የደብተራ ልጅ ነኝ
ደብተራ ማለት ፦
1ኛ፦ ደብተራ ብርሃን ማለት ነው፦ የብርሃን ድንኳን ሊቀ ነቢያት ሙሴ በአምሳለ ንጉሥ ተገልጾ በብርሃን ድንኳን በሰባት የእሳት መጋረጃ 22ቱን ሥነ ፍጥረት በልቡናው ሥሎ ቃል በቃል 570 ጊዜ አነጋግሮታል ፦የደብተራ ልጅ ማለት የብርሃን ልጅ ማለት ነው።ወይም ሰማያዊ ወልደ ሰማያዊ ማለት ነው።
2ኛ፦ደብተራ ኦሪት ናት ባስልኤል ኤልያብን ያህል ጠበብት ሙሴን ያህል ነቢይ አሮንን ያህል ካህን አሥነስቶ ያሳነጻት ናት ። ታቦተ ሕጉ ያለባት አምልኮቱ የሚመሠከርባት ሕጉ የሚነገርባት ድንኳን ደብተራ ኦሪት ትባላለች ፦ የደብተራ ልጅ ማለት የሕግ ልጅ የመቅደስ አገልጋይ ማለት ነው።ሕገ ኦሪትን ያወቀ እንደሙሴ እንደ አሮን ያለ ማለት ነው።
3ኛ፦ደብተራ ድንግል ማርያም ናት በአምሳላዊት ድንኳን በረድኤት ይገለጽ የነበረው እግዚአብሔር በንጽሕና በቅድስና በታነጸች በአማናዊት ደብተራ በእመቤታችን ማህጸን በኩነት ተገልጿልና ደብተራ ትባላለች፦ የደብተራ ልጅ ማለትም የድንግል ማርያም የቃል ኪዳን ልጅ ማለት ነው።እንደ ጴጥሮስ እንደ ጳውሎስ መሆን ነዋ!
4ኛ፦ደብተራ መስቀል መድኅነ ዓለም ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል መሠዊያ ነውና ደብተራ ተብሏል ሕያው ደመ መለኮት የነጠበበት ቅዱስ መስቀል የከበረ ደብተራ ነው፦ የደብተራ ልጅ ማለትም የመስቀል ልጅ ማለት ነው።ወይም መስቀለኛ መስቀላዊ ማለት ነው።
5ኛ፦ደብተራ ርዕሱ ድንኳን ይባላል በዘር በሩካቤ ያይደለ እንበለ ዘር እንበለ ሩካቤ የተወለደ የመድኅን አካሉ ደብተራ ተብሏል ሠዋዒ ተሠዋዒ ተወካፌ መሥዋዕት ነውና እንደ ብሉይ ሊቀ ካህናት ከአፍአ ወደውስጥ ደመ በግዕን ይዞ ለሥርኤት ወደ ደብተራ ኦሪት አልገባም ራሱን በደብተራ ርዕሱ አቀረበ እንጂ፦የደብተራ ልጅ ማለትም የክርስቶስ ልጅ ማለት ነው።በክርስቶስ የሚያምን የክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው።
6ኛ፦ደብተራ ቤተ ክርስቲያን ፦ክርስቲያኖች የሚሰበሰቡባት መቅደሰ ወንጌል ደብተራ ተብላለች አገልጋዮቿም ካህናተ ደብተራ ይባላሉ ፦ የደብተራ ልጅ ማለትም የመቅደስ አገልጋይ ቅዳሴውን የሚቀድስ፣ ቅኔውን የሚቀኝ፣ድጓውን የሚያዜም፣ዝማሜውን የሚዘም ብራናውን የራመመ ቀለሙን የቀመመ ማለት ነው። የረቀቀ የተራቀቀ ምጡቅ መርጌታ ማለትኮ ነው!ከደብተራ ሙያ አንዱን ሳያውቁ መንቀፍ ወፍ ነዳሽ ጉም አፋሽ መሆን ነው።
ለደብተራነት መዐርግ መድረስ ጭንቅ ነው እንጂ ልጅ መሆንስ ቢሹትም አይገኝ።
ደብተራ እያሉ መተንኮስ በይፋ ክርስትናን እና ክርስቲያኖችን በመጥላት የሚደረግ ሥሁት ድንቁርና ነው። ጠንቋይን ለተከበረው ደብተራ መስጠት አይቻልም ጨለማ ከብርሃን ጋር ኅብረት የለውምና።ሀገር በቀል የዕውቀት ሀሳቦችን የደብተራ ዕውቀት ነው አንቀበልም አንሰማም ማለት ግን ኦርጂናል የጣሊያን አእምሮ ነው። ደብተራ ዶክተሮች ሳይኖሩ ዶክተር ነበር።በተውሶ ጭፍን ግልበጣ የተሠራ አእምሮ እውነትን ካልጠላት የተማረ አይመስለውም ማለት ነው? ።ከውሸተኛ ተንኮለኛ ቁም ነገር አገኛለሁ ከማለት ዑቅያኖስ ሜዳ ሁኖ እህል ይዘራበታል ማለት ይቀላል።ወይም ሰሜን ተራራ ደልዳላ ሜዳ ይሆናል ማለት ይሻላል።
ተጻፈ ከደብተራ ልጅ
መምህር ገብረ መድኅን እንየው
No comments:
Post a Comment