ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 15 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, September 25, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 15

 

በተባረከው ወር መስከረም በ15ኛው ቀን #የቀዳሜ_ሰማዕት_ቅዱስ_እስጢፋኖስ ፍልሰተ አፅሙ ነው፣ #የአቡነ_ገብረ_ማርያም_ዘሐንታ እና #አቡነ_ጴጥሮስ_ዘሃገረ_ጠራው ዕረፍታቸው ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቀዳሜ_ሰማዕት_ቅዱስ_እስጢፋኖስ
መስከረም ዐሥራ አምስት በዚች ቀን የዲያቆናት አለቃ የሰማዕታት መጀመሪያ ለሆነ ለቅዱስ እስጢፋኖስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ።
ይህም እንዲህ ነው ከአረፈበት ጊዜ ብዙ ዓመቶች ከአለፉ በኋላ ሦስት መቶ ዓመት ያህል ከዚያም የሚበዛ ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ ሲነግሥ የቀናች ሃይማኖትም ተገልጣ የሕያው እግዚአብሔር አምልኮት በሁሉ ሲዘረጋ ያን ጊዜ የቅዱስ እስጢፉኖስ ሥጋ በአለበት አቅራቢያ የገማልያል ቦታ በትምባል በኢየሩሳሌም በአንዲት ቦታ አንድ ሰው ይኖር ነበር። የዚያም ሰው ስም ሉክያኖስ ነው ተጋዳይ የሆነ እስጢፋኖስም ብዙ ጊዜ በሕልም ተገለጠለት እንዲህም ብሎ አስረዳዉ እኔ እስጢፋኖስ ነኝ ሥጋዬ በዚህ ቦታ ተቀብሮ አለ።
ያም ሉክያኖስ የሚባል ሰው የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ወደ ሆነው መጥቶ በራእይ ያየውን ይህን ነገር ነገረው ኤጲስቆጶሱም ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ያን ጊዜም ሁለት ኤጲስቆጶሳትን፣ ካህናትንና፣ የቤተ ክርስቲያንን ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋራ ይዞ ተነሣ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ በውስጡ ወዳለበት ወደዚያ ቦታ ደርሰው ሊቆፍሩ ጀመሩ ታላቅ ንውጽውጽታም ሆነ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ በውስጡ ያለበት ሣጥን ተገለጠ ከእርሱ እጅግ በጎ የሆነው የሽቱ መዓዛ ሸተተ።
በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስገና ሆነ በምድርም ሰላም ለሰው ነፃነቱ ይሰጠው ዘንድ በጎ ፍቃድ እያሉ ሲያመሰግኑ የመላእክትን ቃሎች ሰሙ ። እንዲህም መላልሰው ሦስት ጊዜ አመሰገኑ ኤጲስቆጶሳቱና ካህናቱም የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በያዘ ሣጥን ፊት ለጌታ ሰገዱ ከዚያም በኋላ ወደ ጽርሐ ጽዮን እስኪያደርሱት ብዙ መብራቶችን አብርተው በመያዝ በማኀሌት ምስጋና እየዘመሩ ተሸከሙት።
ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ በኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆነ የቊስጥንጥንያ ተወላጅ ስሙ እለእስክንድሮስ የሚባል ሰው ነበር ለቅዱስ እስጢፋኖስም ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን ሠርቶለት ሥጋውን አፍልሰው ወደርሷ ወስደው አኖሩት ከአምስት ዓመት በኋላም እለእስክንድሮስ አረፈ ሚስቱም በቅዱስ እስጢፋኖስ አስከሬን ጕን ቀበረችው። ከሌሎች አምስት ዓመቶችም በኋላ የእለእስክንድሮስ ሚስት የቧላን አስከሬን ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ይዛ ልትሔድ አሰበች ባሏንም ወደ ቀበረችው እርሱ ባሏ ወደ ሠራት ቤተ ክርስቲያን ሔደች የባሏ ሥጋ ሣጥን ግን የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በያዘ ሣጥን አምሳል ነበር በእግዚአብሔር ፈቃድ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሣጥን ወስዳ እስከ አስቃላን ከተማ ተሸከመችው ከዚያም ወደ ቊስጥንጥንያ ልትጓዝ በመርከብ ተሳፈረች።
በመርከብ ስትጓዝ ከሣጥኑ ጣዕም ያለው ምስጋናን የምትሰማ ሆነች እጅግም አድንቃ ያን ሣጥን ልታየው ተነሣች በውስጥ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ ያለበት ሣጥን እንደሆነ ተረዳች ይህም የሆነው ክብር ይግባውና በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነም አወቀች ወደ ኢየሩሳሌም ትመለስ ዘንድ አልተቻላትም ይህንንም ታላቅ ጸጋ ስለሰጣት ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገነች።
ወደ ቍስጥንጥንያ አገርም በደረሰች ጊዜ ያቺ ሴት ወደ ንጉሡ ሒዳ የቅዱስ እስጢፋኖስን ዜና ከእርሱ የሆኑትን ተአምራት ወደ ቍስጥንጥንያ አገር ወደብም እንደ ደረሰ ነገረችው ሰምቶም እጅግ ደስ አለው ንጉሡም ከሊቀ ጳጳሳቱና ከካህናቱ ከብዙ ሕዝቦችም ጋር ወጣ ከወደቡም በክብር አንሥተው ወደ መንግሥት አዳራሽ እስከ አስገቡት ድረስ በፍጹም ደስታ እየዘመሩና እያመሰገኑ ተሸክመውት ተጓዙ።
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእርሱ ተአምራትን ገለጠ በሠረገላ ሥጋውን ጭነው በሁለት በቅሎዎች በሚስቡት ጊዜ ቍስጣንጢንዮስ ከሚሉት ቦታም ሲደርሱ የቅዱስ እስጢፋኖስንም ሥጋ በዚያ እንዲያኖሩ ስለ ፈቀደ የሚስቡት በቅሎዎች ቆሙ። አልተንቀሳቀሱም በቅሎዎችንም ይመቷቸው ጀመሩ የቅዱስ እስጡፋኖስን ሥጋ በዚህ ሊያኖሩ ይገባል የሚል ቃል ከአንዱ በቅሎ ሰሙ ይህንንም ያዩና የሰሙ ሁሉም አደነቁ።
እግዚአብሔርንም አመሰገኑት የበለዓምንም አህያ ያናገራት እርሱ እነዚህን የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ የተሸከሙትን በቅሎዎች ያናገራቸው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ንጉሡም በዚያ መልካም የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ይህን የከበረና ንጹሕ የሆነ ዕንቈ ባሕርይ በውስጧ እንዲያኖሩ አዘዘ። ይኸውም ለተመሰገነና ለተባረከ ሐዋርያ የዲያቆናት አለቃና የሰማዕታት መጀመሪያ ለሆነ እስጢፋኖስ ሥጋው ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ጻድቁ አቡነ ገብረ ማርያም ምግባር ሃይማኖታቸው ከቀና፣ ትሩፋት ተጋድሎአቸው ከሰመረ ደጋግ ወላጆቻቸው ከአባታቸው ኒቆዲሞስ እናታቸው አመተ ማርያም በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ኅዳር 24 ቀን ተወለዱ፡፡ ዕደሜአቸው ለትምህርት ሲደር እነዚህ ደጋግ ወላጆቻቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማሩ አሳደጓቸው፡፡
አባታችን በልጅነታቸው የወላጆቻቸውን ላሞች እየጠበቁ ሳለ ከእለታት አንድ ቀን ጌታችን በወጣት አምሳል ተገለጠላቸውና ‹‹ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ለምን እንስሳትን ትጠብቃለህ ደቀ መዝሙሬ ጴጥሮስን ዓሣ ማጥመድን ትተህ ተከተለኝ እንዳልኹት በእንስሳት ፈንታ ሰውን ትጠብቅ ዘንድ …››› አላቸው፡፡ አባታችንም ይህንን በልቡናቸው ሲያወጡ ሲያወርዱ ለ2ኛ ጊዜ ጌታችን በሚያስፈራ ግርማ በእርሻ መካከል ተገለጠላቸው፡፡ ስለዚህም ነገር አባታችን ሲናገሩ ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወጣት አምሳል ሁለት ሰዎች ከእኔ ጋር ሳሉ በእርሻ መካከል ወደ እኔ መጣ፤ እነዚያም ከእኔ ጋር የነበሩት ሁለት ሰዎች ባዩት ጊዜ እጅግ ደንግጠው ከግርማው የተነሣ ወዲያና ወዲህ ወደቁ፡፡ በኋላም ተነሥተው ያዩትን መሰከሩ፡፡ ዳግመኛም በሦስተኛ መምጣት ጌታችን እንዲህ አለኝ፡- ‹ለምን ዘገየህ አብርሃምን ለአባቱ ርስት ለይቼ ያወጣሁት እኔ እንደሆንኹ አላወቅህምን?አለኝ፡፡" ከዚህም በኋላ አባታችን "እናት አባቱን ያልተወ ሊያገለግለኝ አይችልም" (ማቴ 10፥37) የሚለውን የጌታችንን አምላካዊ ቃል ሰምተው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ወጥተው በመሄድ ቀበት በምትባል ቦታ በዓት ሠርተው በጾም በጸሎት እየታደሉ መኖር ጀመሩ፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ያገለግላቸው ዘንድ አንዱን ነብር አዘዘላቸው፡፡ ሰዎችም ከአባታችን በረከትን ለመቀበል ወደ እርሳቸው ይመጡ ነበርና ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ምእመን ወደ አባታችን በመጣ ጊዜ አባታችንን የሚያገለግላቸው ነብር ሰውየውን ዘሎ ያዘው፡፡ ሰውየውም ‹‹አባታችን አድኑኝ›› እያለ ሲጮኽ አቡነ ገብረ ማርያም ከበዓታቸው ወጥተው ነብሩን በመስቀላቸው ቢባርኩት ኃይሉ ደክሞና ለቃላቸው ታዝዞ ሰውየውን ለቀቀው፡፡ አባታችንም ያንን ወጣት ያየውን ነገር ለማንም እንዳይነግር አዘዙት፡፡ አቡነ ገብረ ማርያም እንደ ሊቀ ነቢያት 40 ቀንና 40 ሌሊት እህል ሳይበሉ ውኃ ሳይጠጡ እየጾሙ ወንጌላትን ያነቡ ነበር፡፡ ከመጾማቸውም ብዛት ሰውነታቸው ፍጹም በደከመና አንደበታቸውም መናገር በሳናቸው ሰዓት የብርሃን እናቱ እመቤታችን ተገልጻላቸው ‹‹ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ይህን ያህል ገድል የምትጋደል ሰውነትህንስ የምትታስጨንቃት ለምንድነው?›› በማለት አጸናቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ረሀብና ጥሙ ጠፋላቸው፡፡
በአንደኛውም ቀን ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል ወደ አባታችን መጣ፡- ‹‹ገብረ ማርያም ሆይ በተክለ ሃይማኖት ወንበር ከተሾመ ከመርሐ ክርስቶስ እጅ የመላእክትን አስኬማ ትቀበል ዘንድ ወደ እርሱ ሂድ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ወደ ደብረ ሊባኖስ ከመሄዳቸው በፊት አቡነ መርሐ ክርስቶስ በደብረ ሊባኖስ ሆኖ ይህን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ዐውቆ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እነሆ ከፀሐይ ይበልጥ የሚያበሩ ሦስት ከዋክብት ቅዱሳን ይመጣሉ›› አላቸው፡፡ አቡነ መርሐ ክርስቶስም እንደተናገረው እነ አቡነ ገብረ ማርያም ደብረ ሊባኖስ ደረሱ፡፡ አቡነ መርሐ ክርስቶስም የምንኩስናን ልብስ አለበሳቸው፡፡
አቡነ ገብረ ማርያም ከመነኮሱ በኋላ ወደ በዓታቸው ተመልሰው ከበፊቱ ይልቅ በጾም በጸሎት ሲተጉ ጌታቸን አሁንም ተገለጠላቸውና ‹‹በጾም በጸሎት ብቻ ተወስነህ አትቀመጥ ሂድና ወንጌልን አስተምር፣ ድውያንን ፈውስ፣ ሙታንን አንሣ…›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ዳግመኛም በከበረ እስትንፋሱ እፍ አለባቸውና ‹‹መንፈስ ቅዱስን ተቀበል፤ ይቅር ያልካቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፣ ይቅር ያላልካቸው ኃጢአታቸው አይቀርላቸውም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር ያሰርከው በሰማያት የታሰረ ነው፤ በምድርም የፈታኸው በሰማያት የተፈታ ይሁን›› አላቸው፡፡ ጌታችን ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ‹‹ካህናት በሊቃነ ጳጳሳት አፍ ይሾማሉ አንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ አፍ ተሾምህ›› እንዳላቸውና እንደሾማቸው ሁሉ አሁንም አባታችን አቡነ ገብረ ማርያምን እንዲሁ ብሎ ራሱ ሾማቸው፡፡ አባታችንም እንደታዘዙት ልዩ ልዩ ተአምራትን እያደረጉ ድውያንን እየፈወሱ ሙታንን እያስነሡ ወንጌልን ዞረው አስተማሩ፡፡ ቂሐ ወደምትባል ምድር ገብተው ጎሽ ወደምትባለው ሀገርም ደርሰው ጣዖታትን የሚያመልኩትን የሀገሪቱን ሰዎች አገኟቸው፡፡ ሰዎቹም የሚያመልኩትን ትልቅ ዘንዶ በመስቀሉ ባርኮ ከገደለው በኋላ በውስጧ ወንጌልን እያስተማረ ድውያንን እየፈወሰ ሲቆይ ሰዎቹም አባታችንን ‹‹ቅዳሴ ቀድስልን›› አሉት፡፡ አባታችንም ስለዚህ ነገር ጌታችንን በጸሎት በጠየቁት ሰዓት "ሳትናዘዛቸውና ሳታጠምቃቸው አትቀድስላቸው" የሚል ቃል ከሰማይ ወደ አባታችን መጣ፡፡ ያንጊዜም ሰዎቹን ሁሉ ሰብስቦ በአብ በወልደ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸውና ቅዳሴ ቀድሶ አቆረባቸው፡፡
እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ግብጽ ከዚያም ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስትሰደድ በእግሯ እየሄደች በሞረት ዋሻ በአቡነ ዜና ማርቆስ ቦታ ግራርያ ከሚባል ቦታ ተቀምጣ እንደነበር የሐምሌው ድርሳነ ቅዱስ ዑራኤል ይናገራል፡፡ በኋላም ተጭነው ከእነ ልጇ በዚህ በአቡነ ገብረ ማርያም ገዳም በሆነ ቦታ ስታልፍ ጌታችን ለቅድስት እናቱ ‹‹ይህች ቦታ ሐንታ ትባላለች፣ በኋለኛው ዘመን በስምሽ የሚጠራ የእኔ ወዳጅና ታዛዥ የሆነ የታላቅ ጻድቅ ቦታ ትሆናለች›› ብሎ ስለነገራት በኋላም ትንቢቱ ደርሶ ጻድቁ ገዳማቸውን በዚሁ ቦታ ስለገደሙት ገዳሙ ‹‹አማን ደብረ ሐንታ›› ይባላል፡፡ ጻድቁ በመንዝና በመርሐ ቤቴ ከ1245-1268 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከ19 በላይ የተላያዩ አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል፡፡ ጾም ጸሎተኛ ባሕታዊ ከመሆናቸው በተጨማሪ የወንጌል ገበሬ፣ ጻድቅና ደራሲም ናቸው፡፡
አቡነ ገብረ ማርያም በጣም ከሚታወቁበት ድርሰታቸው አንዱ የማኅሌተ ጽጌን ድርሰት ከታላቁ ሊቅ ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ድርሰቱን በመዝሙረ ዳዊት መጠን 150 አድገው ደርሰዋል፡፡ አቡነ ገብረ ማርያምና አቡነ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌን በጥምረት ሊደርሱት የቻሉት አቡነ ገብረ ማርያም በወሎ ክፍለ ሀገር በወረኢሉ አውራጃ ልዩ ስሙ ደብረ ሐንታ በሚባለው ገዳም የሕግ መምሕር ሆነው በተሾሙበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህም ሁለት ቅዱሳን የዘመነ ጽጌ የማኅሌት አገልግሎትን ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር በአንድነት አግልግለዋል፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡- አንድ ዓመት አቡነ ገብረ ማርያም የክረምት መውጫና የዘመነ ጽጌ ዋዜማ በሆነው መስከረም 25 ቀን ከደብረ ሐንታ መጥቶ ደብረ ብሥራት አቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ገብተው ከመስከረም 25 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለውን የዘመነ ጽጌ የ40 ቀን አገልግሎት ከአቡነ ጽጌ ድንግል ጋር ፈጽመው ኅዳር 8 ቀን ወደ ደብራቸው ደብረ ሐንታ ይመለሳሉ፡፡
በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አቡነ ጽጌ ድንግል ከገዳማቸው ከደብረ ብሥራት ተነሥተው ወደ ደብረ ሐንታ ሄደው እንዲሁ እንደ አቡነ ገብረ ማርያም 40ውን ቀን አግልግሎ ይመለሳል፡፡ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን እንደዚህ እያደረጉ በየተራ አንደኛው ወደ ሌላኛው ገዳም እየሄዱ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ በፍጹም ፍቅርና በትሕትና አብረው ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡
ይኸውም በራሳቸው በአቡነ ገብረ ማርያም ገድል ላይ እና በአቡነ ዜና ማርቆስ ገድል ገጽ 72-73 ላይ በሰፊው ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ የሁለቱ ድርሰታቸው የሆነው ‹‹ማኅሌተ ጽጌ›› ድርሰት የእመቤታችንንና የልጇን የጌታችንን ሥጋዊ ስደት የሚገልጽ ሲሆን በጨማሪም ስደት የማይገባው አምላካችን ወደ አህጉራችን አፍሪካ ተሰዶ የሠራቸውን ድንቅ ድንቅ ተአምራትና የእመቤታችንን ንጽሕናዋን ቅድስናዋን አማላጅነቷን የሚያስረዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡
አቡነ ገብረ ማርያም አዲስ አፍልሰው በሠሯት ቤተ ክርስያን ውስጥ ልጆቻቸው ተሰበሰቡና ‹‹አባታችን ሆይ የት እናድራለን? ማረፊያን ያዘጋጅልን ዘንድ እግዚብሔርን ለምነው›› አሉት፡፡ አባታችንም ‹‹ይህ ሥራ ለእኔ አይቻለኝምና እናንተ ለምኑት›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አባታችን ሆይ አትበትነን›› ብለው ግድ አሉት፡፡ ልጆቹም ግድ ባሉት ጊዜ አባታችን ተነሥቶ ጸለየ፡፡ ስለዚህም ነገር ሲናገር አባታችን እንዲህ አለ፡- ‹‹ከዚህ ነገር አስቀድሞ በቁርባን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣና ይባርከኝ ነበር፣ እናቱ ድንግል ማርያምም ትባርከኝ ነበር፡፡ ስለዚህ ነገር ግን ጌታችን ተቆጣ፣ እምቢ አለኝ፡፡ ከእኔም ፊቱን መለሰ፡፡ እኔም ብዙ አለቀስኹ የእጁን ቡራኬ አጥቻለሁና፡፡ እናቱ ድንግል ማርያምም ፈጽሜ ሳለቅስ ባየችኝ ጊዜ ‹ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ለምን ታለቅሳለህ?› አለችኝ፡፡ እኔም እመቤቴ ሆይ ጌታዬና አምላኬ ፊቱን ከእኔ መልሷልና ስለዚህ አለቅሳለሁ አልኳት፡፡ እመቤታችን ማርያምም የተወደደ ልጇን ‹ልጄ ሆይ ወዳጅህ ገብረ ማርያምን በምን ሥራ አሳዘነህ?› አለችው፡፡ ጌታችንም ለድንግል እናቱ ‹እርሱ አሳዝኖኛል፣ የዮሴፍ ልጅ ያዕቆብ ‹ይህን ዓለም የሚወድ የእግዚአብሔር ጠላት ይሆናል› (ያዕ 4፡4) እንዳለ ከእኔ ፍቅር ይልቅ የዓለምን ፍቅር ወዷልና› አላት፡፡› እናቱ እመቤታችንም የተወደደ ልጇን ‹ልጄ ሆይ ወዳጅህ ገብረ ማርያምን አታሳዝነው ይቅር በለው ባጠባሁህ ጡቶቼ አምልሃለሁ› አለችው፡፡ ጌታችንም ይህን ጊዜ ቅድስት እናቱን ‹የላይኛውን ወይም የታችኛውን ይወድ እንደሆነ ጠይቂው› አላት፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም ከዚያ ቆሞ ነበርና ወደ ለእኔ ‹የላይኛው ያለህ መንግሥተ ሰማያትን ነው፣ የታችኛው ያለህ ይህች ዓለም ናት› አለኝ፡፡ እኔም ያንጊዜ ይህችን ዓለም አልፈልጋትም ነገር ግን ማረፊያ እንዲሰጠን በጸሎቴ የጠየቁት ልጆቼ ከሞቴ በኋላ ተስፋ እንዳይቆርጡ እንዳይበተኑም ብዬ ነው አለኩት፡፡ ጌታችንም ‹‹ገብረ ማርያም ሆይ ለምን ይህንን ታስባለህ? ለልጆችህ እኔ አስብላቸዋለሁና፡፡ ወዳጄ ዳዊት ‹የጻድቃን ልጆች ይባረካሉ፣ ክብርና ባለጠግነት በቤቱ ነው፣ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል› (መዝ 111፡33) ብሎ እንደተናገረ እኔ ለፍጥረት ወገን ሁሉ አስባለሁ› አለኝ፡፡ ይህንንም ብሎኝ ሰላሙን ሰጥቶኝ ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡››
አቡነ ገብረ ማርያም ያደረጓቸው ተአምራት ተነግረው የሚያልቁ አይደሉም፡፡ በብቸኝነት ሳለ በአንዲት አገር የሚኖር ልጁ የሞተበት ሰው የልጁን አስክሬን ወደ አባታችን አምጥቶ በፊታቸው አስቀመጠውና ‹‹አባታችን ሆይ ልጄ እንደሞተ ተስፋዬ ሁሉ ጠፍቷልና አሁን ብትወድ ከሞት አንሣው ባትወድ ግን እዚሁ ቅበረው›› እያለ አቀሰባቸው፡፡ አባታችንም የሰውየውን ሁኔታውን አይተው ፈጽመው አለቀሱ፡፡ ልቡናቸውም ታወከባቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ይጸልዩ ዘንድ ተነሡና ‹‹…በተቀበረ በ4ኛው ቀን አልዓዘርን ያስነሣኸው አሁንም ይህን ሕፃን አስነሣው…›› ብለው ከጸለዩ በኋላ የልጁን እጅ ይዘው ‹‹በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሥ›› ብለው እፍ አሉበት፡፡ ያንጊዜም ሕፃኑ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ አፈፍ ብሎ ተነሣ፡፡ ለአባቱም ‹‹ልጅህን ውሰድ ፈጣሪዬ አስነሣልህ›› ብለው ሰጡት፡፡ ሰውዬውም ከአግራቸው ሥር ሰግዶ የእግራቸውን ትቢያና ሰውነታቸውን ሁሉ ሳመው፡፡ ልጁንም ይዞ ፈጽሞ ደስ እያለው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
በአንዲት ሀገርም አንድ ልጅ ብቻ ያላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ልጁም ወደ አባታችን እየመጣ ‹‹አመንኩሱኝ›› እያለ ሁልጊዜ ይጠቃቸው ነበር፡፡ አንድ ቀንም እንዲሁ መጣና ‹‹አባት ሆይ ካላመነኮሱኝ ወደሌላ ሰው ዘንድ ሄጄ እመነኩሳለሁ›› አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው የፍላጎቱን ፈጸሙለትና አመነኮሱት፡፡ ወላጅ እናቱም መጥታ ልጇ የምንኩስናን ልብስ እንደለበሰ ባየች ጊዜ እያለቀሰች ሄደችና ራሷን ወደ ገደል ውስጥ ጨመረች፣ ሞችም፡፡ ሰዎችም ተሰብስበው አለቀሱላትና አስክሬኗን ተሸከመው ይቀብሯት ዘንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዷት፡፡ ሰዎችም ወደ አባታችን መጥተው ‹‹ሴትዮዋ ከመቀበሯ በፊት መጥተው ይዩዋት›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ወደ አስክሬኗ አልመለከትም›› አሉ፡፡ እነርሱም በእግዚአብሔር ስም ባማሏቸው ጊዜ አባታችን አስክሬኗ ወዳለበት መጡና አዩዋት፡፡ በማግሥቱም ከገነዟት በኋላ አባታችን ከመዝገበ ጸበላቸው በአፏና በጆሮዎቿ ጸበልን ጨመሩባት፡፡ በፊቷም ‹‹እፍ›› አሉባትና ‹‹በጌታዬ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሺ›› አሏት፡፡ ያንጊዜም አፈፍ ብላ ከሞት ተነሣች፡፡ አባታችን ከሞት ያስነሷቸው ሰዎች እንዲሁ በጣም ብዙ ናቸው፡፡
27 ዓመት ሙሉ ሆዱን የታመመ አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አቡነ ገብረ ማርያም በመምጣት ጉዳዩን ሳይነግራቸው አንድ ቀን ቆየ፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን የመጣበትን ጉዳዩን በጠየቁት ጊዜ ‹‹አባት ሆይ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ታመምኩ፣ እህል አልበላም ውኃም አልጠጣም›› አላቸው፡፡ አባታችንም ሆዱን ይዘው በእጃቸው አሻሹትና ምራቃቸውን ቀቡት፡፡ በዚህም ጊዜ በሆዱ ውስጥ ልዩ ልዩ ዓይነት ድንፆች ተሰሙ፡፡ በውሻ ድንፅ አምሳል፣ በድመት ድንፅ አምሳል፣ በዝንጀሮ ድንፅ አምሳልና በቁራዎቸ ድንፅ አምሳል ጮኸ፡፡ አባታችንም ልጁን ‹‹ልጄ ሆይ እግዚብሔር አድኖሃልና ወደ ቤትህ ተመለስ›› አሉት፡፡ ልጁም ‹‹አባቴ ሆይ ተመልሼ ወደቤቴ አንገባም እስከ ዕለቴ ሞቴ ድረስ አልመለስም ከአንተም አልለይም›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹በዚህ መኖር ክፍልህ አይደለምና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለፈወሰህ ወደ ቤትህ ተመለስ›› አሉት፡፡ በደስታም ወደ ቤቱ ሄደና በሌላ ጊዜ ከብዙ ሰዎች ጋር መጥቶ አባታችን ያደረጉለትን ተአምር ለሕዝቡ ሁሉ መሰከረ፡፡
አቡነ ገብረ ማርያም በእንዲህ ዓይነት አገልግሎት በተአምራታቸው ድውያንን እየፈወሱ ሙታንን እያስነሡ በወንጌል ቃል የነፍስን ቁስል እየፈወሱ የጌታችንንም መከራውን እያሰቡ ራሳቸውን ከመከራው ተሳታፊ በመሆን ብዙ ከደከሙ በኋላ በሥጋ ሞት ከማረፋቸው በፊት ቅዱሳን መላእክት ነጥቀው ገነትንና ሲኦልን አሳይተዋቸዋል፡፡ ጌታችንም በመጨረሻ ተገልጦላቸው ‹‹ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ከፍጹም ድካምና መታከት ከኃዘንም ታርፍ ዘንድ ወደ ፍጹም ደስታና ወደ ዘላለማዊ ዕረፍት ወደ እኔ ና›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹ጌታዬ ሆይ ምን ዋጋ ትሰጠኛለህ?›› ቢሉት ጌታችም ብዙ አስደናቂ ቃልኪዳኖችን ሰጣቸው፡፡ ‹‹እንደፈጠርኩህ አግኝቼሃለሁና ክብርህ እንደ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ይሁንልህ›› አላቸውና በቅዱሳን እጆቹ ዳስሷቸው ቢስማቸው ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለይታለች፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን ደግሞ ጠራው ከሚባል አገር ለከበረ ጻድቅ አባት አባ ጴጥሮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህም ቅዱስ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተሰጠ የስእለት ልጅ ነው። በአደገም ጊዜ ለታላቅ ተጋድሎ ክልቡ በቆራጥነት ተነሣ በቀንና በሌሊትም በጾም በጸሎት ተወስኖ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ሆነ። ሰው የሚመገበውንም ምንም አይመገብም በዱር ያገኘውን ጥቂት ሣርን ይመገባል እንጂ።
ደገኛው ምግቡ ግን ክብር ይግባውና የጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ስም ማመስገን ነው። በዚህም ምግባቸው የእግዚአብሔር ምስጋና የሆነ መላእክትን መሰላቸው።
አሎን በሚባል የወንዝ ውኃ ላይም ይመላለስ ዘንድ ተገባው እግሮቹም አይርሱም ሥጋ እንደ ሌለው መንፈስ እስከ ሚሆን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ከችግር ብዛትና ከሚለብሰው የብረት ልብስ ክብደት የተነሣ ሥጋው እጅግ ደርቆ የረቀቀም ሁኖ ነበርና በእንዲህ ያለ ተጋድሎም እግዚአብሔርን ከአገለገለው በኋላ ወደርሱ ሔደ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages