ቅዱስ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ኢትዮጵያዊ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 23, 2021

ቅዱስ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ኢትዮጵያዊ

ቅዱስ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ኢትዮጵያዊ ልደታቸው ታሕሳስ 13 ፣ዕረፍታቸው ጥር 13
___________________________________ ቅዱስ አቡነ ዘርዓ ብሩክ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ ብሉይ ከሐዲስ ያልጐደለባት በክርስቶስና በድንግል እናቱ ኪደተ እግር የተቀደሰች የቅዱሳን መጠጊያ እና ብዙ ቅዱሳንን ከእቅፏ ያፈራች ስለ ሆነች የተባረከች አገር ትባላለች። ሁሉም የአገራችን ክፍሎች ቅዱሳንን አፍርተዋል። በምሥራቅም፣ በምዕራብም፣ በሰሜንም፣ በደቡብም ያሉ አካባቢዎች ሁሉ የቅዱሳን ቤቶች ናቸው። ቅዱሳንን በብዛት ካፈሩ አካባቢዎች አንዱ ደግሞ ምድረ ጐጃም ነው። በጐጃም አካባቢ ከተነሱ ቅዱሳን ደግሞ አንዱና ስመ ጥሩ ጻድቅ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ናቸው። አቡነ ዘርዓ ቡሩክ በብዙ ጐዳና የተለዩ አባት ናቸው። ለመጥቀስ ያህል እንኳ፦ 1.በታሪክ ዓለምን ከበው የያዙ ሁለቱ ግሩማን አራዊት (ብሔሞትና ሌዋታንን) ጥርስ ቆጥረው ብዙ ምሥጢራትንም ተመልክተው ተመልሰዋል። (በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ሳይንሱ በብዙ ድካም ያልደረሰበት ነው።) 2.ጻድቁ በልደታቸው ጊዜ ዓይነ ስውራንን አብርተዋል። ለራሳቸው ግን ይህን የግፍ ዓለም ላለማየት ጸልየው ዓይናቸው እንዲጠፋ አድርገዋል። 3.መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል ቅዱስ ኢያሱ በገባኦን ፀሐይን አቁሟል። ዘርዓ ቡሩክ ግን በጥበበ እግዚአብሔር ፀሐይን ለአምስት ዓመት አቁመዋል። 4.ጻድቁ ከንጽሕናቸው ብዛት አሥራ ሁለት ክንፍ (መንፈሳዊ ክንፍ) ተሰጥቷቸው ነበር። ከዚህ በተረፈም በጾም፣ በጸሎት፣ በትሕርምትና በስብከተ ወንጌል ፍጹም ጽሙድ ነበሩ። ጻድቁ የተወለዱት በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እዚያው ጐጃም ውስጥ ሲሆን አባታቸው ደመ ክርስቶስ እናታቸው ደግሞ ማርያም ሞገሳ ይባላሉ። ወላጆች በልጅ እጦት ተማለው ይህን የተቀደሰ ፍሬ አገኙ። "ጸጋ ኢየሱስ" ብለውታል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቷቸዋልና። ቀጥሎ የወለዱትንም "ተስፋ ኢየሱስ" ብለውታል። ይህም የጻድቁ ታናሽ ወንድም ነው። በሒደት ግን የጸጋ ኢየሱስ ስም በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ዘርዓ ቡሩክነት ተቀይሯል። ጻድቁን ስመ ጥር ካደረጓቸው ሥራዎቻቸው መካከል በአፄ ሱስንዮስ ዘመን የሠሩት ቅድሚያውን ይወስዳል። ነገሩ እንዲህ ነው። በ1598 ዓ/ም በኢትዮጵያ ላይ የነገሡት አፄ ሱስንዮስ ጴጥሮስ ፓኤዝ (ፔድሮ ፓኤዝ) ከሚባል ፈረንጅ መናፍቅ ጋር በፈጠሩት ወዳጅነት ሃይማኖታቸውን ለወጡ። ካቶሊክ (ሮማዊ)ም ሆኑ። በኋላም አልፎንሱ ሜንዴዝ የሚሉት እሾህ መጥቶ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ መናፍቅ እንዲሆን ከንጉሡ ጋር መከረ። ለጊዜው በቤተ መንግሥቱ አካባቢ የነበሩ መሳፍንት ተቀላቀሉ። እየቆየ ግን ዜናው በመላ ሃገሪቱ ተሰማ። በተለይ ከ1609 - 1616 ዓ.ም በተዋሕዶ አማኞችና በመናፍቁ ንጉሥ መካከል ነገሩ ተካሮ ጳጳሱ አቡነ ስምዖን ጠዳ ላይ መገደላቸው ተሰማ። በዚህ ጊዜ ገበሬው ከእርሻው፣ ሴቷ ከማዕድ ቤት፣ ካህኑ ከመቅደሱ፣ ነጋዴው ከገበያው እየወጡ ስለ ቀናችው ሃይማኖት ደማቸውን አፈሰሱ። በበዓት የተወሰኑ በሺህ የሚቆጠሩ ቅዱሳንም ወጥተው ተሰየፉ። በዚህ ጊዜም የግሺው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ዳዊታቸውን አንግበው ለሰማዕትነት ሔዱ። ዓባይ ወንዝ ላይ ሲደርሱ ዳዊታቸውን ወደ ወንዙ ውስጥ ጣሉት። ተሻግረውም ከንጉሡ አደባባይ ደንቀዝ ደረሱ። በጊዜውም ልክ እንደነ ፍቅርተ ክርስቶስና ወለተ ጴጥሮስ እርሳቸውም መከራ ደረሰባቸው። ንጉሡም ሳይገደሉ እንዲታሠሩ አደረገ። በጨለማ እስር ቤትም አምስት ዓመታትን ሲያሳልፉ ትኩስ ምግብን ያመጡላቸው ነበር። እርሳቸው ግን ምግባቸው ሰማያዊ ነበርና አልነኩትም። ከአምስት ዓመት በኋላም ያ ሁሉ ምግብ በተአምራት በትኩስነቱ እየጨሰ ተገኝቷል። ዘርዓ ቡሩክም ከእሥር ተፈትተዋል። እግዚአብሔርም በከሐዲው ንጉሥ ላይ ፈርዶ ፋሲል ነግሷል፤ ሃይማኖት ተመልሷል። ጻድቁም በዓባይ ወንዝ ላይ የጣሉት ዳዊታቸውን ሳይርስ አግኝተውታል። ጐጃም ሲደርሱም ሰይጣን እርሳቸውን መስሎ ሲያስት ስላገኙት ወደ ጥልቁ አስጥመውታል። በተረፈ ዘመናቸው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ብዙ ተጋድለው ጥር 13 ቀን ዐርፈዋል። ድንቅ ሠሪ አባት ናቸውና ዛሬም በግሺ ብዙ ተአምራት ይደረጋሉ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages