ቅዱስ መስቀል - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, September 25, 2022

ቅዱስ መስቀል

 

 

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ታላቅ ክብር ይሰጠዋል፡፡ የመስቀል በዓልም ከዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ ሲሆን በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ይከበራል፡፡  በዓሉም ከዋዜማው መስከረም 16 ጀምሮ ደመራ በመደመር ይከበራል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል ቅድስት ቤተክርስቲያን በደማቅ ሁኔታ በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ በዓል በማስመልከት በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የመስቀልን ምንነት፣ የመስቀልን አገልግሎት፣ የመስቀልን ታሪክ፣ የመስቀልን ክብርና አንዳንድ ተያያዥ ጉዳዮች እንዳስሳለን፡፡

የቅዱስ መስቀል ምንነት: መከራ ክርስቶስ፣ መከራ ክርስትና፣ ዕፀ መስቀል

በቤተክርስቲያን አስተምህሮ “መስቀል” የሚለው ቃል ሦስት መሠረታዊ ቁም ነገሮችን ያመለክታል፡፡ የመጀመሪያው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከሞተ ነፍስ ለማዳን ሲል የተቀበለው መከራና የከፈለው መሥዋዕትነት (የክርስቶስ መከራ መስቀል) ነው፡፡  ሁለተኛው  ደግሞ በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥም ልዩ ልዩ ዓይነት መከራም (መከራ መስቀለ ክርስቲያን) ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል ነው፡፡ በሦስቱም ቁም ነገሮች ነገረ መስቀል (የመስቀሉ ነገር) ከክርስትና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ መስቀል የሰላማችንና የድኅነታችን የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።

የቅዱስ መስቀል አገልግሎት:  የድኅነት ኃይል፣ የእምነት ዓርማ

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋጋ የከፈለበት ቤዛ ዓለም የተከናወነበት እንደመሆኑ መስቀል በቤተ ክርስቲያናችን በሁሉ አገልግሎት ሰፊ ድርሻ ያለውና እንዲሁም በንዋያተ ቅድሳት ላይ የሚውል አቢይ ምልክት ነው:: በነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት “ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው (መዝ 59:4) እንደተባለ ለክርስቲያኖች መስቀል የጠላት ሰይጣን ተንኮል የከሸፈበት ስለሆነ ከአንገታችን፣ ከእጃችን ሳይለይ የክርስቶስን ቤዛነት የምንመሰክርበት የድኅነታችንም ኃይል የተገለጠበት ነው:: አጋንንት የመስቀሉን ምልክት ባዩ ጊዜ ይንቀጠቀጣሉ፤ ካደሩበት ሰው ላይም በፍጥነት ይወጣሉ፡፡ ምእመናን በመስቀሉ ስንዳሰስ ከልዩ ልዩ ደዌ እንፈወሳለን፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልግ ነገር አለ፡፡ ቤተክርስቲያንና ክርስቲያኖች ቅዱስ መስቀል ስንገለገልበት የሕሊናችን ትኩረት በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ ቤዛ የሆነን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ የመስቀሉ ምልክትነት (ዓርማነት) ላይ ነው እንላለን እንጂ የመስቀሉን ቁሳዊ አካል (Physical structure) ላይ አይደለም የሚሆነው፡፡ መስቀል ከእንጨትም ተሠራ ከእንቁ ትኩረታችን መሆን ያለበት ምልክትነቱ፣ ዓርማነቱ ላይ ነው፡፡ ይህም በቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ህይወት የተገለጠ ህያው ምስክር ነው፡፡ መስቀልም የድኅነታችን ኃይል፣ የእምነታችን ዓርማ፣ የቤተክርስቲያናችን ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ስለዚህም የመስቀል ምልክት የሃይማኖታችን መገለጫ እንጂ ለሥጋዊ ሰውነታችን ማጌጫ አይደለም፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ባህል የመድኀኒታችን የክርስቶስ መስቀል በብዙ ተግባራት ላይ በምልክትነት ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል፡፡ ለምሳሌ በየሸማ ልብሶች፤ እንደዚሁም በጆሮ፣ በአንገት፣ በእጅና ሌሎችም ጌጣጌጦች ላይ የመስቀል ምልክት አለ፡፡ ክርስቲያን ልጃገረዶች (በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል) በግንባራቸው፣ በጉንጫቸው፣ በአንገታቸው፣ በደረታቸውና በእጃቸው ላይ በመስቀል ቅርፅ እየተነቀሱ እምነታቸውን ይመሰክሩበታል፡፡ ክርስቲያኖች ከዚህ ዓለም በሞት ስንለይም በመቃብር ሣጥናችን ወይም በሐውልቶቻችን ላይ የመስቀል ምልክት ይቀመጣል፡፡ በቤት ውስጥም ስንተኛና ከእንቅልፋችን ስንነቃ ፊታችንንና መላ ሰውነታችንን በትእምርተ መስቀል እናማትባለን፤ አባቶችና እናቶችም ውሃ ሲቀዱ፣ ሊጥ ሲያቦኩ፣ እንጀራ ሲጋግሩ፣ ምግብ ሲቈርሱ፣ ወዘተ በመስቀል አማትበው ነው፡፡ በአጠቃላይ መስቀል ብዙ ነገር ነው፤ መስቀል በክርስትና ሕይወት ውስጥ በሚደረጉ ተግባራት ኹሉ ያለው ድርሻ ጕልህ ነው፡፡

የቅዱስ መስቀል ታሪክ: ከደብረ ቀራንዮ እስከ ደብረ ከርቤ

የቅዱስ መስቀሉ መቀበር በብሉይ ኪዳን መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ መሣርያ ነበር፡፡ በደላችንን ሊያጠፋ የመጣው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ33 ዓ.ም ለሰው ልጆች ሲል በመስቀል ተሰቀለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖረ፡፡

የቅዱስ መስቀሉ ከተቀበረበት መውጣት፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በ327 ዓ.ም) የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ቅድት ዕሌኒ በዕጣን ጢስ አመልካችነት መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት ቍፋሮ ያስጀመረችበትን የመታሰቢያ በዓል የደመራ በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡ በሀገራችን መስቀል የሚከበርበትን ጊዜ በማስመልከት ሁለት አይነት ትውፊት አለ፡፡ ጎንደር ትግራይና ኤርትራ እንዲሁም በገጠራማው የጎጃምና የወሎ ክፍሎች ደመራ የሚለኮሰው መስከረም 17 ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ መስከረም 16 ቀን ለ17 ዋዜማ ምሽት ላይ ይከበራል፡፡ የዚህን ልዩነት መነሻ መተንተን የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ባይሆንም ቅዱስ መስቀልን ለማግኘት ደመራ ተሰርቶ የተለኮሰው መስከረም 16 ለ 17 አጥቢያ እንደሆነ አባቶቻችን ያስተምራሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት አንዳንዱ አካባቢ በዋዜማው ሌላ አካባቢ ደግሞ በዕለቱ ያከብራሉ፡፡ በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን ደመራ ደምረው በመለኮስ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት በዐደባባይ ያከብሩታል፡፡

ቅድስት እሌኒ ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ. ም. ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ተቈፍሮ የወጣበት መጋቢት 10 ቀንም በቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በተጨማሪም መስከረም 17 ቀን ንግሥት ዕሌኒ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበትን የመታሰቢያ በዓል ታቦት አውጥተው ዑደት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ያከብሩታል፡፡ በ327 ዓ.ም የጌታን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ መስቀል በቅድስት እሌኒ ከተቀበረበት ከወጣና በክብር ለረጅም ዓመታት በኢየሩሳሌም ከተቀመጠ በኋላ ዐረቦች ኢየሩሳሌምን በመውረራቸው ምክንያት በአረማውያን እጅ እየተማረከ ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር ሲንከራተት ቆይቷል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖችም በመስቀሉ መማረክ ያዝኑና ይበሳጩ ስለነበር ጦራቸውን አሰልፈው መስቀሉ ወደሔደበት ሀገር በመዝመት ጦርነት ያካሔዱ ነበር፡፡

ቅዱስ መስቀሉን እንደተከፋፈሉት በ778 ዓ.ም አራቱ አኅጉራት ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ በአራቱ የመስቀሉ ክንፍ የተያያዙት ምልክቶችን በማንሳት የተከፋፈሉ ሲሆን በወቅቱ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ዐረቦች በእስክንድርያ ለሚኖሩ አባቶች የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሮቹ እና እጆቹ ተቸንክረው የተሰቀለበትን ሙሉ መስቀል ላኩላቸው፡፡ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስም በክብርና በጥንቃቄ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡ ይህም የመስቀሉ ክፋይ (ግማደ መስቀል) በእስክንድያ እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በክብር ተቀምጦ ነበር፡፡

የግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መግባት፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የቻለበት 1394 ዓ.ም. ዐፄ ዳዊት ሁለተኛ በነገሡ በ29ኛ ዓመታቸው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን 47ኛው ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል  በወቅቱ የነበረው የግብጽ ፈርዖን አሠራቸው ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን “የእኔን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ መኖር በግብጽ መኖር አትችሉም” ብሎ ከአቅማቸው በላይ ግብር ጣለባቸው፡፡ መከራው የጸናባቸው የግብጽ ክርስቲያኖች “ከደረሰብን መከራና ሊቀጳጳሳችንን ታስፈታልን ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተማጽነናል” ሲሉ ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው፡፡ አጼ ዳዊትም ወታደራቸውን ወደ ግብፅ አዘመቱ፡፡ በወታደሩም ኃይል የዓባይን ወንዝ ለመገደብ ተነሱ፡፡ ይህን የሰሙ የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን እልጋዴን መኳንቱን ሰብስበው “ምን ይሻለናል ብለው ምክር ያዙ” የዐባይን ወንዝ ከምናጣ “ሊቀጳጳሱን አቡነ ሚካኤልን እንፈታለን በክርስቲያኖችም ላይ መከራ አናደርስም” ብለው ቃል በመግባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን ሁለት እልፍ ወቂት ወርቅ እጅ መንሻ አስይዘው ለዐፄ ዳዊት አማላጅ ላኩ፡፡

ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም “ብርና ወርቅ አልፈልግም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ነው የምፈልገው” አሏቸው፡፡ የሀገራችን ሕዝብ በውኃ ጥም ከሚያልቅ ብንስማማ ይሻለናል ብለው መስከረም 10 ቀን 1395 ዓ.ም. ከመስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ጨምረው ሰጧቸው፡፡ መስከረም 10 ቀን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ይከበራል፡፡ ዐፄ ዳዊት መስከረም 10 ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከግብፃውያን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ተቀጸል ጽጌ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡

የመስቀሉ በመስቀለኛ ቦታ መቀመጥ ከዐፄ ዳዊት በኋላ በቦታቸው የተተኩት ዐፄ ዘርዐያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ራዕይ በማየታቸው መስቀሉን በ1443 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በተለያዩ ቦታዎች ለማሳረፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ በደብረ ብርሃን፤ በሸዋ ደርሄ ማርያም፤ በጨጨሆ፤ በአንኮበር፤ በመናገሻ አምባ፤ በእንጦጦ፤ ወዘተ አሳርፈውት አልተሳካላቸውም፡፡ በመጨረሻም መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም. በራዕይ በተነገራቸው ቅዱስ ስፍራ በግሸን ደብረ ከርቤ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አኑረውታል፡፡ መስከረም 21 ቀን ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በታላቅ በዓለ ንግሥ ያከብሩታል፡፡  በአጼ ዳዊት እግር የተተኩት ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል /መስቀሌን በመስቀልያ ስፍራ አስቀምጥ/” የሚል ራእይ በተደጋጋሚ እግዚአብሔር አሳያቸው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉት መልከዐ ምድር ውስጥ የመስቀል ቅርጽ ያለው የቀራንዮ አምሳል የሆነ ቦታ ከፈለጉትና ካጠኑ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል አሁን ግሼ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም ደብረ ከርቤ አሁን እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ቦታ ላይ እንዲያርፍ አደረጉ፡፡

አንዳንድ ወገኖች “መስቀሉን ለምን በዚያ አሳረፉት? ለምን ዛሬ ለሰዎች እንዲታይ ሆኖ አልተቀመጠም?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡  የመስቀሉ ጠላቶች የሆኑት አይሁድ መስቀሉ ድውይን ስለፈወሰ ሙታንን ስላስነሳ ሰዎች እንዳይድኑበት በተንኮል ነበር የቀበሩት፡፡ የክርስቶስ የክብር ዙፋኑ በሆነው መስቀል ላይም ቆሻሻ እንዲደፋበት አድርገዋል፡፡  የመስቀሉ ወዳጆች የሆኑት ኢትዮጵያውያን አባቶች ግን መስቀሉን በመስቀለኛ ቦታ በክብር ነው ያሳረፉት፡፡ በመስቀለኛው ስፍራም ያሳረፉት በየአድባራቱ አዙረው ምድሪቱን ካስባረኩ በኋላ ከፈጣሪ በተሰጣቸው ትዕዛዝ ለመስቀሉ በተፈቀደው ቦታ በግሸን በደብረ ከርቤ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ ጊዜ ሲማረክ የነበረው መስቀልን በክብር ተጠብቆ እንዲቆይ በመስቀለኛው ቦታ አሳረፉት፡፡

የቅዱስ መስቀል ክብር

በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘን ክርስቲያኖች መስቀልን የምናከብረው በመስቀሉ ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ብዙ ነገሮችን ስላገኘን ነው። በክርስቶስ ቤዛነት ሞት ስለተሻረ አጥተነው የነበረውን ሕይወት አግኝተናል። ስለዚህ ነው “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፤” የተባለው። 1ኛ ቆሮ.15፥22። የሰው ልጅ ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ክርስቶስ ሥጋውን የሕይወት እንጀራ አድርጎ በመስቀል ላይ ሰጠን። ይህንንም “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ /የወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን/ ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤” ሲል አረጋግጦልናል። ዮሐ.6፥53-54። 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም፤” ብሎ እንደተናገረ ፍጹም የሆነውን ሰላም የሰጠን በመስቀል ላይ ነው። ይህንንም፡- ሞትን በኃይሉ ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል። ዮሐ.14፥27፤ 20፥19፣26። በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ አርጅቶ የነበረው ሰውነታችን አዲስ የሆነው በመስቀል ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን /ሰውነታችን/ ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን።” ያለው ሮሜ.6፥6። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርቶስ በመስቀሉ ላይ በከፈለው ቤዛነት ከራሱ ጋር አስታረቀን (ታረቀን)፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷል፤” ብሏል። ቆላ.1፥20።

መስቀልን ስናከብር አንዳንዶች ባለማወቅ ወይም እውነተኛውን የወንጌል አስተምህሮ ባለመረዳት “አባትህ የተገደለበትን መሣርያ እንዴት ታከብራለህ?” የሚል አንድምታ ያለው ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ ይህም ስለክርስቶስ ስቀለት ያላቸውን ትክክለኛ ያልሆነ ግንዛቤ ያነፀባርቃል፡፡ ምክንያቱም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ሲል በመስቀል ላይ የተሰቀለው በራሱ ፈቃድ (በፍቅር) እንጂ እነዚህ ወገኖች እንደሚያስቡት አይሁድ አስገድደውት አይደለም፡፡ መስቀሉም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስና በእርሱ ምክንያት የመጣብን ሞት የተሸነፉበት ነው፡፡ መስቀሉ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሰላምን ያደለበት ነው፡፡ መስቀሉ የክርስቶስ የክብር ዙፋኑ ለእኛም የድል ዓርማችን ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ለአርአያነትና ለቤዛነት የመጣው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ጠላትን ድል አድርጎ ቤዛ የሆነን እናንተም በዚህ መስቀል ጠላታችሁ ዲያብሎስን ድል አድርጉበት ብሎ አርአያ ሊሆነንም ጭምር ነው፡፡ እውነተኛዋ ክርስትናም የምታሸንፈው በመግደል ሳይሆን በመሞት፣ በማጥቃት ሳይሆን መከራ በመቀበል፣ በማሳደድ ሳይሆን በመሰደድ፣ በማስገደድ ሳይሆን በማስወደድ፣ በክርክር ሳይሆን በፍቅር ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሀቸው ወዳጆችህም እንዲድኑ” (መዝ. 59፡4) እንዳለ ቅዱስ መስቀል እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ምዕመናን የተሰጠ ልዩ የድኅነት ምልክት ነው፡፡

የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ሊቁ አባታችን ቅዱስ ኤራቅሊስ በሃይማኖተ አበው “እግዚአብሔር ያገለገለባት መቅደስ ወዮ እንደምን ያለች ናት?!” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ 48፡17) ብሎ እንዳመሰገናት እንደ እመቤታችን ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ያገለገለበት ወገኖቹንም ወደ ጽድቅ የመለሰበት የክብር ዙፋኑ (ማቴ. 20፡21) ቅዱስ መስቀል ወዮ እንደምን የከበረ ነው?! ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ/ የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት (በቆሙበት) ቦታ እንሰግዳለን” (መዝ. 131፡7) እንዳለ ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን፡፡ የእግዚአብሔር ማደሪያ በመሆኗ ምድራዊት ጽዮን በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመሰገነችና የጸጋ ስጦታ ምንጭ መሆኗ እንደተነገረ፣ ተራሮችም የእግዚአብሔር ክብር ሲገለጥባቸው “ቅዱስ” (2ኛ ጴጥ 1፡18) እንደተባሉ ከዚያ በበለጠ ክብር የድኅነታችን ምስጢር የተፈጸመበትን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት መገለጫና ዘላለማዊ መቅደስ ቅዱስ መስቀልን እናከብረዋለን፡፡ ምልክታችን፣ አርማችን አድርገነው እንኖራለን፡፡ ምልክትና አርማ ሲባል ግን እንደምድራውያን ሰንደቆች ኃይል የሌለው ተዓምራትን የማያደርግ ሳይሆን እንደ ሙሴ በትር ሰይጣንን የሚረታ (ዘፀ. 14፡16)፣  ቅዱሳን መላእክት ከመስቀሉ ደመ ማኅተም የተነሳ ጠላት ዲያብሎስን እንዳሸነፉት ምዕመናንን የሚያጸና፣ የሚረዳ (ራዕይ 12፡11) ሰማያዊ አርማ ነው፡፡ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለቅዱስ መስቀል ልዩ ክብር ትሰጣለች፡፡ በጸሎቷ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ የባህርይ፣ አምላክን በድንግልና ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የጸጋ ምሥጋና ካቀረበች በኋላ “…ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም ምሥጋና ይገባል፡፡” እያለች ታከብረዋለች፡፡ የመስቀሉ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

 

 

 

 

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages