ክርስቲያናዊ ሕይወት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 8, 2022

ክርስቲያናዊ ሕይወት

 


ሕይወት ዕድል ወይስ ምርጫ

ዕድል ሰዎች እንደሚሰጡት ትርጉም እነርሱን አድራሻ አድርጐ የሚመጣ፣ ያላሰቡትና ያልጠበቁት በረከት፣ በመንገዳቸው ፊት ለፊት የቆመ ማዕድ ማለት ነው፡፡ ሕይወት ግን በቋሚነት የተዋቀረችው በዕድል ሳይሆን በምርጫ ነው፡፡ ሕይወት ዕድል አይደለችም የምንለው፡-

1.             ማንኛውም ፍጥረት በአጋጣሚ ስላልተገኘ፣

2.            እግዚአብሔር ትእዛዝን ለሰው በመስጠቱ፣

3.            የሰው ልጅ ተጠያቂነት ያለውን ሕይወት በመቀበሉ፣

4.            እግዚአብሔር በሰው ጥፋተኝነት ላይ ብይን መስጠቱ ነው፡፡

1.          ማንኛውም ፍጥረት በአጋጣሚ አልተገኘም

በእግዚአብሔር ዕቅድና ዓላማ የሚታየውና የማይታየው ዓለም ተፈጥሯል፡፡ በስህተት የተገኘ፣ ቀስ በቀስም በማደግ ለዚህ የደረሰ ፍጥረት የለም፡፡ ፍጥረቱ በራሱ ላይ ካለው ዓላማ እግዚአብሔር በፍጥረት ላይ ያለው ዓላማ ይበልጣል፡፡ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ትርምስ የሚከሰተው በአጋጣሚ ያልተገኘውን ሕይወት በአጋጣሚ ስንኖረው ነው፡፡ ዕድል የምንለው አጋጣሚ፣ ራሱን በራሱ ለእኛ የናኘ ስጦታ ነው፡፡ እንዲህ የሚባል ቸር የለም፡፡ የስጦታ ሁሉ ባለቤት እግዚአብሔር ነው /ያዕ. 1÷17/፡፡ ሕይወትን ዕድል ስናደርጋት አጋጣሚ እናደርጋታለን፣ ከዚህ ሁሉ በላይ የእግዚአብሔርን ሰጪነት እንቃወማለን፡፡

2.         እግዚአብሔር ትእዛዙን ለሰው መስጠቱ

ሕይወት ረግጠን የምናያት ሳትሆን ዓይተን የምንረግጣት ናት፡፡ ዓይቶ ለመርገጥ ይረዳ ዘንድም እግዚአብሔር ትእዛዝን ለሰዎች ሰጥቷል፡፡ ሰዎች ጠጪነታቸውን፣ ሱሰኝነታቸውን ሳይቀር የ40ና የ80 ቀን ዕድሌ ነው ይላሉ፡፡ ጽድቅና ኃጢአት ግን ምርጫ እንጂ ዕድል አይደሉም፡፡ ሕይወት ወደ ወሰደችን የምንከተላት ሳትሆን ተምነን የምንጓዛት ናት፡፡ ለዚህም ትእዛዝ ተሰጥቶናል፡፡

3.         የሰው ልጅ ተጠያቂነት ያለውን ሕይወት መቀበሉ

ትእዛዝ የሚወጣው ሥልጣን ካለው አካል ነው፡፡ ሥልጣን ያለው አካል ደግሞ በትእዛዙ መሠረት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሔር ትእዛዝን ሰጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ተላላፊ የሆኑትን አዳምንና ሔዋንን እንዲሁም ቃየንን ጠይቋል፡፡ ሕይወት ዕድል ብትሆን ኖሮ ተጠያቂነት ባልኖራት ነበር፡፡ የመጣብን ነገር ነው፣ የማንለውጠው ምርጫ ነው እያልን በኃጢአታችን በተዝናናን ነበር፡፡ ሕይወት ግን ተጠያቂነት ስላላት በዘፈቀደ የምንጓዝበት ዕድል አይደለችም፡፡

4.         እግዚአብሔር በሰው ጥፋተኝነት ላይ ብይን መስጠቱ

ዕድል የሚባል የማንፈልገውን በረከት የሚያጥለቀልቀን፣ ዕድል የሚባል የማንፈልገውን ኃጢአት የሚያሸክመን ነገር የለም፡፡ እግዚአብሔር መርጠን የምንከተለውን ሕይወት ሰጥቶናል፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ለመልካም ሥራችንም ሆነ ለክፉ ሥራችን ብይን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ብይን የሚሰጠው ሕይወት ዕድል ሳትሆን ምርጫ ስለሆነች ነው፡፡

         ሕይወት የመዝራትና የማጨድ ሕግ ናት፡፡ ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው ሲባል ሁልጊዜ ለክፉ የምንጠቀምበት ነው፡፡ በመልካም ነገርም የምናጭደው የዘራነውን ነው፡፡ መልካም ነገርም ክፉ ነገርም ሁለቱም ዘር ነው፡፡ ዘር ከሆነ ሁለቱም ይታጨዳል፡፡ በመዝራትና በማጨድ ድንጋጌ ውስጥ ሦስት ቋሚ ሕጐች አሉ፡-

1.             የዘራነውን የሚመስል እናጭዳለን፡- ስንዴ ዘርተን በምንም መንገድ ገብስ አናጭድም፡፡ ስንዴ የዘራ የሚያጭደው ስንዴ ነው፡፡

2.            ከዘራነው በላይ እናጭዳለን፡- ኪሎ ስንዴ የዘራ ገበሬ በዓመቱ የሚያጭደው የዘራውን ያህል አይደለም፡፡ ከዘራው በላይ ያጭዳል፡፡ ምርት የተትረፈረፈ ነው፡፡ ቃሉ፡- “ነፋስን ዘርተዋል÷ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ” ይላል /ሆሴዕ 8÷7/፡፡

3.            ማንኛውም ዘር የአጨዳ ዘመን አለው፡- አንዳንዱ ዘር እንደ ወር ጎመን በወሩ፣ ሌላው እንደ ገብስ በ3 ወር፣ ሌላው እንደ ጤፍ በስድስት ወር ይታጨዳል፡፡ አንዳንድ ፍሬ ደግሞ በሃያ ዓመት፣ በስድሳ ዓመት ይደርሳል፡፡ መኸሩ ግን አይቀርም፡፡ አንዳንድ ሰው ሲያጠፋ በዕለት ይቀጣል፣ ሌላው ደግሞ ከሃያ ዓመት በኋላ መኸሩ ይደርስበታል፡፡

ሕይወት የመዝራትና የማጨድ ሕግ ከሆነ ሕይወት ዕድል አይደለችም፡፡ በባዶ ሒሳብ ላይ ቼክ ብንፈርም ወንጀል እንደሆነ ሁሉ እንዲሁም ያላስቀመጥነውን መልካምነት መፈለግ ወንጀል ነው፡፡ የምናጭደው የዘራነውን የሚመስል መሆኑን ማሰብ አለብን፡፡

ጌታችን እግሩ ሥር ተቀምጠው ለሚማሩት ይሟገትላቸዋል፡፡ በሌሎች ዘንድ የሚታዩት ሥራን የሚሸሹ፣ ሥራ ፈት ተደርገው ነው፡፡ ማርታ ስለ እህቷ ስለ ማርያም ያለችው ይህን ነው፡፡ ጌታ ግን የሰጠው ምላሽ፡- “ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” የሚል ነው /ሉቃ. 10÷42/፡፡ በዚህ ምላሽ ውስጥ፡-

1.             የእግዚአብሔርን ነገር ወደን ካልጣልነው ማንም ሊወስድብን አይችልም፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፡- “ሰዎች ስምህን ሊያጠፉ ይችሉ ይሆናል፣ የራስህን ጠባይ የምታጠፋው ግን አንተ ብቻ ነህ” ብሏል፡፡ ጌታም የማይሰርቁብን መክሊታችን መሆኑን አባቶች ገልጠዋል፡፡

2.            መልካም ዕድል የምንመርጠው ነው፡፡ “መልካም ዕድል ፈልጐን የሚመጣ ሳይሆን የምንመርጠው ነው፡፡

ሕይወት ዕድል ሳትሆን ምርጫ ናት ብለናል፡፡ በሕይወት ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር የሚሰጠን መልካም የሥራ አጋጣሚ አለ፡፡ ጌታችን ይህን ሲገልጥ፡- “ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች” ብሏል (ዮሐ.9÷4)፡፡ ጌታ ቀን ያለው የሥራ ጊዜን ነው፡፡ ጌታ መሥራት የሚቻልበትን ዘመን “ቀን” አለው፡፡ ያልፋል ማለት ነው፡፡ ቀን በሌሊት ይተካልና፡፡ አንድ ባለሥልጣን ፊት ሆኜ ይህን ጉዳይ አሳውቅልን አሉኝ፡፡ እኔም በእንዲህ ያለ ግንኙነት ከሹም ጋር መቀራረብ አልፈልግም፣ ወንጌሌን ያረክስብኛል አልኩኝ፡፡ የሰማሁት ድምፅ ግን፡- “መናገር በሚደመጡበት ዘመን ነው፣ አሁን እርሳቸው የሚሰሙት አንተን ነው” አሉኝ፡፡ አሳቡን ወደድኩት፡፡ አዎ መናገር በሚደመጡበት ዘመን፣ መሥራት በሚቻልበት ጊዜ ነው፡፡ ጆሮ የምንነፈግበት ዘመን ይመጣል፡፡

ለፊልድልፍያ ቤተ ክርስቲያን ከተላለፈ የተስፋ ቃል አንዱ፡- “እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንም ሊዘጋው አይችልም” የሚል ነው (ራእ. 3÷8)፡፡ የተከፈተ በር የሥራ ዘመን፣ የምንማርከው ትውልድ ነው፡፡

አንድ በንጉሡ ዘመን የተጻፈ መጽሐፍ ላይ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፎቶ ሥር፡-

“አገሬ ኢትዮጵያ ጠንክረሽ ተማሪ

ሁልጊዜ አይገኙም ዕድልና መሪ” ይላል፡፡

ሁለቱ ገጥመው አይገኙም፡፡ ሁለቱ ከገጠሙ ብዙ ታላላቅ ሥራ ይሠራል፡፡

እግዚአብሔር በሕይወት ላይ ልዩ አጋጣሚዎችን ይሰጣል፡፡ እነርሱም፡-

1.             ንስሐ

2.            ትምህርት

3.            የሚመክሩን ሰዎች

4.            የዕረፍት ጊዜ

1-     ንስሐ፡- እግዚአብሔር በግብፅ ላይ ዐሥር መቅሰፍት ያወረደው ኃይሉን በመግለጥ ከፈርዖን ጋር ለመወዳደር አልነበረም፡፡ ለፈርዖንና ለግብፃውያን የንስሐ ዕድል እየሰጠ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የንስሐ ዕድል (መልካም አጋጣሚ) ይሰጣል፡፡ እርሱ ማንም ይጠፋ ዘንድ ፈቃዱ አይደለምና፡፡ ንስሐ ዕድል ከሆነ ይወሰዳል፡፡ ብዙ ሰዎች ንስሓን በማንኛውም ጊዜ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ንስሓ ግን ዕድል ነውና ይወሰዳል፡፡ ንስሓ የምንገባው የንስሓ መንፈስ ሲሰጠን ነው፡፡ እግዚአብሔር የንስሓ ድምፅ ሲያመጣ መንፈሱንም አብሮ ይልካል፡፡ ሰውዬው ወዲያው ታዝዞ ንስሓ ቢገባ መንፈሱ ያግዘዋል፡፡ ነገር ግን ከዘገየ መንፈሱ ይሄዳል ትእዛዙ ይቀራል፡፡ ደጋግመን የንስሓን ድምፅ ከገፋን በመጨረሻ እግዚአብሔር እንደ ፈርዖን ልባችንን በማጽናት ለቅጣት ያመቻቸናል፡፡

2-    ትምህርት፡- ስለ ትምህርት በተነሣ ቁጥር “የትምህርት ዕድል” የሚል ቃል አብሮ ይጠቀሳል፡፡ ትምህርት ዕድል ነው፡ እግዚአብሔር መንፈሳዊ መምህራንን ሲሰጠን ቃሉ እንደ ካፊያ ሲወርድ ይህ ትልቅ ዕድል ነውና መጠቀም ይገባናል፡፡ አሊያ ካልተጠቀምንበት ይወሰዳል፡፡

3-    የሚመክሩን፡- ምክር በብዙ ገንዘብ በሚሸጥበት ዘመን ላይ ያውም የሕይወት ምክር የሚመክሩን እግዚአብሔር የሰጠን ልዩ አጋጣሚ ነውና፡፡ ልንጠቀምባቸው ይገባናል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የአንድ ሽማግሌ ሞት የትልቅ ቤተ መጻሕፍት መቃጠል ነው እንደሚባለው በትምህርት ቤት የማይገኙ በጐ ዕውቀቶች የሚሰጡንን መምህራን ማክበርና መጠየቅ ይገባናል፡፡

4-   የዕረፍት ጊዜ፡- ብዙ ጊዜ ከ21 -30 ባለው ዕድሜ እግዚአብሔር የዕረፍት ዘመን ይሰጣል፡፡ ወጣቶች ትምህርት ጨርሰው ያለ ሥራ ያለ ወዳጅ የሚሆኑበት ጭው ያለ ጊዜ ይገጥማቸዋል፡፡ ጉዳዩ ምን እንደሆነ አይረዱም፡፡ ቀጣዩ ጉዞ ፌርማታው ረጅም የሆነ በረራ ነውና እግዚአብሔር የማንበብያና የጽሞና ጊዜ እየሰጣቸው እንደሆነ ስለማይረዱ በጭንቀት ያልፋሉ፡፡ የጽሞና ጊዜ ማጣት ከባድ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚነግረንን ምክር ተቀብለን ይህን የጽሞና ጊዜ ካላበጀን በስደት፣ በበሽታ፣ በእስር ቤት በመክተት ብቻችንን ያገኘናል፡፡

የእስራኤል ልጆች ከተሰጣቸው ትእዛዝ አንዱ ስድስት ዓመት ሠርተው በሰባተኛው ዓመት ማረፍ፣ ለምድሪቱ ሰንበት መስጠት ነው፡፡ እነርሱ ግን ይህን ትእዛዝ መጠበቅ አቅቷቸው በስስት ለ490 ዓመታት ያህል ባዘኑ ምድሪቱንም አላሳረፏትም፣ በስድስተኛው ዓመት በረከት ሰባተኛውን ዓመት የሚያኖረውን ጌታ ማየት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የባቢሎንን ምርኮ አመጣ፡፡ የባቢሎን ምርኰ 70 ዓመት ነው፡፡ የ490 ዓመታት ሰንበት 70 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ቃሉ፡- “በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፣ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሰንበትን አገኘች” ይላል (2ዜና 36÷21)፡፡

በሕይወታችን ማረፍ አቅቶን እኔ ስቆይ ሁሉም ነገር ይቆማል በሚል አሳብ እንቅበዘበዛለን፡፡ ምናልባት ዛሬ በእስር፣ በስደት፣ በበሽታ የምናልፈው የኖርነውና የምንኖረው በራሳችን ሳይሆን በእግዚአብሔር መሆኑን እንድናስተውል ነው፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር ብቻችንን ሊያገኘን ስለወደደ ነው፡፡ ወዳጅ የብቻ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ወዳጃችን ነውና የብቻ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በፍቅር ሲጠይቁን እምቢ ካልን ቆም አድርጎ ጊዜውን ይወስዳል፡፡

እንግዲህ ተፈጥሮ ለእኛ እንጂ እኛ ለተፈጥሮ አልተበጀንም፡፡ እግዚአብሔር የእኛና የተፈጥሮ አዛዥ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ስንታዘዝ ተፈጥሮ ይገዛልናል፡፡ ተፈጥሮ የምንለው ቀንና ታሪክን የሚጨምር ነው፡፡ ቀኑም ታሪኩም የእኛ እንዲሆን እግዚአብሔርን መያዝ ያስፈልገናል፡፡ ይልቁንም መንፈሳዊ ነገር ምርጫ እንጂ ዕድል ባለመሆኑ ጠንክረን ልንይዘው ይገባል፡፡

በርግጥ ብዙ ሰነፎች በሀብት ሲጥለቀለቁ ብዙ አረጥራጪዎች የከበረ ነገር ሲያገኙ እናያለን፡፡ አዎ እግዚአብሔር መሥራትም መማርም የሚቸገሩትን ይረዳቸዋል፡፡ ጐበዙ በጉልበቱ ሲቆም እግዚአብሔር ደግሞ ደካማውን ያግዛል፡፡ ዕድል የምንለው ብዙ ጊዜ ገንዘብን በመሆኑ ወይም ምድራዊ ነገር ብቻ በመሆኑ አስተሳሰባችን የወረደ ነው፡፡ ይህ ዓለም የተበጀው ለመንፈሳዊ ዓላማ ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊውን ነገር አክብረንና አልቀን መያዝ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ይህን ዓለም ከመፍጠሩ በፊት ያየው የከተሞችን ዕድገት ሳይሆን የቅድስና ኑሮአችንን ነው፡፡ እግዚአብሔር ያየልንን ስንኖር ቤታችን መሠራት ይጀምራል፡፡ ቤትን ጥረትና ምኞት ብቻ አይገነባውም፡፡ ቤተ ሠሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ጌታዬ ሆይ እኔ ላንተ ቤት፣ አንተ ለእኔ ቤት ሥራ ልንል ይገባናል፡፡ ሕይወት ምርጫ ናትና አሁን እንምረጥ! 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages