ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 26 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, November 4, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 26

 

ጥቅምት 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዮሴፍ)
2.ቅዱስ ጢሞና ሐዋርያ ወዲያቆን
3.ቅዱስ አግናጥዮስ
4.ቅዱስ ፊልዾስ
 
ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንአንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ስድስት በዚህች ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያው_ቅዱስ_ጢሞና በሰማዕትነት አረፈ፣ የጌታ ወንድም የተባለው ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_ዮሴፍ መታሰቢያው ነው።

ጥቅምት ሃያ ስድስት በዚህች ቀን ጌታችን ከመረጣቸውና በሽተኞችን ሁሉ ይፈውሱ ዘንድ አጋንንትንም ያወጡ ዘንድ ሥልጣንን ከሰጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ቅዱስ ሐዋርያ ጢሞና በሰማዕትነት አረፈ።
ይህም ቅዱስ ጢሞና ሰማያዊ ሀብትን መለኮታዊ ኃይልን ገንዘብ አድርጎ በሽተኞችን ፈወሳቸው አጋንንትም ተገዙለት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በምድር ሳለ አገለገለው። ወደ ሰማይም ከዐረገ በኋላ ሐዋርያትን አገለገላቸው በሃምሳኛው ቀንም ጰራቅሊጦስ በወረደ ጊዜ የአጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከእርሳቸው ጋር ተቀበለ።
ከዚህም በኋላ ሰባት ሁነው ከተቆጠሩት ዲያቆናት ጋር ሐዋርያት ሾሙት እነርሱ መንፈስ ቅዱስን ዕውቀትንም የተመሉ እንደሆኑ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምስክር ሁኖአል።
በዲቁና አገልግሎትም ጥቂት ከአገለገለ በኋላ ብልቃ ከሚባል አገር በስተምዕራብ በሆነ ስብራ በሚባል አገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾሙት በውስጧም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት አስተማረ ከዮናውያንና ከአይሁድም ብዙዎችን አጠመቃቸው።
የዚያች አገር ገዥም ይህን በሰማ ጊዜ ቅዱስ ጢሞናን ይዞ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃይቶ በእሳት አቃጠለው በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ።

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዮሴፍ መታሰቢያ ነው፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ የጌታችን ወንድም የተባለውና የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የነበረው ነው፡፡
እርሱም የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ ሲሆን ከልጆቹ ሁሉ ትንሹ ነው፡፡ ድንግልና ንጹሕ ሆኖ ከጌታችን ጋር እየተጫወተ አብሮ አድጓል፡፡ የያዕቆብ ወላጅ እናቱ በልጅነቱ ስለሞተችበትና የብርሃን እናቱ የሆነች ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ዮሴፍ አረጋዊ በ83 ዓመቱ ጠባቂ ይሆናት ዘንድ ወደቤቱ ሲወስዳት ድንግል ማርያም ያዕቆብን የሙት ልጅ ሆኖ አግኝታው ከወለደችው ከመድኃኔዓለም ክርስቶስ ጋር አብራ ተንከባክባ አሳድጋዋለች፡፡
ያዕቆብ ከጌታችን ጋር አብሮ እየተጫወተ እያለ አንድ ቀን ትግል ይገጥማሉ፡፡ ያዕቆብም ጌታችንን አንስቶ ጣለው፡፡ ድጋሚ ተያያዙና አሁንም ያዕቆብ ጌታችንን ጣለው፡፡ ሦስተኛ ጊዜም እንዲሁ ሆነና ያዕቆብ የልብ ልብ ተሰማው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ድጋሚ ትግል ሲያያዙ ግን ጌታችን ያዕቆብን ወደ ሰማይ ወርውሮ መሬት ላይ በኃይል ጣለው፡፡ ያዕቆብም እጅግ ደንግጦ "ኃይልህን ደብቀህ ቆይተህ አሁን ምነው እንዲህ ታደርገኛለህ?" ሲለው ጌታችንም "እኔኮ ካልጣሉኝ አልጥልም" አለው፡፡
ከጌታችን ዕርገት በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ሾመውታል፡፡ ብዙዎችንም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሷቸዋል፡፡ ሕዝቡም የታመሙትን ድውያንን ሁሉ እያመጡለት ይፈውሳቸው ነበር፡፡ ከኢየሩሳሌምም ውጭ እየሄደ ያላመኑትንም አስተምሮ እያጠመቀ ቤተ ክርስቲያን ይሠራላቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በጾም በጸሎት ሆኖ በመቆም ብዛት እግሮቹ አብጠው ነበር፡፡
አንድ ቀን አይሁድ ተሰብስበው መጥተው ጌታችን የማን ልጅ እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ወደ ያዕቆብ መጡ፡፡ እነርሱም ወደ ያዕቆብ የመጡት ጌታችን የዮሴፍ ልጅ እንደሆነና የእርሱም የሥጋ ወንድም እንደሆነ እንደሚነግራቸው አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ያዕቆብ ከፍ ካለው ከሦስተኛው መደብ ላይ ወጥቶ ጌታችን የራሱ የያዕቆብና የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን መሰከረባቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ፍጹም አምላክ መሆኑን፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ከአብም ጋር ትክክል እንደሆነ መሰከረባቸው፡፡ ይህንንም በሰሙ ጊዜ አይሁድ እጅግ ተናደው በጽኑ ግርፋት ካሠቃዩት በኋላ ራሱን ቀጥቅጠው ገደሉት ሰማዕትነቱን ሐምሌ 18 ቀን በድል ፈጽሟል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages