ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, September 21, 2022

ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ

 


 ግንቦት ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ዲያቆን ፋሲል በጋሻው

በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣው ኢትዮጵያዊ ያሬድ በሰማያዊው ልዩ ጣዕመ ዜማ ምሳሌ የሆነ ቅዱስ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ የተወለደው ሚያዝያ ፭ ቀን በ፭፻፭ ዓ.ም በአክሱም ከተማ ከአባቱ ከይስሐቅ እና ከእናቱ ከታውክልያ ነበር። ሆኖም በተወለደ በ፯ ዓመቱ አባቱ ስለሞተ እናቱ ለአጎቱ ለጌዴዎን እንዲያሳድገውና እንዲያስተምረው አደራ ሰጠችው፡፡ ያሬድ ከአጎቱ ዘንድ መዝሙረ ዳዊት በሚማርበት ጊዜ ስለሚቆጣውና ስለሚገርፈው መታገሥ ተስኖት ማይኪራህ ወደምትባል ቦታ ሄዶ ተደበቀ፡፡

በዚያም በአንዲት ዛፍ ሥር ተጠግቶ አርፎ በነበረበት ሰዓት አንድ ትል የዛፍ ፍሬ ለመብላት ዛፉ ላይ ለመውጣት ስድስት ጊዜ ሲወድቅ ሲነሣ ከቆየ በኋላ በሰባተኛው ከዛፉ ላይ ወጥቶ የዛፉን ፍሬ ሲበላ ተመለከተ፡፡ ቅዱስ ያሬድ የትሉን ተስፋ አለመቁረጥና ከፍተኛ የሆነ ትጋቱን እንዲሁም ወደላይ ለመውጣት ብዙ ጊዜ እየሞከረ ቢወድቅም ከዓላማው ሳይናወጥ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ ያሰበው እንደተፈጸመለት ተመልክቶ ‹‹ሰውነቴ ሆይ ግርፋትን ለምን አትታገሽም? መከራንስ ለምን አትቀበይም?›› ብሎ ሰውነቱን ከገሠጸ በኋላ ወደ መምህሩ ተመልሶ ‹‹አባቴ ሆይ ይቅርታ አድርግልኝ! እንደቀድሞ አስተምረኝ›› አለው፡፡ መምህሩ ጌዴዎንም ተቀብሎ ያስተምረው ጀመር፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ በአጥቢያው በምትገኝ የአክሱም ጽዮን ቤተክርቲያን ዘወትር እየሄደ ‹‹ዕውቀትና ጥበብ የሚገልጽ የጌታዬ እናቱ እመቤቴ ሆይ! ዓይነ ልቦናዬን ያበራልኝ ዘንድ ለምኝልኝ›› እያለ ይለምን ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የዕውቀት ጽዋ ገልጾሎት በአንድ ቀን ፻፶ መዝሙረ ዳዊት፣ መኃልየ ነቢያት፣ መኃልየ ነቢያት፣ መኃልየ ሰሎሞንና ሌሎችን ትርጓሜ መጻሕፍት የብሉያትና ሐዲሳትን ትርጓሜ መጻሕፍትን ዐወቀ፡፡ (ያሬድና ዜማው ገጽ ፳)

እግዚአብሔርም በሰማያዊ ዜማ በምድራውያን ሰዎች ሊመሰገን በወደደ ጊዜ ቅዱስ ያሬድን ሦስት አዕዋፍ ግእዝ፣ ዕዝል እና አራራይ የሚባሉን የዜማ ስልቶች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት አስተምረውታል፡፡ ወደ በሰማይም በመንፈስ ቅዱስ በመነጠቅ ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን ልዩ በሆነ ጣዕመ ዜማ ሲያመሰግኑ ሰምቶ ወደ ምድር ተመለሰ፡፡ ከዚያም በአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ከታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ አምላኩን እግዚአብሔርን ‹‹ዋይ ዘሰማኩ በሰማይ ዘመላእክትግናይ፣ በሰማያት የሰማሁት የመላእክት ምስጋና ምን ይደንቅ! ምን ይረቅ!›› በማለት በዜማው አመስግኖአል፡፡ ይህንንም በሰማያዊት ኢየሩሳሌም የሰማውን የመላእክትን ዜማ ለደቀ መዝሙር አስተምሮአቸዋል፡፡ (ያሬድ እና ዜማው ገጽ ፳፫፣ ምዕራፍ)

ቅዱስ ያሬድ ሰማያዊ ዜማ በሚያዜምበት ጊዜ ካህናቱ፣ ንጉሡና ምእመናን አዲስ ነገር ሆነባቸው ከዚያም ‹‹እንዴት እንቀበለው? ምልክት ሳናገኝ ብለው›› ማሰብ ሲጀምሩ ንጉሡ አምላካችን ይግልጽልን ብለው ከታኅሣሥ አንድ ቀን እስከ እሑድ ድረስ ሕዝቡ ሱባዔ እንዲይዝ አወጁ፡፡ ከዚያም ከሰኞ ዕለት ጀምረው ነበርና ከሰኞ እስከ እሑድ አንድ ሱባዔ ምሕላ ይዘው በየቀኑ የአክሱም ጽዮን ማርያምን ቤተ ክርስቲያን እየዞሩ ዐራት መቶ እግዚኦታና ዐርባ አንድ በእንተ ማርያም እያደረሱ ምሕላውን አካሔዱ፡፡ በሰባተኛው ቀን እሑድ ምሕላውን ጨርሰው ሲያሳርጉ ጌታ በዕለተ ዐርብ እንደተሰቀለ ሆኖ በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ ተገለጸ፡፡ ከዚህም አያይዞ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ዘበመስቀሉ ተቀነወ ወበነቢያት ተሰብከ መላእክት ወሊቃነ መላእክት ሰብሕዎ ኪያሁ ንሰብክ መድኅነ›› ብሎ ነገረ መስቀሉን በማውሳት የወልድ ምሳሌ በሆነው በዕዝል ዜማ ዘመረ፡፡ ትርጓሜውም ‹‹በነቢያት ትንቢት የተነገረለትና በመስቀሉ ላይ የተቸነከረው ጌታ መላእክትና የመላእክት አለቆች አመሰገኑት፤ እኛም እርሱ መድኃኒት እንደሆነ እንናገራለን›› ማለት ነው፡፡ በዚህ በተገለጸው ምስክርነት መሠረት ዜማው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ መሆኑ ታምኖ ከዚያን ዕለት ጀምሮ የቅዱስ ያሬድ ዜማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ መገልገያ ሆነ፡፡ (ያሬድ እና ዜማው ገጽ ፳፬)

ቅዱስ ያሬድ በግእዝ፣ በዕዝል በዓራራይ ዜማ በዝማሜ እያመሰገነ በነበረበት ጊዜ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀል በዜማው ተመስጠው ዓይን ዓይኑን እያዩ ሳያዉቁት የቅዱስ ያሬድን እግር በያዙት የብረት ዘንግ ወጉት፡፡ ሁለቱም በተመስጦ ስለነበሩ የሆነውን ነገር አላስተዋሉትም ነበር፡፡ ዜማው አብቅቶ ሁለቱም ከተመስጧቸው ሲነቁ ዘንጋቸው በቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ተሰክቶ ብዙ ደም ፈሶት ነበር፡፡ ንጉሡም ደንግጠው እጅግም አዝነው ‹‹ደምህን አፍስሻለሁና የምትፈልገውን ማንኛውንም ነገር ጠይቀኝ እሰጥሃለሁ›› ሲሉ ቃል ገቡለት፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹የምለምነው አንድ ነገር አለ፤ እርሱን ፈጽምልኝ›› አላቸው፡፡ ‹‹የፈለከውን ጠይቅ ፈቅጄልሃለሁ›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹እስካሁን እግዚአብሔር በፈቀደልኝ መሠረት በዚህ ከተማ ከእርሰዎ ጋር ቆይቻለሁ፡፡ ብዙ ደቀ መዛሙርትንም ተክቼያለሁ፡፡ ከእንግዲህ በኋላ የቀረኝን ዘመን በጸሎትና በብሕትውና መኖር እንድችል ከከተማው ራቅ ወዳለ ቦታ ሔጄ ፈጣሪዬን ማገልገል እፈልጋለሁ›› ብሎ የንጉሡን ፈቃድ ጠየቀ፡፡ አፄ ገብረ መስቀልም የቅዱስ ያሬድን ቃል ሰምተው ቢዚያኑም በገቡለት ቃል መሠረት ፈቀዱለት፡፡ ከዚያም ጉዞውን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ሰሜን ተራሮች አደረገ፡፡ በዚያም አሁን በስሙ የታነጸው ቤተ ክርስቲያን ባለበት ቦታ ላይ በምናኔ ተወስኖ ፈጣሪውን በብሕትዉና እያገለገለ ኖረ፡፡ ደብረ ሐዊ ከተባለው ተራራ ላይ  በምናኔ ብዙ ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በጸለምት ዋሻ በአንዱ ግንቦት ፲፩ ቀን በ፭፻፸፩ ዓ.ም ተሠውሯል፡፡

የቅዱስ ያሬድ የድርስት ድርሰቶች

ድጓ፡- ድጓ ማለት ሲሆን  ስያሜውን ያገኘበት ምክንያት የዓመቱ በዓላትና የሳምንታት መዝሙራት ተሰብሰበውና ተከማችተው ስለሚገኙ ነው፡፡ ድጓ ከብሉይ፣ ከሐዲስና ከአዋልድ መጻሕፍት ስለሚጠቅስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን፣ የመላእክትን፣ የነቢያትንና ሐዋርያትን፣ የጻድቃን የሰማዕታትን ክብር ይናገራልና፡፡

ጾመ ድጓ፡- በዐቢይ ጾም ወቅት በነግህ፣ በሠለስት፣ በቅትርና ሠርክ እንዲሁም በሌሊት የሚዘመር መዝሙር ነው፡፡ አጠቃላይ መጽሐፉ ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ማርያምን፣ ነገረ ቅዱሳንን፣ ነገረ መላእክት፣ ነገረ ቤተ ክርስቲያን የሚዘከር እንዲሁም የጾምን፣ የጸሎትንና የምጽዋትን ጠቃሚነት የሚስተምር ነው፡፡

ምዕራፍ፡- ምዕራፍ ማረፊያ ማለት ነው፤ የተደረሰውም በጠለምት ነው፡፡ የምዕራፍ መጽሐፍ ይዘት የዘወትርና የጾም ምዕራፍ ተብሎ በሁለት ክፍል የተከፈለ ሲሆን የዘወትር ምዕራፍ ዓመቱ ሳይጠብቅ በዓመቱ ውስጥ ባሉት ሳምንታትና በዓላት ወቅቱን እየጠበቀ በአገልግሎት ላይ የሚውል ነው፡፡ የጾም ምዕራፍ የሚባለው ደግሞ በጾመ ዐርባና በአንዳንድ የምሕላ ቀኖች የሚዘመር ነው፡፡

ዝማሬ፡- ዝማሬ ማለት ምስጋና ማለት ነው፡፡ ዝማሬንና መዋሥዕትን በደቡብ ጎንደር ዙር አባ በሚባል ቦታ ደርሶታል፡፡ የዝማሬ አገልግሎት በቅዳሴ ጊዜ ከድርገት በኋላ የሚቃኝ፣ የሚዜም፣ የሚዘመር፣ የጸሎተ ቅዳሴውን ዓላማ ተከትሎ የሚሄድ የአገልግሎት መጽሐፍ ነው፡፡

መዋሥዕት፡- አውሥአ መለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ምልልስ፣ ሰዋስወ ነፍስ›› ማለት ነው፡፡ ለአዕርጎ ነፍስ በፍትሐት ጊዜ የሚደርስ ነውና ያስ ይሁን ለሙት ድርሰት ደርሶ ማዘንን ከማን አግኝቶታል ቢሉ መልሱ ከዳዊት የሚል ይሆናል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች ለቤተ ክርስቲያን የሰጡት ጥቅም  

ሀ. ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ያሬድ በኩል ሰማያዊ ዜማ ተቀብላ ከሰማውያን መላእክት ጋር ሁልጊዜ  አምላክን ታመሰግናለች፡፡

ለ. ቤተ ክርስቲያን ለብሉይና ሐዲስ መጻሕፍትንና ሌሎችም የቤተ ክርስቲያን  መጻሕፍት ክርስቶስ ምጽአት ድረስ አምናና ታምና ልጆቿን የምታስተምር መሆኗ ያረጋግጥልናል፡፡

ሐ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጥ የሆነ ጣዕመ ዜማ እንዲኖራት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ከቅዱስ ያሬድ በረከት ረድኤት ያሳትፈን፤ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተረዳኢነት አይለይን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀል ክቡር

ምንጭ፡- መዝገበ ታሪክ ቁጥር ፪  

     ያሬድና ዜማው ሊቀ ካህናት ጥዑመ ልሳን

     ዕሴተ ትሩፋት ዘቅዱስ ያሬድ ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን

     የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ቅዱስ ያሬድ ታደሰ ዓለማየሁ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages