እንኳን ለግሸን ደብረ ከርቤ: ለብዙኃን ማርያምና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 1, 2022

እንኳን ለግሸን ደብረ ከርቤ: ለብዙኃን ማርያምና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ግሼን ደብረ ከርቤ
 
ሃገራችን ኢትዮጲያ ሃገረ እግዚአብሔር መሆኗን ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ (መዝ.67, አሞጽ.9:7)
ሕዝቦቿ የድንግል ማርያምና የቅዱሳን አሥራት ናቸው።
የኢትዮጲያውያንን ያህል ድንግል ማርያምን የሚወድ ለቅዱስ መስቀሉ ክብርን የሚሰጥ: ቅዱሳንንም የሚዘክር ያለ አይመስለኝም። እመ ብርሃንም ፈጽሞ ትወደናለች። ለዚህ ቅንጣት ታህል አንጠራጠርም።
በዓለም እስከ አሁን ድረስ የሁለቱ ( የታቦተ ጽዮንና የቅዱስ ዕፀ መስቀሉ) መገኛ እንቆቅልሽ ነው። ለእኛ ግን ሁለቱም ያሉት በቤታችን ውስጥ ነውና እንመሠክራለን። ክብር ለቀደምት አበው ይድረሳቸውና አስፈላጊውን መንፈሳዊና ሥጋዊ ዋጋ ለፍለው ታቦተ ጽዮንን እና ቅዱስ ዕፀ መስቀሉን አምጥተውልናል።
 
በዚህች ዕለትም የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ከርቤ ግሼን ማረፉን አስበን በዓል እናከብራለን። ይኸውም ደጉ አፄ ዳዊት በሠይፈ አርዕድ የተጀመረውን ጥረት ቀጥለው በኃይለ እግዚአብሔር አሕዛብን አስደንግጠው: እመ ብርሃንንም በፀሎት ጠየቁ።
 
የአምላክ እናትም ረድታቸው ቅዱስ ዕፀ መስቀሉን ከኩርዓተ ርዕሡ : ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ከሳላት ምስለ ፍቁር ወልዳ እና ከብዙ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር ተላከላቸው። እርሳቸው መስከረም 10 ቀን መስቀሉን ተቀብለው: በዓሉን በተድላ አክብረው በመንገድ በ1396 ዓ/ም ዐርፈዋል።
 
አፄ ዳዊት ካረፉ በኋላ ቅዱስ መስቀሉ ለ30 ዓመታት ተቀምጧል። አፄ ዘርአ ያዕቆብ እስከ ነገሠበት 1426 ዓ/ም ድረስም ከ6 በላይ ነገሥታት አርፈዋል።
 
አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከነገሠ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለቅዱስ መስቀሉ በመካነ ንግሡ ደብረ ብርሃን ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ሲያስብ ጌታችን በራዕይ "አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል" አለው። ከዚህ ቀን ጀምሮ ደጉ ንጉሥ የመካነ መስቀሉን ቦታ ይፈልግ ዘንድ ከሠራዊቱ ጋር ደክሟል።
 
በመጨረሻም በነገሠ በ10 ዓመታት ግሼንን አምባሰል (ወሎ) ውስጥ አግኝቷል። ሐሴትን አድርጓል። ቦታዋ በሥላሴ ፈቃድ በትእምርተ መስቀል የተፈጠረች ናትና እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያንን አንጾ መስቀሉን በብረት: በመዳብ: በናስ በብር: በወርቅ ለብጦ : ዐፈር እንዳይነካው አድርጐ አኑሮታል።
 
በቦታውም ተአምራት ተደርገዋል። ጻድቁ ዘርዓ ያዕቆብም ጤፉት' የሚባል መጽሐፍን ጽፎ እዚያው አኑሮታል። መጽሐፉ እንደሚለው በሃገራችን ያለው ግማደ መስቀሉ (የቀኝ እጁ) ብቻ ሳይሆን ሙሉው ዕፀ መስቀል ነው። ይህ የተደረገውም መስከረም 21 ቀን ነው።
 
ብዙኃን ማርያም/ ጉባኤ ኒቅያ
 
ዳግመኛ ይህች ዕለት ' ብዙኃን ማርያም ትባላለች።
በቁሙ ሲታይ ድንግል ማርያም የብዙ ቅዱሳን የጸጋ እናት መሆኗን ያለክታል። በምሥጢሩ ግን በዚህች ዕለት በሃገረ ኒቅያ በእመቤታችን እና በአምላክ ልጇ የሚያምኑ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት መሰባሰባቸውን የሚያጠይቅ ነው።
የሊብያው ሰው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ: 2348 ምሑራን በመላው ዓለም ተሰበሰቡ።
ጥሪው የተላለፈው በወርኀ ሚያዚያ ሲሆን በመንገድ ችግር ሁሉም ተጠቃለው ኒቅያ የገቡት በዚህ ቀን ነበር።
ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸወ የቀና : ምግባራቸው የጸና 318ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ።
እነዚህ አባቶች ሊቃውንት "ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን። 318ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ: ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ: የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው። የጉባኤውን ዜና ግን ሕዳር 9 ቀን የምንመለከት ነንና የዚያ ሰው ይበለን። ይህች ቀን ለአባቶቻችን የሱባኤ መጀመሪያ ናት።
 
 ቅዱሳን ቆጵርያኖስ እና ዮስቴና 
 
ቆጵርያኖስ ማለት ሀገር እያስጨነቀ የሶርያ ጠንቅ ዋይ (መተተኛ) የነበረ ሰው ነው። ከሥራዩ ብዛት የተነሳ አጋንንትን የሚፈልገውን ያዛቸው ነበር። በዚያ ሰሞን ታዲያ ወደ አንጾኪያ ሔዶ የለመደውን ሊሠራ አሰበ። እንዳሰበውም ሔደ።
በአንጾኪያ ደግሞ ስም አጠራሯ የከበረ : ክርስትናዋ የሠመረ ድንግልናዋ የተመሠከረና ደም ግባቷ ያማረ አንዲት ወጣት ነበረች። ስሟም ዮስቴና (የሴቶች እመቤት) ትባላለች። እንዲህ ነው ስምና ሥራ ሲገጣጠሙ።
 
በወቅቱ ደግሞ የእርሷ ጐረቤት የሆነ አንድ ሰው በቁንጅናዋ ተማርኮ "ላግባሽ ቢላት አይሆንም አለችው። ምክንያቱም እርሷ መናኝ ናትና። በጥያቄው አልሳካ ቢለው በሃብት ሊያታልላት እገልሻለሁ ብሎ ሊያስፈራራት: በሥራይ (በመስተፋቅር) ሊያጠምዳት ሞከረ። ነገር ግን አልተሳካም። ምክንያቱም ሟርት በእስራኤል ላይ አይሰራምና። በመጨረሻ ግን ወደ ቆጵርያኖስ ሔዶ "አንድ በለኝ አለው። ቆጵርያኖስም ይሔማ በጣም ቀላል ነው" ብሎ ወዲያው አጋንንትን ጠራቸው። ሒዳችሁ ያችን ወጣት አምጡልኝ ሲልም ላካቸው። አጋንንቱ ወደ ቅድስት ዮስቴና ሲሔዱ ግን መላእክት ወርደው ቤቷን በእሳት አጥረውታል። ተመልሰው አልቻልንም" አሉት። እርሱም" አንዲት ሴት ካሸነፈቻችሁማ እኔም ክርስቲያን እሆናለሁ "ብሎ አስፈራራቸው። አጋንንቱም በማታለል አንዱ ሰይጣን እርሷን መስሎ ሌሎቹ ደግሞ አስረውት መጡ።
 
ቆጵርያኖስ ይህን ሲያይ ደስ ብሎት "እሠይ ምጽአትኪ ኦ ዮስቴና እግዝእቶን ለአንስት- የሴቶች እመቤት ዮስቴና እንኳን ደህና መጣሽ" ሲል: ስሟ ገና ሲጠራ ደንግጠው አጋንንት እንደ ጢስ ተበተኑ። "ለዛቲ ቅድስት በኀበ ጸውዑ ስማ: ከመ እንተ ጢስ ተዘርወ መስቴማ" እንዳለ መጽሐፍ።
 
ቆጵርያኖስ በሆነው ነገር ተገርሞ "ስሟን ሲጠሩ እንዲህ የራዱ ወደ እርሷማ እንደት ይቀርባሉ" ብሎ ተነሳ። መጽሐፈ ሥራዩን በሙን አቃጠለ። ሃብቱንም ለነዲያን አካፍሎ ሒዶ ክርስቲያን ሆ። የሚገርመው ድንግል ነበርና ከብዙ ተጋድሎ በኋላ ዲቁናና ቅስናን ተሾመ።
አምላክ መርጦታልና የቅርጣግና ጳጳስ ሆኖ ተመርጦ የክርስቶስን መንጋ በትጋት ጠብቋል። ቅድስት ዮስቴናም ገዳም አንጻ : ደናግሉን ሰብስባ ንጽሕናን ስታስተምር ኑራለች። በመጨረሻም በዚህ ዕለት ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስቶስን ካልካዳችሁ በሚል ብዙ አስቃይቶ አንገታቸውን አሰይፏል።
 
 ቸር አምላክ በኃይለ መስቀሉ ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን። የቅዱሳኑ ጸጋ ክብርም አይንሳን።
መስከረም 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ ቅዱሳን በዓላት
1.ግሸን ደብረ ደርቤ
2.ብዙኃን ማርያም
3. 318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት
4.ቅዱስ ቆጵርያኖስ ሰማዕት
5.ቅድስት ዮስቴና ድንግል
6.ቅድስት ጢባርዮስ ሐዋርያ
ወርኃዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
2.አበው ጎርጎርዮስ
3.አበው ምዕመነ ድንግል
4.አበው አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ
እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል። ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ።
ዲያቢሎሰን ግን ተቃወሙ። ከእናንተም ይሸሻል
ወሰብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages