መስከረም ፮ ታላቁ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ቅዱስ ኢሳይያስ ዕረፍቱ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

መስከረም ፮ ታላቁ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ቅዱስ ኢሳይያስ ዕረፍቱ

ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ___________________________ መስከረም ፮ ታላቁ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ቅዱስ ኢሳይያስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ኢሳይያስ ማለት ‹‹እግዚአብሔር ደኅንነት ነው›› ማለት ነው፡፡ አባቱ አሞጽ ይባላል ሆኖም ‹‹ነቢዩ አሞጽ›› ሳይሆን ሌላኛው አሞጽ ነው (፪ኛ ነገ ፲፱፣፩ ፣ ኢሳ ፩፣፩)፡፡ ይህ ታላቅ ነቢይ ለይሁዳ በነገሠ በ፭ቱ ነገሥታት ዘመን አስተምሯል፤ ትንቢት ተናግሯል፡፡ እነዚህም ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝ፣ ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው፡፡ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የቤተ- መንግሥት አማካሪ ነበር፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በመጀመሪያ ነቢይ እንዲሆን የተጠራው ዖዝያን በሞተበት ዓመት ነው፡፡ አስቀድሞ የነበረው ንጉሡ አዛርያስ ሀብተ ክህነት ሳይኖረው ሊያጥን ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ እያየ ነቢዩ ኢሳይያስ ወዳጁ ስለሆነ ሳይገሥጸው ቀረ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርም ስለድፍረቱ ዖዝያንን በለምጽ አነደደው፡፡ እግዚአብሔርም በዖዝያን ፈንታ ኢዮአታምን አነገሠወው፡፡ ኢሳይያስም ባለሠገሠጹ ከንፈሩ ላይ ለምጽ ወጣበት፡፡ ኑሮውም ከሰው ተለይቶ በጨለማ ቤት ሆነ፡፡ ሀብተ ትንቢቱንም ተቀማ፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ከልቡ ተጸጽቶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ንስሓ ስለገባ እግዚአብሔር ንስሃውን ተቀበለው፡፡ ንስሓውንም እንደተቀበለው ያውቀው ዘንድ እግዚአብሔር በረዥም ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ኪሩቤል ዙፋኑን ተሸክመውት፣ ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" እያሉ ሲያመሰግኑት ተገለጠለት፡፡ ኢሳ 6፡1፡፡ መልአኩንም ልኮ ከለምፁ ፈወሰው፡፡ ሀብተ ትንቢቱም መለሰለት፡፡ ንስሓን የሚቀበል የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን፡፡ በንጉሡ በአካዝ ዘመነ መንግሥት የሶርያና የሰማርያ ሠራዊት ወደ ይሁዳ በዘመቱ ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ አካዝን በእግዚአብሔር እንዲታመን እንዳይደነግጥ መከረው፡፡ አካዝ ግን ጠላቶቹን እንዲቋቋምለት ለማድረግ ለአሦር ንጉሥ ግብር ይልክለት ነበር( ኢሳ ፯፣፩-፲፯ ፣ ኢሳ ፰፣፩-፻፲፬፣ ፪ኛ ዜና መ ፳፰፣፲፮-፳፩)፡፡ የአሦርም መንግሥት እየተስፋፋ ሲሄድ የይሁዳ አለቆች ለእርዳታ ወደ ግብፅ ተመለከቱ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ይህንን ሲያይ እግዚአብሔርን ከመማጸን ይልቅ ወደ ውጭ መመልከታቸው በእግዚአብሔር አለማመን መሆኑን ገልጾ ተናገረ፡፡ የአሦር ንጉሥም የይሁዳን ከተሞች በእጁ አድርጎ በኢየሩሳሌም ላይ ዛቻ ሲናገር ኢሳይያስ ስለ አሦራውያንና ስለ ንጉሣቸው ሰናክሬም መሸነፍ ተነበየ፡፡ በትንቢቱም መሠረት የአሦር ሠራዊት በአንዲት ሌሊት ቸነፈር ተመቷል (፪ኛ ነገ ፲፰፣ ፲፱፡፡ ፪ኛ ዜና ፴፪፣፲፮-፳፩፣ ኢሳ ፴፮፣፩-፳፩)። ይኸውም የፋርሱ ንጉሥ ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ከቦ ሳለ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ቃል ተናገረ፡፡ ጻድቁ ንጉሥ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ዘንድ ለነቢዩ ኢሳይያስ መልእክት ላከበት፡፡ ኢሳይያስም በጸሎት እግዚአብሔርን ከጠየቀ በኋላ በጸሎቱ ያገኘውን መልስ ለንጉሥ ሕዝቅያስ ‹‹አትፍራ በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ ብሎሃል›› አለው፡፡ በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰናክሬም ሰፈር መጥቶ ከፋስ ሠራዊት 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) ሠራዊቶቹን በአንዲት ሌሊት ገደላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞት በደረሰ ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ ‹‹እግዚአብሔር ‹ትሞታለህ እንጂ አትድንም› ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ››› አለው፡፡ ሕዝቅያስም ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ በእጅጉ ሲያለቅስ እግዚአብሔር ዳግመኛ ነቢዩን ወደ ንጉሡ ላከው፡፡ ‹‹የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፣ እነሆ በዘመንህ ላይ ፲፭ ዓመት ጨመርኩልህ›› ብለህ ነገረው አለው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ሄዶ ለንጉሥ ሕዝቅያስ ነገረው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ዳግመኛም በአካዝ ዘመን እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡- ‹‹እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ! ስሙ፣ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፤ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ! ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች (ኢሳ ፯፣፲፬)። ነቢዩ ዳግመኛም ክብር ይባውና ስለጌታችንም መከራ ትንቢትን ሲናገር እንዲህ አለ፡- ‹‹የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፡፡ መልክና ውበት የለውም፣ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፣ እኛም አላከበርነውም፡፡ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን፡፡ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ፡፡ ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፣ ዕድሜውም ይረዝማል፣ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል፡፡ ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል. ኃጢአታቸውን ይሰከማል፡፡ ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፣ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፣ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፣ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፣ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ ( ኢሳ ፶፫፣፩-፲፪)፡፡ ነቢዩ ይህንን የመድኃኔዓለምን መከራ ሞቱን በትንቢት የተናገረውና ያስተማረው ከጌታችን ልደት ከ913 ዓመት በፊት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ዳግመኛም ስለ እስራኤል መማረክና ከምርኮም ስለ መመለሳቸው ትንቢትን ተናገሯል፡፡ እንዲሁም በሕዝቅያስ ልጅ በንጉሥ ምናሴ ላይ ትንቢትን ተናገረ፡፡ ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ገሠጸው፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ምናሴ ተቆጥቶ ነቢዩ ኢሳይያስን በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ ከእግሮቹ መሀል ጀምሮ እስከ ጭንቅላቱ ድረስ ለሁለት ሰንጥቆ ገድሎታል፡፡ ነቢዩም ሰማዕትነቱን በዚሁ ፈጽሟል፣ ረድኤት በረከቱ ይደርብን አሜን። #እንዲሁም መስከረም ፮ ቀን የዋልድባው የአቡነ ሳሙኤል ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው። የቅዱሱ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን አሜን። #ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሰማዕቷ ቅድስት ሰብልትንያ ሰማዕትነቷን በድል ፈጸመች፡፡ ሰማዕቷ ቅድስት ሰብልትንያ በ፱ ዓመቷ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ጭፍሮች ይዘው እጅና እግሯን አሥረው ከሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሯት ነገር ግን ጌታችን ፍጹም ጤነኛ አድርጎ አዳናት፡፡ ዳግመኛም ይዘው እያሠዋዩአት ሳለ በሥቃይ ውስጥ ሆና ውኃ ጥም እጅግ በጠናባት ጊዜ ጌታችንን በጸሎት ጠይቃ ውኃ አፍልቃ ከጠጣች በኋላ ጌታችንን አመስግናና ነፍሷን አደራ ሰጥታ ራሷን ከእሳቱ ውስጥ ወርውራ ምስክርነቷን በክብርና በድል ፈጽማለች፣ ረድኤት በረከቷ ይደርብን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages