ምክረ አበው ክፍል ሦስት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

ምክረ አበው ክፍል ሦስት

የመጨረሻው ዘመን ዋዜማ ላይ ስለምንገኝ ነገሮችን በመንፈሳዊ ዓይን እንመርምር የሰው ልጅ ኅሊናውን የጣለበት በተሰጠው አእምሮ ክፉና ደጉን መለየት አቅቶት አእምሮውን መንፈሱንም ለማይረባ ፍላጎት አሳልፎ የሰጠበት ዘመን ነው።

ጸሎት ተናግሮተ ምስለ እግዚአብሔር ፣ ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት መንገድ ከመሆኑም በላይ ንቁ ላልሆነው የአእምሮችን ክፍል መልዕክት የምናስተላልፍበት መንገድ ነው፣ ደግሞም ምስጋናና ጸሎት ሕይወትን የሰመረ ያደርጋሉ። 

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ቁርጥ ውሳኔ መወሰን የተበላሸውን ማንነት ለመለወጥ ትልቅ ሚና አለው። ከቁርጥ ውሳኔ በዘገየን ቁጥር ከለውጥ ኃላፊነት እየሸሸን ነው። 

 እንዝላልነትና ቸልተኝነት የክርስትና ሕይወትን ይጎዳሉ ጥቂት እርሾ ብዙውን ሊጥ እንዲያቦካ ትንሽ ስንፍና የብዙ ዓመት ተጋድሎን ያበላሻልና። 

ተስፋ የእምነት መሠረት የመኖር ህልውና ናት፣ ሕይወት በተስፋ ካልተደገፈች አሰልቺ መሆኗ አይቀሬ ነው። 

ዘወትር እግዚአብሔርን ለመምሰል ራስህን አስለምድ መንፈሳዊ ልምምድ ለሥጋም ለነፍስም የሚጠቅም ከመሆኑም በላይ እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው።

 በበጥቂቷ የምድራዊ ሕይወትህ በሁለት ልብ አታነክስ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ መውጣት እንደማይቻል ሁሉ ከክፋት ደግነት ይሻላልና በመልካም ጎዳና በበጎ ኅሊና ተጓዝ። 

ከሁሉም በላይ ሰብአዊነት ይቀድማልና ሰውን ከውጫዊም ሆነ ከውስጣዊ ማንነቱ ባሻገር በሰውነቱ አክብር ሰውን እግዚአብሔር በእጆቹ ተጠብቦ በአምሳሉ የሰራው ብቸኛ ፍጥረት ነውና። 

በምንምና በማንም ላይ አትፍረድ። የሰው ሕይወቱ በምድር ላይ ብርቱ ሰልፍ ስለሆነ ከጎስቋላና ሐዘንተኛ ሰዎች ጀርባ ምን ዓይነት ፈተናና መከራ እንደደረሰ አታውቅምና። 

 የተሳሳቱትን ሁሉ አትንቀፍ በወደቁ ሰዎችም አትላገድ አትቀልድም፣ ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም ፣በክፋ ዘመን የወደቁም በደግ ዘመን ይነሳሉ። አንተም ነገ የምትሠራውን ስህተትህንና መውደቂህንም አታውቅምና። 

አንደበቱን ከሚያሳምር ይልቅ የሚገስጽ ሞገስን ያገኝበታል። ነገር ግን ተግሳጽን ከማይቀበል ምክርን ለማይሰማ ሰው ጥበብን አትናገር ።ጥበብ በአላዋቂዎች መንደር የተናቀች ናት በጠቢባን መንደር ግን ዋጋዋ ከነጭ እንቁ የከበረ ነው ስለዚህም እንቁዎቻችን በእርያዎች ፊት መጣል አይገባም በእግራቸው ረግጠው ክብሩን ያቃልሉታና። 

ቅዱሳን በሚያልፍና ጊዜያዊ ብልጭልጭ ዓለም ውስጥ እየኖሩ የማያልፈውን ኅቡዕ የሆነውን መንፈሳዊ ና ዘላለማዊ መኖሪያ በእምነት የተመለከቱ የእምነት አርበኞች ናቸው።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages