ሚያዝያ ፲፭ ግጻዌ(ዐቢይ ጾም/ኒቆድሞስ፮ኛ ቀን) - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 23, 2021

ሚያዝያ ፲፭ ግጻዌ(ዐቢይ ጾም/ኒቆድሞስ፮ኛ ቀን)



ሚያዝያ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
መጥምቁ ዮሐንስ (ጸዓተ ነፍሱ) ፣
ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሀገረ ሜራ (ከ318ቱ ሊቃውንት) ፣
ቅዱስ አጋቦስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)፣ 
ቅድስት እለእስክንድርያ ሰማዕት፣
 አቡነ አቢብ ጻድቅ 
 
ወር በገባ በ፲፭ የሚታሰቡ በዓላት
ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ፣ 
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)፣
ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ፣
 ቅድስት እንባ መሪና፣
 ቅድስት ክርስጢና
ንግሥት ወሰማዕት ቅድስት እለእስክንድርያ፡-


ሚያዝያ 15-ቅዱስ ጊዮርጊስ በተአምራቱ ያሳመናት የከሃዲው ንጉሥ የዱድያኖስ ሚስት እለእስክንድሪያ በሰማዕትነት ዐረፈች፡፡ ይህችውም ቅድስት እለእስክንድርያ የሰማዕታት አለቃ ታላቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ በትምህርቱና በተአምራቱ ያሳመናትና በጌታችን ስም ሰማዕትነትን የተቀበለች የንጉሡ የዱድያኖስ ሚስት ናት፡፡ ከሃዲውና ጣዖት አልምላኪው ባሏ ንጉሥ ዱድያኖስ ከ70 ነገሥታት ጋር ሆኖ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሦስት ጊዜ ገድሎት ጌታችን ከሞት ካስነሣው በኋላ ንጉሡ መልሶ ያባብለው ጀመር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ንጉሡን
ዱድያኖስን ከነጣዖታቱ በሰው ሁሉ ፊት ሊያዋርደው ፈልጎ እንዲህ አለው፡- ‹‹ለጣዖትህ ከሰገድኩና ከሠዋሁለት በመንግሥትህ ሁሉ ሁለተኛ አድርገህ
እንደምትሾመኝ የነገርከኝ ነገር ደስ አሰኝቶኛልና በሰው ሁሉ ፊት ለምታመልከው ለአጵሎን እሰግድ ዘንድ ሕዝቡም ሁሉ ለጣዖትህ ስሠዋ ይመለከቱ ዘንድ እንዲሰበሰቡ በአዋጅ ነገር›› አለው፡፡ ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ የነገረው እውነት መስሎት እጅግ ተደስቶ እስኪነጋ ድረስ ብሎ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ሚስቱ እልፍኝ አስገባው፡፡ የንጉሡም ሚስት እለእስክንርያ
ብቻዋን ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተገናኘች ጊዜ ሰማዕቱ የዳዊትን መዝሙር ሲጸልይ ሰማችው፡፡ ጸሎቱንም ሲጨርስ ይጸልይ ስለነበረው ነገር ጠየቀችው፡፡ ‹‹ክርስቶስ ብለህ የጠራኸ እርሱ ማነው?›› አለችው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ይህን ጊዜ ስለ ጌታችን ለንግሥቲቱ አስተማራት፡፡ ከብሉይና ከሐዲስም መጻሕፍትን እየጠቀሰ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ እነርሱ እስካሉበት ዘመን ድረስ ያለውን የሃይማኖትን ነገር በሚገባ አስተማራት፡፡ ንግሥቲቱም ‹‹በአምላክህ አምኛለሁና ስለ እኔ አምላክህን ለምንልኝ›› አለችው፡፡ ስለ ክፉው ባሏ ስለ ንጉሡ እንዳትፈራ አጽናናትና ሲሰግድ ሲጸልይ አደረ፡፡ በነጋም ጊዜ ነጉሡ አስቀድመው በተነጋገሩት መሠረት መጥቶ ለጣዖቱ እንዲሰግድና እንዲሠዋ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መልዕክት ላከበት፡፡ ንጉሡም ‹‹ገሊላዊው ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነውና ኑ ተመልከቱ›› ብሎ 70ውን ነገሥታትና ሕዝቡን ሁሉ በአዋጅ ሰብስቦ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም አስቀድሞ ፈውሶት የነበረውን አንዱን ሕፃን ጠርቶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሄዶ ጣዖቱን እንዲጠራው ላከው፡፡ ‹‹የማታውቅ ዕውር የሆንክ ዲዳ ደንቆሮ አጵሎን ሆይ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ ጊዮርጊስ ይጠራሃል›› ብሎ በላከበት ጊዜ በጣዖቱ ላይ አድሮ ራሱን ያስመልክ የነበረ ሰይጣን እጅግ ደነገጠ፡፡ ሮጦም ወጥቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ፊት በፍርሃት ቆመ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሰይጣኑ ያደረበትን ጣዖት ‹‹አንተ በምስል ውስጥ የምትናገረው በእውነት የእነዚህ የከሃዲዎቹ አምልክ ነህን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ በምስል ውስጥ ያለው የሰይጣን መንፈስም ‹‹ጌታዬ ሆይ ተወኝ አታጥፋኝ፣ እኔስ አምላክ አይደለሁም…›› እያለ ከአዳም ጀምሮ የሰው ልጆችን እንዴት እንደሚያስት በነገሥታቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት መሰከረ፡፡ አሁንም በጣዖቱ ውስጥ አድሮ ራሱን እያስመለከ መሆኑንና ወደፊትም የሰው ልጆችን ሁሉ በልዩ ልዩ መንገድ ከፈጣሪያቸው እየለየ ወደ ሲኦል እንደሚያወርዳቸው ተናገረ፡፡ በጣዖቱ ያደረው ሰይጣን በሰው ሁሉ ፊት ይህን ሁሉ ከተናገረ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስም ወደ አምላኩ ከጸለየ በኋላ ምድር አጵሎንን አፏን ከፍታ እንድትውጠው አደረገ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ‹‹በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አምናል›› እያሉ ጮኹ፡፡ ንጉሡም ይህን ሲያይ በንስሓ ተመልሶ ከማመን ይልቅ እጅግ ተቆጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሰረው በኋላ ‹‹የተነጋገርነው ለጣዖቶቼ እንድትሠዋላቸው አልነበረምን? ለምን ቃልህን ለወጥክ?›› እያለ በታላቅ ቁጣ ተናገረው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ‹‹አንተ ሰነፍ ጎስቋላ የአእምሮ ድሃ የሆንክ ራሱን ሊረዳ ያልቻለው አምላክህ የሌሎቹን ነፍስ ሊረዳ እንዴት ይችላል? ጌታችን በጌትነቱ ለፍርድ በመጣስ ጊዜ ምን ታደርግ ይሆን?›› አለው፡፡ ንጉሡም እጅግ ተቆጥቶ ልብሱን ቀዶ ተነሥቶ ወደ ንግሥቲቱ ወደ እለእስክንድርያ ገባና ቅዱስ
ጊዮርጊስ ያደረገበትን ነገራት፡፡ እርሷም ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስን ከማሠቃየት ይልቅ የሚጠቅምህን ዕወቅ፣ አምላኩ እውነተኛ አምላክ ነውና በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ እመን›› አለችው፡፡ ንጉሡም ‹‹ሚስቴ እለእስክንድርያ ሆይ ይህ ጊዮርጊስ አስማቱን አደረገብሽ እንዴ?›› ሲላት እርሷም ‹‹የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቃል ጠርቶኛል በእርሱ አምኛለሁ›› አለችው፡፡ እርሱም ከአንደበቷ የክርስቶስን ስም በሰማ ጊዜ ጠጉሯን ይዞ እየጎተተ ወደ ነገሥታቱ ወስዶ ከመካከላቸው አቆማትና የሆነውን ነገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እጅግ አስፈሪ የሆኑ ሥቃዮችን ካሳያት በኋላ ራቁቷን አድርጎ በራስ ጸጉሯ ሰቀላት፤ ደሟም በምድር ላይ እስኪፈስ ድረስ ሥጋዋን ቆራረጠው፡፡ በመከራዋ ውስጥ ሆና ቅዱስ ጊዮርጊስን ባየችው ጊዜ ‹‹የእግዚአብሔር ቅዱሱ ሆይ በታላቅ ሥቃይ ውስጥ ነኝና ወደ መሐሪው አምላክህ ለምንልኝ››
አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ከጌታችን የማይጠፋውን የሕይወትን አክሊል እንድትቀበይ ጥቂት ታገሺ›› አላት፡፡ ከዚህም በኋላ ከተሰቀለችበት አውርደው በመሬት ካስተኟት በኋላ አራት ጎልማሶች ሊያነቃንቁት የማይችሉትን ትልቅ ድንጋይ አንከባለው በሁለቱ ጡቶቿ ላይ ጫኑባት፡፡ ዝፍጥም አፍልተው በጡቶቿ ላይ ጨመሩባትና እጅግ አሠቃዩአት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ዳግመኛ ‹‹ጌታዬ ሆይ ምን ላድርግ? በክርስቶስ ስም የምትሰጠውን የጥምቀት ጸጋ ባለመቀበሌ እኔ አዝኛለሁ ልቤም ልትፈርጥ ደርሳለችና አንተ እንደመራኸኝ ተስፋ ያደረኩትን ክብር እንዳላጣ የመንግሥተ ሰማይ ደጃፍ የገነት በሮች እንዳይዘጉብኝ እፈራለሁ›› አለችው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም መልሶ ‹‹ስለዚህ ነገር አትዘኝ፣ እነሆ በደምሽ ተጠምቀሻልና ጥምቀትንስ አግኝተሻል፡፡ እነሆ ቅዱሳን መላእክት ሊያጠምቁሽ የሕይወትንም አክሊል ሊያቀዳጁሽ ሰላምንም ሊሰጡሽ ይጠብቁሻል›› አላት፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተናዶ አንገቷን በሰይፍ አስቆረጣት፡፡ ቅድስት እለእስክንድርያም በዓለም ላይ ስላሉ ኃጥአን  ሁሉ እየለመነች ሰማዕትነቷን ሚያዝያ 15 ቀን ፈጽማ መላእክት ቅድስት ነፍሷን ወደ ገነት አስገቧት፡፡ የንግሥት ወሰማዕት ቅድስት እለእስክንድርያ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ አሜን። 
የመጥምቁ ዮሐንስ አንገት ከተቆረጠች በኋላ 15 ዓመት በአየር እየበረረች ስታስምር ኖራ በዚህ ዕለት ስለማረፏ፡- የመጥምቁ ዮሐንስ ቅድስት ነፍሱ
ከተቆረጠች ራሱ ጋራ በአየር ውስጥ እየበረረች 15 ዓመት ስታስተምር ከኖረች በኋላ ጥቅምት 30 ቀን በዐረቢያ ምድር በግልጽ ታይታለች፡፡ ሙሉውን ታሪክ የጥቅምት ፴ ስንክሳር ላይ ይመልከቱ።
 
በግብፅ ቤተክርስቲያን የከበረችበት

 በዚች ዕለት ሚያዝያ ፲፭ በዚች ቀን የሀገረ ሜራ ኤጲስቆጶስ በሆነ በኒቆላዎስ ስም ለያዕቆባውያን ወገን በግብጽ አገር ያለች ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት መታሰቢያ ሆነ። ይህም ኒቆላዎስ ስለ ከሀዲው አርዮስ በኒቅያ ከተማ ከተሰበሰቡት ከሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሃይማኖታቸው ከቀናች ኤጲስቆጶሳት አንዱ ነው።  ይቺም በእስክንድርያ ምሥራቅ ያለች ቤተ ክርስቲያን በአባ ሲኖዳ ገድል የታወቀች ናት።
ይህም ቅዱስ በተጋድሎው እጅግ ከፍ ከፍ አለ በዲዮቅልጥያኖስም መኳንንት ፊት እምነቱን በመግለጥና በመታመን ብዙ መከራና ሥቃይ ደረሰበት። ከሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት የከበሩ ሊቃውንት ጋራ በአንድነት ለመሰብሰብ እስቲደርስ እግዚአብሔር ጠብቆ አተረፈው። የዚህም አባት ተአምራቶቹ የበዙና በአራቱ ማእዘን የተገለጡ ናቸው በሰላም በፍቅርም አረፈ። በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።
 
ሐዋርያው አጋቦስ ሰማዕት ሆነ

በዚችም ዕለት ከሰባ ሁለቱ አርድእት የአንዱ ሐዋርያ ቅዱስ አጋቦስ መታሰቢያው ነው። እርሱም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይታወሳል በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ ትንቢት እንደተናገረ ሁለተኛም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ታላቅ ረኃብ እንደ ሚመጣ ተናግሮ ትንቢቱም ተፈጽሞ ረኃብ ቸነፈር መጥቶ ብዙዎች ሕዝቦችን አጠፋቸው። እነሆ ከገድሉ የቀረውን የካቲት አራት ቀን ጽፈናል። በጸሎቱ የምትገኝ በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages