አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ሰባት በዚች ቀን #ቅዱስ_ኤዎስጣቴዎስ ሁለቱ ልጆቹና ሚስቱም በሰማዕትነት አረፉ፣ ያለ ደም ማፍሰስ ሰማዕት የሆነች #ቅድስት_ጤቅላ አረፈች፣ የቀራጮች አለቃ የነበረ #ቅዱስ_አንጢላርዮስ አረፈ፣ የደብረ ጽጌ #አባ_ዮሐንስ አረፈ።
መስከረም ሃያ ሰባት በዚች ቀን ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሁለቱ ልጆቹና ሚስቱም በሰማዕትነት አረፉ።
ይህ ቅዱስም ለሮም መንግሥት የጭፍራ አለቆች ከሆኑት ውስጥ ነው የቀድሞ ስሙ ቂዶስ ነው እግዚአብሔርንም አያውቅም ነበር ግን ብዙ ምጽዋትን በመስጠት ለድኆችና ለችግረኞች ይራራል ስለዚህም ክብር ይግባውና ጌታችን ድካሙ ከንቱ ሁኖ እንዲቀር አልወደደም።
በአንዲት ቀንም አውሬ ሊያድን ኤዎስጣቴዎስ ወደ ዱር ወጣ እርሱ አዳኝ ነውና ዋልያም አግኝቶ በቀስት ሊነድፈው ወደደ ያን ጊዜም በዋልያው በቀንዶቹ መካከል በመስቀል አምሳል ጌታ ተገለጸለት። የመስቀሉም ብርሃን እስከ ደመና ደርሶ ነበር ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚያ ብርሃን ውስጥ ተናገረው ስሙንም አስረዳው ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ወደ ኤጲስቆጶስ ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቁ አዘዘው።
ክብር ይግባውና ጌታችንም ከዚህ በኋላ ችግርና ፈተና እንደሚመጣበት በመጨረሻም ስለ ከበረ ስሙ ምስክር ሁኖ ደሙን አፍስሶ እንደሚሞት አስረዳው። ኤዎስጣቴዎስም ሰምቶ ከተራራው ወርዶ ወደ ቤቱ ሔደ። ጌታችን ያዘዘውንም ለሚስቱ ነገራት ከዚህም በኋላ ወደ ኤጲስቆጶሱ ሔደው ከልጆቻቸው ጋራ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ የቀድሞ ስሙንም ለውጦ ኤዎስጣቴዎስ ተባለ።
ከጥቂት ቀኖች በኋላ በዚያች አገር ታላቅ ችግር መጣ የኤዎስጣቴዎስም ገንዘቡ ሁሉ አልቆ ወንዶችና ሴቶች ባሮቹ ተበተኑ ወደሌላ አገርም ሊሰደድ ወዶ ልጆቹንና ሚስቱን ይዞ በመርከብ ተጫነ። ወደ ወደቡም በደረሱ ጊዜ መርከበኞች የመርከብ ዋጋ ከእርሱ ፈለጉ የሚሰጣቸው የመርከብ ዋጋ ባላገኘ ጊዜ ስለ መርከብ ዋጋ የመርከቡ ሹም ሚስቱን ወሰዳት የአታክልት ጠባቂም አደረጋት።
ከዚያም ኤዎስጣቴዎስ እያዘነና እያለቀሰ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ሔደ ውኃ ወደ መላበትም ወንዝ ደረሰ አንዱንም ልጁን ከእርሱ ጋር ሊአሻግረው ይዞት ገባ አሻግሮትም ከወንዙ ዳር አኖረውና ሁለተኛውን ልጁን ሊአሻግረው ተመለሰ ግን አላገኘውም። ተኵላ ወስዶታልና ያሻገረውንም አንበሳ ነጥቆ ወሰደው ኤዎስጣቴዎስም ከሚስቱና ከልጆቹ ስለ መለየቱ ታላቅ ኀዘንን አዝኖ መሪር ልቅሶን አለቀሰ ምክሩ ታላቅ የሆነ ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ግን ሁሉንም በየአሉበት ያለ ጥፋት ጠበቃቸው።
ከዚህ በኋላም ኤዎስጣቴዎስ ወደ አንዲት አገር ሒዶ በዚያ የአትክልት ጠባቂ ሁኖ ብዙ ቀኖችን ኖረ። ከእነዚያ ቀኖችም በኋላ የሮም ንጉሥ ሙቶ በርሱ ፈንታ ለኤዎስጣቴዎስ ወዳጁ የሆነ ሰው ነገሠ ኤዎስጣቴዎስንም ፈለገው ግን አላገኘውም ኤዎስጣቴዎስንም ይፈልጉት ዘንድ ወደ ሀገሩ ሁሉ መልእክተኞችን ላከ። ከመልእክተኞችም አንዱ ኤዎስጣቴዎስ ወዳለበት ደርሶ በአታክልቶች ዘንድ አግኝቶት አወቀው እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሡ ወሰደው ንጉሡም በበጎ አቀባበል ተቀብሎ የጭፍራ አለቃ አድርጎ ሾመው።
ከዚህም በኋላ ንጉሡ ከሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ወጣቶችን ሰብስቦ የጦር ሠራዊት ጭፍራ ያዘጋጅ ዘንድ ኤዎስጣቴዎስን አዘዘው እነዚያ ተኵላና አንበሳ የወሰዳቸው የኤዎስጣቴዎስ ሁለት ልጆቹ በአንዲት አገር አድገዋል። ግን እርስበርሳቸው አይተዋወቁም ወጣቶችንም የሚመለምሉ መልምለው ወደ አባታቸው ኤዎስጣቴዎስ አቀረቧቸው እርሱም ሳያውቃቸው የመዛግብት ቤት ጠባቂዎች አደረጋቸው።
እናታቸውንም አረማዊ የሆነ የመርከቡ ሹም በወሰዳት ጊዜ የአታክልቶች ጠባቂ አደረጋት። እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ሁሉ በንጽሕና ጠብቋታልና እነዚያ ሁለቱ ልጆቿ እርሷ ወዳለችበት የአታክልት ቦታ ደረሱ እነርሱም የልጅነታቸውን ነገር ይነጋገሩ ነበር። እርሷም ሰምታ ልጆቿ እንደሆኑ አውቃ ያን ጊዜ ጠራቻቸውና እርሷ እናታቸው እንደ ሆነች ነገረቻቸው አንገት ላንገት ተያይዘው አለቀሱና እርስ በርሳቸው ተሳሳሙ ወደ ኤዎስጣቴዎስም ሔደው ከእነርሱ የሆነውን ሁሉ ነገሩት። እርሱም እርሷ ሚስቱ እንደሆነች እነዚያም ልጆቹ እንደ ሆኑ አወቀ እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ ታላቅ ደስታም ደስ አላቸው ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ስለ አደረገው በጎ ነገር እያደነቁና እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በአንድነት በአንድ ቦታ ኖሩ።
ኤዎስጣቴዎስንም የሚወደው ንጉሥ በሞተ ጊዜ በእርሱ ፈንታ ጣዖት የሚያመልክ ሌላ ንጉሥ ነገሠ። ኤዎስጣቴዎስንም ጠርቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ወደርሱ አቅርቦ ለአማልክት ዕጣን አሳርጉ አላቸው። እሊህ ቅዱሳንም እንዲህ ብለው መለሱለት እኛ የረከሱ አማልክትን አናመልክም የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመልከዋለን እንጂ። በዚያንም ጊዜ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ጽኑ ሥቃይንም አሠቃዩአቸው እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት አስነሣቸው።
ሁለተኛም በበሬ አምሳል በተሠራ ነሐስ ውስጥ እንዲጨምሩአቸው አዘዘና በዚያ ጨምረው እሳትን በላያቸው አነደዱ ነፍሳቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ክብር ይግባውና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።
በዚህችም ቀን ያለ ደም ማፍሰስ ሰማዕት የሆነች ቅድስት ጤቅላ አረፈች። የዚች ቅድስት ወላጆቿ ከመቄዶንያ ሰዎች ውስጥ ባለጸጎች ናቸው እርሷንም እንደ ሀገራቸው ባህል በተግሣጽ በምክር አሳደጓት እነርሱ ጣዖትን የሚያመልኩ ናቸውና።
ሐዋርያ ጳውሎስም ወደዚች አገር በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲህ እያለ ሊአስተምር ጀመረ ዐውቀው ድኆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት ለነርሱ ናትና። ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው እነርሱ ደስ ይላቸዋልና።
ከዚህም በኋላ በጭልታ ወረደች ለሚጠብቃትም ዘበኛ እንዳይናገርባት የወርቅ ወለባዋን ዋጋ ሰጠችውና ወደ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ ሔደች። እርሱም በደስታ ተቀብሎ የክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራት።
በማግሥቱም እናቷ እየፈለገቻት በመጣች ጊዜ ከቅዱስ ጳውሎስ ዘንድ አብራ ተቀምጣ አገኘቻት ከዚያም ወደ መኰንን ሒዳ ልጇን ክርስቲያን እንደሆነች ከሰሰቻት። መኰንኑም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋራ እንዲያመጧት አዘዘ አስቀድመው ቅዱስ ጳውሎስን ወደ እሳት እንዲወረውሩት አዘዘ እግዚአብሔርም አዳነው።
መኰንኑም የቅድስት ጤቅላን ቅጣት እንዲያዩ የሀገር ልጆችን ሰበሰበ ከዚህም በኋላ ወደ እሳት እንዲወረውሩዋት አዘዘ። በዚያን ጊዜ በክርስቶስ ማዕተብ ራሷን አማትባ ራስዋን በራስዋ ወደ እሳት ወረወረች ማንም ያያት ሳይኖር ከእሳት ውስጥ ወጥታ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሔደች የራስዋን ጠጒር ቆርጣ ወገቧንም ታጥቃ ቅዱስ ጳውሎስን ተከተለችው።
መኰንኑም ደኅንነቷን በሰማ ጊዜ ያዛት ሃይማኖቷንም እንድትተው አስገደዳት አይሆንም ባለችውም ጊዜ አንበሶችና ድብ ከሚያድሩበት እንዲጨምሩዋት አዘዘ። እነርሱም ሰገዱላትና የእግሮቿን ትቢያ ላሱ። ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው መኰንኑና ወገኖቹ አመኑ አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ በክርስቶስም መንጋዎች ውስጥ ሆኑ።
እርሷ ቅድስት ጤቅላም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን በማስተማር ቅዱስ ጳውሎስን እያገለገለችው ኑራ በሰላም አረፈች።
ይህ ባለጸጋ በድኆች ላይ ምንም ምን ርኅራኄ የሌለው ነው ከእነርሱም አንዱ እኔ ሔጄ ከእርሱ ምጽዋት ተቀብዬ ብመጣ ምን ትሰጡኛላችሁ አላቸው እነርሱም አንተ ከእርሱ ምጽዋትን ካገኘህ ያልከውን እንሰጥሃለን አሉት በዚህም ነገር ከተከራከሩ በኋላ ወደ አንጢላርዮስ ቤት ሒዶ ምጽዋትን ለመነው አንጢላርዮስም ከመሶቡ እግር የደረቀ ለከት ዳቦ አንሥቶ በመበሳጨት ወርውሮ የድኃውን ራስ ፈቃው ድኃውም ወደ ባልንጀሮቹ ተመልሶ ያንን ለከት አሳያቸው።
በዚያቺም ሌሊት አንጢላርዮስ በሕልሙ ራእይን አየ እርሱ በፍርድ አደባባይ ቁሞ ሳለ የጠቆሩ ሰዎች ስለ ክፋቱ ብዛት ሲከራከሩት ብርሃን የለበሱ ሰዎች ደግሞ ከዚች ለከት ዳቦ በቀር በርሱ ዘንድ ያደረገውን ምጽዋት አላገኘንም ብለው ሲያዝኑ በሚዛንም በመዘኑዋት ጊዜ ከኃጢአቱ ሁሉ ተስተካከለች። በዚያንም ጊዜ ነቃ በልቡም ሳልወድ የሠራሁት ይህን ያህል ጠቃሚ ከሆነ ወድጄ ብሠራውማ እጥፍ ድርብ የሆነ ዋጋ የማገኝ አይደለምን አለ።
ከዚህም በኋላ ተነሥቶ ገንዘቡን ጥሪቱን ሁሉ አውጥቶ ለድኆችና ለችግረኞች መጸወተ። ገንዘቡንም ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ከሩቅ ቦታ ድኆች መጥተው ምጽዋትን ለመኑት እርሱም ገንዘቡን ሁሉ እንደ ጨረሰ ነገራችውና እጅግ አዘኑ እንዳዘኑም አይቶ እንዲሸጡት ፈቀደላቸው እነርሱም ሸጡትና የሽያጩን ገንዘብ ተከፋፈሉ።
በተሸጠበትም እንደባሪያ እያገለገለ ኖረ የጌታው ባሮችም በሚያሳዝኑት ጊዜ ብርሃናዊ ሰው ተገልጦ አትዘን የተሸጥክበትን ዋጋ እኔ ተቀብዬዋለሁ እነሆ በእጄ ውስጥ አለና ይለዋል።
ከዚህም በኋላ አስቀድሞ ከነበረበት የመጡ ሰዎች ሥራውን በገለጡበት ጊዜ በሥውር ሸሽቶ ወደ ከተማው በር ደረሰ በሩን የሚጠብቀውም ዲዳና ደንቆሮ ነበር። አንጢላርዮስም በሩን ክፈትልኝ በአለው ጊዜ ከአፉ በእሳት አምሳል ወጥቶ በረኛውን ነካው ያን ጊዜ አንደበቱ ተፈታ ጆሮዎቹም ሰሙ በሩንም ከፍቶለት ወደ በረሀ ሔደ በዚያም ገድሉን ፈጽሞ አረፈ።
ሰዎችም በአጡት ጊዜ ወደ በሩ መጡ በረኛውም የሆነውን ሁሉ ነገራቸው ከቅድስናውና ከተአምራቱም የተነሣ እጅግ አደነቁ።
በዚህችም ቀን ደግሞ የደብረ ጽጌ አባ ዮሐንስ አረፈ። ይህም ቅዱስ አብዝቶ ከመጾሙ ተግቶም ከመጸለዩ የተነሣ ሥጋው ጠውልጎ እንደ ደረቀ ምድር ሆነ። በአንዲትም ቀን በጋን የመላ ውኃ በአፈሰሱበት ጊዜ ከሥጋው ድርቀት ብዛት የተነሣ ከእርሱ ምንም አልነጠበም።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment