የጥቅምት ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተጉባኤ ጥቅምት ፳፭ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, November 4, 2022

የጥቅምት ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተጉባኤ ጥቅምት ፳፭ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም

 





ጥቅምት ፳፭ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም

አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከጥቅምት ፲፬ እስከ ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም ድረስ ፳፪ የመወያያ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ባካሔደው ጉባኤ በባለ ሙያዎች ተጠንቶ የቀረበውን ሕገ ቤተክርስቲያን ማሻሻያዎችን ጨርምሮ ያጸደቀ ሲሆን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን አሰራሮቿን ለማዘመንና የምታከናውናቸው ተግባራት ሁሉ በህግና በመመሪያ የተደገፉ ከመሆን ባለፈ ነባር መመሪያዎችም ዘመኑን በሚመጥኑ መመሪያዎች እንዲሻሻሉ ማድረግ የሚያስችሉ ደንቦችንም አጽድቋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከፍ ሲል ከተገለጹት
ነጥቦች በተጨማሪ ለቤተክርስቲያናችን አገልግሎት መቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ልዩ ልዩ ወሳኔዎችንም አስተላልፏል።
በ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በጀት ዓመት በጠቅላይ ቤተክህነት ደረጃ ሊተገበሩ ለታቀዱ ዕቅዶች ማስፈጸሚያ የሚሆን በጀትም አጽድቋል።በአጠቃላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዚህ ዓመት ጉባኤው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቅሙ፣ለህግና ሥርዓት መስፈን የሚያገለግሉ፣ተቋማዊ አሰራርን የሚያጠናክሩ፣ግልጽ የአሰራር ሥርዓትን የሚፈጥሩ ደንቦችን በማጽደቅና ውሳኔዎችን በማስተላለፍ
ጉባኤውን በስኬት አጠናቋል።
የዘንድሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እጅግ ጠቃሚ ውሳኔዎች የተላለፉበት ብቻ ሳይሆን ለወትሮው ከቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ጀምሮ የሚስተዋሉ የድጋፍና የተቃውሞ ሰልፎች፣ የፊርማ ማሰባሰብ ሂደቶችና በብፁዓን አባቶች ቤት በመዞርና በቤታቸው በር ስር የአቤቱታና የአድማ ወረቀቶችን መበተን ያልታየበት ፍጹም ጸጥታ፣መረጋጋትና ስክነት የተሞላበት የጉባኤ ጊዜ ነበር።ለወትሮ ብፁዓን አባቶች ከጉባኤ ሲወጡ ከጉባኤው አዳራሽ ጀምሮ ብፁዓን አባቶችን በመከተል ይታወቁ የነበሩ ነባር የሲኖዶስ ጉባኤ ሰሞን ታዋቂ ደንበኞችም አደብ የገዙበት የጉባኤ ወቅት ነበር።
ይህ ሁሉ ሥርዓት እና የህግ መከበር ሂደት ፍጹም ባልተለመደ መልኩ በዘንድሮ ጉባኤ ላይ እንደምን ሊከበር ቻለ?የሚል ጥያቄ ስናነሳም መልሱ ከጉባኤው ቀደም ብሎ የተሰሩ ሥራዎች ውጤት መሆኑን እንገነዘባለን።
ይህን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚከናወነውን ጉባኤን ክብርና ሞገስ ለማስጠበቅም ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ ከቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዩወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያከናወኗቸው የቅድመ ጉባኤ ሥራዎች ውጤት መሆኑንም መገንዘብ ይገባል።
ሁለቱ ብፁዓን አባቶች ቤተክርስቲያን የጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት በመገንዘብና ለተቋማዊ ክብርና ልዕልና መከበር ካላቸው ተመሳሳይ አቋም በመነሳትም በኃላፊነት የሚመሯቸውን የሥራ ኃላፊዎች በማስተባበርና በመምራት ባከናወኗቸው የቅድመ ጉባኤያት ተግባራት
እነሆ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ደረጃ የ፵፩ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ፍጹም በተረጋጋ፣በሰከነና የቤተክርስቲያናችንን ክብር ሊመጥን በሚችል መልኩ የተከናወነበትን አዲስ ታሪካዊ ሂደት መመልከት ችለናል።ለዚህም ሁለቱን ብፁዓን አባቶቻችንን ልናመሰግናቸውና ልናከብራቸው ይገባል።
በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም በአባቶች መካከል መከባበርና መደማመጥ በቤተክርስቲያን ልዕልናና ክብር ዙሪያ ተመሳሳ
አቋም በመያዝ፣ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገትና ለአገልግሎቷ መቀላጠፍ በሚጠቅሙ ህግጋት ዙሪያ የጋራ ስምምነት ላይ በመድረስ ያለ አንዳች ልዩነት በፍቅርና በመከባበር ጉባኤውን በስኬት በማጠናቀቅ የቤተክርስቲያናችንን ከፍታ ያሳዩን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አባላትም ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።
የጉባኤው ሂደት የተቃናና የተሳካ ሆኖ ጉባኤው በተያዘለት አጀንዳ መሰረት ሀሳቦች በአግባቡ ተንሸራሽረው ሁሉም የተስማሙበት ሀሳብ ገዥ ሆኖ እንዲጸድቅ የማድረጉን ሂደት በፍጹም ቅንነትና አባታዊ ኃላፊነት ጉባኤውን በርዕሰ መንበርነት የመሩት ቅዱስ አባታችንም ለዚህ ጉባኤ መሳካት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም።
የቅዱስ ሲንዶስ ጸሐፊውም የጉባኤው ሂደት ህጋዊ አሰራርን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን፣ውይይቶች በአጀንዳ ቅደም ተከተል መሰረት ውሳኔ እንዲያገኙና ውሳኔ የተላለፈባቸው ቃለ ጉባኤዎችም በወቅቱ ተነበው እንዲፈረሙ በማድረግ ያከናወኑት ኃላፊነት የተሞላበት ተግባርና ያስመዘገቡት ውጤት የሚመሰገን ነው።ከብጹዕ የቅዲስ ሲኖዶስ ጸሐፊው ጋር የሚሰሩ ጸሐፊዎችም ትጋትና፣ትህትና፣ዕውቀትና ታዛዥነታቸው የሚደነቅ ሲሆን የውይይቱን ቃለ ጉባኤ በአግባቡ በመመዝገብና በወቅቱ ለፊርማ በማቅረቡ ሂደት የተዋጣሐት ሥራ የሰሩ በመሆናቸው ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።
በአጠቃላይ ከዚህ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በቤተክርስቲያናችን የተከናወኑ አበይት ጉባኤያት እጅግ በተሳካና ባማረ መልኩ መከናወን የቻሉት በጠቅላይ ቤተክህነትና በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ደረጃ በተሰሩት ቅንጅታዊ ሥራዎች በመሆኑ በተቋም ደረጃ ለተሰሩ ሥራዎች ሁሉ ሁለቱ የቤተክርስቲያናችን
ተቋማት ምስጋናችን ይድረሳቸው።
ለወደፊትም በመናበብ፣ በመረዳዳት፣በመተሳሰብና ቅድስት ቤተክርስቲያንን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሥራዎችን በማከናወን የበለጠ ሰርተን ውጤት ለማስመዝገብ እንድንችል የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።አሜን።
                           Source:  የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን
                                         ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
                                     ጥቅምት ፳፭ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
                                             አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages