ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 13 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 22, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 13

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሦስት በዚችም ዕለት የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የከበረ አባት #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ መታሰቢያው ነው፤ #የመነኰስ_ቅዱስ_ዘካርያስም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

ጥቅምት አስራ ሦስት በዚችም ዕለት የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የከበረ አባት ዮሐንስ አፈወርቅ መታሰቢያው እንደሆነ ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል።
ይህም አባት ከእስክንድርያ አገር ሰዎች ወገን ነው የአባቱም ስም አስፋኒዶስ የእናቱም ስም አትናሲያ ነው እሊህም እጅግ ባለጸጎች ነበሩ ይህንንም ልጃቸውን በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት ትምህርትንና ጥበብንም ሁሉ አስተማሩት እርሱ ወደ አቴና ሔዶ በመምህራን ቤት ተቀምጦ ትምህርትን ሁሉ ተምሮ በዕውቀቱ ከብዙዎች በላይ ከፍ ከፍ ብሏልና።
ከዚህም በኋላ ገና በታናሽነቱ መነኰሰ የዚህንም የኃላፊውን ዓለም ጣዕም ንቆ ተወ ከእርሱም ቀድሞ በዚሁ ገዳም ቅዱስ ባስልዮስ መንኵሶ ነበር በአንድነትም ተስማምተው ብዙ ትሩፋትን ሠሩ ወላጆቹም በሞቱ ጊዜ ከተውለት
ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ እንጂ ከዚያም በምንኵስና ሥራ በመጠመድ ፍጹም ገድልን እየተጋደለ ኖረ።
በዚያም ገዳም ሶርያዊ ጻድቅ ሰው ስሙ ሲሲኮስ የሚባል መነኰስ ነበረ እርሱም ወደፊት የሚሆነውን በመንፈስ ቅዱስ ያይ ነበር በአንዲት ሌሊትም ለጸሎት እየተጋ ሳለ ሐዋርያትን ጴጥሮስንና ዮሐንስን አያቸው ወደ ዮሐንስ አፈወርቅ ገብተው ጴጥሮስ መክፈቻ ሰጠው ወንጌላዊ ዮሐንስም ወንጌልን ሰጠው እንዲህም አሉት በምድር ያሠርከው በሰማይ የታሠረ ይሆናል በምድርም የፈታኸው ደግሞ በሰማያት የተፈታ ይሆናልና በውስጥህ መንፈስ ቅዱስ ያደረብህ አዲስ ዳንኤል ሆይ የክብር ባለቤት ከሆነ ከታለቅ መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ወደ አንተ ተልከናልና ዕወቅ እኔም የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የተሰጠኝ ጴጥሮስ ነኝ።
ሁለተኛውም እኔም በመጀመሪያው ስብከቴ በከበረ ወንጌል ቃል አስቀድሞ ነበረ ያልኩ ይህም ቃል በጠላት ላይ የእሳት ሰይፍ የሆነ ዮሐንስ ነኝ። ለአንተም ከክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ወገኖችህ ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ታሳድጋቸው ዘንድ ዕውነተኛ አእምሮ ደግሞ ተሰጥቶሃል።
ጻድቅ ሲሲኮስም ይህን ራእይ በአየ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ቸር ታማኝ እረኛ ሁኖ እንደሚሾም ዐወቀ። ከዚህም በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በላዩ ወርዶ አደረበትና ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ ዲያቆን ሁኖ ሳለም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ብሉያትንና ሐዲሳትን ተረጐመ። በአንዲት ሌሊትም ቅዱስ ዮሐንስ ሲጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ በድንገት እንደ በረድ ነጭ በሆነ ልብስ ተገለጠለት ቅዱስ ዮሐንስም ሲያየው ደንግጦ በምድር ላይ ወደቀ መልአኩም አርአያውን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታየው ወዳጄ አዲስ ዳንኤል ሆይ አትፍራ ተነሣ አለው የቅዱስ ዮሐንስም ልቡ ተጽናንቶ ጌታዬ አንተ ማነህ ግርማህ አስፈርቶኛልና አለው የእግዚአብሔር መልአክም ትሠራው ዘንድ የሚገባህን ልነግርህ ወዳንተ የተላክሁ ነኝ።
አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘህን ለመሥራት ልብህን አበርታ ቃልህ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በአራቱ ማእዘን ይደርሳልና እልፍ አእላፋትም ትምህርትህን ተቀብለው ትእዛዝህን ሰምተው ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር ተመልሰው ይድናሉና በእግዚአብሔር መንግሥትም ውስጥ የጸና የብርሃን ዐምድ ትሆናለህና። እነሆ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አንተ ይመጣል ከእርሱም ጋራ ሁሉም ካህናትና ዲያቆናት በየማዕረጋቸው የሚያዝህንም አድርግ የእግዚአብሐር ትእዛዝ ነውና ልትተላለፍ አይገባህም አለው። ከዚህም በኋላ ያ መልአክ ለአባ ፊላትያኖስ ተገልጦ ቅዱስ ዮሐንስን ቅስና እንዲሾመው አዘዘው በማግሥቱም ሊቀ ጳጳሳቱ መጣ ከርሱ ጋራም ካህናት አሉ ይህን ቅዱስ ዮሐንስንም ይዞ ቅስና ሾመው።
የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳትም በአረፈ ጊዜ ንጉሥ አርቃድዮስ ልኮ አስመጥቶ ቅዱስ ዮሐንስን በቍስጥንጥንያ ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾመው አባቶቻችን ሐዋርያት እንደሚያደርጉት በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ላይ ጸና ሕይወትነት በአላቸው ትምህርቶችና ተግሣጾች ሕዝቡን ሁልጊዜ የሚአስተምር ሆነ። ከኤጲስቆጶሳትም ሆነ ከመንግሥት ወገን ሕግን የሚተላለፉትን ሁሉ ይገሥጻቸዋል ማንንም አይፈራም ፊት አይቶም አያደላም።
የንጉሥ አርቃድዮስ ሚስት አውዶክስያም ገንዘብ ወዳጅ ስለሆነች የአንዲት ድኃ መበለት ቦታዋን በግፍ ወሰደች ያቺ መበለትም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥታ ንግሥት አውዶክስያ ቦታዋን እንደነጠቀቻት ነገረችው እርሱም የደኃዋን ቦታዋን መልሺላት ብሎ ከብዙ ምክር ጋር እንድትመልስላት ንግሥት አውዶክስያን ለመናት እርሷ ግን እምቢ በማለት አልታዘዘችለትም። ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውን ደሙን እንዳትቀበል አውግዞ ለያት።
ቍጣንና ብስጭትንም ተመልታ ስለ ክፉ ሥራቸው ከሹመታቸው እርሱ የሻራቸውን ኤጲስቆጶሳት ሰበሰበች እነርሱም ንግሥቲቱን ስለ ተቃወመ ስደት እንደሚገባው በእርሱ ላይ ተስማምተው ጻፉ እርሷም አጥራክያ ወደ ሚባል ደሴት ሰደደችው።
ከዚያም በደረሰ ጊዜ የዚያች ደሴት ሰዎች በክፉ ሥራ ጸንተው የሚኖሩ ከሃድያን ሁነው አገኛቸው ቅዱስ ዮሐንስም አስተማራቸው ገሠጻቸውም በፊታቸው ስለ አደረጋቸው ድንቆች ተአምራት ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው።
የሮሜ ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ስደት በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ በንጉሥ አርቃድዮስ ላይም በመቆጣት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ላኩ ከዚህ ከክፉ ሥራ ተጠበቅ ትእዛዛችንንም ተቀብለህ የከበረ
ዮሐንስን ከስደቱ ከአልመለስከው በአንተና በእኛ መካከል ሰላም አይኖርም። መልእክታቸውንም በአነበበ ጊዜ እጅግ አዘነ ሚስቱንም አግዶ ልኮ ቅዱስ ዮሐንስን ከስደቱ መለሰው በተመለሰ ጊዜም የቍስጥንጥንያ ሰዎች በመመለሱ ታላቅ ደስታ አደረጉ። ከጥቂት ቀኖች በኋላም ንግሥቲቱ ወደ ክፋቷ ተመልሳ ሁለተኛ ወደ አጥራክያ ደሴት ሰደደችውና በዚያው አረፈ።
ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳት ዮናክኒዶስም በሰሙ ጊዜ መልእክትን ላኩ ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ እስከምትመልሰው ድረስ ሥጋውንና ደሙን እንዳትቀበል አውዶክስያን አወገዛት። ከዚህም በኋላ የከበረ ዮሐንስን ይመልሱት ዘንድ ንጉሥ ላከ ግን ሙቶ አገኙት ሥጋውንም ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ አደረሱት። የከበረ ዮሐንስም በተሰደደበት አገር እንደአረፈና ሥጋውንም ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ እንዳመጡ ወደ አባ ዮናክኒዶስ መልእክት ጽፈው አስረዱት። ሁለተኛም የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውንና ደሙን እንዳትቀበል ልኮ አውድክስያን አወገዛት እየለመነችውም ስምንት ወር ያህል ኖረች በብዙ ልመናም ፈታት።
ነገር ግን ጭንቅ በሆነ ደዌ እግዚአብሔር አሠቃያት ያድኗት ዘንድ ገንዘቧን ለባለ መድኃኒቶች ጥበበኞች እስከ ሰጠች ድረስ ግን አልዳነችም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መቃብርም ሔዳ በእርሱ ላይ ያደረገችውን በደል ይቅር ይላት ዘንድ እየሰገደችና እያለቀሰች ለመነችው እርሱም ይቅር አላት ከደዌዋም ፈወሳት። ጌታችንም ከሥጋው ታላላቅ ድንቆች ታአምራትን ገለጠ።
ስለርሱም እንዲህ ተባለ በአንዲት ዕለትም ከንጉሥ አርቃዴዎስ ጋር ተቀምጦ ሳለ ንጉሡ እንዲህ አለው አባቴ ሆይ ስለ አንድ ቃል እንድታስረዳኝ እለምንሃለሁ። ይህም ቃል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በልቤ ውስጥ ይመላለሳል ወንጌላዊ ማቴዎስ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምን የበኵር ልጅዋን እስከ ወለደች ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም ስለምን አለ ወንዶች ሴቶችን እንደሚአውቋቸው ዮሴፍ አወቃትን አለው።
የከበረ ዮሐንስም ንጉሥ ሆይ እንዲህ አትበል እንዲህ አንተ እንደምትለው አይደለም የከበረች ድንግል እመቤታችንስ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሆድዋ ውስጥ በነበረ ጊዜ የእርሱ ኅብረ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋር መልኳ ይለወዋወጥ ነበር። በንጹሕ ብርሌ ውስጥ ውኃ በጨመሩ ጊዜ ውኃ መስሎ እንደሚታይ ወይን ጠጅም ቢጨምሩ ያንኑ መስሎ እንደሚታይ ወይም ከውስጡ በተጨመረው ቀይም ቢሆን ቀልቶ እንደሚታይ ቅጠልያም ቢገባበት ቅጠልያ መስሎ እንደሚታይ። ድንግልም በሆድዋ ውስጥ የልጅዋ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋራ መልኳ ይለዋወጥ ነበር። እንደ ሮማን አበባ የምትቀላበት ጊዜ አለ እንደ ናርዶስም የምታብለጨልጭበት ጊዜ አለ የለመለመ ቅጠል የምትመስልበትም ጊዜ አለ ከወለደች በኋላ ግን አልተለወጠችምና ዮሴፍ በአንድ በቀድሞው ኅብረ መልኳ ተወስናለት መልኳን ተረዳ ማለት ነው አለው። በዚያን ጊዜ በንጉሥ አዳራሽ ውስጥ ከወርቅ የተሠራ የእመቤታችን አምላክን የወለደች የድንግል ማርያም ሥዕል ነበረችና አፈ ወርቅ ዮሐንስ ልሳነ ወርቅ ዮሐንስ አፈ በረከት ዮሐንስ መልካም ተናገርክ የሚል ቃል ከእርሷ ወጣ።
ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያሉት በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት በዚያን ጊዜ ንጉሥ አዝዞ ወርቅ ሠሪ አስመጥቶ ለከበረ ዮሐንስ የወርቅ ልሳን አሠርቶ ለሚያየው ሁሉ መታሰቢያ ምልክት ሊሆን አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ሥዕል ዘንድ ሰቀለው። ቅዱስ ዮሐንስንም ከዚያች ቀን ወዲህ ልሳነ ወርቅ ብሎ ጠራው አፈ ወርቅም ተብሎ እስከዛሬ ተጠራ።

ዳግመኛም በዚችም ቀን ደግሞ የመነኰስ ዘካርያስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። የዚህም መስተጋድል የአባቱ ስም አቃርዮስ ነው። ይህም አቃርዮስ የምንኲስና ልብስ ሊለብስ ሽቶ ለሚስቱ ነገራት እርሷም በነገራት ነገር ተስማማች። ወንድና ሴት ሁለት ልጆች አሉአቸው እነርሱንም ከእናታቸው ዘንድ ትቶ እርሱ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዶ ከአንድ አረጋዊ አባት መነኰስ ዘንድ በዚያ መነኰሰ።
ከጥቂት ወራትም በኋላ በሀገር ውስጥ ረኃብ ሆነ ሚስቱም ልጆቿን ይዛ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወደባሏ አቃርዮስ መጣች በረኃብም ስለ ሆነው ችግር ነገረችው አቃርዮስም እነሆ እግዚአብሔር በመካከላችን ፍርድን አድርጎ ልጆቻችንን አካፈለን እኔም ወንዱን ልጄን እወስዳለሁ አንቺም ሴት ልጅሽን ውሰጂ አላት ይህንንም ብሎ ልጁን ወሰደ ይኸውም ዘካርያስ ነው እርሷም ሴቷን ልጅዋን ይዛ ተመለሰች።
ከዚህም በኋላ ልጁን ዘካርያስን ወደ ቅዱሳን አረጋውያን አቀረበው እነርሱም በላዩ ጸለዩ ባረኩትም እርሱ ፍጹም መነኲሴ እንደሚሆንም ትንቢት ተናገሩለት።
ዘካርያስም ከበጎ ሥራ ጋር በገዳም ውስጥ አደገ መልኩም እጅግ ያማረ ነው ስለርሱም ጉርምርምታ ሆነ መነኰሳቱም እርስበርሳቸው ይህ ወጣት ይህን ያህል እጅግ መልከ መልካም ሲሆን በገዳም ውስጥ በመነኰሳት መካከል እንዴት ይኖራል ተባባሉ።
ዘካርያስም ስለርሱ መነኰሳት እንዳንጐራጐሩ በሰማ ጊዜ ናጥራን ወደሚባል ተራራ ስር ወደአለች ዐዘቅት ሔደ ልብሱንም አውልቆ በረግረግ ውስጥ ተኛ ሥጋውም ተነፋፍቶ ጠቆረ ተመላልጦም ቈሰለ ብዙ ዘመንም በደዌ እንደኖረ ሆነ፤ ከዚህም በኋላ ልብሱን ለብሶ ወደ ገዳም መጣ ያወቀውም የለም። ከብዙ ቀኖችም በኋላ አባቱ አስተውሎ ልጁ ዘካርያስ እንደ ሆነ አወቀውና መልክህን የለወጠው ምንድን ነው ብሎ ጠየቀው አርሱም ያደረገውን ሁሉ ነገረው።
በእሑድ ቀንም ሥጋውንና ደሙን ሊቀበል ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ እግዚአብሔርም ያን ጊዜ ሥራውን ለአባ ኤስድሮስ ገለጸለት እርሱም ዘካርያስ የሠራውን ለወንድሞች መነኰሳት አስረዳቸው እነርሱም አስቀድሞ እንደ ሰው ሁነህ መጣህ ዛሬ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ሁነህ መጣህ አሉት።
ይህ አባት ዘካርያስም በብዙ ገድል ሲጋደል ኖረ ትሕትናን ቅንነትን ያማረ የትሩፋትን ሥራ ሁሉ ገንዘብ አደረገ አባቱም ስለርሱ እኔ በገድል ብዙ ደክሜአለሁ ነገር ግን ከልጄ ሥርዓተ ገድል አልደረስኩም ብሎ ተናገረ።
በዚህ ተጋድሎውም አርባ አምስት ዓመት ኑሮ እግዚአብሔርን ከአገለገለው በኋላ በፍቅር አንድነት አረፈ መላ ዘመኑም ሃምሳ ሁለት ነው። ከዚህም ሰባቱን ዓመት በወላጆቹ ቤት አርባ አምስቱን በገዳም ኖረ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages