የመስከረም ፲ የቅዱሳን በዓላት ጼዴንያ ማርያም - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

የመስከረም ፲ የቅዱሳን በዓላት ጼዴንያ ማርያም

_____________ መስከረም ፲ ዕለት ጸዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ከሣላት ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር የተገለጠበት ዕለት ነው፡፡ ጼዴንያ በምትባል ሀገር ማርታ የምትባል ደግ ሴት ነበረች፡፡ ይህች ደግ ሴት በቤቷ ትልቅ አዳራሽ ሠርታ እንግዶችን እንደ አባታችን አብርሃም ተቀብላ አብለታ አጠጥታ ማደሪያ ቦታም ሰጥታ ታስተናግድ ነበር፡፡ አባ ቴዎድሮስ የሚባል ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ መሽቶበት ከማርታ ቤት በእንግድነት አደረና ጠዋት ሊሄድ ሲነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ሲነግራት ‹‹የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተህ አምጣልኝ ዋጋውን ልስጥህ›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ገንዘቡን ሥዕሉን ሳመጣልሽ ትሰጪኛለሽ›› ብሏት ሄደ፡፡ ኢየሩሳሌምም ደርሶ ቅዱሳት መካናትን ተሳልሞ ሥዕሉን ረስቶ ሳይገዛ ሲመለስ «አደራ ጥብቅ አይደለምን? ያቺ ሴት አደራ ያለችህን ለምን ረሳህ» የሚል ድምፅ ሰማ፡፡ በጣም ደንግጦ ተመልሶ ሄዶ ገዝቶ በረሃ በረሃውን መጓዝ ጀመረ፡፡ በመንገድም እየተጓዘ አንበሳ ሊበላው እየሮጠ ወደ እርሱ ሲመጣበት አየ፡፡ መነኩሴው አንበሳውን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፣ ተንቀጠቀጠ ደንግጦ ቁሞ ሳለ ያች ሥዕል ከአንበሳው ጩኸት ሰባት እጅ በሚበልጥ አስፈሪ ድምፅ ጩሃ ተናገረች፡፡ ያን ጊዜ አንበሳው ደንግጦ ፈጥኖ ሸሸ፡፡ መነኩሴውም መንገዱን ቀጠለ፡፡ በመንገዱም ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወጥተው ወንበዴዎች ሊቀሙትና ሊገድሉት ከበቡት፡፡ ከሥዕለ ማርያሟም እንደ መብረቅ ያለ ታላቅ ቃል ወጣ፡፡ ወንበዴዎችም እጅግ ፈርተው ሸሽተው ከጫካው ውስጥ ገቡ፡፡ ያም መነኩሴ እነኚህን የሚያስደንቁ ተአምራት በተመለከተ ጊዜ በልቡ «ለእኔ ረዳት ትሆነኝ ዘንድ ወደ ሀገሬ ይዣት እሄዳለሁ እንጂ ለላከችኝ ሴት አልሰጥም» ብሎ ወደ ሀገሩ ሊሄድ በመርከብ ተሳፈረ፡፡ በባሕር ላይም ሳለ ጽኑ ነፋስ ተነስቶ መርከቡን እየገፋ ማርታ ወዳለችበት ሀገር ወደ ጽዴንያ ዳርቻ አደረሰው፡፡ ማደሪያም ስለሌለው ወደ ደጓ ሴት ወደ ማርታ ቤት ከእንግዶች ጋር አብሮ ገብቶ አደረ፡፡ ሲነጋ ወጥቶ ሊሄድ ከደጃፍ ሲደርስ ደጃፉ ጠፍቶት ከአጥሩ ሲታገል ዋለ፡፡ ማርታም «አባቴ ያመመህ የደከመህ ትመስላለህ ዛሬ ደግሞ እዚህ እደርና ነገ ትሄዳለህ» አለችውና አደረ፡፡ በሁለኛውም ዕለት እንደ መጀመሪያው ቀን በሩን አልፎ መሄድ አቃተውና እዚያው ማርታ ቤት አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን መውጣት ፈልጐ አሁንም ከአጥሩ ጋር ሲታገል አይታ «አባቴ የሆንከው ምንድነው? እነሆ ዛሬ ሦስተኛ ቀንህ ነው» አለችው፡፡ መነኩሴውም «ይህችን ተአምረኛ ሥዕል አልሰጥም ብዬ ነው፡፡ እኔኮ ሥዕል ከኢየሩሳሌም ግዛልኝ ያልሽኝ መነኩሴ ነኝ» ብሎ ሥዕለ ማርያምን አውጥቶ ሰጣት፡፡ እርሷም እጅግ በጣም ተደስታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ በሥዕሏም ፊት ሰግዳ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ምስጋናን አቀረበች፡፡ ተቀብላም ሥዕል ቤት አሠርታ በክብር አስቀመጠቻት፡፡ ይህችም ሥዕል ቅዱስ ሉቃስ የሳላት ናት፡፡ ሥጋ የለበሰች ትመስላለች፡፡ ከፊቷም ወዝ ይንጠባጠባል፡፡ በዚህችም ሥዕል ብዙ ተአምራት ተደረገ ሕሙማን ተፈወሱ፣ ዐይነ ስውራን ማየት ቻሉ፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው ሊቀ ጳጳስ ተአምሯን ሰምቶ ሥዕሏ ወደ ማርታ ቤት የገባችበት ዕለት መስከረም 10 ቀን እንዲከበር ሥርዓት ሠራ፡፡ ይህም በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ሁልጊዜ ይከበራል፡፡ የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ ፍቅሯን ጣዕሟን ታሳድርብን፣ ልጇ አምላካችን ምህረቱን ቸርነቱን ያብዛልን አሜን። #በዚች ዕለት መስከረም ፲ የጌታችን ቅዱስ መስቀል አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የገባበት ዕለት ነው፡፡ አምላካችን ለበዓሉ በሰላም ካደረሰን መስከረም ዓሥራ ሰባት ቀን በዝርዝር እናየዋለን፡፡ የቅዱስ መስቀሉ ፍቅር ይደርብን አሜን። ሰማዕቷ ቅድስት መጥሮንያ ______________________ መስከረም ፲ በዚህች ዕለት የከበረች ቅድስት መጥሮንያ በሰማዕትነት ዐርፋለች፡፡ ሰማዕቷ ቅድስት መጥሮንያ የአንዲት አይሁዳዊት ሴት አገልጋይ ነበረች፡፡ አሠሪዋ አይሁዳዊ ሴትም ቅድስት መጥሮንያን ክርስቲያን በመሆኗ ብቻ ሸክም ታበዛባትና ታንገላታት ነበር፡፡ ከሃይማኖቷም አውጥታ ጌታችንን ማመንን ልታስተዋት ብዙ ሞከረች፡፡ በአንዲት ዕለትም አይሁዳዊቷ ይዛት ወደ ምኩባራባቸው ሄደች፡፡ ቅድስት መጥሮንያ ግን ወደ ምኩራባቸው ሳትጋ ተመልሳ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ጸሎት አደረገች፡፡ ወደ ቤታቸው ተመልሰው በገቡ ጊዜ አሠሪዋ ‹‹ወደ እኛ ምኩራብ ለምን አልገባሽም?›› ብላ ጠየቀቻች፡፡ ቅድስት ቅድስት መጥሮንያም ‹‹ከእናንተ ምኩራብ እግዚአብሔር ርቋልኮ፣ እንዴት ወደ እርሱ እገባለሁ! በውስጧ ልገባባት የሚገባኝ ቦታዬ ግን ክብር ይግባውና ጌታችን በከበረ ደሙ የዋጃት ይህች ቤተ ክርስቲያን ናት›› አለቻት፡፡ አሠሪዋ አይሁዳዊትም ከቅድስት መጥሮንያ ይህንን በሰማች ጊዜ እጅግ ተቆጥታ በኃይል ደበደበቻት፡፡ በጨለማ ቤት ውስጥ ዘጋችባትና ያለምግብና ያለመጠጥ ለ4 ቀን አሠረቻት፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ውጭ አውጥታ በጅራፍ ታላቅ ግርፋትን ገርፋ ድጋሚ በእሥር ቤት ጣለቻትና በዚያው ተንገላታ ዐረፈች፡፡ ነፍሷንም እግዚአብሔር ተቀብሎ የሰማዕታትን አክሊል አቀዳጃት፡፡ አሠሪዋ ግን ሥጋዋን አውጥታ በመጣል በዚያም መጥሮንያ ራሷን የገደለች አስመሰለች፡፡ ቅድስት መጥሮንያ ራሷን የገደለች ስለመሰለ አይሁዳዊቷን ሴት ግን ማንም የመረመራት የለም፡፡ ነገር ግን ለተገፉ የሚፈርድ፣ ለተበደሉ የሚበቀል እውነተኛ ዳኛ ልዑል እግዚአብሔር ቁጣው በዚያች አይሁዳዊ ሴት ላይ ወረደ፡፡ ከደርቧ ላይ ስትወርድ ድንገት ወድቃ በዚያው ከመቅጽበት ሞተች፡፡ በነፍሷም ወደ ዘላለማዊ እሳት ሄደች፡፡ ረድኤት በረከቷ ይደርብን አሜን። እንዲሁም በዚች ዕለት ከከሃዲው ከሆሎፎርኒስ እጅ በጥበቧ እስራኤልን ያዳነቻቸው ጥበበኛዋ ዮዲት ዐረፈች፡፡ ዳግመኛም በዚች ዕለት ቅድስት አትናስያና ሦስት ልጆቿ መታሰቢያ በዓላቸው ነው። የቅዱሳኑ ሁሉ ረድኤታቸው በረከታቸው ይደርብን አሜን። ምንጭ : ስንክሳር ዘወርኅ መስከረም ፲

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages