ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 12 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, December 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 12

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ ቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣
ቅዱስ_ሚካኤል_ኢያሱን እንደ የተረዳበት ቀን ነው፣ ለቅዱሳኑ_ዱራታኦስ_እና_ቴዎብስታቅዱስ_ሚካኤል ተዓምር ያደረገበት ነው፣ የባህራን_ቀሲስ መታሰቢያ ነው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ የጻድቁ_በእደ_ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ የሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_አባት_ፊላታዎስ እረፍቱ ነው።


ኅዳር ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን ለሰው ወገን የሚያዝንና የሚራራ በእግዚአብሔር ጌትነት ዙፋን ፊት ሁልጊዜ በመቆም ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ በሰማያትም ለሚኖሩ ኃይሎች ሁሉ አለቃቸው ለሆነ ለቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

ዳግመኛ በዚህች ዕለት ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን የተረዳበት ቀን ነው።
ይህም በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በታላቅ ክብር ሁኖ የነዌ ልጅ ኢያሱ ያየው ነው ከእኛ ሰዎች ወገን ነህን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ አለው። እኔስ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ አሁንም ወዳንተ መጥቻለሁ አለው ።
ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደለትና በእኔ በባሪያህ ዘንድ ምን አቁሞሃል አለው ። የእግዚአብሔር የሠራዊቱም አለቃ ሚካኤል ኢያሱን የቆምክባት ምድር የከበረች ቦታ ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው ኢያሱም እንዳለው አደረገ ።
እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው በውስጧ ያለውን ንጉሧን ከኃያላኑና ከአርበኞቹ ጋር በእጃችሁ ኢያሪኮን እነሆ አስገባታለሁ ። ይህም የከበረ መልአክ ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋር በመሆን ገድላቸውን እስከ ሚፈጽሙ የሚያጸናቸውና የሚያስታግሣቸው ነው ።
ስለዚህም ስለ ልዕልናውና ስለ አማላጅነቱ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ለመታሰቢያው በዓል ተሠራለት እርሱ ስለ እኛ የምድሩን ፍሬ ይባርክልን ዘንድ ዝናሙንም በጊዜው እንዲአወርድልን የወንዙንም ውኃ እንዲመላልን ነፋሱንም የምሕረት ነፋስ እንዲአደርግልን ሁሉንም የተስተካከለ እንዲአደርግልን ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ይማልድልናልና።

ቅዱሳኑ ዱራታኦስ እና ቴዎብስታ የቅዱስ ሚካኤል ወዳጆች ናቸውና በዚህች ዕለት ይታሰባሉ።
እንዲህም ሆነ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው እነርሱም ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ ለዚህም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉት አጡ ዱራታዎስም ሽጦ ለበዓሉ መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱን ልብስና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሔደ ።
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኰንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለት ወደ ባለ በጎች ሒዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ ሁለተኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ሒዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ግን መልአኩ ወደ ቤቱ ሳይደርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ ወደ ባለ ሥንዴም እንዲሔድና የሚሻውን እንዲሁ በርሱ ዋስትና እንዲወስድ አዘዘው ዱራታዎስም ቅዱስ ሚካኤል እንዳዘዘው አደረገ ።
ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ በረከትን ሁሉ ቤቱ ተመልቶ አገኘው ። እጅግም አደነቀ የዚህንም የከበረ መልአክ የበዓሉን መታሰቢያ እንዳስለመደ አደረገ ። የተራቡ ድኆችን ሁሉንም ጠርቶ መገባቸውና ወደየቤታቸው አሰናበታቸው።
ከዚህም በኃላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው ። ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንዲሠነጥቅ አዘዘው ። በሠነጠቀውም ጊዜ ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ተገኘ ። ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስንና ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ ለባለ ዓሣውና ለባለ ሥንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ ። በኋላኛውም መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል ።
እነርሱም ሲሰሙ ስለዚህ ነገር ደነገጡ። እርሱም ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም አላቸው ። ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት ወጣ ። እነርሱም ሰገዱለት ተአምራቱም የማይቁጠር ብዙ ነው ።

ዳግመኛም በዚህች እለት የባህራን ቀሲስ መታሰቢያ ነው።
የዚህ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተአምራቱ ብዙዎች ናቸው ። ከእነርሱም አንዱ ይህ ነው ። እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ ሰው ነበረ አርሱም የከበረ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ይልቁንም በሰኔና በኅዳር ወር አብልጦ ያከብር ነበር ። በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ ። ይህን እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የሚካአልን በዓል በሚያደርግበት ጊዜ ይጠላውና ያቃልለው ነበር ለድኆች ስለ መራራቱም ይዘባበትበት ነበረ ። የሕይወቱ ዘመንም ተፈጽሞ የሚሞትበትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ የክቡር መልአክ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ታደርግ ዘንድ ምጽዋት ሰጭም ትሆን ዘንድ ሚስቱን አዘዛት ።
ከዚህም በኋላ አረፈና ገንዘው ቀበሩት ሚስቱም ፀንሳ ነበረች የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ ምጥ ያዛት በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሳለችም እንዲህ ብላ ጸለየች የእግዚአብሔር መልአኩ ሆይ ራራልኝ በእርሱ ዘንድ ባለሟልነት አለህና በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኔ ለምንልኝ ። ይህንንም በአለች ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ ከችግርም ዳነች መልኩ ውብ የሆነ ወንድ ልጅንም ወለደች የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት ጥሪቱንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዝዟል ባለጸጋውም በቤቱ በዐልጋው ላይ ሳለ ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ ።
ይህንንም በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ደረሰበት ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመረ ነገር ግን ክብር ይግባውና ጌታ ይጠብቀው ነበር ። ከዚህም በኋላ ያ ባለጸጋ ምክንያት አዘጋጅቶ የሚያገለግለኝ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ ልጅሽን ስጪኝ እኔም እየመገብኩና እያለበስኩ አሳድገዋለሁ ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ አላት ።
ይህንንም ነገር ከባለጸጋው በሰማች ጊዜ ስለችግሯ እጅግ ደስ አላት ልጅዋንም ሰጠችው እርሱም ሃያውን ወቄት ወርቅ ሰጣት ልጅዋንም ወሰደው የምሻው ተፈጸመልኝ ብሎ ደስ አለው ።
ከዚህም በኋላ በልጁ ቁመት ልክ ሣጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አስገብቶ ዘጋበት እስከ ባሕርም ተሸክመው ወስደው በባሕር ጣሉት ክብር ይግባውና በጌታችን ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሠጥም ከዚያች አገር የሃያ ቀን መንገድ ያህል ርቃ ወደምትገኝ ወደ አንዲት አገር ወደብ እስከሚደርስ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ ።
በባሕሩም አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበረና ሣጥኑን በውኃ ላይ ተንሳፎ አየው እርሱም ከባሕሩ አውጥቶ ወደ ቤቱ ወሰደው ይህንም ሣጥን እንዴት እንደሚከፍተው ያስብ ጀመረ ይህንም ሲያስብ ወደ ባሕሩ ይሔድ ዘንድ ጌታችን በልቡናው ኃሳብ አሳደረበት ወዲያውኑም ተነሥቶ ወደ ባሕሩ ሔደና አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰው አገኘ ።
ዓሣ አጥማጁንም መረብህን በኔ ስም ጣል ለሚያዘውም ዓሣ ዋጋውን እሰጥሃለሁ አለው አጥማጁም እንዳለው አደረገ ያን ጊዜም ታላቅ ዓሣ ተያዘ ዋጋውንም ሰጥቶ ዓሣውን ተቀበለ ዓሣውንም ይዞ ወደቤቱ ሔደ ለራትም ይጠብሰው ዘንድ አረደው በሆዱም ውስጥ መክፈቻ አገኘ ። በልቡም ይህ መክፈቻ ይህን ሣጥን ይከፍተው ይሆን አለ በሣጥኑ ቀዳዳም በአስገባው ጊዜ ፈጥኖ ተከፈተ በውስጡም ይህን ታናሽ ብላቴና አገኘ ። ልጅ የለውም ነበርና ታላቅ ደስታ ደስ አለው ጌታችንንም አመሰገነው። ሕፃኑንም በመልካም አስተዳደግ አሳደገው ሕፃኑም አድጎ ጐልማሳ ሆነ ።
ከብዙ ዘመናትም በኋላ ያ ባለ ጸጋ ተነሥቶ ወደዚያ አገር ሔደ በመሸም ጊዜ ወደ በግ ጠባቂው ደጅ ደረሰ በግ ጠባቂውን እስከ ነገ የምናድርበት ማደሪያ በአንተ ዘንድ እናገኛለን ኪራዩንም እሰጥሃለሁ አለው በግ አርቢውም እንዳልክ ይሁንና እደር አለው ባለጸጋውም በዚያ አደረ ።
ራት በሚቀርብም ጊዜ ሕፃኑን ባሕራን ብሎ ጠራው ባለጸጋውም ሰምቶ ልጅህ ነውን ብሎ ጠየቀው በግ ጠባቂውም አዎን ታናሽ ሕፃን ሆኖ ሳለ ከባሕር አግኝቼዋለሁና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጄ ነው አለው ባለጸጋውም በምን ዘመን አገኘኸው አለው እርሱም ከሃያ ዓመት በፊት ብሎ መለሰለት ። ያን ጊዜም እርሱ ወደ ባሕር የጣለው መሆኑን አውቆ እጅግ አዘነ ።
በማግሥቱም ጎዳናውን ሊጓዝ በተነሣ ጊዜ ሰይጣናዊ ምክንያት አመካኝቶ በግ ጠባቂውን እንዲህ አለው ዕገሊት ወደምትባል አገር በቤቴ የረሳሁት ጉዳይ ስለ አለ እንድልከው ልጅህን ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ እኔም የድካም ዋጋውን ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ አለው ። የብላቴናውም አባት ስለ ገንዘቡ ደስ ብሎት ልጁ ባሕራንን ሰጠው እንዲህም ብሎ አዘዘው ልጄ ባሕራን ይህ የከበረ ሰው ስለ ጉዳዩ ወደ ቤቱ ይልክህ ዘንድ ና ወደ ቤትህም በሰላም ትመለሳለህ ። ባሕራንም አባቴ ሆይ እሽ በጎ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ።
ያን ጊዜም ባለጸጋው ወደ መጋቢው እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ ይችን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው ማንም አይወቅ በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎ አሸጋት ። ለባሕራንም ሰጠው ለመንገዱም የሚሆነውን ስንቅ ሰጠው ባሕራንም ተነሥቶ ጉዞውን ጀመረ ሲጓዝም ሰንብቶ የአንዲት ቀን ጐዞ ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው አለው ወደ ዕገሌ አገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለጸጋ የተጻፈች መልእክት ናት አለው ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ አለው እርሱም ስለ ፈራ ሠጠው ።
በዚያን ጊዜም የከበረው መልአክ ሚካኤል ያቺን የሞት መልእክት ደመሰሳት በእርሷ ፈንታም በንፍሐት ለውጦ እንዲህ ብሎ ጻፈ ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ሰው ይቺ ደብዳቤ ደርሳ በምትነበብበት ጊዜ ልጄ እገሊትን አጋቡት በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና እኔን አትጠብቁኝ ። እኔ ብዙ እዘገያለሁ የኔ ሹም ዕገሌ ሆይ በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት ከዚህ በኋላ አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ወደ ባለጸጋው ቤት ሒደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጬልሃለሁ አለው ። ባሕራንም እሺ ጌታዬ ያዘዝኽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ።
ባሕራንም ወደ ባለጸጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው በአነበባትም ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ አስተውሎም አርግጠኛ እንደሆነ አወቀ ። ከዚህም በኋላ ለባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለጸጋውን ልጅ አጋቡት ። አርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ ።
ከዚህ በኋላ ባለጸጋው ከሔደበት መመለሻው ጊዜ ሁኖ በደስታ የሆነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ይህ የምሰማው ምንድነው ብሎ ጠየቀ እነርሱም ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት እነሆ ለአርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው ። ገንዘብህንና ጥሪትህን ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝክ ሰጥተውታል አሉት ። ይህንንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ በድንገትም ሞተ ።
ባሕራንም በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ሆነ የተገለጸለትና ከመገደል ያዳነው የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል እንደሆነ ሊገድለው የሚሻውን የባለጸጋውን ጥሪቱን ሁሉ ያወረሰውም እርሱ እንደ ሆነ ተረዳ የዚህንም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ጀመረ ቤተ ክርስቲያንም ሠራለት የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕሉን አሥሎ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ አደረገው ከእርሱም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ባሕራንም ቅስና ተሹሞ እስከ ዕለተ ሞቱ በዚያች ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ሁኖ ኖረ በዚህ በከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤል አማላጅነት ከእናቱና ከአባቱ ከልጆቹም ጋራ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ ።

በዚችም ቀን የኢትዮጵያ ንጉሥ የጻድቁ በእደ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ።
በዕደ ማርያም" ማለት "በማርያም እጅ" እንደ ማለት ነው:: እኒህ ሰው የኢትዮዽያ ንጉሥ ሲሆኑ የነገሡትም በ1460 ዓ/ም ነው:: ደጉ አባታቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሲያርፉ በመንግስቱ ተተክተው ሃገራችንን አስተዳድረዋል:: ድርሰት ደርሰዋል:: አብያተ መቃድስ አንጸዋል::
በተለይ ለቅኔ ትምሕርት ማበብ ልዩ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገራል:: ልክ በነገሡ በ10 ዓመታቸው ግን መንግስተ ምድር በቃኝ ብለው በምናኔ በርሃ ገብተዋል:: በዙፋናቸውም አፄ እስክንድር ተተክተዋል:: ጻድቁ ንጉሥ ግን ቅዱስ ሚካኤልን ይወዱት ነበርና በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

በዚችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ ሦስተኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ፊላታዎስ አረፈ። በሹመቱ ወራትም የኢትዮጵያ ንጉሥ ወደ ኖባ ንጉሥ ወደ ጊዮርጊስ እንዲህ ብሎ የመልእክት ደብዳቤ ጻፈ ወንድሜ ሆይ ከሊቀ ጳጳሳት ቆዝሞስ ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ጳጳስ ስለ ሌለን እኛ በታላቅ ችግር ውስጥ እንዳለን ዕወቅ ።
ይህም የሆነው ተንኰለኛው ሚናስ በተንኰልና በሐሰት ነገር የከበረ ጳጳሳችንን ጴጥሮስን ከሹመቱ ወንበር እንዲሰደድ ስለ አደረገው ነው። ስለዚህ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት እስቲአልፉ ለሀገራችን ጳጳስ አልተላከልንም ።
አሁንም ስለ እግዚአብሔር ብለህ ስለ ቀናች ሃይማኖትም በድካም ከእኛ ጋር አንድ በመሆን ስለእኛ ወደ ግብጽ ሊቀ ጳጰሳት ወደ ቅዱስ ፊላታዎስ ጳጳስ ይልክልን ዘንድ ከራስህ ደብዳቤ እንድትጽፍለት እለምንሃለሁ የሚል ነበር ።
በዚያንም ጊዜ የኖባ ንጉሥ ጊዮርጊስ ለኢትዮጵያ አገር ጳጳስን ይሾምላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ ወደ አባ ፊላታዎስ ጻፈ ይህ ቅዱስ ፊላታዎስም ልመናውን ተቀብሎ ከአስቄጥስ ገዳም ስሙ ዳንኤል የሚባል አንድ ጻድቅ መነኰስ አስመጣ እርሱን ጵጵስና ሹሞ ወደ ኢትዮጵያ አገር ላከው ወደ እነሱም በደረሰ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰዎች በታላቅ ደስታ ተቀበሉት ። በዚህም አባት ፊላታዎስ ዘመን ብዙ ተአምራት ተገልጠዋል በሰላምም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages