፵፩ ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ 29 የአቋም መግለጫ ነጥቦች በማውጣት ተጠናቀቀ!! - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 22, 2022

፵፩ ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ 29 የአቋም መግለጫ ነጥቦች በማውጣት ተጠናቀቀ!!

፵፩ ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ 29 የአቋም መግለጫ ነጥቦች በማውጣት ተጠናቀቀ!!(ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ)
ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ፵፩ ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ 29 የአቋም መግለጫ ነጥቦችን በማውጣት በሰላም ተጠናቀቀ።
የጉባኤው አርቃቂ ኮሚቴ አባል የሆኑት መጋቤ አእላፍ በላይ ጸጋዬ ባለ 29 የአቋም መግለጫ ነጥቦችን ለጉባኤው አስደምጠዋል።
ከአቋም መግለጫዎቹ መካከል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ያቀረቡት ሀገራዊ የሰላም ጥሪና ተልዕኮ የጉባኤውም አቋም መሆኑ ቅድምያ ተጠቅሷል፤ በመሆኑም በሀገራችን የተከሰተው ጦርነት በፍጥነት በሰላምና በውይይት እንዲፈታ ጉባኤው አሳስቧል።
ብሔር ብሔረሰቦች በልሳናቸው ወንጌልን እንዲማሩ፣ ትምህርተ ወንጌልን በጋዜጣና በመጽሔት ጭምር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሀገሪቱ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለምእመናን በበቂ ሁኔታ እንዲደርስ ቢሠራ የሚሉትም የጉባኤው የአቋም መግለጫዎች ናቸው።
ከመንፈሳዊ ኮሌጆች የሚወጡ ደቀመዛሙርት በተመደቡበት ሀገረ ስብከት በትጋት እንዲያስተምሩ፣ ኮሌጆችም ቁጥራቸው እንዲበዛና ደቀመዛሙርትን የመቀበል አቅማቸው እንዲጨምር፣ በስብከተ ወንጌል መሣሪያነት ሰላምን ማምጣት እንደሚገባ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ የሰበካ ጉባኤ ማሻሻያ እንዲደረግ፣ ከተገልጋይነት አገልጋይነት ይቅደም፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር እንደሚገባ በአቋም መግለጫው ተጠቅሰዋል።
የተለያዩ የሰጥታ ችግሮች በነበረባቸው አከባቢዎች የመልሶ ግንባታ እንዲካሄድ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ያሬዳዊ ዝማሬ አቀራረብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሳቢና ማራኪ እየሆነ መምጣቱ የሚያስደስት በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ልማትን በማጠናከር ቤተክርስቲያን በገቢ ራሷን እንድትችል መሥራት ይገባል የሚሉትም የአቋም መግለጫው ነጥቦች ናቸው።
ወልጃ አልባ ሕጻናትን ከአድባራትና ከገዳማት ጀምሮ መንከባከብና ማሳደግ እንደሚገባ፣ የመንግሥትም ሆኑ የግል ሚዲያዎች የሚያስተላልፉት መልእክት ምእመናንን የሚከፋፍል ሳይሆን ወደ አንድነት የሚያመጣ እንዲሆን መረጃዎችን መርጠው እንዲያስተላልፉ፣ ማንኛውንም በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በጋራ መከላከል እንደሚገባ፣ ቤተክርስቲያኒቱ ከዐባይ ባንክ ጋር አብሮ የመሥራት የስምምነት ሰነድ መፈራረሟ ለቤተክርስቲያኒቱ የሚጠቅም መሆኑ፣ በቤተክርስቲያኒቱ ሊሠራ የታሰበው የሕክምና ማዕከልም ቤተክርስቲያኒቱን የሚመጥን እንደሆነ በአቋም መግለጫው ተደምጧል።
፵፩ ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ሪፖርትን ከማዳመጥ ባሻገር በአሁናዊ የቤተክርስቲያን ተግዳሮቶችና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን በማካሄድ ለቅዱስ ሲኖዶስ ግብዓት የሚሆኑ የመወያያ ሃሳቦችን ያፈለቀ እንደነበርም ተገልጿል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይህንን የመወያያ መርሐግብር በማመቻቸት ትልቁን ድርሻ በመወጣታቸው ከጉባኤው ምስጋና ተችሯቸዋል።
በተያያዘም በመንፈሳዊ አገልግሎት፣ በልማትና በገቢ ጥሩ ውጤት ላመጡ ሀገረ ስብከቶች በየደረጃቸው የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፵፩ ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው ጉባኤውን በጸሎት ዘግተዋል።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages