ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 25 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, November 4, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 25

 

ጥቅምት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
2.አባ ዕብሎይ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
4.ቅዱሳን አብርሃምና ሐሪክ
5.ቅዱሳን አሞኒና ሙስያ (የታላቁ ዕብሎ ወላጆች)
 
ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.ቅዱስ አቡፋና ጻድቅ
6.ታላቁ አባ ቢጻርዮን

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አምስት በዚህች ቀን ቅዱስ_አቡነ_አቢብ (አባ ቡላ) አረፈ፣ የመላእክት አምሳል የሆነ አባ_እብሎይ አረፈ፣ የከበረ ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፣ የደብረ ሊባኖሱ አባ_ሕፃን_ሞዐ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ነው።

ጥቅምት ሃያ አምስት በዚህች ቀን ታላቅና ክብር የሆነ አቢብ የተባለ መስተጋድል አባ ቡላ አረፈ።
የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብርሃም የእናቱም ስም ሐሪክ ነው እነርሱም ከሮሜ አገር ሉፊ ከሚባል አውራጃ ናቸው በዘመናቸውም ከሀዲው ንጉሥ መክስምያኖስ በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራ ስለ አመጣ ስደት ሁኖ ነበርና እነርሱም በስደት ብዙ ዘመን ኖሩ።
ልጅንም በአጡ ጊዜ የተባረከ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ በጾም በጸሎት ተወስነው ወደ እግዚአብሔር ለመኑ የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም ተገለጠላቸውና ፍሬ የመላበትን ዘለላ ሰጣቸው።
ይህም ቅዱስ በተፀነሰ ጊዜ በቤታቸው አጠገብ ታላቅ ዛፍ በቀለ በቅጠሉም ላይ በሮማይስጥ ቋንቋ ቡላ የእግዚአብሔር አገልጋይ በጽዮንም አድሮ የሚኖር የያዕቆብ ፈጣሪ ያከበረው የሚል ጽሑፍ ነበረበት።
በተወለደም ጊዜ ክርስትና ሳያስነሡ ዓመት ሙሉ አኖሩት እመቤታችን ማርያምም ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ለሰለባስትርዮስ ተገልጣ ወደ አብርሃም ቤት ሒዶ ሕፃኑን እንዲአጠምቀው አዘዘችው እርሱም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው ስሙንም ቡላ ብሎ ሰየመው እናትና አባቱም ሳይነግሩት ቡላ ስለ ሰየመው አደነቁ ዕፁብ ዕፁብ አሉ።
ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ በጸለየ ጊዜ የቊርባን ኅብስትና ወይን የተመላ ጽዋ ከሰማይ ወረደ እርሱም ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ከሕፃኑ ጋር አቀበላቸው በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ የአንድ ዓመት ልጅ ሲሆን በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ አብ በግብር በአካል በሰም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ ወልድ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት በአብ ከወልድ ጋር አንድ የሆነ መንፈስ ቅዱስ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው ብሎ ተናገረ።
ከጥቂት ዘመንም በኋላ አባትና እናቱ ኅዳር ሰባት ቀን ሙተው ሕፃኑ ብቻውን ቀረ።
ሕፃኑም ዐሥር ዓመት በሆነው ጊዜ ለጣዖት መስገድን የሚያዝ ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ቡላም በሰማ ጊዜ ወደ መኰንኑ ሒዶ የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ መኰንኑም በአካል ታናሽነቱን አይቶ እጅግ አደነቀ በዚያንም ጊዜ በችንካር እንዲቸነክሩት ሥጋውንም እንዲሠነጣጥቁት ቆዳውንም ከዐጥንቱ እንዲገፉ እጆቹንና እግሮቹንም በመጋዝ እንዲቆርጡ ጀርባውንም እንዲገርፉ በሾተሎችና በጦሮች መካከል አድርገው ከመንኰርኵር ውስጥ እንዲጨምሩት ዳግመኛም በመንገድ ላይ እንዲጐትቱት አዘዘ የመላእክት አለቃ ሚካኤልም መጥቶ አዳነው ያለ ጉዳትም ጤነኛ አደረገው።
ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ መኰንን ሒዶ እርሱንና የረከሱ ጣዖቶቹን ረገመ መኰንኑም ተቆጥቶ በሚያዝያ ወር ዐሥራ ስምንት ቀን ራሱን በሰይፍ ቆረጠው ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው ወደ አንድ ገዳምም ወስዶ የምንኲስና ልብስንና አስኬማን በመስቀልም ምልክት አለበሰው። እንዲህም አለው ከቅዱሳን ጻድቃን አንድነት ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር አዝዞሃል።
ያን ጊዜም ቅዱስ አባ ቡላ ከደረቅ ተራራ ላይ ወጣ ያለ ማቋረጥም በውስጧ እየተጋደለ ኖረ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራውንና ስቅለቱን በአሰበ ጊዜ ከረጅም ዕንጨት ላይ በመውጣት ራሱን ወደታች ሁል ጊዜ ይወረውር ነበር።
በአንዲትም ቀን ከዛፍ ላይ በተወረወረ ጊዜ ሰይጣን ሊገድለው ስለ በረታበት ሞተ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና መድኃኑታችን ከሞት አነሣውና እንዲህ አለው ከእንግዲህ ስምህ ቡላ አይሁን አቢብ ይባል እንጂ የብዙዎች አባት ትሆናለህና።
እርሱም የክርስቶስን ፍቅር እጅግ ጨመረ ፊቱንም እየጸፋ ሥጋውን በየጥቂቱ እየቆረጠ ጀርባውንም ሰባት መቶ ጊዜ እየገረፈ ኖረ ጌታችንም ይፈውሰው ነበር በየእሑድም ቀን ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም እንደተወለደ በሌሎች ቀኖችም እንደተያዘና ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበለ ሁኖ ይገለጽለት ነበር።
ስለዚህም ሳይበላ ሳይጠጣ አርባ ሁለት ዓመት ኖረ ዳግመኛም ናላው ፈስሶ እስቲአልቅ ዐሥራ ሁለት ወር በራሱ ተተክሎ ኖረ። በአንዲትም ቀን የጌታችንን መከራ በአሰበ ጊዜ ሰይፉን በአንጻሩ ተከለ ከዕንጨት ላይም ወጥቶ በላዩ ወድቆ ሞተ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም ከአእላፍ መላእክት ጋር መጥታ የእኔና የልጄ ወዳጅ ሰላምታ ይድረስህ አለችው ። ከበድኑም ቃል ወጥቶ የሰማይና የምድር ንግሥት እመቤቴ ሰላምታ ይገባሻል አላት እርሷም በከበሩ እጆቿ ዳሥሣ ከሞት አስነሣቸው።
ዕድሜውንም ፈጽሞ ከዚህ ዓለም የሚወጣበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ በእጁ ልዩ የሆኑ አክሊሎችን የሚያበሩ ልብሶችንም ይዞ ተገለጠለት ወዳጄ አቢብ ሆይ በማያልቅ ተድላ ደስታ ደስ አሰኝህ ዘንድ ወደእኔ ና ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ እኔ ኃጢአቱን አስተሠርይለት ዘንደ በራሴ ማልኩልህ ወይም ለተራቆተ የሚያለብሰውን ለተራበም የሚያጠግበውን ለተጠማ የሚያጠጣውን የገድልህን መጽሐፍም የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውንና የሚሰማውን በጸሎትህም የሚታመኑትን ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እምራቸዋለሁ ይህንም ብሎ አፉን ሳመው በደረቱም ላይ አድርጎ ወደአየር አወጣው የመላእክትንም ምስጋና በሰማች ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ገባች።

ዳግመኛም በዚህችም ቀን ደግሞ አክሚም ከሚባል አገር የመላእክት አምሳል የሆነ አባ እብሎይ አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አሞኒ የእናቱ ስም ሙስያ ነው ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሆኑ በሕጉ ጸንተው የሚኖሩ ድኆችንና መጻተኞችን የሚወዱ የሚረዱ ናቸው።
ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም ሙስያም ዕንጨት የያዘ ብርሃናዊ ሰው በቤቷ ውስጥ ሲተክለውና ወዲያውኑ ለምልሞ አብቦ ሲያፈራ ያ ብርሃናዊው ሰውም ከዚህ ፍሬ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል ሲላት እርሷም ከፍሬው ወስዳ ስትበላና በአፏ ውስጥ ጣፋጭ ሲሆንላት በልቧም ፍሬ ይሆንልኝ ይሆን ስትል ራእይን አየች።
ከእንቅልፏም በነቃች ጊዜ ራእይን እንዳየች ለባሏ ነገረችው እርሱም እርሷ እንዳየችው ያለ ማየቱን ነገራት እግዚአብሔርንም አብዝተው አመሰገኑት ትሩፋትንና ተጋድሎን በመጨመር በየሁለት ቀን የሚጾሙ ሆኑ ምግባቸውም እንጀራና ጨው ነው።
ይህን ቅዱስ እብሎይን በፀነሰችው ጊዜ እናቱ በገድል ወንዶችን እስከምታሸንፍ ድረስ በየሌሊቱ ሁሉ አንድ ሽህ ስግደትን ትሰግዳለች ሕፃኑን እስከ ወለደችው ድረስ ዘጠኝ ወር ያህል እንዲህ ስትጋደል ኖረች።
በወለዱትም ጊዜ እብሎይ ብለው ሰየሙት በጐለመሰም ጊዜ የምንኩስናን ልብስ ሊለብስ ወደደ ምክንያትም እስቲያገኝ እንዲህ ኖረ አቢብ የሚባል ወዳጅ ነበረውና እርሱ በሌሊት ወሰደው ከላዕላይ ግብጽ በሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም ውስጥ መነኰሰ በገድልም በመጠመድ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።
ከጥቂት ወራትም በኋላ በጥቅምት ወር ሃያ አምስት ቀን አባ አቢብ አረፈ ያን ጊዜ አባ እብሎይ አብሎግ ወደሚባል ገዳም ሔደ ወደርሱም ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እርሱም በበጎ አምልኮ እግዚአብሔርን መፍራትን የሚያስተምራቸው ሆነ።
ቅዱስ አቢብም በአረፈበት ቀን መታሰቢያውን ሲያደርጉ ይህ ቅዱስ አባ አብሎይ ወንድሞች ሆይ በአባ አቢብ ስም ዛሬ ጸሎትን የሚጸልየውን ኃጢአቱን እግዚአብሔር ያስተሰርይለታል በዕረፍትህ መታሰቢያ ቀን የአባ አቢብ ፈጣሪ ሆይ ኃጢአቴን ሁሉ ተውልኝ ብሎ አንዲት ጸሎትን የሚጸልየውን ሁሉ እኔ ኃጡአቱን እተውለታለሁ ሲል ቃል ኪዳን ሰጥቶታልና አላቸው።
በዚያችም ሰዓት ከመነኰሳት አንዱ አረፈ እነርሱም ሊገንዙት በዚያ ቁመው ሳሉ አባ እብሎይ ስለ ተናገረው ቃል ከመነኰሳት አንዱ ተጠራጠረ በዚያንም ጊዜ ያ የሞተው ተነሥቶ ይናገር ዘንድ ጀመረ አባ እብሎይ ስለተናገረው ቃል ለምን ትጠራጠራላችሁ ለአባታችን አቢብ በመታሰቢያው ቀን በዚህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ሰጥቶናልና አላቸው ። ይህንንም ብሎ ተመልሶ አረፈ መነኰሳቱም አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
ይህ አባ እብሎይም ብዙ ዘመናት ኖረ ልጆቹ መነኰሳትም በዙ ብዙ ገዳማትም ተሠሩለት። የኖረበትም ዘመኑ በታላቁ አባ መቃርስ ዘመን ነው የአባ እብሎይንም የትሩፋቱን ዜና አባ መቃርስ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኘበት እርሱን እያጽናና እያረጋጋ መነኰሳት ልጆቹንም እግዚአብሔር የሚወደውን በመሥራት ያጸናቸው ዘንድ መልእክትን ጻፈለት።
ይህንንም በአስቄጥስ ገዳም ሁኖ አባ መቃርስ ሲጽፍ አባ እብሎይ በላዕላይ ግብጽ ሳለ በመንፈስ ቅዱስ አውቆ በዙሪያው ያሉትን መነኰሳት እንዲህ አላቸው። እነሆ ማጽናናትን የተመላች መልእክትን አባ መቃርስ ጻፈልን። ከዚህም በኋላ ከአባ መቃርስ ዘንድ የተላኩትን መነኰሳት ሁሉ ወጥተው በደስታ ተቀብለው አስገቧቸው መልእክቱንም በመነኮሳቱ ሁሉ ፊት አነበቡ በታላቅ ደስታም ደስ አላቸው።
ይህም አባ እብሎይ ወደ አባ አሞንዮስ የሔደ ከእርሱ ዘንድም የምትኖረውን ስሟ የዋሂት የተባለችውን የተቀደሰች ሴት ያየ ነው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው ወዶ በየካቲት ወር በአምስተኛው ቀን አረፈ እኛ ግን የአባ እብሎይን ዜና ከወዳጁ ከአባ አቢብ ጋር ጻፍን።

በዚህችም ቀን ዳግመኛ አቅፋሐስ ከሚባል አገር ሰማዕት ለሆነ ለቅዱስ ዮልዮስ ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው።
ይህም ቅዱስ ዮልዮስ በሀገረ ጥዋ በሰማዕትነት በአረፈ ጊዜ በገድሉ እንደተጻፈ ዲዮቅልጥያኖስ ከጠፋ በኋላ ጻድቅ ሰው ቈስጠንጢኖስ ሳይጠመቅ ነገሠላቸው በጥቂት ወራትም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ የቤተ ክርስቲያንም ሥልጣን ከፍ ከፍ አለ ከሀድያን ነገሥታት ለገደሏቸው ንጹሐን ሰማዕታት በስማቸው አብያተ ክርስቲያናት ታነፁ።
ስለ ቅዱሳን ሰማዕታትም ስለ ሥጋቸው እንዲአስብ ገንዞ በመሸከም ወደ አገራቸው እንዲአደርሳቸው ከአገልጋዮቹም ጋር ገድላቸውን እንዲጽፍ እግዚአብሔር እንደአቆመውና እንደጠበቀው ከዚህም እርሱ ራሱ በሰማዕትነት እንዴት እንደ ሞተ የቅዱስ ዮልዮስን ዜና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በሰማ ጊዜ ስለበጎ ተጋድሎው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ቅዱስ ዮልዮስን አመሰገነው ።
ስለዚህም ለቅዱስ ዮልዮስ ያማረች ቤተ ክርስቲያን በግብጽ አገር ሠርተው ሥጋውን በውስጧ ያኖሩ ዘንድ ንጉሡ ወደ ግብጽ አገር ብዙ ገንዘብ ላከ በዚያንም ጊዜ ንጉሡ እንዳዘዘ አነፁለት ። የቅዱስ ዮልዮስንም ሥጋ አፍልሰው በውስጧ አኖሩት ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስም ከኤጲስቆጶሳቱ ጋር አከበራት እንደዛሬዪቱም ቀን በዓል አከበረባት ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

በዚህችም ቀን የደብረ ሊባኖሱ አባ ሕፃን ሞዐ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ነው። በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር 25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡ አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች አራት ወንድሞች አሏቸው፡፡
እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣ ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ ዜናማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡
ከ47ቱ የሀገራችን ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸው በኋላ በኃይል የተነፈሱባት ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን እየፈወ ነው፡፡
ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ጻድቁ ጥር 25 ቀን ልደታቸው፣ ጥቅምት 25 ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ሲሆን ሐምሌ 25 ደግሞ ዕረፍታቸው ነው፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages