ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 14 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 22, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 14

 

ጥቅምት ዐሥራ አራት በዚች ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን #አቡነ_አረጋዊ ተሰወሩ፣ የቊስጥንጥንያ ንጉሥ የቴዎዶስዮስ ልጅ #ቅዱስ_ገብረ_ክርስቶስ አረፈ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የሆነ አንዱ #ቅዱስ_ሐዋርያ_ፊልጶስ አረፈ፣ ከሮሜ ሀገር የሆነ የከበረ የእግዚአብሔር ሰው #ሙሽራው_ቅዱስ_ሙሴ አረፈ።
ጥቅምት ዐሥራ አራት በዚህች ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) የተሰወሩበት ነው።
እኚህ አባት ከ9 ቅዱሳን አባቶች አንዱ ሲሆኑ
አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉስ ነበሩ፡፡ እናታቸው ንግስት እደና ይባሉ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስማቸው ዘሚካኤል ነው፡፡ ጥበብ መንፈሳ ሲማሩ አድገው ወደ እስክንድርያ ገዳም ገቡ፡፡ አበምኔቱ አባ ጳኩሚስ በፈቃደ እግዚአብሔር የመጡ መሆናቸውን አውቀው መዓረገ ምንኩስና ሰጥተዋቸዋል፡፡
የንጉሳዊ የቅንጦት ኑሮ ንቀው ትተው ገዳም ገብተው በምንኩስና ተወስነዋል፡፡ አባታችን በተጋድሏቸውም ከአባ እንጦንስ፣ ከአባ ጳውሊ እና ከአባ መቃርስ ቀጥሎ በአራተኛ ማዕረግ አበ መነኮሳት ሆነው ተመርጠዋል።
በገዳመ ዳውናስ 7 ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ሮም ተመልሰው ሲያስተምሩ የሀገራችን ኢትዮጵያን ዜና ሰምተው ለመምጣት በ480 ዓ.ም ከአባ ፍሬምናጦስ በኋላ መንገድ ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በክንፉ ተሸክሞ አክሱም አድርሷቸዋል፡፡
ተመልሰውም ሄደው ስለ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መስክረዋል፡፡ ሐዋርያ ሳይላክላት በሃይማኖት በምግባር ጸንታ ትኖራለች ብለው ለሰባቱ ዘመዶቻቸው አበው መነኮሳት ነገሯቸው፡፡ ስምንቱም ጓዛቸውን ጠቅልለው በሮም ነግሶ የነበሩ ይስሐቅን (አባ ገሪማን) ጨምረው ንጉስ አልአሜዳ በነገሰ በአምስተኛ ዓመት ማለትም በ480 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ሆነው መጥተዋል፡፡
አባ አረጋዊ እናታቸው ቅድስት እድናን ደቀ መዝሙራቸውን ማትያስን አስከትለው እግረ መንገዳቸውን እያስተማሩና ድውያንን እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ደረሰዋል፡፡
ከእግረ ደብር ሆነው አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ በንግግሩ ሐሰት የሌለበት አምላካችን በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር 90/91፥11-16 ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስደሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል፡፡
ወዲያው ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ ቦታውም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሏል፡፡ በዚያ ዕለት ግማሽ ህብስት በልተው ጠገቡ፤ ከዚያ በኋላ ግን ምድራዊ ሕብስት አልተመገቡም፡፡ በሰንበተ ክርስታያን ከቅዳሴ በኋላ ሕብስተ ሰማያዊ እያመጡላቸው ይመገቡ ነበር እንጂ፡፡ ኋላም ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺህ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል፡፡
ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ ምድራዊ መንግስትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግስቴን አወርሰሃለሁ ብሎ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት ሾመውላቸው በዚህች ዕለት በዚያው በደብረ ዳሞ ተራራ በስተምስራቅ አቅጣጫ ተሰውረዋል፡፡

በዚህችም ቀን ዳግመኛ የቊስጥንጥንያ ንጉሥ የቴዎዶስዮስ ልጅ የቅዱስ ገብረ ክርስቶስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህም ቴዎዶስዮስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው ሚስቱም በጎ የምትሠራ እግዚአብሔርንም የምትፈራ ናት ስሟም መርኬዛ ነው። እነርሱም ልጅ ስለሌላቸው ያዝኑ ነበር ወደ ኢየሩሳሌምም ሒደው ስእለትን ተሳሉ ቸር መሐሪ ወደሆነ እግዚአብሔርም ለመኑ እርሱም ልመናቸውን ተቀበሎ ይህን ያማረ ልጅ ሰጣቸው ስሙንም አብደልመሲህ ብለው ሰየሙት ትርጓሜውም ገብረ ክርስቶስ ማለት ነው ። የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ የሥጋዊንም ትምህርት አስተማሩት ።
አድጎ በጕለመሰም ጊዜ የሮሜውን ንጉሥ ልጅ አጭተው እንደ ሥርዓቱ አጋቡት ከሌሊቱ እኩሌታም በሆነ ጊዜ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ተነሥቶ ወደሙሽራዪቱ ገባ እጅዋንም ይዞ ከእርስዋ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ ። ከዚያም የሃይማኖት ጸሎት በአንድ አምላክ እናምናለን የሚለውን እስከ መጨረሻ ጸለየ የተሞሸረበትንም ልብስ ከላዩ አውልቆ የግምጃ ልብስን ለበሰ ወደ ሙሽሪቷም ሒዶ ራስዋን ሳማት እንዲህም እያለ ተሰናበታት እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኑር ከሰይጣን ሥራ ሁሉ ያድንሽ ። እርሷም አልቅሳ ጌታዬ ወዴት ትሔዳለህ ለማንስ ትተወኛለህ አለችው እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ እተውሻለሁ እኔም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ልከተለው እሔዳለሁ የአባቴ መንግሥት አላፊ ነውና አንቺም መሐላሽን አስቢ አላት ያን ጊዜ መሐላዋን አስባ ዝም አለች ።
ለሠርጉም የታደሙት ሁሉ እንደተኙ በሌሊት ወጥቶ ሔደ ወደ ባሕርም ዳርቻ ደርሶ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞችን አገኘ የዓመት መንገድ ወደሚሆን አርማንያም እስከሚደርስ ከእነርሱ ጋር ተጓዘ ።
ነግቶ ወደ ሠርጉ አዳራሽ አባትና እናቱ በገቡ ጊዜ ሙሽራውን ልጃቸውን አላገኙትም ሙሽሪትንም ልጃችን ወዴት አለ ብለው ጠየቋት እርሷም እንዲህ አለቻቸው ። በሌሊት ወደ እኔ ገባ መሐላን አማለኝ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ ራሴንም ስሞኝ ከእኔ ዘንድ ወጣ እኔም እያለቀስኩ ብቻዬን አደርኩ ነገርዋንም ሰምተው ወድቀው በመጮህ ታላቅ ልቅሶን አለቀሱ ።
በዚያችም ጊዜ በሀገሮች ውስጥ ሁሉ ልጁን ገብረ ክርስቶስን ይፈልጉት ዘንድ ንጉሡ አምስት መቶ አገልጋዮቹን ላከ ለድኆችና ለምስኪኖችም ምጽዋት አድርገው የሚሰጥዋቸውን ብዙ ገንዘብን ሰጣቸው ።
ገብረ ክርስቶስ ግን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በአርማንም አገር በተሠራች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ደጅ የሚኖር ሆነ ። አባቱ የላካቸውም ሁለቱ አገልጋዮች ከዚያ ደርሰው ስለርሱ መረመሩ ግን ወሬውን ማግኘት ተሳናቸው ለድኆችም ምጽዋትን ሰጡ እርሱም ከድኆችም ጋር ምጽዋትን ተቀበለ ።
በዚያም ዐሥራ አምስት ዓመት ከኖረ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለአንድ ቄስ ተገለጸችለት ቦታውንም አመልክታ እንዲህ አለችው ። የእግዚአብሔር ሰው ገብረ ክርስቶስን ይዘህ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስገባው ከውጭ አትተወው ቄሱም እመቤታችን እዳዘዘችው አደረገ ።
ከዚህም በኋላ የተመሰገነ ገብረ ክርስቶስ በሌሊት ተነሣ ከእመቤታችንም ሥዕል ፊት ቁም ጸለየ እንዲህም አላት እመቤቴ ሆይ የተሠወረ ሥራዬን አንቺ ለምን ገለጥሽ አሁንም ወደሚሻለኝ ምሪኝ ይህንንም ብሎ የእመቤታችንን ሥዕሏን ተሳልሞ በሌሊት ወጥቶ ወደ ባሕሩ ወደብ ደረሰ ወደሌላ ሀገርም ሊሔድ ወዶ በመርከብ ተሳፈረ። ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ከአባቱ አገር ደረሰ የአባቱና የእናቱም ባሮች እየናቁትና እየሰደቡት በአባቱ ደጅ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ ።
ሲገቡና ሲወጡም ሽታው እንዳያስጨንቀን ይህን ምስኪን አስወግዱልን ይላሉ ወጭትና ድስትም አጥበው በላዩ ይደፉበታል ውሾችም እንዲናከሱበትና እንዲበሉት የሥጋ ትርፍራፊ ይጥሉበታል ውሾች ግን ቁስሉን ይልሱለት ነበር እንደዚህም አብዝተው አሠቃዪት ።
ከዚህም በኋላ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ለመነ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአባቴና ለእናቴ ባሮች በደል እንዳይሆንባቸው ወዳንተ ውሰደኝ ። በዚያንም ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው ። ከዚህም በኋላ ገድሉን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ጻፈ በእጁም ጨብጧት አረፈ ።
በእሑድ ቀንም ሕዝቡ ሁሉና ካህናቱ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር በቅዳሴ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳሉ የእግዚአብሔርን ሰው በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ቤት ፈልጉት የሚል ቃል ከሰማይ ሰሙ በዚያን ጊዜ ሔደው በአረፈበት ቦታ አገኙት። በእጁም ውስጥ የተጨበጠ ክርታስን አዩ ሊወስዷትም ሽተው መውሰድ ተሳናቸው ።
በአንድነትም በጸለዩ ጊዜ እጁ ተፈትታ ወስደው አነበቧት አባትና እናቱም ልጃቸው እንደሆነ አወቁ ታላቅ ጩኸትም ሆነ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ አክብረውም ቀበሩት መቃብሩም በሽተኞችን ሁሉ በመፈወስ ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራትን የሚያደርግ ሆነ ።

ዳግመኛም በዚህች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የሆነ አንዱ ቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስ አረፈ። ጌታችንም በቂሣርያ አገር ውስጥ በአለፈ ጊዜ በውስጧ አስተማረ ትምህርቱንም ሰምቶ ክብር ይግባውና ጌታችንን አምኖ ተከተለው ከሰባ ሁለቱ አርድዕትም ጋር ተቆጠረ ።
ጌታችንም ይሰብኩ ዘንድ ሁለት ሁለት አድርጎ በላካቸው ጊዜ ከእርሳቸው አንዱ ይህ ደቀ መዝሙር ነው ። ከመድኃኒታችንም ዕርገት በኋላ ሐዋርያት ከሾሟቸው ከሰባቱ ዲያቆናት ውስጥ የተቆጠረ ነው ። እርሱም ወደ ሰማርያ ወርዶ አስተማረ ብዙዎችንም አሳምኖ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ። ከዚህም በኋላ የተጎዳውን ሥራየኛ ሲሞንንም አጥምቆት ነበር እርሱ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በገንዘብ ሊገዛ አስቧልና ።
ከዚህም በኋላ ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ይሔድ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን አዘዘው በሔደም ጊዜ ለኢትዮጵያ ንግሥት ለህንደኬ በጅሮንዷ የሆነ ጃንደረባውን አገኘው እርሱም እንደ በግ ሊታረድ መጣ የሚለውን የነቢይ ኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር ።
ፊልጶስም ጃንደረባውን የምታነበውን ታስታውለዋለህን አለው ። ጃንደረባውም ያስተማረኝ ሳይኖር እንዴት አውቃለሁ አለ ። ፊልጶስም ስለ ጌታችን ስለ መከራው ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት ስለሆነው ሞቱ እንደተነገረ ተረጐመለት ። ጃንደረባውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አመነ ያን ጊዜም በፊልጶስ እጅ ከወንዝ ውኃ ውስጥ ተጠመቀ ከውኃውም በወጡ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም ።
ፊልጶስም ወደ አዛጦን ከተማ ደረሰ እያስተማረም እስከ ቂሣርያ ሔደ በከተማዎች ሁሉ በመዞር ወንጌልን ሰበከ ከአይሁድና ከሳምራውያንም ብዙዎችን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ። ለሐዋርያ ፊልጶስም ከእርሱ ጋር ወንጌልን የሚሰብኩ አራት ሴቶች ልጆች ነበሩት ። አገልግሎቱንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ ።

በዚህችም ቀን ከሮሜ ሀገር የሆነ የከበረ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ አረፈ ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አውፊምያኖስ የእናቱ አግልያስ ነው እነርሱም እግዚአብዘሔርን የሚፈሩ እጅግም ባለጸጎች ናቸው ። አብዝተውም ይመጸውታሉ ሁልጊዜም ይጸልያሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓትም ይጾማሉ ድኆችንና ችግረኞችንም ሳይይዙ አይበሉም ።
ነገር ግን ልጆች የሏቸውም ነበር የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ የተባረከ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለምኑት ነበር ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ ይህን መልኩ እጅግ ያማረ የከበረና የተባረከ ልጅን ሰጣቸው በወለዱትም ጊዜ በርሱ ደስ ብሏቸው ለድኆችና ለምስኪኖች ታላቅ ምሳ አደረጉ ስሙንም ሙሴ ብለው ሰየሙት ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ሰው ማለት ነው ስለእርሱ እግዚአብሔር ልመናቸውን ሰምቷልና ።
ከዚህም በኋላ ሙሴን በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት መንፈሳዊና ሥጋዊ ትምህርትን ጥበብን ሁሉ አስተማሩት ። አድጎም በጎለመሰ ጊዜ አባቱ አውፊምያኖስ ሚስቱ አግልያስን እነሆ ልጃችን ሙሴ አደገ ሚስትን ልናጋባውና በጋብቻውም ደስ ሊለን ለእኛ ይገባናል አላት ። የሙሴ እናት አግልያስም ሰምታ በዚህ ነገር ደስ አላት ከሮሜ አገር ታላላቆች ሰዎች ወገንም መልኳ እጅግ ያማረ አንዲት ብላቴና አጋቡት ። ታላቅ ሠርግንም በማዘጋጀት ሸልመው አስጊጠው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጋብቻ ሥርዓት አክሊላትን አቀዳጇቸው ። ከዚህ በኋላ ሥጋውንና ደሙንም ተቀብለው ወደሚሠረጉበት ቤት ገቡ ።
ከዚህም በኋላ በማግሥቱ አውፊምያኖስ ሚዜውን ጠርቶ እንዲህ አለው ሙሽራው ወደ ሙሽሪቷ ገብቶ የጋብቻውን ሕግ እንዲፈጽም ንገረው ያ ሚዜውም በነገረው ጊዜ ወደ ሙሽራዪቷ ገባ ድንቅ የሆነ ውበቷንና ደም ግባቷን ተመለከተ በልቡም አስቦ እንዲህ አለ ይህ ሁሉ ውበትና ደም ግባት አላፊ ጠፊ አይደለምን ። ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያዊት መንግሥቱ የሚደርስበትን መንገድ እንዲመራው እግዚአብሔርን ለመነው ።
ሙሽራዪቱንም እንዲህ አላት የተባረክሽ እኅቴ ሰላም ይሁንልሽ የእግዚአብሔርም ፍቅር አንድነት ከአንቺ ጋር ይኑር ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እስከምንገናኝ ደኅና ሁኚ ። ይህንንም በሚላት ጊዜ ልብሶቹን አውልቆ ሰጥቷት ከእርሷ ዘንድ ወጣ የተሞሸረበትንም ልብስ ለውጦ ከባሕር ዳርቻ እስከሚደርስ መንገዱን ተጓዘ ።
ልብሶቹንም ሁሉ ሽጦ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ሰጠ እርሱም ጨርቅ በመልበስ እንደ ድኃ ሁኖ ቁራሽ እንጀራ እየለመነ በየጥቂቱ እየተመገበ እስከ ሀገረ ሮሀ ድረስ ሔደ ።
ከዚያም በደረሰ ጊዜ ወደቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ ለሮሀ ንጉሥ ለአቃርዮስ በስብከቱ ወራት የተላከለትን ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥዕልና የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ከሥዕሎቹ ተሳልሞ በረከትን ተቀበለ ወደ ልዑል እግዚአብሔርም ፈጽሞ እያመሰገነ ጸለየ ። ወጥቶም ኑሮውን ከድኆችና ከምስኪኖች ጋር አደረገ ።
ከዚህም በኋላ መጸለይና መጾምን ጀመረ እስከ ምሽትም ይጾማል በቀንና በሌሊትም ጸሎቱን አያቋርጥም ምጽዋትንም ከድኆች ጋር ተቀብሎ እርሱ መልሶ ለሌሎች ይሰጣል ።
በዚያቺም ዕለት በነጋ ጊዜ ወደ ሠርጉ አዳራሽ አባትና እናቱ ሲገቡ ሙሽራው ልጃቸው ሙሴ በጫጉላው ቤት እንደ ሌለ ሰሙ ደስታቸውም ወደ ኀዘን የሠርጉም ዘፈን ወደ ልቅሶ ወደ ዋይታ ተለወጠ ።
ከዚህም በኋላ አውፊምያኖስ ባሮቹን ጠርቶ ብዙ ገንዘብን ሰጣቸው እንዲህም አላቸው ልጄን እስከምታገኙት ድረስ ሁለት ሁለት እየሆናችሁ ወደ ሀገሩ ሁሉ ሒዱ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ስጡአቸው ። እነርሱም በሀገሩ ሁሉ ተበታተኑ ። ከአባቱ አገልጋዮችም ሁለቱ አገኙት ግን አላወቁትም ምጽዋትንም ከድኆች ጋር ሰጡት ቅዱስ ሙሴም አውቋቸው እንዲህ ብሎ አመሰገነ ጌታዬ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስለ አንተ ፍቅር ከአባቴ ባሮች እጅ ምጽዋትን እቀበል ዘንድ ለዚህ ታላቅ ክብር አድለህኛልና አመሰግንሃለሁ ።
የአባቱ አገልጋዮችም ብዙ ወራት በሁሉ አገሮች ሲዞሩ ኑረው ወደ አውፊምያኖስ ጌታቸው ተመለሱ ። የእግዚአብሔር ሰው ቅዱስ ሙሴም ከሰንበት ቀኖች በቀር እህልን የማይቀምስ እስቲሆን ድረስ ተጋድሎውን በመጨመር በየሁለትና በየሦስት ቀኖች የሚጾም ሆነ ።
ከዚህም በኋላ እመቤታችን የከበረች ድንግል ማርያም ከዚያች ቤተ ክርስቲያን ካህናት ውስጥ ለአንድ ደግ ጻድቅ ቄስ ተገልጻ እንዲህ አለቸው በጥዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ውጣ ከምሰሶ አጠገብ ብቻውን ቁሞ የሚጸልይ ሰው ታገኛለህ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ግባ በለው በውጭ አትተወው ጾሙ ጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት መዓዛው ጣፋጭ እንደሆነ ዕጣን ተቀባይነትን አግኝቷልና ።
ሲነጋም ያ ቄስ ወደ ቅዱስ ሙሴ ሒዶ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ግባ አለው ሙሴም አባቴ ሆይ በከበረ ቦታ ላይ መቆም የማይገባኝ ኃጢአተኛ ነኝና ተወኝ አለው ቄሱም ወደ ቤተ መቅደስ አስገባህ ዘንድ ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ወዳንተ ተልኬአለሁ ብሎ መለሰለት ወደ ቤተ መቅደስም ያስገባው ዘንድ እንዳዘዘችው ነገረው ከዚህም በኋላ አስገባው ።
ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ወደ ሀገረ ጠርሴስ ይሔድ ዘንድ አስቦ እርሷም የሐዋርያው ጳውሎስ አገር ናት እንዲህም አለ እስከ ዕለተ ሞቴ በውስጥዋ እኖራለሁ ሥጋው ምንም በሮሜ አገር የሚኖር ቢሆንም የትውልድ አገሩ ናትና በረከትን እቀበላለሁ ብሎ ነው ።
በሌሊትም ወጥቶ ወደ ባሕር ዳርቻ ሔደ ወደ ጠርሴስም ይሔድ ዘንድ በመርከብ ተጫነ በባሕር መካከልም ታላቅ ነፋስ ተነሣባቸው ባሕሩም ከነፋሱ ኃይል የተነሣ ታወከ ወደየትም እንደሚሔዱ አያውቁም ነበር ቀኑ ጨልሞባቸዋልና ስለ ነፍሳቸውም ድኅነት ወደ እግዚአብሔር ለመኑ በዚያንም ጊዜ ባሕሩ ጸጥ ብሎ ታላቅ ደስታ ሆነ ብርሃንም ታየ ወደ ሮሜ ሀገር ወደብም እንደ ደረሱ አወቁ ።
ቅዱስ ሙሴም ተነሥቶ በመርከብ ውስጥ ያሉትን በሰላምታ ተሰናብቷቸው ጉዞውን ጀመረ በልቡም እንዲህ አለ ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ እንግዲህ እስከ ዕለተ ሞቴ ራሴን ለማንም እንዳልገልጥ ሕያው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያውቀኝ የለምና በአባቴ ደጅ እኖራለሁ ይህንንም ብሎ ወደ አባቱ ቤት ተጓዘ ።
በመንገድም ላይ አባቱን ተገናኘው ብዙ ሰውም ተከትሎት ነበር የእግዚአብሔር ሰው ሙሴም ቀረብ ብሎ አባቱ የተቀመጠበትን ፈረስ ልጓሙን ያዘ እንዲህም አለው እግዚአብሔር የባረከህ ያከበረህ አንተ ደግ ሰው እግዚአብሔርም ኃጢአትህን ይቅር ይበልህ የልብህንም ልመና ይስጥህ እኔም መጻተኛ ድኃ ሰው እንደ ሆንኩ እወቅ ለመጻተኛነቴና ለችግረኛነቴ የምትራራ ሁነህ ከማዕድህ ፍርፋሪ ልትመግበኝ ከወደድህ መኖሪያዬን በቤትህ አንጻር በደጃፍህ አድርግልኝ ዋጋህንም የሚሰጥህ እግዚአብሔር ነውና ።
በዚያንም ጊዜ አውፊምያኖስ የልጁ የሙሴን ስደት አስታውሶ በተቃጠለ ልብ አለቀሰ መኖሪያውንም በቤቱ ደጅ እንዲሠሩለት አዘዘለት። ሁለተኛም ከአገልጋዮቹ አንዱን በሚያሻው ነገር ሁሉ እንዲአገለግለው አዘዘው ።
የእግዚአብሔር ሰው ሙሴም ያን የሚያገለግለውን ወንድሜ ሆይ ከሰንበት ቀኖች በቀር መብልና መጠጥ እንዳታመጣልኝ እለምንሃለሁ ይኸውም ከቁርባን በኋላ ግማሽ እንጀራና የጽዋ ውኃ ብቻ ነው አለው ። በጾምና በጸሎትም እየተጋደለ በዚያ በአባቱ ደጅ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ ።
ሰውን የሚወድ ቸር ጌታችን ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው ወዶ ተገለጠለት እንዲህም አለው የመረጥሁህ አንተ ብፁዕ ነህ አንተ ፈቃዴን ፈጽመሃልና በዚህ ዓለም ከደስታ ኃዘንን ከብልጽግና ድኅነትን መርጠሃልና እኔም የማይጠፋ ብልጽግናን እሰጥሃለሁ ዳግመኛም ስምህን የሚጠራ መታሰቢያህንም ለሚያደርግ የተራበውን ለሚያጠግብ የተጠማውን ለሚያጠጣ የተራቈተውን ለሚያለብስ ገድልህንም ለሚጽፍ ወይም ለሚያጽፍ ስለ ስምህ በጎ ሥራ ሁሉ ለሚሠራ ቃል ኪዳንን ሰጠሁህ ። በሰማያዊት መንግሥትም በጎ ዋጋን እሰጠዋለሁ ተጠራጣሪ ካልሆነ በዚህ ዓለምም እጠብቀዋለሁ ከበጎ ነገር ሁሉ ምንም አላሳጣውም ።
አሁንም ከአራት ቀን በኋላ እወስድሃለሁ ምርጦቼ ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት ከአሉበትም አኖርሃለሁ ይህንንም ብሎ ከእርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ በታላቅ ክብር ዐረገ ።
ቅዱስ ሙሴም ከእግዚአብሔር ዘንድ ይህን ጸጋ በተሰጠ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ያን የሚያገለግለውንም ወንድሜ ሆይ እንግዲህ ስለ እኔ ከመድከም ታርፋለህና ወረቀትና ቀለም አምጣልኝ አለው። ያ አገልጋይም ከአነጋገሩ የተነሣ አድንቆ ወረቀቱንና ቀለሙን አመጣለት የከበረ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ገድሉን ሁሉ ጻፈ በአራተኛውም ቀን ያቺን የጻፋትን መጽሐፍ በእጁ ጨበጣት በእሑድ ቀንም በሰላም አረፈ ። መላእክት ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት ለሚያገለግሉት የዘላለም ተድላ ደስታ ለሚሰጥ ለነበረና ለሚኖር ፈጣሪያችን ምስጋና ይሁን እያሉ ነፍሱን ተቀበሏት ።
ሕዝቡም ሁሉ በቅዳሴ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው እያሉ ከመሠዊያው በላይ የጌታቸውን ሕጎቹንና ሥርዓቱን የሚያደርጉ ደጎች አገልጋዮች ባሮች የተመሰገኑ ናቸው እነርሱ ወደ ዘላለም ተድላ ደስታ ይገባሉና የሚል ቃልን ሲጮህ ሰሙ ።
ሊቀ ጳጳሳቱና ኤጲስቆጶሳቱ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ሕዝብም ሁሉ በሰሙ ጊዜ በላያቸው ታላቅ ፍርሀት ወደቀባቸው ። የቅዳሴውም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ይህን ምሥጢር ይገልጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በመጸለይ ማለዱ በዚያንም ጊዜ የእግዚአብሔርን ሰው በአውፊምያኖስ ቤት ፈልጉት እነሆ እርሱ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጥቷልና የሚል ቃልን ሰሙ ።
ሊቀ ጳጳሳቱም ይህን ነገር ሰምቶ አውፊምያኖስን ጠራውና ይህ ታላቅ ጸጋ በቤትህ ውስጥ ሲኖር በሕይወቱ ሳለ እንድንጎበኘው በረከቱንም እንድንቀበል ለምን አልነገርከንም አለው አውፊምያኖስም እንዲህ ብሎ መለሰ ክቡር አባት ሆይ ቅድስናህ ይመስክር ይህን የሚመስል በቤቴ ውስጥ እንዳለ አላወቅሁም ።
በዚያንም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱ ከሁሉ ካህናትና ሕዝብ ጋር ተነሥቶ ወደ አውፊምያኖስ ቤት ሔደ የከበረ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴንም በአረፈበት ቦታ አገኙት ክርታሱም በእጁ ውስጥ ነው ሊቀ ጳጳሳቱም ያቺን ክርታስ አንሥቶ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ የአውፊምያኖስ ልጅ እናቱም አግልያስ እስከሚለው ስሙ እስቲደርስ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አነበባት። እናትና አባቱም በሰሙ ጊዜ ደነገጡ መራር ልቅሶንም አለቀሱ ቤተሰቦቻቸውም ሁሉ ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ አጽናንቶ ጸጥ አደረጋቸው።
በዚያንም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱ የሐር ልብስ አስመጥቶ በክብር ገነዘው ወደ ቤተ ክርስቲያንም ወስደው ከሥጋው እስከሚባረኩ በቤተ መቅደስ አኖሩት። ካህናቱና ሕዝቡ ሁሉ ከዚህም በኋላ ብዙ በሽተኞች ዕውሮች ሐንካሶች ደንቆሮዎች ዲዳዎች መጥተው ከሥጋው በተሳለሙ ጊዜ ሁሉም ከደዌያቸው ዳኑ በዚያችም ቀን ታላቅ ደስታ ሆነ።
ሕዝቡም በበዙ ጊዜ የልጁን የሙሴን ሥጋ ከዐልጋው ላይ እንዳይጥሉት አውፊምያኖስ ፈራ ብዙ ገንዘብም አምጥተው ይበትኑ ዘንድ አገልጋዮቹን አዘዛቸው። ሥጋውን ትተው ወደ ተበተነው ገንዘብ ይሔዳሉ ብሎ አስቦ ነበር ግን ከቶ አንድ እንኳ ወደ ገንዘብ የሔደ የለም ።
ከዚህም በኋላ ሥጋውን በታላቋ በሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አኖሩ ከሥጋውም ብዙ ድንቆች ተአምራት ተደረጉ ዕውሮች አይተዋልና ሐንካሶችም ቀንተው ይሔዳሉና ደንቆሮዎችም ይሰማሉና ለምጻሞችም ይነጻሉና አጋንንት ያደሩባቸውም ይወጡላቸዋልና ሁሉም ካለባቸው ደዌ ይድናሉና።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages