድቶቻቸውን “ሰው ሲመጣ በበሩ እየተመለከታችሁ እንድትነግሩኝ” ብለው ዳዊታቸውን እየደገሙ ሳሉ ረዳታቸው ውሻ አዩና “አባ ውሻ መጣ” አሏቸው፡፡ አባም “እ! ብለው ውሻ መጣ ሰው መጣ፤ ሰው መጣ ነገር መጣ ” ብለው ወደ ባሕር ገቡ፡፡ በገቡም ጊዜ እዚህ ነበር የማይባል ድንጋይ ከውኃው ወደ ላይ ገፍቶ (አንሥቶ) አወጣቸው፡፡ ይህ ድንጋይም በአሁኑ ሰዓት በዚያው ይታያል፡፡ ባላባቶችም “አባ ከዐፄ ፋሲል ተልከን ነው፡፡ ‘የአባቴን ምላስ ግዝቱን ፈቶ የሚመልስ መነኩሴ ካገኘሁ ተዋሕዶ ሃይማኖትን እመልሳለሁ’ ብለው ቃል ስለገቡ ነውና ማስረጃ የንጉሡ ማኅተም ይኸው” ብለው ባሳይዋቸው ጊዜ በደስታ አብረዋቸው በመሄድ ከእነ አባ ዓምደ ሥላሴ ጋር በመጸለይ አዋጅ አስነግረው “ፋሲል ይንገሥ፣ ካቶሊክ ይፍለስ፣ ተዋሕዶ ይመለስ፣ የዐፄ ሱስንዮስ ምላስ ይመለስ፣ እግዚአብሔር ይፍታህ” ሲሉ ተጎልጉሎ የነበረው ምላሳቸው ተመለሰ በዚያን ጊዜ ዐፄ ሱስንዮስ “ብቆይ ዓመት ብበላ ገአት/ገንፎ/” ብለው በመናገር ምላሳችው፤ እንደ ቀድሞው ሆነላቸው፡፡ ዐፄ ሱስንዮስም ለንሰሓ ሞት በቅተው፣ መንግሥታቸውን ለልጃቸውን አውርሰው በክብር አርፈው በታላቁ ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ አፅማቸው ከብዙ ነገሥታት አፅም ጋር ይገኛል፡፡
በዚያን ጊዜ ያች ደገኛ አገልጋይ ጎንደር የዐፄ ግንብ እንደሚሠራ ለዐፄ ፋሲል ትንቢት ተናግራለች፡፡ይህ ቦታ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረና ዛሬም ድረስ ድንቅ ተአምራት እየገለፀበት ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ለግንዛቤ ያህል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
፩) ንጉሡ ዐፄ ፋሲልም የጻድቁን ቦታ ሳይረሱ መንግሥታቸው ከጸናላቸው በኋላ ለገዳሙ ርስት ጉልት ሊሰጡ በተጓዙ ጊዜ ከአፋፍ ቆመው “የት ነው የጻድቁ በዓት?” ሲሉ “ይህ ወይራና ጽድ የበዛበት በፊታችን የምናየው ነው” ሲሏቸው “ይህ ጭው ያለው ዱር ነው?” ሲሉ “አዎ” አሏቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የቦታው ስያሜ “ጩጊ” ለመባል በቃ፡፡ የጻድቁ በኣት መጸለያ ዋሻም በስማቸው “ምእመነ ድንግል” እንደተባለ አለ፡፡ ጻድቁም በሕይወት እንደነ ሄኖክ፣ ኤልያስ፣ ቅዱስ ያሬድ እና አባ ዮሃኒ በህቡእ አሉ፡፡
፪) የጻድቁ መጸለያ ቦታ በተፈጥሮው የተሸነቆረ መስኮት አለው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ መኻን የሆኑ ሁሉ በመስኮቱ ወጥተው ሲመለሱ ማየ ዮርዳኖሱን ጠጥተው ሲሳሉ ልጅ ለማግኘት ይበቃሉ፡፡ ይህን ቃል ኪዳን የሚያውቁ ጳጉሜን በሙሉ በማየ ዮርዳኖሱ በመጠመቅ ትልቅ ሐብተ ፈውስ ያገኛሉ፡፡
፫) የዮርዳኖሱን ጸበል የጠጣ ሲሞት ሥጋው አይፈርስም፣ አይበሰብስም፡፡ እንኳን በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረው ሰው እንስሳቱ እንኳን አካላቸው ሳይፈርስ ይቆያል፡፡ ለማስረጃ ያህል እንኳን 16 የሚሆኑ ፍየሎች አካላቸው ሳይፈርስ 400 ዘመን ያስቆጠሩ አሉ፡፡
፬) በ1968 ዓ.ም. አንድ ዛፍ ከወንዝ ዳር ወድቆ አንድ ገበሬ ለማገዶ ሲፈልጠው እስከነ ምሳሩ ተነሥቶ ቆሞ በሥሩም ሰባት ጸበል ፈልቶ ብዙ ህሙማንን ፈውሰዋል፡፡
፭) ሰኔ 21 ቀን 1988 ዓ.ም. አንድ ዛፍ በእርሻ መካከል ስለወደቀ ለማስወገድ ከሥሩ በእሳት ቢያቃጥሉት ሥሩን ትቶ ከጫፍ እየነደደ ከወደቀበት ተነሥቶ ቆሟል፡፡
፮) በቦታውም ላይ የብዙ ቅዱሳን አፅም ይገኛል፡፡
የመረጃ ምኝጭ፡- ገዳሙ ካዘጋጀው በራሪ ጽሁፍ የተገኝ 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages