መልካም የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ይሁንልን። ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ፣ አደረሰን፣ ፳፻፲፬ ዓ.ም።
መስከረም ፫ ቀን አባ ዲዮናስዮስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ሲሆን እርሱም የትንሣኤ ሙታንን ድርሳን የደረሰው ነው፡፡ ይኸውም ‹‹ነፍስ ከሥጋ ጋር ትሞታለች፣ በትንሣኤም ከሥጋ አብራ ትነሣለች›› የሚሉ መናፍቃን ከዐረቢያ አገር በመነሳታቸው ቅዱስ ዲዮናስዮስ በግብጽ የአንድነት ገባዔ አድርጎ ቢያስተምራቸው እምቢ ቢሉት ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ስለ ትንሣኤ ሙታን የሚነገረውንና የነፍስን ረቂቅነት፣ ዘላለማዊና ሕያዊት መሆኗን የሚናገር ድርሳን ደረሰ፡፡ እግዚአብሔርንም ሲያገለግል ኖሮ በሰላም አርፎ ወደ ሚወደው አምላክ ሄደ፣ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ አሜን፡፡
አቡነ አንበስ ዘአዘሎ
__________________
በአንበሳ ላይ ተጭነው ይጓዙ የነበሩት ኢትዮጵያው ጻድቅ አቡነ አንበስ ዘአዘሎ እረፍታቸው ነው፡፡ ከቅድስናው የተነሣ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው በአንበሳ ላይ ተጭኖ ነው፡፡ ተአምራትን በማድረግና ወንጌልን በማስተማር በጾም ጸሎት አብዝቶ የደከመ ሲሆን ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሌት ተቀን በጸሎት ይተጋ የነበረ ታላቅ አባት ነው፡፡ አቡነ አንበስ ትውልዱ ትግራይ አድዋ በእንጭጮ ወረዳ ነው፡፡ በስሙ ትግራይ አድዋ "እንጭጮ አቡነ አንበስ ገዳም" እና በትግራይ ሽሬ ሁለት ትላልቅ ገዳማት አሉት፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ደጋግሞ የጠቀሳቸው ሲሆን የያሬድንም የድርሰቱን የአቋቋም ሥርዓት ያመጡት አቡነ አንበስ ናቸው፡፡
አቡነ አንበስ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ጊዜ የነበሩ ሲሆን እሳቸውንም አንበሶች ያገለግሏቸው ነበር፡፡ ጻድቁ አቡነ አንበስ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር የተገናኘ ትልቅ ታሪክ አላቸው፡፡ የላዕላይ ግብጹ አባ ብንያም፣ በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና የአዘሎው አቡነ አንበስ እነዚህ 3ቱ ቅዱሳን ከየአሉበት በአንበሳቸው ተጭነው ዝቋላ አቡዬ ዘንድ እንደደረሱ የአቡዬ አንበሶች የ3ቱንም ቅዱሳን አንበሶች ዋጡዋቸው፣ አቡዬም በዚህ አዝነው ከበዓታቸው ወጥተው አንበሶቻቸውን ‹ትፉ› ብለው የበሉአቸውን አንበሶቻቸውን አስተፍተዋቸው ለ3ቱም ቅዱሳን የተበሉባቸውን አንበሶቻቸውን መልሰውላቸዋል፡፡ ይኸውም የሆነው እኝዲህ ነው፡- አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዝቋላ 7ቱ ሊቃነ መላእክት እየረዷቸው 70 ሺህ እልፍ አጋንንትን በእሳት ሰይፍ ፈጅተው ካጠፏቸው በኃላ ወደ ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡ ከዚህም በኀላ መንፈስ ቅዱስ የጠራቸው ሦስቱ ቅዱሳን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ አቡነ አንበስ ዘአዘሎ እና የላዕላይ ግብጹ አቡነ ብንያም በአንበሶቻቸው ሆነው ወደ ጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ምድረ ከብድ ገዳም መጡ፡፡ አባታችን ግን ስለተሰወራቸው እስከ 7 ቀን ድረስ በምህላ ሰነበቱ፡፡ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሶችም መጥተው የ፫ቱን ቅዱሳን አንበሶች በልተውባቸው ተሰወሩ፡፡ 3ቱም ቅዱሳን ፈጽመው ደነገጡ፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም የቅዱሳኑን ሀዘንና ድንጋጤ ተመልክተው በታላቅና በሚያስፈራ ግርማ ሆነው ስልሳ ነብሮችንና ስልሳ አንበሶችን አስከትለው ተገለጡላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ከአቡዬ ግርማ የተነሣ ስለደነገጡ እንዳይፈሩም አረጋጉአቸው፡፡
ከዚህም በኃላ አባታችን "በምን ምክንያት ወደዚህ ገዳም ወደ እኔ መጣችሁ?" አሏቸው፡፡ ሦስቱ ቅዱሳን እንዲህ አሉ፡- "ጸሎትህ ቅድስት እንደሆነች ባወቅን ጊዜ ወደ አንተ መጣን፤ አንተ በሁሉ ርእሰ ባሕታውያን ነህና የእግዚአብሔርን ሥራ ትነግረን ዘንድ መጣን፤ ባላገኘንህም ጊዜ እስከ 7ቀን አለቀስን" አሉት፡፡ ዳግመኛም "አንበሶችህ መጥተው አንበሶቻችንን ደማቸውን ጠጡ ቆዳቸውንም በጥፍራቸው በጣጠሱ" ብለው ነገሯቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ሲሰሙ አንበሶቻቸውን "እስከ ዕለቴ ሞቴ ድረስ በእግሬ ከረገጥኩት ትቢያ በቀር ምንም እንዳትበሉ ታዛችሁ የለምን? እግዚአብሔር ያላዘዛችሁትን ለምን በላችሁ? በሉ አሁንም የበላችሁትን ትፉ" አላቸው፡፡ እነዚያም አንበሶች አፋቸውን ከፍተው አንዳች ሳያስቀሩ አጥንታቸውን ሥጋቸውን በሙሉ ተፉአቸው፡፡ ጻዲቁ አባታችንም ወደ ምሥራቅ ተሠልሰው እግዚአብሔርን ከለመኑ በኃላ በአንበሶቹ ሥጋ ላይ ባረኩና "በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ" አሏቸው፡፡ አንበሶቹም እንደ ዓይን ፈጥነው ተነስተው እንደ ቀድሞው ሆኑ፡፡ የአቡነ አንበስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን አሜን፡፡
አቡነ ሙሴ ዘገዳመ ሲሐት፡
______________________
በበረሃ ዝናብን ያዘነበ፣ አራዊት ሁሉ እየተገዙለት፣ አርባ አምስት ዓመታት በታላቅ ተጋድሎ የኖረ በኀላም ሰይጣን በፈተና ጥሎት የነበረና በኀላም የሰይጣንን ድል ያደረገው አቡነ ሙሴ ዘገዳመ ሲሐት ዕረፍቱ ነው፡፡ በሲሐት ገዳም ውስጥ በታላቅ ተጋድሎ ይኖሩ የነበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ የሚመገቡትም የዘንባባ እንጨትና የወደቁ የዘይቱን ፍሬ ነበር፡፡ እነዚህንም ቢሆን አንድ ወፍ ከሚበላው የበለጠ አይመገቡም ነበር፡፡ ልብሳቸውም ከዘንባባ ቅጠል የተሠራ ሰሌን ነው፡፡ የዱር አራዊት ሁሉ ይገዙለት የነበረ ሲሆን የጸሎት ጊዜው ሲደርስ ብቻ እንዲሄዱ ይነግራቸዋል፡፡ ድርቅ ሲሆንባቸውም መጥተው በፊቱ ይቆማሉ፡፡ አቡነ ሙሴም የልባቸውን ፍላጎት በመንፈስ ቅዱስ ስለሚያውቅ ዝናብ በጸሎቱ እንደዘንብላቸው ያደርጋል፡፡ እንዲህም እያደረገ ከአራዊቱ ጋር እየኖረ በጾም በጸሎት እየተጋ 45 ዓመት ተቀመጠ፡፡
ነገር ግን አቡነ ሙሴ መጻሕፍትን የሚውቁ አልነበሩም፡፡ ሰይጣንም በኑሮአቸው ቀናባቸውና በተለያየ ሁኔታ እየተገለጸ በፈተና ሊጥላቸው አሰበ፡፡ ከበዓታቸው ሆነው ሳለ ዘመኑ ያለፈበት እጅግ የደከመ ሽማግሌ መስሎ በመንገድ ሲያዘግም ታያቸው፡፡ አቡነ ሙሴም ገዳማዊ መናኝ መስሏቸው ሄደው አምጥተው ከገዳማቸው አስገቡት፡፡ የዱር አራዊቱ ግን ሰይጣን መሆኑን ዐውቀውት ሸሽተው ሄዱ፡፡ አቡነ ሙሴም ሀገሩን፣ ሃይማኖቱንና ኑሮው እንዴት እንደሆነ ጠየቁት፡፡ በሽማግሌ የተመሰለው ሰይጣንም ‹‹እኔ በዓለም ኃጢአት በመሥራት ብዙ ዘመን ኖርኩ፣ አንዲት ሴት ልጅንም ወለድኩ፡፡ ከዚያም የዓለምን ኃላፊነትና ጠፊነት አሰብኩ፡፡ ከዓለምም ወጥቼ በበረሃ ውስጥ 40 ዓመት ኖርኩ፡፡ ልጄን ያገባት እንደሌለ ባሰብኩ ጊዜ በዚህ ነገር ምክንያት ወደ አንተ መጣሁ፣ ከአንተ በቀር የሚያገባት የለምና በሞትኩ ጊዜ የምትቀብረኝ አንተ ነህ፣ ብዙ ሃብትና ብዙም የአትክልት ሥፍራዎች ስላሉኝ ሁሉንም አንተ ትወርሳለህ›› አላቸው፡፡ አቡነ ሙሴም ደንግጠው ‹‹እኔኮ መነኩሴ ነኝ፣ ይህን ማድረግ አይቻለኝም›› አለው፡፡ ሽማግሌውም ‹‹የተመረጡት ጻድቃን ሆነው ሳለ ሚስቶች የነበሯቸው እነ አብርሃምን፣ ሙሴን፣ ዳዊትን…›› ከብሉይ መጻሕፍት ምስክር ማስረጃ አድርጎ እየጠቀሰ አስረዳው፡፡ በዚህም የአቡነ ሙሴን ልብ ወደ ተንኮል አዘነበለው፡፡ ሽማግሌውም በውስጡ ያጌጠች ቆንጆ ልጅ ያለችበት የተሸለመ አዳራሽ በምትሐት አሳየውና ሕመም ያገኘው መስሎ እየደከመ መጣ፡፡ የሞተም መሰለ፡፡ አቡነ ሙሴም አልቅሶ ገንዞ ቀበረው፡፡ ልጅቷ ወዳለችበት ያማረ አዳራሽ ሊገባ ሲል በነፋስ ተመስሎ ወደ ኋላ አዙሮ ጣለውና ወደቀ፡፡ አባ ሙሴም ወደ ልባቸውም ሲመለሱ ልጅቷን፣ አዳራሹን፣ የአትክልቱንም ቦታ አጡት፡፡ ወደ በዓታቸውም ተመልሰው የወዳደቁ ፍራፍሬዎችን አንስተው ለመብላት ሲሉ ሌላ ጊዜ እንደማር እየጣፈጣቸው ይመገቡት የነበረው ፍሬ ዛሬ ግን እንደ እሬት እጅግ መራራ ሆነባቸው፡፡ የዱር አራዊቱም ፈጽመው ራቋቸው፡፡ በጣም እርቧቸው ሳለ ወደ በዓታቸው ተመለሱ፡፡
አሁንም ያ ሰይጣን ወደ እስክንድያ የሚሄድ ሽማግሌ ነጋዴ መስሎ በአህያ ላይ ተቀምጦ ታያቸው፡፡ መብልና መጠትም ይዞ ነበር፡፡ አቡነ ሙሴንም ከእርሱ ጋር ወስዶ ወደ አንድ አገር አድርሶ ከዚያ ተዋቸው፡፡ ለ3ኛ ጊዜም ሰይጣን በገዳም በምናኔ በምትኖር ሴት መነኩሴ ተመስሎ ተገለጠላቸው፡፡ እርሷም ውኃ የምትቀዳ መነኩሴ መስላ ቀረበችው፡፡ አቡነ ሙሴንም ‹‹ሥራህ ምንድነው?›› አለችው፡፡ አቡነ ሙሴም መነኩሴ እንደሆነና አሁን ሰይጣን በፈተና እንደጣለው የደረሰበትን ሁሉ ነገራት፡፡ እርሷም በልቧ ሳቀችበትና ወደቤቷ ወስዳ አብልታ አጠጥታ አጠገበችው፡፡ ከዚያም በብዙ ሽንገላ የጋብቻን ነገር አሳሰበችው፡፡ እጅግ ብዙ ገንዘብ እንዳላት፣ የሟች የንጉሥ ልጅ እንደሆነችም ነገረችው፡፡ ልቡም እንዳዘነበለ አይታ አይሁዳዊት መሆኗን በመንገር ብዙ ተስፋ አስደረገችው፡፡ ‹‹ወደ በረሃ ሄደን ቀብሬ ያኖርኩትን ብዙ ወርቅና ገንዘብ አውጥተን እንጠቀምበት›› በማለት ወደ በረሃ ወሰደችው፡፡ ትልቅ ተራራ ላይ ይዛው ከወጣች በኋላም ተለወጠችበት፡፡ እንዲህም አለችው፡- ‹‹እኔ ብዙዎችን ያሳትኩ ሰይጣን ነኝ፣ አንተንም ከገዳምህ አውጥቼ ሃይማኖትህንም አስካድኩህ፣ እነሆ በዚህ በረሃ ሙተህ ነፍስህ ወደ ገሃነም ትወርዳለች›› ብላው ተሰወረች፡፡ አቡነ ሙሴም ወደ ልቡ በተመለሰ ጊዜ በግራኝም በቀኝም መመለሻ መንገድ አጣ፡፡ ምድር ጠበበችውና አዙሮት ወድቆ በፊቱ ላይ አፈር እየነሰነሰ ጮኸ፡፡ ነፍሱም ከሥጋው ለመለየት እስከደረሰች ድረስ በምድር ላይ እየተንከባለለ ፈጣሪውን ተማጸነ፡፡
መሐሪና ይቅር ባይ አምላከም የቀድሞ ዘመን ተጋድሎውን አስቦ በቸርነቱ ራርቶለት ያጽናናው ዘንድ መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም ‹‹አይዞህ አትፍራ ኃጢአትህ ተሠረየችልህ፣ ከሰባት ቀንም በኋላ ታርፋለህ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሳሙኤልም መጥቶ ይቀብርሃል›› አላቸው፡፡ ሳሙኤልም መጥቶ ንጉሥ ኢጋቦም በበረሃ አንጾአት ወደነበረች ገዳም ወሰደው፡፡ እርሷም የተሰወሩ ቅዱሳን የሚሰበሰቡባት ከዓለማውያን ሰዎች ተሰውራ የምትገኝ ገዳም ናት፡፡ ሳሙኤልም መሥዋዕትን ሲያሳርጉ አድርሶት አቡነ ሙሴ ሥጋ ወደሙን ከተቀበለ በኋላ መስከረም ፫ ቀን በሰላም አርፎ ሳሙኤል ቀብሮታል፡፡
የአቡነ ሙሴ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን አሜን፡፡
Post Top Ad
Saturday, October 2, 2021
Tags
# ነገረ ቅዱሳን
Share This
About አትሮንስ ሚዲያ
ነገረ ቅዱሳን
Labels:
ነገረ ቅዱሳን
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Post Bottom Ad
Author Details
Templatesyard is a blogger resources site is a provider of high quality blogger template with premium looking layout and robust design. The main mission of templatesyard is to provide the best quality blogger templates which are professionally designed and perfectlly seo optimized to deliver best result for your blog.
No comments:
Post a Comment